ከጥቂት ዓመታት በፊት የጋምቤላ ክልል በርካታ ፀረ ሠላም ኃይሎች የሚንቀሳቀሱበት ክልል የነበረ ሲሆን፤ በርካታ ንጹሃንም ለህልፈት መዳረጋቸው ይታወሳል። በተለይም የጋምቤላ ነፃ አውጪ ግንባር እና ከዚህ ቡድን ጋር አብረው የሚሰሩ አካላት የክልሉን ኢንቨስትመንት፣ ሰላምና ደህንነት አደጋ ውስጥ ጥለውበት የቆዩ መሆኑ የቅርብ ዓመታት ትውስታ ነው።
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጋምቤላ ነፃ አውጪ ግንባር የሠላም ሥምምነት ከተፈጠረ በኋላ እፎይታ ስለመገኘቱ እየተገለፀ ይገኛል። በክልሉ ያለስጋት ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ ስለመቻሉም እየተጠቆመ ነው። ቀደም ሲል የነበረው ስጋት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
ይህ ቡድን በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መሞከሩ ክልሉን የተረጋጋ እንዲሆነ እያስቻለው ነው። በአሁኑ ወቅት ከአንዱ ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ ለመንቀሳቀስ ዋስትና የሚሰጡ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ሲሆን፤ ይህ ህብረተሰቡን እንዲረጋጋ አድርጎታል።
ቀደም ባሉት አመታት በክልሉ ይፈጠሩ ከነበሩ ሁኔታዎች መካከል ለአብነት ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ከደቡብ ሱዳን በመጡ ሙርሌ ጎሳዎች በጋምቤላ ክልል የተፈጠረው የነዋሪዎች ሞት ይታወሳል። በተጨማሪ ልጆች እና እንስሳት ተወስደዋል፤ ታግተዋልም። ይህን ችግር ለመመከት በወቅቱ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የጋምቤላ ክልል የፀጥታ መዋቅር በሙሉ ከፍተኛ ትግል ማካሄዳቸውም ይታወሳል። በዚህም በርካታ ልጆች እና እንስሳት የተመለሱ መሆናቸውም ይታወቃል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሰፊ ከሚዋሰኑ አገራት መካካል አንዷ ስትሆን፤ በዚህ በሚዋሰኑ አካባቢዎችም በርካታ ችግሮች ሲፈጠሩ መቆየታቸውም ይታወቃል። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች የሚነሱ ሲሆን፤ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው የመልክዓ ምድር አቀማመጥና የጸረ ሠላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ለችግሩ መባባስ አንድ ምንጭ መሆኑም ይጠቀሳል። በዚህ አካባቢም ዘርፈ ብዙ ወንጀሎች የሚከሰቱ ስለመሆኑም በተደጋጋሚ ይነገራል። ድንበር ዘለል ወንጀል መባባሱም በእዚህ የተነሳ ስለመሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎች ጭምር የሚያስረዱት ነው።
የሙርሌ ጎሳዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ ተነስተው ደቡብ ሱዳን ድረስ የሚዘልቁ ወንዞችን ተገን አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። አብዛኞቹም ወንዙን ተከትለው የሚመጡ ናቸው። አካባቢው በተፈጥሮ ደንም የታደለ ስለመሆኑ ይነገርለታል። አካባቢው በጣም ሰፊና እና ጥቅጥቅ ያለ ጫካ አለ። በዚህ አካባቢ ደግሞ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሾልከው የሚገቡበት አጋጣሚም ይፈጠራል።
በድንበር አካባቢ ወንዝ እና ጫካ አለ። በዚህ ህዝቡ እንደፈለገው መውጣት እና መግባት ይችላል። ነገር ግን ድንበሩን ለመቆጣጠር እና የጸጥታ መዋቅሩን ለማጠናከርም ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውንና በአሁኑ ወቅትም እየተከናወነ መሆኑ ይነገራል።
አዲስ ዘመን ከጋምቤላ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቸንኮት ቾት ጋር የክልሉን አጠቃላይ የሠላምና ፀጥታ ሁኔታ፣ ቀደም ሲል በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች ብሎም በቀጣይ ሊከናወኑ የታሰቡ ተግባራትን አስመልክቶ ቃለ መጠይቅ አድርጎ ፤ በዚህ መልኩ አቅርቦታል።
አዲስ ዘመን፡- አሁናዊ የጋምቤላ ክልል ሠላምና ፀጥታ እንዴት ይገለፃል?
አቶ ቸንኮት፡- የክልሉ አሁናዊ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ በጣም የተረጋጋ ነው። ሰሞኑን የተወሰነ ግጭት ለመፍጠር የሞከሩ አካላት ነበሩ፤ ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት በፍጥነት ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ አድርገናል።
በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ከበርካታ ወጣቶች ጋር በተለያዩ ደረጃዎች መክረናል። በዚህም የታሰበውን ውጤት ማምጣት ችለናል። የማረጋጋት ሥራዎችን ሰርተን ውጤታማ ሆነናል። በፀጥታው ዘርፍ ላይ የሚሰሩት አካላት በሙሉ ተናበው ሲሰሩ ቆይተዋል። በአሁን ወቅት የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮችም ተናበው እየሰሩ ናቸው። በዚህም ችግሮች ሲያጋጥሙ በፍጥነት ለመቆጣጠር አስችሎናል ።
በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ክልል የትኛውም አቅጣጫ ለመንቀሳቀስም ሆነ ለመውጣትና ለመግባት አስቸጋሪ ሁኔታ የለም። ይህም በጥረትና በትዕግስት በመሥራት የመጣ ውጤት ነው። ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ ትልቅ ድርሻ አለው።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ያሉ ግጭቶች እና የፀጥታ ችግር መነሻ ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ቸንኮት፡– በክልሉ ቀደም ሲል ይንቀሳቀሱ የነበሩት ይታወቃሉ። ለአብነትም የጋምቤላ ነፃ አውጭ ግንባር አንዱ ነው። የአሁኑ ግጭት ግን ከእነዚህ ጋር የሚገናኝ አይደለም። ይህ ቡድን ትጥቅ ፈትቶ በሰላማዊ መንገድ ለመኖር እና ለመታገል ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅሏል። የተለያዩ ጥርጣሬዎች እና ግምቶች ቢኖሩም ተፈጥሮ የነበረው ግጭት መነሻው የጋምቤላ ነፃ አውጭ ግንባር ነው የሚል ግምገማ የለንም።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ከጋምቤላ ነፃ አውጪ ግንባር ጋር የሠላም ሥምምነት መደረጉ ይታወሳል። በህብረተሰቡ ዘንድ የነበረው ስሜትና ያገኛችሁት ምላሽ ምን ይመስላል?
አቶ ቸንኮት፡– እንግዲህ ከዚህ ቡድን ጋር የተደረገው ሥምምነት ውጤታማ ነው። የመጀመሪያው ሥራችን ከማህበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ መነጋገርና መወያየት ነው። በዚህም ሁላችንም የሚጠበቅብንን እየሠራን ቆይተናል። የጋምቤላ ነፃ አውጪ ግንባር በሰላማዊ መንገድ ወደ ክልሉ ገብቷል። ይህ ብዙ ስጋቶችን ቀንሷል።
አዲስ ዘመን፡- ምን ዓይነት ስጋቶችን ቀነሰ?
አቶ ቸንኮት፡- የጋምቤላ ነፃ አውጪ ግንባር ሠላም ሥምምነት ከተፈጠረ በኋላ እፎይታዎች ተገኝቷል። ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ ተችሏል። ቀደም ሲል የነበረው ስጋት አሁን የለም። ከአንዱ ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ ለመንቀሳቀስ በትራንስፖርት ላይም ሆነ በመንገድ ላይ የሚፈጠር ችግር የለም። ይህ ህብረተሰቡን እንዲረጋጋ አድርጎታል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ፀረ ሰላም ኃይሎችም የሚተባበራቸው አካል ባለመኖሩና አመቺ ሁኔታ ባለማግኘታቸው በራሳቸው ጊዜ ከክልሉ እየተገፉ ነው። ግንባሩ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ ወደ ሰላማዊ ትግል መምጣቱ እንደ ክልል በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት።
በዋነኝነት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች አንዳንድ የጸጥታ ችግሮች እየተከሰቱ የክልሉ ነዋሪዎችም ሆኑ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ እኛ በመምጣት የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ሰላም አደጋ ላይ ነበር። የየዕለት ሥራቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ለመከወን የሚችሉበት ሁኔታም አልነበረም።
ቡድኑ እንቅስቃሴውን ያደርግ የነበረው በጫካ አካባቢ በመሆኑ አርሶ አደሩ በነጻነት የእርሻ ስራውን ማከናወን አስቸጋሪ ስለሚሆንበት ከሰላሙ በተጨማሪ በምርታማነቱም ላይ ችግር ፈጥሮ ነበር። በአጠቃላይ ዜጎች ይንቀሳቀሱ የነበረው በስጋት ውስጥ ነበር።
አሁን ግን ከጋምቤላ ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ሰላም በመፈጠሩ ግድያን ጨምሮ በአንዳንድ ቦታዎች የነበሩ ወንጀሎች ቀርተዋል። እንደ ክልልም የነበረው ስጋት በመቀረፉ ክልሉ በዚህ ረገድ ያለበትን የሰላም ችግር ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- የቀነሰውን ስጋት በምሳሌ አስደግፈው በደንብ ያብራሩልኝ?
አቶ ቸንኮት፡- በርካታ ስጋቶች ቀንሰዋል። አሁን ከሌሎች ፀረ-ሠላም ኃይሎች ጋር አብረው በመተባበር አይሰሩም። ቀደም ሲል በጫካ ውስጥ ግድያ ነበር፤ አሁን ግን ይህ የለም። ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና የመሳሰሉትን ተያያዥ ወንጀሎችን ለመፈፀም ይጠቀሙበት ነበር። ይህንንም በብዛት ማስቀረት ተችሏል።
ቀድሞ ከነበረው ግጭት በመውጣት አሁን ሰላማዊ ህይወት ቀጥሏል። በጫካ ውስጥ የነበረው ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ የህብረተሰቡም ስጋት ቀንሷል። በዚህ መልኩ ብዙ ስጋቶች መቀነሳቸውን እንደማሳያ መጥቀስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ስጋቱን ከመቀነስ ጎን ለጎን ለቡድኑ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ተሰጥቷል?
አቶ ቸንኮት፡- አዎ! እነዚህ ታጣቂዎች ከአንድ ወር በላይ የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል። በተሃድሶው አገራዊ ህገ-መንግስቱን በተመለከተ እና መከበር ስለሚገባቸው ህጎች በሚገባ ሰልጥነዋል። የሠላም ዕሴት ግንባታ እና አስፈላጊነት እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ላይም በሰፊው የተሃድሶ ስልጠና ወስደዋል። ልምዶች እና ህጎችን እንዳይቀላቀሉም ስልጠናዎችን በሰፊው ተሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከውስጣዊ ችግሮች በተጨማሪ ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳዎች ተደጋጋሚ ጥቃት የክልሉ ጸጥታ ስጋት ነበር። በዚህ ዓመትስ?
አቶ ቸንኮት፡- የሙርሌ ጎሳዎችን ጥቃት በተመለከተ በተለያዩ መድረኮች እያነሳን ነው። እስካሁን ሁነኛ መፍትሄ አልተገኘም። በአሁኑ ወቅትም ጭምር በአኝዋኽ ዞን የእነዚህ ጎሳዎች እንቅስቃሴ አለ። በኑዌር ዞንም የሙርሌ ጎሳ ጥቃት እና እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ ይስተዋላል። እነዚህ ጎሳዎች በተበታታነ መንገድ ይመጣሉ። አንዳንዴ ደግሞ ተደራጅተው ይመጣሉ። ሆኖም ጉዳት ከማድረስ አልታቀቡም። እኛም የሚያደርሱትን ጉዳት ዝም ብለን እየተመለከትን አይደለም። ባለን የፀጥታ መዋቅር እየመለስናቸው ነው።
ይህም ሆኖ በቅርቡ በኑዌር ዞን ላይ ትልቅ ጥቃት አድርሰዋል። የአስር ሰዎችም ሕይወት አልፏል። በአኮቦ ወረዳም በተመሳሳይ ችግር ነበር። እስካሁንም የእነዚህ አካላት እቅስቃሴ አለ። እኛም በሚሊሻዎች እየተጠቀምን ነው። ሚሊሻዎቻችን በየጫካው አሰሳ ያደርጋሉ። እስካሁን ድረስም ሚሊሻዎቻችን በየጫካው ይገኛሉ። ይህ ሁሉ ጥረት በቂ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- የሚደረገው ጥረት በቂ ያልሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ቸንኮት፡– ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር እንዋሰናለን። በጣም ሰፊ ከመሆኑም የተነሳ ክፍት ነው። በዚህ አካባቢ በሰፊው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ለማስገባት ጥረት ይደረጋል።
ድንበሩ ክፍት በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ መጠበቁ አስቸጋሪ ነው። ወሳኝ የሆኑ ቦታዎችና ለኮንትሮባንድ አመቺ ይሆናሉ ተብለው በሚታሰቡ አካባቢዎች የተጠናከረ ጥበቃ ይደረጋል። እንደዚህም ሆኖ የሚያደርሱትን ጥቃቶችና ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ማስቆም አልተቻለም።
እስካሁን ችግሮችን መመከት የቻልነው የራሳችንን ኃይል በማጠናከር ነው ። በአሁኑ ወቅት የአገር መከላከያ ሰራዊት ወደ ድንበር አካባቢ በሰፊው በመንቀሳቀስና ከሚሊሻዎቻችን ጋር ተናበው እየሰሩ በመሆናቸው ብዙ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው።
በሚደረገው ጥረት ሙሉ ለሙሉ የእነዚህን ጎሳዎች ጥቃት ማስቆም አልተቻለም። እንደሚታወቀው በአገራዊ ሪፎርሙ ሥራ መሰረት የክልላችን ልዩ ኃይል ወደ ሪፎርም የገባ በመሆኑ ክፍተት አለ። እነዚህን ሃይሎች የሚተካ ሌላ የፀጥታ ኃይል እንዲመደብ ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት አካላት ጋር ተነጋግረን ነበር። በዚህም መሰረት የተመደቡ የፌደራል ፖሊስ አባላት አሉ።
የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትም አሉ። ይሁንና ግን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የተመደበው ኃይል በቂ አይደለም። በዚህ ላይ ክፍተቶች አሉ። በሂደት ግን በተነጋገርነው መጠን እንደሚገቡ ይጠበቃል። በእንቅስቃሴ ላይም በርካቶች እንዳሉ ይታወቃል። ይህ ከሆነ የሚገመተው ስጋት እንዳይደርስ ያደርጋል። ይህም ብቻ ሳይሆን የሙርሌ ጎሳዎችን ጥቃት ከመከላከል አልፎ ያሰቡትን በፍፁም እንዳያሳኩ የማድረግ አቅም መፍጠር ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በችግሩ ዙሪያ ከደቡብ ሱዳን የአገር ሽማግሌዎች ጋር ለመምከር አልተሞከረም?
አቶ ቸንኮት፡– የደቡብ ሱዳን የአገር ሽማግሌዎች ጋር ለመወያየት ብቻችንን አንወስንም። በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገው ግንኙነት የሚወስነው የፌደራል መንግስት መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም በተወሰነ ደረጃ በድንበር አካባቢ የምንወያይበት መንገድ ቢኖርም እኛ በራሳችን ስልጣን ብቻ የምናደርገው የለም። ይህ በራሱ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የእነዚህን ጎሳዎች ጥቃት ለመመከትና ድንበር አካባቢ ጥበቃ አስተማማኝ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ቸንኮት፡- በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ የተጠናከረ ጥበቃ ማድረግ ይገባል። ችግሩን በአንድ ጊዜ ማጥፋት እንደማይቻል እሙን ነው። ነገር ግን በተናበበ እና በተጠናከረ ጥበቃ ችግሩን በከፍተኛ ደረጃ ማቃለል እንችላለን። ይህን ለማድረግ ደግሞ የክልሉ መንግስት ብቻ ሳይሆን የፌደራል መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ የደቡብ ሱዳን መሪዎችም ድንበር አካባቢ ያለውን ችግር በመገንዘብ መተባበር አለባቸው። በአጠቃላይ የጸጥታ ኃይሎች የተጠናከረ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ላይ እኛም አቅደን እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የክልሉን ሠላም ከሚያደፈርሱት ኃይሎች መካከል አንዱ ከፍተኛ የሆነ የስደተኞች ቁጥር በክልሉ መኖሩና ከካምፕ በመውጣት በሁሉም የክልሉ ከተሞች መንቀሳቀሳቸው እንደሆነ ይነገራል። በዚህ ጉዳይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ቸንኮት፡- የስደተኞች ጉዳይ ብዙ ስጋት አይሆንም። ነገር ግን በክልልችን ያለው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በሌሎች ዓለማት እንደምናየው አይደለም። በሌሎች አገራት የስደተኞች ካምፕ የራሱ የሆነ አጥር አለው። ለብቻው ይከለላል። ወደ ከተማ ለመሄድ ከተፈለገም ዝም ብለው አይገቡም፤ ከተማ ውስጥ የሚገቡት ፍቃድ ሲሰጣቸው ብቻ ነው። ነገር ግን በጋምቤላ እንደዚህ ዓይነት አካሄድ የለም። ስደተኞች እንደፈለጉ ይገባሉ፤ እንደፈለጉም ይወጣሉ። ይህ የሆነው ደግሞ ካምፖቹ በጣም ሰፊ ከመሆናቸው የተነሳ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምን ያክል ስደተኞች በክልሉ አሉ፤ የፀጥታ ስጋትስ አልሆኑም ማለት ነው?
አቶ ቸንኮት፡- እኔ ቁጥራቸውን በትክክል አላውቅም። ይህን የሚቆጣጠረው ሌላ አካል ነው። ነገር ግን ቁጥራቸው ይብዛ እንጂ ለክልሉ የጸጥታ መዋቅር ስጋት ሆነው አላገኘናቸውም።
አዲስ ዘመን፡- ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት፣ በፀጥታ እና የጋራ ጉዳዮች ላይ ያላችሁ መስተጋብር ምን ይመስላል?
አቶ ቸንኮት፡- እኛ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የተሻለ መቀራራብ እና መነጋገር አለ። አንጻራዊ ሠላም አለ። ከኦሮሚያ ክልል፣ ከደቡብ ምዕራብ ክልል፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር እንዋሰናለን በጋራ ጉዳዮችም ጋር እንነጋገራለን። የጋራ መድረኮች አሉን። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችም አሉን። በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ክልሎች ጋር ያለው የሠላም ሁኔታ በጣም ጥሩ የሚባል ነው። በየመድረኮቹም የሚነሱት እና የተገኙትም ነጥቦች አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ የሚያሳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ በጣም ይተባበራል። እኛም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚጠበቅብንን ሥራ እያከናወንን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ተደጋጋሚ ግጭቶች እየተከሰቱ የበርካታ ዜጎች ህይወት ማለፉን ይሰማ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እየተስተዋሉ አይደለም። በአንጻሩ የተሻለ የሰላም ሁኔታ እየታየ ነው። ይህ እንዴት ሊመጣ ቻለ ?
አቶ ቸንኮት፡- እንግዲህ ከዚህ በፊት የነበረው የአኟክ እና የኑየር ግጭት የተዛባ አመለካከት በማህበረሰቡ ውስጥ የነበር በመሆኑ የተፈጠረ ነው። በዚህም አንድ ሰው መሪ ሲሆን፤ ማንነቱን የማስቀደም ነገር ነበር። ይሄ ግን ያለፈ ነገር ነው። ከለውጡ ወዲህ ግን የተደረገ ትልቅ ለውጥ አለ። የለውጡ መሪዎች የውስጥ ፓርቲ አንድነት ተከትለን በእህትማማችነት እና በወንድማማችነት በህብረት በጀመርነው ጉዞ ያለፈውን አራት አመት ያለ ምንም የጎላ ችግር ማሳለፍ እና ለህብረተሰቡም ሰላምን ማስፈን ችለናል።
ባለፉት አራት አመታት ምንም ግጭት ተፈጥሮ ያልነበረ ቢሆነም፤ በቅርቡ በአንድ ሁለት ቀበሌዎች አካባቢ በኑየር እና አኟክ መካከል በተፈጠረ ችግር በከተሞች ረብሻ ተከስቶ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉም ነገር ተረጋግቶ አካባቢው ወደቀደመ ሰላም መመለስ ተችሏል። ይህም የሆነው በአጭር ግዜ በውስጥ ኃይል ብቻ በተሰራው ሰፊ ርብርብና ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂነት ለማስፈን ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ቸንኮት፡- ሠላምን ለማስቀጠል የብልጽግና መስመርን በመያዝ በወንድማማችነትና እህትማማችነት ህብረታችንን በማጠናከር መንግስት በራሱ የጸጥታ አካላት ሠላም በማስከበር የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ይሆናል። ከዚሁ በተጓዳኝም አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራም የሚሰራ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት የፖሊስ ሚና ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ ግምገማ እየተካሄደ ነው። በዚህም በግጭት ወቅት ፖሊሶች ሲሰሩ የነበሩትን ነገር በመገምገም የነበራቸውን ሚና በመለየት፤ በየወረዳው ተጠያቂ የሚሆን ካለ በህጉ መሰረት የሚጠየቁበት አግባብ ይኖራል። ይህ የህግ የበላይነት የማስከበሩ ስራ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የተደረጉ የአመራር ሽግሽጎች እና አጠቃላይ ክልላዊና አገራዊ ሪፎርሙ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል ?
አቶ ቸንኮት፡- ለውጡ ሲመጣ አዲሱ አመራር ሥራውን የጀመረው የሐሳብ ለውጥ በማምጣትም ነው ። የተወሰዱት ትምህርቶችም የፓርቲ አንድነትን እና የአመራር አንድነትን ማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ይህ ሲታይ በሪፎርም የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል የሚለውን ድምዳሜ ይሰጣናል።
አዲስ ዘመን፡- ጋምቤላ ክልል የበለጠ ፀጥታውን ለማጠናከር ሌሎች ክልሎች እንደ ተሞክሮ ሊወስዱት ወይንም ሊሰጠው የሚችለው ነገር ምንድን ነው?
አቶ ቸንኮት፡- ከእኛ ክልል በፀጥታው ረገድ ከሌሎች ክልሎች በተለይ ከድሬዳዋ በርካታ ነገሮችን ለመማር ችለናል። በተለይ የማህበረሰብ ፖሊሲ እንቅስቃሴዎችን እንደተሞክሮ በመውሰድ በእኛም ጋር ለመተግበር እየሰራን ነው። አደረጃጀታችን ተመሳሳይ ቢሆንም በእኛ ክልልም የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አሰራርን ጀምረን የምናስፋፋው ይሆናል። ይህም ከፀጥታው በተጨማሪ በከተሞች ያሉ ስርቆቶችን እና ሌሎች ወንጀሎችንም ለማስቀረት ስለሚጠቅመን በስፋት የምንሄድበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እያመሰገንኩ፤ ተጨማሪ ሐሳብ ካልዎት መጨመር ይችላሉ።
አቶ ቸንኮት፡– እኔም አመሰግናለሁ። የክልላችን ሠላም ለማረጋገጥ ብሎም የኢትዮጵያ ሰላም እውን ለማድረግ ሁላችንም ትልቅ ኃላፊነት አለብን። ህብረተሰቡ ደግሞ የፀጥታ ኃይል ዋነኛ አጋዥ በመሆኑ ሊተባበር ይገባል። ይህን ማሳካት ከተቻለ እና መናበብ ካለ የሚፈለገው ሠላም ይሰፍናል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2015