የአፍሪካ ቀንድ ከድርቅ አልፋታ ካለ ከአራት አሠርታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ አሁን፤ አሁን ደግሞ በየ10 ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ በየዓመቱ እየተደጋገመ መምጣት ጀምሯል፡፡ ድርቁም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ አስከፊነት እየተሸጋገረ ከሰው እስከ እንስሳት መልክዓ ምድሩን ጨምሮ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋነኝነት ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፤ ኬንያና ጂቡቲ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ምስራቅ አፍሪካ በድርቅ ሲጎዳ ኖሯል፡፡ ለችግሩ መከሰት ደግሞ በዋነኝነት ከአየር መዛባት ጋር በተያያዘ የሚፈጠረው የዝናብ መዋዠቅ እንደሆነ አስምሮበታል፡፡ ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እ.ኤ.አ. በ2011 በተከሰተው ቸነፈር ህጻናትን ጨምሮ ከሩብ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡
በምግብ ደህንነትና ሥነ ምግብ ላይ የሚሠራው ዓለም አቀፋዊ ተቋም የሆነው (ኤፍ.ኤስ.ኤን. ደብሊው.ጂ) ባወጣው ልዩ የድርቅ ዘገባ መሠረት ከ8 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የአርብቶ አደር ቤተሰቦች ለምግብና ለኑሮ የሚተማመኑባቸውን ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት ድርቁ ገድሎባቸዋል። በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ በኬንያ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮንና በሶማሊያ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ከብቶች በመሞታቸው ከእነሱ የሚገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው የወተት ምርትም እንዲታጣ ሆኗል።
በድርቁም አንዳንድ አካባቢዎች ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕፃናት በቀን አንድ ብርጭቆ ወተት ለማግኘት መቸገራቸውን በምሕፃሩ ፋኦ ተብሎ የሚታወቀው የምግብና የእርሻ ድርጅት ገልጿል። እንግዲህ ለአርባ ዓመታት ያህል እየተመላለሰ የሰዎችንና የእንስሳትን ሕይወት የሚቀጥፈው ድርቅ ለዘመናት መፍትሄ ሳይገኝለት ቆይቷል፡፡ መንስኤው እየታወቀ መፍትሄ ላይ ያልተደረሰበት ምክንያትም እንቆቅልሽ እንደሆነ ቆይቷል፡፡
ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ ሥልጣን የመጡት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለዘመናት ሲንከባለል ለመጣው ጥያቄ መልስ ይዘው የመጡ ይመስላል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ለአርባ ዓመታት ያህል እየተመላለሰ መጠነ ሰፊ ጉዳት እያደረሰ ያለው ድርቅ መነሻው የአካባቢ መራቆት ነው፡፡ መፍትሄውም ከዚህ ብዙ የሚርቅ አይደለም፡፡ መፍትሄው የተራቆተውን አካባቢ መልሶ እንዲያገግም ማድረግና አካባቢውን በደን ማልበስ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና ከጅምሩ ተረድተውታል፡፡
በእርግጥ ከዚህ ወቀደም የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረትን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ከዳግምዊ ሚኒልክ ጀምሮ ያሉ መሪዎች በየዘመናቸው ችግኞችን ሲተክሉ ኖረዋል፡፡ ሆኖም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስተዋጽኦ ግን በአይነቱ ለየት ያለና ግዝፈት ያለውም ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ ሃያ ሚሊዮን ዛፎችን ለመትከል ማቀዷን ይፋ ሲያደርጉ ከልቡ የተቀበለው ጥቂቱ ነበር፤ ለመዘባበት የሚሞክሩም ብዙ ነበሩ፡፡ ሆኖም በመጀመርያ ዙር ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል እቅድ በመያዝ በአንድ ቀን ብቻ ደግሞ ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በዘመቻ በመትከል ኢትዮጵያ ታሪክ መጻፍ ቻለች፡፡
ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩና የተረዱ ወገኖች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት የሚካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ ዘመቻ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ የችግኝ ተከላው የአገሪቱን የአረንጓዴ እጽዋት ሽፋንን እንዳሳደገ፤ ብሎም የአየር ንብረት ለውጥን እየተከላከለ እና የሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ሲመሰክሩ ተደምጠዋል። በተወካዮች ምክር ቤት አባላትና በገለልተኛ አካላት በተደረገ ጥናትና በመንግሥት የሚደገፈው የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዳስታወቀው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2019 ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ ውስጥ 83 ነጥብ 4 በመቶው እንዲሁም እአአ በ2020 ከተተከሉት ውስጥ ደግሞ 79 በመቶው ጸድቀዋል።
በተጨማሪ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አገሪቱን በአረንጓዴ ከማልበስ በሻገር በጥቂት ዓመታት ውስጥም ለምግብነት ሊውሉ የሚችሉ። እንዲሁም የችግኝ ተከላን ከግብርና ጋር አቀናጅቶ በማካሄድ አቦካዶን እንዲሁም ፓፓያን የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን ጨምሮ የተለያዩ ችግኞች እንዲተከሉ ያስቻለ ሲሆን፤ ይህም አጠቃለይ በአገሪቱ ላለው የምግብ ሥርዓት ትልቅ ፋይዳ የሚያመጣም ነው።
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የደን ሽፋን መልሶ እንዲያገግም ማድረግ የአየር እርጥበትን ለመጠበቅ ይረዳል ይላሉ። ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ የሚመጣውን ድርቅ እስከወዲያኛው ለመሸኘት ዋነኛ ምፍትሄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጀመረችውም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከራሷ አልፎ ለአካባቢውም መድህን ይሆናል ለማለት ያስደፍራል። ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ባሻገር ካለው አፍሪካ አቀፍ የታላቁ የአረንጓዴ ግድግዳ ልማት ፕሮጀክት ዕቅድ ጋር የተያያዘም ነው።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውም ጥረት በአውሮፓውያኑ እአአ 2007 ላይ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የተጀመረውን የታላቁ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት እንዲሳካ የሚያደርግም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጂቡቲ እስከ ሴኔጋል የሚዘረጋ 8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የዛፎች ከለላ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው። የአፍሪካ ህብረት የያዘው ዕቅድም እስከ እአአ 2030 ድረስ በሚለማው የአረንጓዴ ግድግዳ ደን የሰሃራ በረሃ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንዳይስፋፋ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አስተዳደር ከመምጣቱ በፊት የአፍሪካ ህብረት የያዘው ዕቅድ ከዕቅድነት ብዙም የዘለለ አልነበረም፡፡ ከአፍሪካ ህብረት በተገኘውም መረጃም ህብረቱ የአረንጓዴ ዐሻራን በተመለከተ ያከናወነው ሥራ ከ15 በመቶ ብዙም የዘለለ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ክንውኑን በእጥፍ ለማሳደግ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ነው፡፡
ኢትዮጵያ በመጀመርያው ዙር 25 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ከመቻሏም በላይ በዘርፉ ባለፋት አራት ዓመታት ከ767 ሺህ በላይ የስራ ዕድል መፍጠር ችላለች፡፡ የ25 ቢሊዮን ችግኝ ተከላን ዕውን ለማድረግ ያስቻሉም ከ120 ሺህ በላይ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ተመስርተዋል፡፡
ይህንኑ ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም ሰኔ አንድ ቀን ሁለተኛውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ጀምራለች፡፡ በዚሁ መርሃ ግብር የመጀመርያ ዓመትም ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የተተከሉትን ችግኞች ቁጥር ከ31 ቢሊዮን በላይ ለማድረስ ዕቅድ ይዛለች፡፡ በቀጣይ ሶስት ዓመታት መጨረሻ ደግሞ 50 ቢሊዮን ችግኞች የሚተከሉ ይሆናል።
ኢትዮጵያ እንዳጠቃላይ በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መጨረሻም ከ50 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ታሪክ ለመጻፍ መዘጋጀቷ ይታወቃል፡፡ አገሪቱ ባለፉት አራት ዓመታት ካላት ስኬት አንጻር ሲመዘንም ያቀደችውን ወደ መሬት ለማውረድ ብዙም እንደማትቸገር መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ በትግራይ ሙሉ በሙሉ ሰላም መስፈኑ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ በመላ አገሪቱ እንዲተገበር አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም