አገራችን ብዙ ዋጋ ካስከፈለን ጦርነት ወጥታ የሰላም አየር መተንፈስ ከጀመረች ወራቶች ቢቆጠሩም፤ ጦርነቱ ከፈጠረው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነልቦናዊ ስብራቶች በአግባቡ አላገገመችም። ከነዚህ ስብራቶች ለማገገምም ብዙ የቤት ሥራዎች ይጠብቋታል።
በጦርነት የወደሙ ማኅበራዊ መገልገያ ተቋማትን ጨምሮ፣ የመሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት፤ በጦርነቱ የልብ ስብራት የደረሰባቸውን ዜጎች ሕይወት ወደ ቀደመ ቦታው እንዲመለስ ለማድረግ የሚደረገው ሀገራዊ ጥረት በብዙ መልኩ ለሀገርና ለሕዝብ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሆን ይታመናል።
በተለይም አሀገሪቱ ላለፉት አምስት ዓመታት ካለፈችባቸው የፈተና መንገዶች፣ እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከወደሙ አያሌ ምጣኔ ሃብታዊ ሃብቶች አንጻር፤ እነዚህን ስብራቶች አክሞ ለመሻገር ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልጋት ተደጋግሞ እየተነገረ ነው። ይሄን ሁሉ ሀብት ደግሞ በሀገር ውስጥ ብቻ ማሰባሰብና ማግኘት የሚቻልበት ዕድል ባለመኖሩ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ተደጋጋሚ ጥሪዎች እየተደረጉ ነው።
መንግሥት ፈተናዎችን ተሻግሮ የቤት ሥራዎቹን ለመወጣት ጦርነቱን በውይይት/በሰላም ስምምነት እንዲቋጭ ከማድረግ ጀምሮ፤ በጦርነቱ ወቅት እና ከዚያም በፊት ሆነ በኋላ እንደሀገር ሲፈታተኑን የኖሩ እና ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።፡ በዚህም ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየታዩ ነው ።
በተለይም እንደሀገር አንገት የሚያስደፋን ተመጽዋችነት ለዘለቄታው ከላያችን ላይ ለማውረድ በምግብ እህል እራሳችንን ለመቻል የሚረዱ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ለዚህም የበጋ ስንዴ እርሻን ጨምሮ በስንዴ፣ ሩዝ እና ሌሎችም አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እየተገኘ ያለው ስኬት ተጠቃሽ ነው።
ይሁን እንጂ ለዓመታት ብሔራዊ ክብራችንን እየተገዳደረ የሚገኘውን ተመጽዋችነት ከሀገራችን ስምና ከሕዝባችን ጫንቃ ላይ ለመጣል የሚደረገው ጥረት፤ በይቻላል መንፈስ ሀገራዊ መነቃቃትን በመፍጠር ብዙ መሥራት/መልፋትን የሚጠይቅ እንደሆነ ይታመናል።
ዓለም አቀፉም ኅብረተሰብም ቢሆን በኢትዮጵያ የታየው ሀገራዊ መነቃቃቱ የፈጠረው ስኬት ለሌሎች ሀገራትን ሕዝቦችም የነጋቸው ተስፋ ሰጪ ተሞክሮ መሆኑን በመገንዘብ ተገቢውን ድጋፍ መስጠት ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያ እንደ አገር ከመጣችባቸው የፈተና መንገዶች አንጻር ይህን የማድረግ የሞራል ግዴታም አለበት።
በተለይም ከትናንት ያደሩ የቤት ሥራዎቻችንን፣ ብሩህ ነጋችንን ታሳቢ አድርገን ዛሬ ላይ ለምንሠራቸው ሥራዎች ተግዳሮት እንዳይሆኑ እና ወደ ኋላ እንዳይመልሱን ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከፍ ያለ ኃላፊነት ይጠበቅበታል። ይሄ ኃላፊነትም ነገን ብሩህ ለማድረግ የተጀመረውን ሀገራዊ መነቃቃትን ከመደገፍ እና ለስኬቶቹ እውቅና ከመስጠት የሚጀምር ነው።
ከዚህ ውጪ ጥቃቅን ክፍተቶችንና የጥቂቶች እንከኖችን በመፈለግ እነዚህን እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሕዝባችን እራሱን ለመሆን የጀመረውን መነቃቃት የሚያደበዝዙ፤ ብሔራዊ ክብሩንና ሥነልቦናውን የሚጎዱ ተግባራትን በአደባባይ መፈጸም ከሁሉም በላይ የሞራል ተጠያቂነት መፍጠሩ የማይቀር ነው።
በዚህ ረገድ በተለይም ተረጅነትን አሸንፎ ለመውጣት እያደረግናቸው ያሉ ብሔራዊ ጥረቶች ተስፋ ሰጭ እየሆኑ ባለበት ወቅት፤ የርዳታ እህል ተሰርቋል በሚል ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውሉ የርዳታ አቅርቦቶችን በማቋረጥ ተረጂ ዜጎችን ለከፋ አደጋ ተጋላጭ ማድረግ ተገቢ ያልሆነ የሞራል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ስህተት ነው።
በርግጥ በችግሩ ዙሪያ ክስ የሚሰነዝሩ አካላት ከክሳቸው በስተጀርባ እውነት ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡ ይህ ሊረጋገጥ የሚችለው ግን “ከሳሽና ተከሳሽ” በሚያቀርቡት ሃሳብ ላይ ተመሥርቶ በገለልተኛ አካል በሚደረግ ማጣራት ብቻ ነው። እነሱ ከሳሽ እነሱ ዳኛ በመሆን የሚደርሱበት ውሳኔ ግን በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።
ተቋማቱ የርዳታ አቅርቦቶችን በራሳቸው ተቋማዊ አደረጃጀት ለተረጂው ሕዝብ የሚያቀርቡበት አሠራር ባለበት ሁኔታም አንድን አካል/መንግሥትን በተናጠል ተጠያቂ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ በራሱ ችግሩ ግልጽነት የጎደለው ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ችግሩ እንኳን ተፈጽሞ ቢሆን ተገቢውን ተጠያቂነት ማስፈን የሚያስችል አይደለም።
ምክንያቱም በሀገሪቱ ለሚገኙ ተረጂዎች የሚቀርበው የእርዳታ አቅርቦት ባልተገባ መንገድ እንዲቋረጥ ያደረጉ ተቋማት፤ ከሁሉም በፊት በችግሩ ዙሪያ ተገቢውን ማጣራት ከሚመለከታቸው የፌደራል ሆነ የክልል መንግሥታት ጋር በማድረግ ለችግሩ ባለቤት ሊሰጡ ይገባ ነበር። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ቀደም ሲል ክሱን ለመመርመር ካቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት የሚያስችላቸው የተመቻቸ ሁኔታ ነበር።
ከዚህ ውጪ እራሳቸው ከሳሽ እና ዳኛ ሆነው አሁን ላይ በርዳታ ፈላጊ ዜጎቻችን ጉሮሮ ላይ የወሰኑት የርዳታ አቅርቦቶችን የማቋረጥ ውሳኔ ከተቋማቱ ተልዕኮ ጋር የማይጣጣም፤ ከጉዳዩ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸውን ቀድሞውንም የችግሩ ሰለባ የሆኑትን ተረጂ ዜጎችን ለተጨማሪ አደጋ የሚዳርግ ነው።
በመሆኑም በመጀመሪያ ደረጃ፣ እነዚህ የእርዳታ ተቋማት ካለባቸው ዓለም አቀፍ ኃላፊነት አንጻር ተፈጠረ ለተባለው ችግር ባለቤት ለማግኘት መንግሥት ካቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ጋር ተቀናጅተው ለመሥራት እራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። በሁለተኛ ደረጃም፣ የደረሱበት ያልተገባ ውሳኔ ችግሩ የማይመለከታቸውን ዜጎች ያለ ኃጢያታቸው መቅጣት በመሆኑ ውሳኔውን ዳግም ሊያጤኑት ይገባል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም