ወንጀል ማኅበራዊ ክስተት እንደመሆኑ መጠን በማናቸው ጊዜ ሲፈፀም ቅጣት የማይቀር ሆኖ ይመጣል፡፡ የቅጣት አወሳሰንን ወጥና ትክክለኛ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ (manual) ወጥቶ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ በሕግ አውጭው በተወሰነው መሰረት በሀገራችን የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል በ2002 ዓ.ም. መመሪያ ቁጥር 1/2002 ወጥቶ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ መመሪያው የቅጣት ወጥነትና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው ቢሆንም ውስንነቶችና ክፍተቶችም ነበሩበት፡፡ በመሆኑም ውስንነቶቹንና ክፍተቶችን ለመቀነስ በጥናት ላይ በመደገፍ በ2006 ዓ.ም. የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 ወጥቶ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የተሻሻለው መመሪያ የቅጣት ተገማች፣ ወጥነት እና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ቢኖርም የሕግ ባለሙያዎችም ሆኑ የፍርድ ቤት ሂደትን የሚከታተሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መመሪያው አሁንም ውስንነቶችና ክፍተቶች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡
የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያው ያስገኛቸው ጥቅሞች፣ ክፍተቶቹና ተግዳሮቶቹ እንዲሁም ወደ ፊት ሊከተላቸው ስለሚገባ አቅጣጫ በተመለከተ ከፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ተወካይ የሆኑትን አነጋግረናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑና መመሪያውን በማዘጋጀት ሂደት በዋናነት የተሳተፉትን በማነጋገር ሀሳባቸውን አቅርበናል፡፡
አቶ ታምራት ኪዳነማርያም የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያዎች ማህበርን ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም. በፕሬዚዳትነት መርተዋል፡፡ በዓቃቤ ሕግነት እና በዳኝነት አገልግለዋል፡፡ ለብዙ ዓመታት በማናቸውም ፍርድ ቤቶች ጥብቅና ለመቆም የሚያስችል ፈቃድ ያላቸው ጠበቃ በመሆን ሠርተዋል፡፡
አቶ ታምራት በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‹‹የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ከመውጣቱ በፊት በተለያዩ ዳኞች ፊት የሚቀርቡ ተመሳሳይ አይነት ጥፋት ያጠፉ ወንጀለኞች በተመሳሳይ አይነት ሁኔታ ላይ ያሉ ሆነው የተለያዩና አልፎ አልፎ በጣም የተራራቁ ቅጣቶች ይሰጡ ነበር፡፡ የዳኞች ማዘንና አለማዘን ቅጣት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ነበረው፡፡ መመሪያው ከወጣ በኋላ አንድ ወንጀል የፈፀመ ሰው በተለያዩ ዳኞች ፊት ቀርቦ ቅጣት ሲወሰንበት የነበረውን ልዩነት አጥብቦ አቀራርቦታል፤ የዳኞችን ሥራ አቅልሎ እንደ መደመርና መቀነስ የማስላት አይነት አድርጎታል፡፡
አሁን ድረስ ካሉበት ክፍተቶች አንደኛው የሰፋና የተንዛዛ ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶችን ዘርዝሮ የማስቀመጥ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ለእያንዳንዱ ወንጀል ማክበጃና ማቅለያ ከመሥራት ይልቅ ለሁሉም የሚሆን ማክበጃና ማቅለያ ከተፃፈ በኋላ የእያንዳንዱ ዋጋ ስንት እንደሆነ ቢቀመጥ፤ ያልተፃፈላቸውን ደግሞ ዳኛ ዋጋ ሰጥቶ አስቀምጦ ቅጣት እንዲጥል ሥርዓት ባለው መንገድ መጠነኛ ሥልጣን ቢሰጥ የተሻለ አሠራር ይሆን ነበር፡፡ ይህን ሀሳብ መምህርና ጠበቃ የሆኑት አቶ ኑሩ ሰይድ በ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ባሳተመው ጆርናል ላይ አቅርበውታል፡፡ ሁለተኛው ሕግ አውጪ ያወጣውን ሕግ በተግባር ሲያሻሽል ይታያል፤ ለምሣሌ በሕጉ ከባድ ወንጀል በማለት መነሻ ወለሉን አንድ ዓመት ብሎት ከሆነ በመመሪያው ያንኑ ምክንያት ጠቅሶ ወንጀሉ ከባድ ከሆነ ተብሎ ከሕግ አውጭው ከፍ አድርጎ አውጥቶ የሚገኝበት ሁኔታ አለ፡፡
አንድ ምክንያት እየተደጋገመ ተጠቅሶ ቅጣትን መልሶ ማክበድ (መቆለል) የለበትም፤ ይህ የሕግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፤ ተከሳሾችን ይጎዳል፡፡ የወንጀል ሕጉ ሲወጣ ዋና ዓላማና መርህ ያደረገው መበቀል ሳይሆን አርሞና አስተምሮ ጥሩ ዜጋ አድርጎ ወደ ኅብረተሰቡ መመለስ ነው፡፡ አንድ ችግር እቀርፋለሁ ተብሎ ሌላ ችግር ከሚያመጣ መፍትሔ የተባለውን ለጊዜውም ቢሆን ማዘግየት ይሻላል፡፡
ሌላው የሚጠቀሰው ደግሞ አንድ የማክበጃም ሆነ የማቅለያ ምክንያት ዋጋው አንድ ብቻ ነው፤ አንድ ምክንያት ክብደቱ ከፍተኛ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ካለ ለዳኞች መጠነኛ ነፃነት ሰጥቶ ሁለትም ሦስትም ዋጋ መስጠት እንዲችሉ ሥርዓት ቢዘጋጅለት መልካም ነው፡፡ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ሲሻሻል በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያሉ የሚመለከታቸውን ምሁራንን ያካተተ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር የሚገኝ ጉዳዩን የሚከታተል ባለቤት የሚሆን ክፍል ቢኖረው ለሥራው መሳለጥና በጥናት ላይ የተደገፈ እንዲሆን ያግዛል›› ብለዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ጌታቸው በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ዓቃቤ ሕግ በመሆን ሠርተዋል፤ አሁን ደግሞ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማጽደቅና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት ባልደረባ ናቸው፡፡ በወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ላይ ያላቸው አስተያየት ሲያብራሩ ‹‹በወንጀል ድንጋጌዎች ላይ የተቀመጠው የቅጣት መጠን ልኬቱ ሰፊ ነው፡፡ ከ1-5፣ 5-10 እና 5-15 ዓመት እያለ ለፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ለተመሳሳይ ወንጀል አፈፃፀም፣ ማቅለያና ማክበጃ ምክንያት ቅጣት ሲጣል አተገባበሩ ከዳኛ ዳኛ፣ ከችሎት ችሎት፣ ከፍርድ ቤት ፍርድ ቤት የተለያየ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ቅጣቶች ግልፅ፣ ተቀራራቢ እና ተገማች እንዲሆኑ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኗል፡፡
በወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 ቅጣቶች ግልፅ፣ ተቀራራቢ እና ተገማች እንዲሆኑ ለተወሰኑ ወንጀሎች ቢሆንም ደረጃ መውጣቱ፤ ደረጃ ላልወጣላቸው ወንጀሎችም በምን መልኩ ደረጃ እንደሚወጣላቸው ያስቀመጠው አካሄድ ስላለ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነበር፡፡ በተሻሻለው መመሪያ ቁጥር 2/2006 ላይ መጠነኛ ቢሆንም መካተት ይገባቸዋል የተባሉ ወንጀሎች ቀርበዋል›› ብለዋል፡፡
አቶ ሰለሞን አክለውም ‹‹የቅጣት አወሳሰን መመሪያው ክፍተቶችም አሉበት፡፡ ክፍተቶች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የቃላት አጠቃቀሞች ግልጽ ያልሆኑባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ለምሣሌ የወንጀል ሕግ 540 ላይ ‹የሟች ድርጊት መንስኤ ከሆነ..› የሚል አለው፡፡ መቼ? የሚለው ግልጽ ስላልሆነ ሊሞት ሲል ነው ወይስ ከዚያ ቀደም ብሎ የሚለው ለትርጉም የተጋለጠ ነው፡፡
በወንጀል ሕጉ 693/2 ላይ በቸልተኝነት ደረቅ ቼክ ማውጣት አንድ ደረጃ ያለው ነው፡፡ በቸልተኝነት አስር ሺ የፃፈ፣ አንድ ሚሊዮንም ሆነ አስር ሚሊዮን የፃፈውን ሁሉንም ተመሳሳይ አድርጎ በአንድ ደረጃ ያያል፤ እንደ ገንዘቡ መጠን ደረጃዎቹ ሁለትና ሦስት ቢሆኑ ተገቢ ይሆናል፡፡ በሙከራ ደረጃ የቀሩ ወንጀሎች ከቅጣት ማቅለያ አንፃር ምን ያህል እንደሚቀሉ የቀረበ ማቅለያ የለም፡፡ አንዳንድ ዳኞች አንድ፣ ሁለት እና ሦስት እርከን ይቀንሳሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ‹ሙከራ አያስቀንስም› ብለው በተመሳሳይ ጉዳይ የተለያዩ ውሣኔዎች ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ የወንጀል ድንጋጌዎች ለምሣሌ ‹ከስድስት ወር በማያንስ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ እስራት ያስቀጣል› የሚሉ አሉ፤ በመመሪያው ማቅለያ ሲወሰድ ልዩ ሕጉ ካስቀመጠው መነሻ በታች በመውሰድ የሚወሰንበት ሁኔታ አለ፡፡ በመመሪያ ቁጥር 2/2006 ላይ እርከን ያልወጣላቸውን ፍርድ ቤት ደረጃ ሲያወጣ ‹ቸልተኝነት ነው ወይስ ሆን ብሎ፤ የሚለውን የሐሳብ ክፍላቸውን ያያል› ይላል፡፡ ይህ ነገር ደግሞ የወንጀል ማቋቋሚያ ነው፡፡ የወንጀል ማቋቋሚያ የሆነን ነገር የቅጣት ደረጃ ምክንያት ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡
የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ በባህሪው በየጊዜው ያጋጠሙ ችግሮችን በጥናት በመለየት ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልገው ስለሆነ ቋሚ ባለቤት ያስፈልገዋል፡፡ ስለሆነም ተቋማዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ባለቤት ካለው ብዙ የወንጀል ድንጋጌዎች ደረጃና እርከን ይወጣላቸዋል፤ እስከ አሁን የወጡት ሩብ እንኳን አይሆኑም፡፡ ደረጃ ላልወጣላቸው ብቻ ሳይሆን ‹በመመሪያ ቁጥር 2/2006 ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ምንድን ናቸው?› ተብሎ ተጠንቶ ባለድርሻ አካላት ሀሳባቸውን አንሸራሽረው የተሻለ የሚባለው ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቶ በመመሪያው ውስጥ እንዲካተት ተደርጎ የተሻለ ፍትሃዊነት ማምጣት ይቻላል›› ብለዋል፡፡
ዳኛ ፋሲካ አበራ በዓቃቤ ሕግነት አገልግለዋል፤ አሁን በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ናቸው፡፡ እርሳቸውም በመመሪያው ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‹‹ተመሳሳይ ለሆኑ ወንጀሎች ቅጣት ተገማች መሆን ሲገባው ከዳኛ ዳኛ የሚጣለው ቅጣት የተለያየ ነበር፡፡ በ2002 ዓ.ም. መመሪያው ሲወጣ ለተመሳሳይ ወንጀል ተቀራራቢ ቅጣት የመወሰን ሁኔታ አምጥቷል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ቅጣት ተገማች እንዲሆን አድርጓል፤ የዳኞችንም ሥራ አቅሏል፡፡ መመሪያው የማይዳስሳቸው ቦታዎችን አንድ ዳኛ ምንን ተከትሎ ነው ቅጣትን ሊወስን የሚችለው የሚለውን ተገቢ አካሄዶችን አስቀምጧል፡፡ ይህ ይሁን እንጂ መመሪያው የተወሰኑ ውስንነቶች ነበሩት፡፡ ለምሣሌ በፍርድ ቤት ውስጥ ተደጋግመው የሚቀርቡ ወንጀሎች እርከንና ደረጃ አልወጣላቸውም ነበር፤ ደረጃና እርከን ላልወጣላቸው ወንጀሎች እንዴት ቅጣት እንደሚጣል የነበረው ገለፃ አጠር ያለ ነበር፤ መነሻ ቅጣቶችን በተመለከተ ምን ሁኔታዎች መታየት አለባቸው የሚለው አልነበረውም ›› ብለውናል፡፡
ዳኛ ፋሲካ ተሻሽሎ በ2006 ዓ.ም. ስለወጣው መመሪያ ሲናገሩም ‹‹ተሻሽሎ መመሪያው ሲወጣ እርከንና ደረጃ ያልወጣላቸው ወንጀሎች መጠነኛ ቢሆንም ቁጥራቸው ጨምሯል፤ ደረጃ እርከን ላልወጣላቸው ወንጀሎች ምን ምን ሁኔታዎች ይከተላል፣ እንዴት ነው ቅጣት የሚጣለው የሚለውን ዝርዝር ሁኔታዎች አቅርቧል፡፡ መነሻ ቅጣቶችን በተመለከተ ምን ሁኔታዎች መታየት አለባቸው የሚለውን አካቶ አቅርቧል፡፡ እነዚህ ነገሮች በመካተታቸው ቅጣቶች የበለጠ ተገማች ሆነዋል፡፡ የቅጣት ውሣኔዎች የበለጠ ተቀራራቢ ሆነዋል፡፡ ለዳኞችም ሥራቸውን አቅሏል፡፡
ይሁን እንጂ በሥራ ሂደት የሚታዩበት ክፍተቶች አሉበት፡፡ አሁንም ተደጋግመው ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ወንጀሎችን ለምሣሌ የገቢና ጉምሩክ ወንጀሎችን እንደ ደረሰኝ አለመቁረጥ፣ ታክስ ማጭበርበርና መሸሸግ የመሳሰሉትን አላካተተም፤ እንዲሁም እርከን አወሳሰን ላይ ለአንድ ማቅለያ ወይም ማክበጃ ምክንያት አንድ እርከን ብቻ መያዙ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም ተደጋግመው ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ወንጀሎችን ወደፊት በሚሻሻለው መመሪያ ማካተት ይገባል፤ እርከን አወሳሰን ላይ ለአንድ ማቅለያም ሆነ ማክበጃ ምክንያት አንድ እርከን ብቻ መሆኑ ቀርቶ እንደ ምክንያቱ ክብደት ሁለትም ሦስትም እርከን የሚሆንበት ሥርዓት ያለው አሠራር እንዲኖር ቢደረግ የተሻለ ነው›› ሲሉ ከመከሩ በኋላ፤ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያው የፍትህ ሥርዓቱ ቁልፍ እና የፍርድ ቤት ሥርዓትን የሚመራ መሆኑን ያስታውሳሉ፤ የወንጀል ባህሪዎች እንደየወቅቱ ሊቀያየሩ የሚችሉ መሆናቸውን አመልክተው ጉዳዩን የሚከታተለው ባለቤት ኖሮ፣ የሚመለከታቸው የሕግ ባለሙያዎች በኮሚቴነት ተካተውበት በየጊዜው መመሪያውን ማሻሻል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዳኞች ቅጣትን በዘፈቀደ ሳይሆን የሚወስኑት መመሪያን ተከትለው፣ ተጠያቂነት ባለው ሁኔታ የሚወስኑ መሆኑን ለኅብረተሰቡ ዕቅድ ተይዞለትም ይሁን በተለያዩ አጋጣሚዎችም ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ዳኛ አልማው ወሌም ሌላው አስተያየት ሰጪ ናቸው፤ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት ለአለፉት አስር ዓመታት በዳኛነት እየሠሩ ይገኛሉ፤ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በተቋቋመው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያን በሚያየው ኮሚቴ ውስጥ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በመመሪያው ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‹‹መመሪያው ከመውጣቱ በፊት ውሣኔዎች ተገማች አልነበሩም፤ ከችሎት- ችሎት፣ ከዳኛ- ዳኛ፣ ከፍርድ ቤት – ፍርድ ቤት ወጥነት ያለው ውሣኔ አይወሰንም ነበር፡፡ አንድ ዳኛ በተመሳሳይ ሁኔታ ያለን ወንጀል ዛሬ የወሰነበትን ቅጣት ትቶ የዛሬ ወር የተለየ ቅጣት ሲወስን ይታይ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2002 ዓ.ም. የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ሲወጣ አንድ ወንጀለኛ ሲከሰስ ምን ያህል ሊቀጣ እንደሚችል መስፈርቶችን አስቀምጦ መገመት በሚያስችል መልኩ ተሠርቶ ጥቅም ላይ በመዋል አገልግሏል›› ይላሉ፡፡
ዳኛ አልማው ወሌ መመሪያውን መሰረት በማድረግ ሲሠራ የታዩ ክፍተቶች እንደ ነበሩ ያስታወሱ ሲሆን፣ ለምሣሌም በተግባር የታየው የስርቆት ወንጀል ላይ ቅጣት የማነስ እንዲሁም በቼክ ላይ የሚፈፀመው ወንጀልና የሚጣለው ቅጣት የተጋነነ መሆንን አንስተውልን ነበር፡፡
እንደ ዳኛ አልማው ወሌም ገለፃ በ2006 ዓ.ም. በተሠራው ማሻሻያ ላይ ጥናት በማድረግ ባለድርሻ አካላትን በተለይ ዳኞችን ሁለትና ሦስት ጊዜ በረቂቁ ላይ በሰፊው በማሳተፍ ተገቢ ግብዓቶች ተገኝተው በተሻለ መጠን የሕግ አውጭው ሀሳብ እንዲጠበቅ በማድረግ ደረጃዎቹ እንዲዘጋጁ ተደርጓል፡፡ መመሪያው ከተሻሻለ በኋላ በተግባራዊ አፈፃፀም ምን ችግር አጋጥሟል? ክፍተቶቹ ምንድን ናቸው? በሚል ጥናት አልተደረገም፡፡ ሌሎች አገሮች ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ እንደገና የተሻሻለውን ያያሉ፡፡ ክፍተቶች ካሉ ያስተካክላሉ፤ በተስተካከለው መሰረት ሥራው እንዲሠራ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ በዚህ ተሞክሮ ያላት አሜሪካ ባለፈው ዓመት የተሻሻለውን በዓመቱ እንደገና በማየት መሻሻል የሚገባውን በማካተት ታሻሽላለች፡፡ በዚህ ሀገር ያለው ችግር ሊከሰት የቻለው የቅጣት አወሳሰኑ ሥርዓትን ተቋማዊ አለማድረግ ያመጣው ነው፡፡ ለዚህ ሥራ ጉዳዩን በተሟላ ሁኔታ የሚመራ በሕግ አግባብ የተቋቋመ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች የተሟላና የሚመራ ሥርዓት ያለው ተቋም ያስፈልጋል፡፡
ዳኛ አልማው ወሌም «ሕግ አውጪ ያወጣውን የማሻሻል ሁኔታ ይታይበታል» ለተባለው ምላሻቸውን ሲሰጡ «መመሪያው በመሰረታዊነት ከሕግ አውጪው መንፈስ መራቅ የለበትም፤ ሕግ አውጪው ያስቀመጠውን እንዳለ በመያዝ በቅጣት አወሳሰን ጊዜ ልዩነትን ሙሉ በሙሉ እንኳን ባያስወግድ በተቻለ መጠን የተቀራረበ ውሣኔ እንዴት ሊወስኑ ይችላሉ? የሚለውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሚሠራ ነው፡፡ በወንጀል ማቋቋሚያነት የተጠቀሰን ምክንያት እንደገና በድጋሚ በመመሪያው በቅጣት ማቅለያነት ወይም ማክበጃነት እንደገና መጠቀም ከቅጣት አወሳሰን መርህ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፤ ይህ ይሁን እንጂ እንደዛ አይነት ችግር በመመሪያው ላይ የለም ብሎ ሙሉ ለሙሉ መናገር አልችልም፤ አልፎ አልፎ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህንን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለማቃለል የሚያስችል መመሪያ በአንዴ ይወጣል ማለት አይቻልም፡፡ በየጊዜው በአተገባበር የሚታዩ ችግሮችን መፈተሽና ጥናት ማድረግ፣ ከባለሙያዎች ጋር መወያየትና የተገኘውን ግብዓት መሰረት በማድረግ በማሻሻል መሥራት ያስፈልጋል›› ብለውን ነበር፡፡
ዳኛ አልማው ወሌም አቶ ኑሩ ሰይድ በ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ባሳተመው ጆርናል ላይ የፃፉትን ማንበባቸውን ገልፀው ‹‹ሕግ አውጪው ማቅለያና ማክበጃ ምክንያቶችን ‹ጠቅላላና ልዩ› በሚል አስቀምጧል፡፡ ሁሉንም ግን ዘርዝሮ አልጨረሰም፤ ይህ ከሕግ አውጭው ብዙም አይጠበቅም፡፡ የቅጣት መመሪያው ላይ ዘርዝረን ለእያንዳንዱ ደረጃ እናስቀምጥለት የሚለው ተነስቶ ታይቷል፡፡ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ታይቶ በወቅቱ ሊሆን የሚችል ሆኖ አልተገኘም፤ ተዘርዝሮም የሚጨረስ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቱ በተቻለ መጠን ማቅለያ ወይም ማክበጃ የሚለውን ይያዝ፤ ዋጋው አንድ ይውጣ ወይም ይውረድ በሚል ተወስኖ ታልፏል፡፡ ወደፊት የሚያሠራ ከሆነ በጥናት ታይቶ ሊወሰድ ይችላል፡፡
‹ለአንድ ከፍተኛም ሆነ ቀላል ምክንያት የሚያዘው ዋጋ አንድ እርከን ብቻ ነው የሚያዘው› በሚል ለተነሳው፤ በእርከኑ ላይ አንዳንዱ ላይ 27፣ 29፣ 31 እያለ ሁለት እርከን ሲሄድ ቆይቶ 31 ብሎ 34 የሚልበት ሁኔታ አለ፡፡ በተግባር ያጋጠመን ስላለ ‹የድርጊቱ አፈፃፀም የሰውየውን አደገኛነትም ሊያሳይ በሚችል ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ከተገነዘበ ወደ አልተፈለገ የቅጣት አወሳሰን እንዳይወስደው ውስን ቢሆንም ከወዲሁ ሰንጠረዙ ላይ አመላክተን እንለፍ› በሚል የተሠራ ሥራ አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከመመሪያው የሚያስወጣ ምክንያት ካለ ሊያሳምን በሚችል መልኩ ምክንያትን ጠቅሶ መወሰን እንደሚቻል መመሪያው ስላስቀመጠ በዚያ አግባብ ቅጣቱን መወሰን ይቻላል›› ብለዋል፡፡
አክለውም ‹‹በቅጣት አወሳሰን መመሪያው ላይ በወንጀል ሕጉ ስለ ቅጣት አወሳሰን የቀረቡ መሰረታዊ መርሆዎች ሊታለፉ እንደማይገባ የተመለከተ ነገር አለ፡፡ በልዩ ሕጉ ትንሹ ቅጣት ‹ይህን ያህል ነው› ብሎ ከተመለከተ የፈለገ ማቅለያ ቢቀርብም ፍርድ ቤቱ ከዚያ በታች መውረድ አይችልም፡፡ መታየት ያለበት በልዩ ሕጉ የተመለከተው የቅጣት መነሻ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ከልምድ ማነስ ሊወስኑ ይችላሉ፤ በይግባኝ ሊታረም የሚችል ነው፡፡
የወንጀል ማቋቋሚያ የሆነን ነገር የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ እንዲሆን ተፈልጎ አይደለም የተቀመጠው፡፡ መጀመሪያውኑ የወንጀል ማቋቋሚያ መሆን አለመሆናቸው ፍርድ ቤቱ እንዲለይ ነው፡፡ ከዚያ አፈፃፀሙ ምን ያህል ቀላል፣ ከባድ እንደሆነ በመለየት ቅጣት እንዲወስን ነው፡፡ በመሆኑም ‹ሆን ተብሎ ነው የተፈፀመው ወይስ አይደለም፤ በቸልተኝነት ነው የተፈፀመው ወይስ አይደለም› የሚለውን እንዲያገናዝብ እንጂ እንደገና የቅጣት ማቅለያ እንዲያደርገው አይደለም፡፡ የቅጣት ማቅለያ ተብሎ የወንጀል ሕጉ ላይ የተመለከቱትን ነገሮች እንደገና ቅጣት ሲወስን መልሶ የሚይዝበት ወይም ዋጋ የሚሰጥበት አግባብ አይኖርም፡፡ መመሪያው ላይ ይህን አመላክተን ነው ያለፍነው፡፡ የዳኞች የመረዳትና የአፈፃፀም ችግር እንጂ የመመሪያው ክፍተት ወይም ከዋናው ሕግ በወጣ መልኩ ለዳኞች ስለሰጠ አይደለም፡፡
መመሪያውን ስንሠራ ቃላትን በተመለከተ የተቸገርንባቸው ቦታዎች አሉ፤ ግልፅነት የሚጎላቸውም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ‹በደም ፍላት› ሰው መግደል የሚል አሻሚ ነው፡፡ አንድ ሰው በደም ፍላት ሰው ገደለ ሲባል በንግግር ሊሆን ይችላል፤ በድርጊት ሊሆን ይችላል፤ ይህን ለዳኛው የተውነው አለ፡፡ ይህ ይሁን እንጂ ለዳኞች ማሰሪያ የሆነ ሐተታ ምክንያት ማቅረብ የሚል አለ፡፡ ‹የሟች ድርጊት መንስኤ ከሆነ የሚለው መቼ? በሚል ለትርጉም የተጋለጠ ነው› በሚል የተነሳው ቀደም ሲል ሊሆን አይችልም፤ ቀደም ሲል ከሆነ ገዳዩ ሟችን የገደለው ቂም ይዞ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ 540 ላይ ሊወድቅ የሚችልበት አግባብ የለውም፤ ቂምን መሰረት አድርጎ የተፈፀመ በማለት ከባድ የሰው አገዳደል ወደሚለው 539 ነው የሚሄደው፡፡ 540 ላይ የሚወድቀው ተራ የሆነ የሰው ግድያ በዕለታዊ ፀብ ሊፈፀም የሚችል ሲሆን ብቻ ነው» ብለዋል፡፡
ዳኛ አልማው ወሌ ቀጥለውም ‹‹በቸልተኝነት ደረቅ ቼክ ማውጣትን በተመለከተ ስለ መሸሸግ የሚለውን ደረጃ ስናወጣ አይተነዋል፡፡ ‹በቸልተኝነት የተፈፀመ ሆኖ የገንዘብ መጠኑ ግን ሊለያይ ይችላል፤ የገንዘብ መጠኑን መሰረት በማድረግ የቅጣት መጠኑንም በዚያው ልክ ከፋፍሎ ማየት ይገባል› የሚለውን አስተያየት በመቀበል እንደክፍተት በማየት ወደ ፊት ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል፡፡
‹በሙከራ ደረጃ የቀሩ ወንጀሎች ከቅጣት ማቅለያ አንፃር የቀረበ ስለሌለ የተለያየ ውሣኔ ይሰጣል› በሚል የተነሳው ችግሩ በተግባር የሚታይ ነው፡፡ መመሪያ ቁጥር 1/2002 ለሙከራ ምን ያህል ማስቀነስ እንዳለበት አስቀምጦ ነበር፡፡ በኋላ ስናጠናው ‹ህጉ በመደቡ ይቀጣል› ይላል፤ በማቅለሉ ሂደት ደግሞ አንቀፅ 27 ንኡስ አንቀፅ 3 ላይ ‹ፍርድ ቤት በመሰለው ማቅለል ይችላል› በሚል ለፍርድ ቤት ሰፊ ሥልጣን ያለው መሆኑን ስለሚያሳይ በዛ አግባብ ቀርፀን ብናልፍ ይሻላል በሚል በመመሪያ ቁጥር 2/2006 አልፈን ተውነው፡፡ አሁን ‹ዳኞች ባልተገባ ሁኔታ እየያዙት ነው፤ በተመሳሳይ ጉዳይ ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች የቅጣት መጠኑ የተለያየ እየሆነ ይታያል፤ ማሰሪያ የሆነ ነገር ያስፈልጋል› የሚል ሐሳብ በባለሙያዎች እየተገለፀ ይገኛል፡፡ አሁን በጥናቱ ላይ አልተካተተም፤ ለወደፊቱ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ተገቢ ሥራ መሥራት ይገባል እላለሁ፡፡
የመመሪያው ዋና ዓላማ ፍትህን ሟሟላት ነው፡፡ የተዘበራረቀና ተገማች ያልሆነ የፍትህ ሥርዓት እንዳይኖር መመሪያው አስተዋጽኦ አርድጓል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለውን መመሪያ ለማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ በሂደት ላይ በመሆናቸው በጥናት ላይ በመመስረት መሻሻል የሚገባቸው ተሻሽለው ሥራው ተጠናቆ በዚህ ዓመት ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ለዚህ ሥራ መፋጠን የባለ ድርሻ አካላትን ማሳተፍ ላይ የአስተዳደሩ ግፊትና ቁርጠኝነት ወሳኝነት አለው፡፡ በኮሚቴው በኩል በፍጥነት ለመሥራት ዝግጁ ነን›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር ተፈሪ ገብሩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዳኛ እና የመጀመሪያው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቀረፃን ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር አብረው የሠሩ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ከዳኝነት ሥራቸው በተጨማሪ በጠቅላይ ፍርድ ቤት በተሰየመው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ሥርዓትን ተቋማዊ ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎች ላይ በሚደረግ ጥናት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው፡፡
በመመሪያው ላይ ሐሳባቸውን ሲሰጡ ‹‹መመሪያው ከመውጣቱ በፊት የቅጣት አወሳሰንን ወጥነትና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ሲባል የወንጀል ሕጋችን ያለበት ጉድለት ምንድን ነው? ቅጣቱ ወጥና ትክክለኛ እንዳይሆን ያደረጉ ድንጋጌዎች አሉት ወይ? የወንጀል ሕጉ ክፍተት ካለው ክፍተቶቹን ሊደፍን የሚችል የፍ/ቤቶች ተግባራዊ አሠራር አለ ወይ? በሚል ጥናት ተደርጓል፡፡ በተደረገው ጥናት ማረጋገጥ የተቻለው የወንጀል ሕጉ ከሆነ ነገር ላይ ተነስቶ ቅጣት ማክበድ ወይም ማቅለል እንደሚቻል ቢነግረንም ከምን ላይ እንደምንነሳ ስለማይነግረን ስለቅጣት መነሻ አወሳሰን ችግር አለበት፤ እያንዳንዱ የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ የሚኖረው አስተዋጽኦ ምን ሊሆን እንደሚችል በተመለከተ በግልፅ የተቀመጠ አልነበረም፤ የፍርድ ቤቶች የ50 እና 60 ዓመት ልምድ የሚያሳያው በተመሳሳይ ጉዳይ፣ ድርጊት አፈፃፀም እና የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ ምክንያቶች ምንም እንኳን አንድ አይነት ቅጣት ይቀጣ ባይባልም ተመሳሳይ የሆነ ቅጣቶች አልነበሩም፡፡
ከሕጉም ከተግባራዊ አሠራሩም ክፍተቶች ስለነበሩ በመሰረታዊ ጥናት ላይ በመመስረት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፍትህ ሥርዓቱን ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው ለማድረግ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መመሪያ ቁጥር 1/2002 ወጥቷል፡፡ በመመሪያ ሥራ ላይ ልምድ ያላቸው አገሮች ‹የመመሪያ ሥራ እያደገ እንዲሁም እየተሻሻለና እያማረ የሚሄድ ነው› ይላሉ፡፡ ልምድ የወሰድንባቸው አገሮች በየዓመቱና በየሁለት ዓመቱ መመሪያቸውን በጥናት በሂደት ያሻሽላሉ፡፡
ሕግ አውጭው ካወጣው የወንጀል ሕግ ጋር የሚቃረንና የተለየ ውጤት ያለው መመሪያ ማውጣት ተገቢና ተቀባይነት የለውም፡፡ በየወቅቱ መመሪያው በጥናት ላይ በመመስረት የሚሻሻለው ሕግ አውጭው ሊደርስበት ካሰበው ዓላማና ግብ ውጭ እንዳይሄድና ወደ ዓላማውና ግቡ ለመቅረብና ለመጠጋት እንዲቻል ነው፡፡ መመሪያ ቁጥር 2/2006 የተሻሻለው በዚሁ መንፈስ ሲሆን አሁን ደግሞ መመሪያ ቁጥር 3 በሚል የማሻሻል ሥራው በሂደት ላይ ስለሚገኝ ያሉትን ክፍተቶች በጥናት ላይ በመመስረት ሊስተካከሉ የሚችሉበት አግባብ ይኖራል፡፡ መመሪያው ሲወጣም ሆነ ሲሻሻል ታሳቢ የተደረጉ ነገሮች ምን እንደሆኑ ጠጋ ብሎ ማየትና ከታች እስከ ላይ ያሉትን ሁኔታዎች መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ሳይጠና የቀረበ አድርጎ ባይወሰድ፤ አላሠራ ያለውን ጥናት ተደርጎ አሁንም መሻሻል የሚችልበት አግባብ መኖሩን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
የቅጣት አወሳሰን የሥራ ክፍልን ተቋማዊ በማድረግ ማደራጀት በተመለከተ ከታሰበበት ቆይቷል፤ ወደ ተግባር ለመቀየር በጥናት በማስደገፍ ዝግጅት ማድረግ የተጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ በመመሪያ አስደግፎ የመሥራት ልምድ የተወሰደባቸው አገራት ለቅጣት አወሳሰን ዝግጅትና ክትትል እራሱን የቻለ ኮሚሽንና ካውንስል በሕግ በማቋቋም ባለቤት ሰጥተውት ይከታተላሉ፡፡ በሀገራችን እስከአሁን እየተሠራበት ያለው አካሄድ ለተወሰነ ጊዜ ባለሙያዎች ይሰበሰቡና ጥናት አድርገው መመሪያ ካዘጋጁ በኋላ የሚበተኑበት ሁኔታ ነበር፤ ይህም በመሆኑ ክፍተቶች ይፈጠራሉ፡፡ ለወደፊቱ ግን ተቋማዊ ማድረጉ ታምኖበት የታሰበው ነገር እራሱን የቻለ ጽሕፈት ቤት ና ኃላፊ ይኖረዋል፤ በሥሩ ተገቢ ባለሙያዎች ይኖሩታል፡፡ አጠቃላይ ዓላማው ሕግ አውጭው ለፍርድ ቤቱ የሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መተግበርና ማስቻል ነው፤ መመሪያው በአግባቡ ተደርጓል ወይስ አልተደረገም? ከወንጀል ሕጉ መንፈስ ውጭ የሆነ ውጤት አስከትሏል ወይስ አላስከተለም? በተግባርስ ምን ያጋጠሙ ችግሮች አሉ? የሚለውን በየጊዜው ማጥናትና ተግባራዊ ማሻሻያ ማድረግ ነው፡፡
ተቋማዊ በሆነ መልኩ መሠራቱ የቅጣት አወሳሰኑን በተመለከተ በየጊዜው መረጃ እንዲሰበሰብ፣ እንዲጠና እና አስፈላጊ የሆኑ የወንጀል ድንጋጌዎች እየተለዩ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ በአጭር ጊዜ ተሻሽለው እንዲዘጋጁ የማድረግ ዕድልን ሰፊ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከቅጣት አወሳሰን መመሪያዎች ጋር የተገናኙ ስልጠናዎችን እና የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን ተከታትሎ መሥራት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊነት ተደርጎ የሚወሰድ ይሆናል፡፡ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የበላይ አስተዳደር የሚወሰን ቢሆንም ጥናቱና ሥራው ተጠናቆ በዚህ ዓመት ተቋማዊ ሆኖ ወደ ተግባር የሚገባ ይመስለኛል›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል በ2002 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ መመሪያው በ2006 ዓ.ም. ተሻሽሎ እስከ አሁን ድረስ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ በመውጣቱ ያስገኛቸው ጥቅሞች አሉ፤ በአፈፃፀም የታዩ ክፍተቶችም አሉ፡፡ በመሆኑም መመሪያውን የማዘጋጀት ሥራ ተቋማዊ በሆነ መልኩ በማደራጀት በዓመት ወይም በሁለት ዓመት መመሪያው ላይ የሚታዩትን ክፍተቶች በጥናት ላይ በመደገፍ ማሻሻል ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ስለሆነ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ተቋማዊ የማድረጉን ጉዳይ በአፋጣኝ ተፈፃሚ እንዲያደርጉ እናሳስባለን፡፡
ዘመን መፅሄት ጥቅምት 2011
ከስሜነህ ደስታ