ሙስና ቅንቅን ነው፤ ቅንቅን ደግሞ ሰላም አይሰጥም:: ሙስናም እንዲሁ ነው፤ የአገርን ኢኮኖሚ ያቆረቁዛል:: ቅንቅን ሲያሳክክ እንጂ በውል አይስተዋልምና የሙስናም አሰራር እንዲሁ ረቂቅ በመሆኑ አገርን ገዝግዞ ለመጣል የሚያስችል አቅሙን ለማዳከም የተዘረጋውን መረብ መበጣጠስ የግድ ይላል:: ይህ ደግሞ የብዙዎችን ትብብር ይፈልጋል::
ዋናው ቁም ነገር ግን ሙስና እንዳይከሰት ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ መገንባት ነው:: ከዚህ አኳያ ሰርቶ መለወጥ የሚፈልግና ከሙስና የጸዳ ትውልድ እንዲኖረን ለማድረግ እንዲሁም በሙስና የተዘፈቀውን አካል አጣርቶ ከማቅረብና ከመከታተል አኳያ ምን እየተሰራ ነው ሲል አዲስ ዘመን የፌዴራል ሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የጸረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴው አባል ከሆኑት ከዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል::
አዲስ ዘመን፡- ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በዚህ ዓመት ምን ጠንካራ ነገር ሰርቷል ከሚለው ጥያቄያችንን ብንጀምርስ?
ዶክተር ሳሙኤል፡– ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው:: በዋናነት የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ ላይ ሥልጠና በመስጠትና ለዜጎች ግንዛቤ በመፍጠር ላይ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ሙስና እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከል ላይ ይሰራል:: ለሙስና መከላከል ያግዛሉ ብለን የቀረጽናቸው ስትራቴጂዎች አሉ::
የሙስና ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን በሁሉም ተቋማት ላይ ማጥናት፣ መለየትና ለእሱ ደግሞ የመከላከያ ዘዴ መዘርጋት አንዱ ስራችን ነው:: ሌላው የሚሾሙ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የመንግሥት ሰራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ካሳወቁ በኋላ ያንን ሀብት በምናረጋግጥበት ጊዜ ችግሮች ካሉ ተጠያቂ ማድረግ ሌላው ተግባር ሲሆን በዚህም እየሰራን እንገኛለን::
ሌላው ሥራችን ሙስና ከመከሰቱ በፊት ሒደት እያለ ማቋረጥ ሲሆን፣ ይህ አስቸኳይ ሙስና መከላከል ተብሎ የሚጠራ ነው:: ይህ ማለት ሙስና ሊሰራ በሒደት ላይ እያለ ከሕዝቡ ለኮሚሽኑ ጥቆማ ስለሚደርሰው ሙስናው ሳይከሰት አስቀድሞ ማቋረጥ ማለት ነው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ስራዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሰሩ ቆይተዋል::
በዚህ ኮሚሽን ብቻ በዚህ ዓመት ወደ 57 የሚሆኑ ጉዳዮች ገና ከጅምራቸው በሒደት ላይ እያለ እንዲቋረጡ ተደርገዋል:: እያንዳንዳቸው ጉዳዮች በብዙ ሚሊዮን ብር ሙስና ሊሰራባቸው ያሉ ጉዳዮች በሒደት ላይ እያሉ ተቋርጠዋል::
አዲስ ዘመን፡- ምን ማለት ነው? ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ በምሳሌነትስ ሊጠቅሱ ይችላሉ?
ዶክተር ሳሙኤል፡- አስቸኳይ የተባለበት ምክንያት ሙስናው ሒደት ላይ እያለ መቋረጡ ሲሆን፣ ይህም በጥቆማ መልክ ለኮሚሽናችን የሚመጣ ጉዳይ ነው:: ለምሳሌ የግዥ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፤ ጉዳዩ ከሙስና ጋር ንኪኪ ያለው ስለመሆኑ በሕዝቡ ጥቅማ ይደርሰንና ጥቆማው አግባብ ነው? ወይስ አይደለም? በሚል የማጣራት ስራ እንሰራለን:: ሒደቱም ከመጠናቀቁና ሙስና ከመሆኑ በፊት ያቆማል:: ይህ እንግዲህ ለእኛ የተሰጠ የ45 ሰዓት ሥልጣን ነው:: ማስቆም ብቻ ሳይሆን ተቋሙ እርምጃ እንዲወስድ እናሳወቃለን:: ብሎም ጉዳዩ ወደሕግ ሔዶ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይደረጋል:: በዚህ ዓመት ብቻ በዚህ አይነት መልኩ ወደ 57 ያህል ጉዳዮችን ማቋረጥ ችለናል::
ለአብነት ያህል ጤና ሚኒስቴር በዚህ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የአጎበር ግዥ እያካሔደ ነበር:: በዚህ የግዥ ሒደት ውስጥ አንድ የቡድን መሪ የማረጋገጫ ሰነድን በማጭበርበር ለተወዳዳሪ ድርጅት አሳልፎ በመስጠቱ ድርጅቱ አሸነፎ ነበር:: ይህ ጉዳይ ሒደት ላይ እያለ ጥቆማው ደረሰን፤ እኛም ጉዳዩን ፈተሽን፤ እንደተባለውም የማጭበርበር ስራ ስለመሆኑ አረጋገጥን:: ይህ በማጭበርበር ሊያልፍ የነበረው ወደ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ነው:: ይህ ለአብነት ያነሳሁት አንድ ጉዳይ ብቻ ነው::
በመሬት በኩል ቢወሰድ በካርታ ማጭበርበር እየተከናወነ ያለ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በሒደት ላይ እያለ እያስቆምን ነው፤ እናስቆማለንም:: ከእነዚህ 57 ጉዳዮች መካከል በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ ፍንትው ብሎ እንዲወጣና ሕዝቡም ግንዛቤ እንዲያኝም ጭምር በምርመራ ጋዜጠኝነት እያሰራን እንገኛለን::
ከሕዝብ በጣም በርከት ያሉ የሙስና ጥቆማዎች ይመጣሉ:: ከበርካታ ጥቆማ ውስጥ የሙስና ፍሬ ነገር ያለው ሆኖ ከተገኘ ለዓቃቤ ሕግ፤ ለፖሊስ ይላካል:: በእርግጥ ከሚመጣ በርካታ ጥቆማ ውስጥ ሙስና የማይሆነው ጥቂቱ ብቻ ሲሆን፣ አብዛኛው ሙስና መሆኑ እርግጥ ነው:: ከጥቂቱ ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው::
ጉዳዩን ለፍትህ ተቋማት አሳልፎ መስጠት ብቻ ሳይሆን የፍትህ ተቋማትንም ጭምር ሌላ ሙስና እንዳይፈጠር መከታተል ሁሉ በኮሚሽኑ ይሰራል:: እንደሚታወቀው ሕግ ማስከበሩ ቀደም ሲል በዚህ ኮሚሽን ሲሰራ የነበረ ነው:: ምርመራ ያለው ደግሞ ፖሊስ ዘንድ ነው:: ክስና ክርክሩ ፍትህ ሚኒስቴር ዘንድ ነው፤ ጉዳዩ በሒደት ፍርድ ቤት ድረስ ይሔዳል:: እንዲያም ሆኖ እኛ አፈጻጸሙን እንከታላለን:: ሪፖርትም እንቀበላለን:: በአገር ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ ስምምነት መሰረት ሪፖርቱን ለሚመለከታቸው እናቀርባለን:: ይህን ስናጤን አሁን በጥሩ ሁኔታ በመሰራት ላይ ይገኛል::
ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል የትውልድ ግንባታ ከመገንባት አኳያ ግን ገና ብዙ ስራ ይጠብቀናል:: ነገር ግን መስራት ካለብን ስራ አኳያ እና ካቀድነው አኳያ መልካም ነው ብለን ወስደናል::
ሌላው ተቋሙን ሪፎርም ከማድረግ አኳያ ብዙ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው:: ኮሚሽኑ አሁን ያለበትን ህንጻ አድሶ መግባት የቻለውም በዚህ ዓመት ነው:: አሁን ያለንበት ህንጻ ከመሰራቱ በፊትም ሆነ ይህ ህንጻ እያለ በዓመት ወደ 21 ሚሊዮን ብር የሚያስወጣ ወጪ ለኪራይ ይወጣ ነበር:: ይህን አሁን ማስቀረት ተችሏል::
ተቋሙ ራሱን በማዘመን ላይ ይገኛል:: እንደሚታወቀው ከዚህ ቀደም ያለንበት ህንጻ የታጨቀው በሀብት ምዝገባ ሰነድ ነበር:: ይህን ሰነድ ሙሉ ለሙሉ ስካን በማድረግ ዲጂታላይዝ ማድረግ ችለናል:: ይህ በጣም ጥሩ ሲሆን፣ የትኛውም ሀብት ማስመዝገብ የሚጠበቅበት ሰው የራሱን ሀብት ባለበት ሆኖ በተንቀሳቃሽ ስልኩ መመዝገብ መቻሉ ነው:: ለምሳሌ አምባሳደር ሆኖ አንድ ሰው ውደ ውጭ አገር ቢሄድ ሰነድ ለመላክ ፖስታ ፍለጋ ውጣ ውረድ ውስጥ መግባት አይጠበቅበትም:: እዛው ባለበት አገር ሆኖ ሀብቱን ማስመዝገብ ይችላል:: በእርግጥ ሰው አስቀድሞ ያለኝ ሀብት ይህ ነው ብሎ ማሳወቅ ነበረበት፤ ይሁንና ይህ ተቋም ግን ምን አለህ በማለት ሲመዘግብ ቆይቷል፤ እየመዘገበም ነው::
አዲስ ዘመን፡- የሀብት ምዝገባ ሒደቱ ዲጂታላይዝ መሆኑ ያመጣው ለውጥ አለ?
ዶክተር ሳሙኤል፡- ከዚህ ቀደም የነበረው ክፍተት የሚፈለገው ዳታ ሙሉ በሙሉ ለመላክ መቸገር ነበር:: በተለይም ጉዳዩን ተራ አድርጎ የማየት ነገር ይንጸባረቅ ነበር:: አሁን ዲጂታላይዝ ማድረጋችን ጥሩነቱ ለአንደኛው መጠይቅ መረጃ በአግባቡ ሞልተን እስካላጠናቀቅን ወደሌላኛው መጠይቅ መሻገር አለመቻላችን ነው፤ ስለዚህ ፎርሙ ራሱ ምላሽ እንድንሰጥ የሚያስገድድ ነው:: በዚህ ሰዓት ግለሰቡ የሚሞላውን መረጃ እያረጋገጠ ነው የሚሞላው:: በመሆኑም የሞላውን ሁሉ የሚሞላው በተጠያቂነት ነው:: በዛ አጋጣሚ የሞላው ነገር ስህተትም ከሆነ ተጠያቂ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- ስህተት የሚሆነው እንዴት ነው?
ዶክተር ሳሙኤል፡– ለምሳሌ አንድ የራሱ የሆነን ቤት ሳያስመዘግብ ቢቀርና በእኛ የማጣራት ስራ ብናገኘው ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ተብሎ ይያዛል:: ስለዚህ የእሱ ሀብት አይሆንም ማለት ነው:: ምክያቱም በሰዓቱ ማሳወቅ ነበረበት:: ስለዚህ ይህ መሆኑ አሰራራችንን ዲጂታላይዝ በማድረጋችንም ጭምር ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ የመረጃ ጥራት ይኖረዋል:: ሌላው ዲጂታል የመሆኑ ጥቅም ከዚህ ቀደም ሰዎች በርቀት ቦታ ላይ ነኝ ወይም ረስቼ ነው የሚሉና መሰል ምክንያችን ያስወግዳል:: በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለው የመረጃ ደህንነት የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን እያዘመንን ነው:: በሙከራ ስንሰራ የቆየን ቢሆንም አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ወደስራ እንዲገባ እያደረግን እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡- የሀብት ማስመዝገብ ስራው ለዓመታት የዘለቀ ነው፤ ዋና ግቡ ሀብት ማስመዝገብ ብቻ ነው? ከዛስ በኋላ ያለው ነገር ምንድን ነው?
ዶክተር ሳሙኤል፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ሀብት መመዝገብና ማሳወቅ መጀመሪያውኑ የእኛ ስራ አልነበረም:: መንግሥት ሕግ አውጥቷል:: ይህ ሀብት የመመዝገቡ ስራ በሰነድ ስላልነበር የምንሰራው እኛ ነን:: በአሁኑ ሰዓት ግን ምዝገባውን ወደዲጂታል ስለቀየርን የሚመለከተው ሰው የሚመዘገበው ራሱ ነው ማለት ነው:: እኛ የሚጠበቅብን ማስታወቂያ ማውጣት ነው:: አዋጁ የሚለው ሀብትህን ማሳወቅና ማስመዝገብ ነው:: ስለዚህ እኛ ደግሞ የፈጠርነው ምቹ ሁኔታ ግለሰቡ ራሱ ሀብቱን እንዲያሳውቅ ነው::
ስለዚህ የእኛ ቀጣይ ስራ የሚሆነው የተመዘገበው ሀብት ትክክል ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ማጣራት ነው:: የሙስና መከላከል ጉዳይ ቁም ነገሩ ይህ ነው:: ለምሳሌ እኔ እንደ አንድ የመንግሥት ኃላፊ የማገኘው የወር ደመወዝም ሆነ ጥቅም በግልጽ ይታወቃልና በባንክ አካውንት ውስጥ የተቆለለ ብር የሚኖረኝ ከሆነ ግን ከየት አመጣህ ሊባል ይገባል:: ዋናው የኮሚሽኑ ስራ የሚያጠራጥሩ ሀብቶች እዚህም እዚያም ሲገኙ ከየት አመጣህ? ማለት ነው:: በነገራችን ላይ አሁንም ቢሆን በዚህ የማጣራት ስራ መጠየቅ የተገባቸውን ግለሰቦች እየጠየቅን ነው:: ለፍትህ ተቋምም ክስ እንዲመሰርቱ እየላክን ነው:: እንዳጋጣሚ የራሱ ሆኖ እያለ ግለሰቡ ያላስመዘገበው ሀብት ካለም እናጣራለን:: ትክክለኛ የሆነ የራሱ ሀብት ከሆነ ደግሞ በማጣራት እንዲያስመዘግብ ይደረጋል:: ለምሳሌ በዚህ ዓመት ብቻ የ 17 ሰው አጣርተን ልከናል:: አምና ደግሞ የ 28 ሰው ልከናል::
አዲስ ዘመን፡- ክትትላችሁ ምን ይመስላል? አጣርታችሁ የላካችኋቸው ሰዎች በአግባቡ ተጠያቂ ሆነዋል?
ዶክተር ሳሙኤል፡- ይህንን መጠይቅ ያለባችሁ የፍትህ አካሉን ነው:: በዚህ ዓመትም በተለይ ትኩረታችን በአመራሩ ላይ ሲሆን፣ ይህን የማጣራት ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን:: በሒደት ደግሞ ወደሰራተኛውም የምንወርድ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ሀብታቸውን በውጭ አገር ይሰውራሉ ይባላልና ይህን የምትከታተሉት እንዴት ነው?
ዶክተር ሳሙኤል፡– በውጭ አገር ያለውም ቢሆን ጥቆማው ከደረሰን ጥናት አካሂደን ምርመራ እናደርጋለን:: ዓቃቤ ሕግ ደግሞ ባለው አሰራር መሰረት ከሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማትና የዓለም አቀፍ ስምምነቶችንም ተጠቅሞ ሀብት የማስመለስ ስራውን ይሰራል:: የእኛ ሚና ግን እያንዳንዱ ተመዝጋቢ ሀብቱን ማሳወቅ፤ ካሳወቀ በኋላ ማረጋገጥ ላይ መስራት ነው:: በዋናነት ደግሞ ለፍትህ አካል የመረጃ ምንጭ ነን::
አዲስ ዘመን፡- በክልል ደረጃ ያለው የሀብት ምዝገባ ምን ይመስላል? አዋጅ ያላወጡ ክልሎችም አሉና እንዴት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል?
ዶክተር ሳሙኤል፡- የሀብት ምዝገባ ሒደቱ በክልል ደረጃም በጥሩ ሒደት ላይ ይገኛል፤ በእርግጥ አዋጅ ያላወጡም ነበሩ፤ በአሁኑ ሰዓት ግን አብዛኛዎቹ እያወጡ ነው:: እስካሁንም አዲስ የተቋቋመውን ክልል ጨምሮ ማለት ነው:: ድሬዳዋ ሲጠቀም የነበረው የፌዴራሉን ነበር:: አዲስ የተቋቋሙትም አሁን ይጀምራሉ:: በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ኮሚሽኑ አዲስ ነው የተቋቋመው:: እስካሁንም ሲሰራ የነበረው በፌዴራሉ ነበር:: ከዚህ አኳያ የሀብት ምዝገባው በየክልሉም እየተከናወነ ይገኛል:: ይህ ደግሞ ለሙስና መከላከል ጥሩ መሳሪያ ነው::
አዲስ ዘመን፡- አስቀድመው እንደጠቀሱት ኮሚሽኑ የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣን የለውም፤ ይህ ስራችሁን በተፈለገው ልክ ለመወጣት እንቅፋት አልፈጠረባችሁም?
ዶክተር ሳሙኤል፡– በብዙ ሰዎች ዘንድ ኮሚሽኑ የቀድሞው ሥልጣኑ ባለመኖሩ አሰራሩን ዘገምተኛ ያደርግበታል የሚል ግምት አለ፤ ይህ ግን ስህተት ነው:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ በእንዲህ አይነት አሰራር እየሰራን ያለነው እኛ ብቻ አይደለንም:: ዓለም አቀፉንም ስምምነት በማማሏት የተቋቋሙ በተለያዩ አገሮች እንደ እኛ አይነት አሰራር የሚከተሉ አሉ::
አሰራሩ ሲቋቋም በሶስት አማራጭ ነው:: አንዱ ሙሉ በሙሉ በሥነ ምግባር ማስተማር፣ ማሠልጠንና ግንባታ ላይ ብሎም መከላከሉ ላይ አተኩሮ የሚሰራና ሙስናን በሲስተም የሚቆጣጠር ነው:: በሲስተም የሚቆጣጠሩ በአብዛኛው የሚስተዋለው በአደጉ አገሮች ነው:: ይህ ማለት እያንዳንዱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዘመናዊ የሆነበት አገር ማለት ነው:: ትንሽ ከዚህ መለስ ያሉት ደግሞ መከላከሉን ይጨምሩበታል:: ሕግ ማስከበሩ ግን ሁሉም ዘንድ ያለ ነው::
ማስተማሩ ላይ እየሰሩ መከላከሉ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ እንደ እኛ አይነት አሰራርን የሚከተሉ አገራት በርካታ ናቸው:: እኛ ሕግ ማስከበሩንም አልተውንም:: እንደማንኛውም ወንጀል የፍትህ ዘርፉ በዚህ ላይ እየሰራ ነው::
በሰው አዕምሮ ያለው ነገር ምርመራውና ክሱ ወደ ፍትህ ዘርፉ በመሄዱ ተቋሙ የተዳከመ ይመስለዋል:: በሙስና መከላከል ስራ ትልቁ ጉዳይና ዘላቂ መፍትሄው የዜጎችን ሥነ ምግባር መገንባት ነው:: ሌብነትና ስርቆትን የሚጠየፍ ትውልድ ላይ ገና በአግባቡ አልሰራንም:: በተለይ እንደ እኛ አይነት ትልቅ አገር መስራት የሚጠበቅባት የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ ላይ ነው:: መንግሥትም ትኩረት እንዲደረግ የሚፈልገውም ሆነ የሚያምነውም በዚህ ስራ ላይ ነው::
አዲስ ዘመን፡- እስካሁኑስ ቢሆን ትውልድ ግንባታ ላይ መስራት ያልተቻለው ለምንድን ነው?
ዶክተር ሳሙኤል፡- በሰዎችም ሆነ በሌላው አካል ጉዳዩ ከመፈጸሙ በፊት መከላከል ላይ ያለው ትኩረት አነስተኛ ነው:: በእርግጥ ሰውም የሚፈልገው ‹‹እከሌ የተባለ ግለሰብ በሙስና ወንጀል ይህን ያህል ተቀጣ›› የሚለውን ነው:: ነገር ግን ዋና መፍትሔ የሚሆነው ዜጎችን በሥነ ምግባር ማነጽ ነው:: እንደሚታወቀው ለኢትዮጵያውያን ይህን ማድረግ የሚከብድ አይሆንም:: ምክንያቱም ባህላችንም ኃይማኖታችንም ለዚህ የሥነ ምግባር ግንባታ ስኬት ደጋፊ መሆን የሚችሉ ናቸውና ነው::
ነገር ግን በዚህ ላይ ኮሚሽኑ ብቻ ሳይሆን ዜጋውም እንደ ዜጋ አብሮ መስራት ሲገባው ኮሚሽኑ ሕግ ማስከበር አብሮ ቢሰጠው በሚል ላይ መረባረቡ ብዙ ወሳኝ ጉዳይ ነው የሚል አተያይ የለኝም፤ ምክንያቱም ችግርን ማድረቅ ከምንጩ መሆን ስላለበት ነው::
ሌላው ሙስና ከተፈጸመ በኋላ ለማስቀጣትና ለመቅጣት ከመሯሯጥ ቀድሞ መከላከል ወሳኝ ነው:: ምክንያቱም ሙስና ከተሰራ በኋላ በወንጀል ማስጠየቁ ወጪው ብዙ ነው:: ሙሰኛው የወሰደውን ገንዘብ ማስመለስ በራሱ ሙሰኛውን ለማስጠየቅ ከሚወጣ ወጪ በታች ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ ቀድሞ መከላከል ላይ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል::
በሥነ ምግባር ግንባታው ላይና መከላከሉ ላይ መስራት የግድ ይላል:: በዚህ ዙሪያ ኮሚሽኑም ራሱ በደንብ አልሰራም:: ኮሚሽኑም ሆነ ሌሎች ፍትህ ተቋማትም የሚረባረቡት መመርመሩና መክሰሱ ላይ ነው:: ይህ ግን በእኔ አተያይ ስህተት ነው:: ፖሊስ በአሁኑ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ እያደረገ እያስከሰሰም ጭምር ነው:: የምርመራ ስራውን እንዲያጠናክር ፖሊስን ማጠናከር ደግሞ ተገቢ ነው:: የምርምራ ስራ በሙስና የታጀበ እንዳይሆን ፖሊሱ ራሱ በሥነ ምግባር የታነጸ እንዲሆንም ማድረግ ያስፈልጋል::
ዓቃቤ ሕጉም ክስና ክርክሩን በብቃት ለመርታት እንዲቻል ሥነ ምግባር ላይ መስራት ተገቢ ነው:: ፍርድ ቤት አካባቢም የሙስናን ሁኔታ በልዩ ትክረት እንዲሰሩ ማድረግ ነው:: ከዚህ ጎን ለጎን በአንዳንድ ዳኞች ዘንድ የሥነ ምግባር ችግር እንዳይኖር ማድረግ ወሳኝ ነው:: ምክንያቱም በፖሊሱም በዓቃቤ ሕጉም ሆነ በዳኛው ዘንድ ሥልጣኑ ስላለ አንዳንዱ በሌላ አካል እጁ እንዳይጠመዘዝ ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል:: ስለዚህ ማስተማሩና መከላከሉ ነው ትልቁ ጉዳይ እንጂ ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሥልጣኑ ወደራሱ ተመልሶ ቢመጣ የተለየ ጥርስ አያወጣም:: ሕግ የማስከበር ስራ ከሆነ ተልዕኮ የተሰጣቸው ተቋማት አሉና ያንን እነርሱ ያስፈጽማሉ::
ትውልድን የመቅረጽ ኃላፊነትም ቢሆን በዋናነት ኮሚሽኑ ይስራው እንጂ የኃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ቤተሰብ እንዲሁም መገናኛ ብዙኃንና ሌሎች መሰል ተቋማት ሁሉ አብረው ሊረባረቡበት የተገባው ጉዳይ ነው:: መከላከል ላይ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የየተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ናቸው:: የየራሳቸውን ተቋማት አሰራር በየጊዜው ማሻሻል አለባቸው::
አዲስ ዘመን፡- ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ምን ያህል ተናባችሁ እየሰራችሁ ነው?
ዶክተር ሳሙኤል፡- ብሔራዊ የጸረ ሙስና ኮሚቴ የመቋቋሙም አንዱ ምክንያት እሱ ነው:: ትልቁ ጉዳይ ተቋማት ተቀናጅተው አብረው እንዲሰሩ ነው:: የተዋቀሩ ተቋማት በመረጃ ልውውጥም የሚደጋገፉትም በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ ናቸው:: ኮሚሽኑ፣ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ ኢንሳ፣ ፋይናንስ ደህንነት እነዚህ ተቋማት አንድ ላይ የመጡበት ዋናው ምክንያት ቅንጅት ለመፍጠር ነው:: ጉዳዩ በብሔራዊ ደህንነት የተዋቀረበት ምክንያት በትኩረት መመራት ስላለበት ነው:: ሙስናን ከብሔራዊ ስጋትነት ለማውረድ እየተረባረብን ነው::
የእኛ ተቋም ከፍትህና ከፖሊስ ጋር ያለው ስራ መደበኛ ነው:: ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ግን የእነርሱ ሥራ ነው:: ጠንካራ የምርመራ ሥራ ማካሔድን ይጠይቃል:: አስተማሪ የሆነ የሕግ ማስከበር ስራ ከመስራት አኳያ ድክመት አለ:: ለዚህም ነው ይህን ድክመት ለመቅረፍ ኮሚቴው ተረባርቦ የሙስና መዝገቦችንም በልዩ ሁኔታ ለማየት የሚሰራው::
አዲስ ዘመን፡- ቅንጅቱን የፈጠሩት ትልልቅ ተቋማት ናችሁና የተመዘገበ ውጤት ይኖር ይሆን?
ዶክተር ሳሙኤል፡– የተመዘገበ ውጤት አለ:: አንደኛ የስድስት ወር ሪፖርቱም እንደሚያሳየው በአገር አቀፍም በክልልም ደረጃ በርካታ የምርመራ ሥራ ተሰርቷል:: እየተሰራም ነው:: ሌላው ደግሞ ብዙ መዝገብም ተዘጋጅቶ ክስ ተጀምሯል:: የተወሰኑትንም ወደማስቀጣት እየተደረሰ ነው:: አሁን በተጀመረው ሒደት ተጠናክሮ ከቀጠለ በአገር አቀፍ ደረጃ በጣም ብዙ ጉዳዮችን መቆጣጠር ይቻላል የሚል እምነት አለኝ:: ይህ አሰራር አገሪቱ የተለያዩ ፈተናዎች እያሉባት ለመስራት መሞከር በራሱ ትልቅ ተነሳሽነት ነው:: እንዲያውም በዚህ አጋጣሚ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ሳላመሰግን ማለፍ አልፈልግም:: ብሔራዊ አጀንዳ ሆኖ ሕዝቡም ንቅናቄ የፈጠረበት ጉዳይ ሆኗልና::
አዲስ ዘመን፡- እንደዛም ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርንና ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የሚፈጸሙ ሙስናዎች አሉ፤ ይህን ከመከላከል አኳያስ ምን እየተሰራ ነው?
ዶክተር ሳሙኤል፡- ሙስናን ወደብሔርና ኃይማኖት የማጠጋጋቱ ምስጢር በደንብ ግልጽ መሆን ያለበት ይመስለኛል:: ይህ ሙሰኞች የሚፈጥሩት ስልት ነው:: ሌባ ብሔርም ኃይማኖትም የለውም:: የሚሰርቀው ግለሰብ ነው:: ከሰረቀ በኋላ የዚህ ብሔር፤ የዚያኛው ኃይማኖት ብሎ ነገር መኖር የለበትም:: ሙስና ሰርቶ በየመንደሩ መደበቅም አይቻልም::
የሙሰኛ ብልጠቱ የሚሰርቀው መውጫውን አዘጋጅቶ ነው:: ቢያዝ እንኳ ለማምለጥ የሚያመቸውን ሰበብና ምክንያት አዘጋጅቶ ነው:: ሲፈልገው ስርቆቱን እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ከፖለቲካው ጋር ያያይዛል:: ግለሰቡ የሙስና ወንጀል መፈጸሙ በማስረጃ ከተረጋገጠ ከየትኛውም ኃይማኖት ይሁን ብሔር አሊያም የፖለቲካ ፓርቲ ቢሆን ስለፈጸመው ወንጀል ይጠየቃል::
አዲስ ዘመን፡- አሁኑ አሁን መብትን ወይም አገልግሎትን በገንዘብ እስከመግዛት ተደርሷል፤ ይህስ እስከመቼ ይዘልቃል?
ዶክተር ሳሙኤል፡– መብትን በገንዘብ መግዛት ለተባለው በአንድ በኩል የሕዝብን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ መስራትን ይጠይቃል:: መብት በገንዘብ መግዛት የለበትም:: አልገዛም ብሎ መከራከርም አንድ ጉዳይ ነው:: ተቋማትም ትክክለኛ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው:: መብት ገዥም ሆነ ሻጭ ያልተገባውን አካሔድ ለማስተካከል ኃላፊነት አለባቸው::
ይህን ለማስተካከል በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንም ሥልጠና ጀምረናል:: በዚህም ግንዛቤ እየፈጠርን ነው:: ከዚህ ጋር ተያይዞም የሚደርሱን ጥቆማዎች አሉ:: በተለይ ደግሞ የሙስና መቀበያችንን ዲጂታል አድርገናል:: የትኛውም አካል የትኛውም ስፍራ ሆኖ ያልተገባ ቅብብልን የሚያይ ከሆነ እዛው ፎቶ አንስቶም ሆነ ድምጽ ቀርጾ ሊልክልን ይችላል::
ምንም እንኳ ሁሉም የስልክ ተጠቃሚ ነው ማለት ባያስደፍረንም ጥቂት የማይባል የኢትዮጵያ ሕዝብ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ነውና ያንን ለማድረግ ብዙም አይከብድም:: ነገር ግን ይህ ብቻውን መፍትሔ ነው ለማለት ሳይሆን አንድ አማራጭ ነው:: ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጾች ሁሉ መኖራቸው የሚዘነጋ አይሆንም ማለት ነው:: በአሁኑ ወቅት ብዙዎች ሙስና ሲጠየቁ እየቀረጹ ሐቁ እንዲወጣላቸው ማስረጃቸውን እያደረሱን ነው::
ከዚህም የተነሳ በርካታ ርምጃ በመወሰድ ላይ ነው:: መረጃውን በሚሰጡን ላይ ደግሞ አንዳች ስጋት አይደርስባቸውም:: ተገቢ የሆነ ጥበቃ ይደረጋል:: ስለዚህ መብትን ወይም አገልግሎትን በገንዘብ መሸጥም ሆነ መግዛት ይሉት አባዜ ከዚህ በኋላ ከባድ የሚሆን ነው:: የምናጋልጠውም በቀጥታ ነው:: ለዚህ ማስተማሪያ የሚሆኑ ትምህርትም በመጠናቀቁም ከሰሞኑ በሚዲያ ለመልቀቅ ተዘጋጅተናል::
ሌላው ቀርቶ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ተሰጥቶት በውጭ አገር ያለ ዜጋችንም ያልተገባ ስራ ሲሰራ ቢገኝ እንዲሁ በተፈጠረው ፕላትፎርም ይላክልናል:: በዚህ ወቅት የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚው ቁጥር ወደ 40 በመቶ ያሻቀበ በመሆኑ መረጃ ለመቀባበሉ ብዙም የምንቸገር አይመስለኝም::
አዲስ ዘመን፡- በየተቋሙ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች መቋቋማቸው ይታወቃል፤ ይሁንና አንዳንዴ ያሉበት ተቋም አመራሮች ነጻ ሆነው እንዳይሰሩ የሚገድቧቸው ጊዜ እንዳለ ይነገራልና በጸረ ሙስና ትግሉ ምን ያመጣው ፋይዳ አለ?
ዶክተር ሳሙኤል፡– እዚህ ላይ ጥሩ ነገሩ የሕግ ማዕቀፍ አለ፤ ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ይፈለጋል:: እነዚህ አካላት በየተቋማቱ ያስቀመጥናቸው ትንንሽ ኮሚሽኖች ናቸው ማለት ነው:: በጥያቄ መልክ ያነሳሽው ጉዳይ መኖሩ ትክልል ነው:: የጸረ ሙስና ትግል አመራሩን የትግሉ አካል ሳይደረግ የሚመራ አይደለም::
አንዳንድ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ያለተቋሙ አመራር የሚሄድ አይደለም:: አንዳንድ ክፍሎች ግን ራሳቸውን የተቋሙ ተቆጣጣሪ አድርገው ተቀምጠዋል:: ይህ ግን ስህተት ነው፤ ስራቸው ምንድን ከተባለ ተጠሪነታቸው ለአመራሩ ነው:: አመራሩን ማገዝ ማማከር ነው:: እነሱ እያሰቡ ያሉት የድሮውን ሕግ ማስከበሩን ነው:: ሥራው መሆን ያለበት ሥነ ምግባርን በተመለከተ ሰራተኞች ሥልጠና መስጠት፣ ሀብታቸውን እንዲያሳውቁ ማድረግ፣ አመራሩን ማማከርና ስጋት የሆኑ ሙስናዎችም የት የት ላይ ነው ያሉት? በሚል ማጥናት ነው:: ካጠኑ በኋላ ለአመራሩ ያቀርባሉ:: ሥነ ምግባራቸው የተጓደለ አመራሮች ካሉ ጥቆማ ያደርጋሉ:: ዋናው ግን ማሰልጠንና ክትትል ማድረግ ነው::
ነገር ግን አንዳንዶቹ እየሰሩ ያሉት በዚህ አግባብ አይደለም:: እንደማስፈራሪያ የሚጠቀሙ አሉ:: ይህን አካሄዳቸውን በየጊዜው እያረምን ነው:: በሚፈለገው ደረጃ በአግባቡ እየሰሩ ያሉ መኖራቸው ደግሞ አይካድም፤ ከዚህ አኳያ በስራቸው የሚሸለሙ አሉ:: አመራሩንና ሠራተኛውን የጸረ ሙስናው ትግል አጋር ማድረግ አለባቸው::
አዲስ ዘመን፡- ትራንስፓራንሲ ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩትም ሆነ ሌላው ዓለም አቀፍ ተቋም ኢትዮጵያን ከሙስና አኳያ የሚያስቀምጣት ደረጃ ይመጥናታል ይላሉ?
ዶክተር ሳሙኤል፡– ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሌላው አገር ግምት ነው የሚያስቀምጠው:: በተለይም የኅበረተሰቡን እይታ ነው የሚያስቀምጠው:: ይህ ደግሞ እውነታ ላይሆን ይችላል:: እሱ መረጃ እንደወረደ መወሰድ የለበትም፤ ሰውን የሚያሳስት ነው:: በተለይ በታዳጊ አገራት ጦርነቱ፣ የኑሮ ወድነቱም ጭምር ስላለ እንደማንኛው ዓለምአቀፍ ተነሳሽነት እንዳለው አካል አጥንቶ የራሱን ግምት ያስቀምጣል:: ለምሳሌ አንድ ሰው በኢትዮጵያ ስላለ ሙስና በሚጠይቅበት ጊዜ ያ ሰው በተለያዩ የኑሮ ውድነትና በሌላም ነገር ውስጡ ተይዞ ስለሚሆን ‹‹ሁሉም ሙሰኛ ነው›› የሚል ምላሽ ሊሰጥ ይችላል::…
አዲስ ዘመን፡- …ነገር ግን ይህ ጥናቱ በሰዎች ላይ ተመስርቶ የሚቀርብ ነውና እንዴት ልክ ላይሆን ይችላል?
ዶክተር ሳሙኤል፡– …ሙስና ማለት ወንጀል ነው፤ ትክክለኛ ማስረጃ እስከሌለ ድረስ ተጠያቂው አካል ‹‹ሁሉም ሙሰኛ ነው›› ብሎ የሚናገረው ነገር የሚሆነው አሉባልታ ነው:: ስለዚህ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት:: ነገር ግን አመላካች መሆኑ አይካድም:: ምክንያቱም ሕዝቡ በዛ ልክ ተማርሮ ለምን ይናገራል የሚለው ሲስተዋል አንዳች ነገር እንዳለ ጠቋሚ ነው ማለት ይቻላል::
ነገር ግን በህዝቡ የሚነገረውን መረጃ እኛም አንንቅም:: እኛም ከዚህ በኋላ የሕዝቡን አመለካከት እናጠናለን:: አስቀድሜ የጠቀስኩት በተንቀሳቃሽ ስልኩ ሕዝቡ ያለው እውነታ እንዲያሳውቀን ሁሉ መደላድል ፈጥረናል:: አገራችን ከሙስና የጸዳች ከሆነች የኢንቨስትመንት ፍሰትም በዛው ልክ የሚጨምር ይሆናል:: ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም መልካም የሆነ ነገር ለማድረግ ሲፈልጉ እንደዚህ አይነቶችን መረጃዎች ይመለከታሉና ከሙስና የጸዳች አገር እንድትኖረን ማድረግ የሁላችንም ድርሻ ነው::
ኮሚሽኑ ግን በቀጣይ የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ ላይ የሚያተኩር ይሆናል:: ይህን የሚያከናውነውን ከሕዝቡ ጋር በመሆን ነው:: መከላከል ላይም እንዲሁ በጥልቀት አጠናክረን የምንሔድበት ይሆናል:: የሀብት ምንጭን ደግሞ በጥልቀት ወደማጣራት ስራ እንገባለን:: በየጊዜው የምንደርስበትን መረጃ ደግሞ ለሕዝቡ ይፋ እናደርጋለን:: በተለይ የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታና ብሔራዊ የጸረ ሙስና ፖሊሲ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ተግባራዊ እናደርገዋለን:: የሚሻሻሉ ሕጎችና መመሪያዎችም አሉና እሱን ተግባራዊ እናደርጋለን::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::
ዶክተር ሳሙኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2015