
አቶ አቤ ሳኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት
ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳሉ ነበር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተቆራኙት። የዚያኔ ባንኩ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይማሩበት ከነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምጣት ለተወሰኑ ተማሪዎች የሥራ ቅጥር ቃለ መጠይቅ ያደርጋል። ከእነዚያ ተማሪዎች መካከል ታዲያ እርሳቸው ከሁሉም ልቀው አንደኛ ይወጣሉ። ታላቅ የፋይናንስ ተቋም የሆነውን የኢትዮጵን ንግድ ባንክም ይቀላቀላሉ። የዛሬው የዘመን እንግዳችን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ።
አቶ አቤ፣ በባንኩ መቀጠርና ማገልገል ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ትልቁን የፋይናንስ ተቋም ለመምራት የወሰደባቸው ጊዜ ሰባት ዓመት ከሰባት ወር ብቻ ነበር። ይህ ማለት በኢትዮጵያም ሆነ በባንኪንግ ኢንዱስትሪ ታሪክ በተመረቁ በሰባት ዓመት ከሰባት ወር ብቻ የባንክ ፕሬዚዳንት መሆን የቻሉ የመጀመሪያው ሰው ያደርጋቸዋል ማለት ይቻላል። እርሳቸው ባንኩን የተቀላቀሉት ገና በልጅነታቸው ነው። በመሃል ወደ ኦሮሚያ ባንክ ሔደው ባንኩን ከማቋቋም ጀምሮ ሠርተው ከመመለስ ውጭ ወደሌላ ተቋም አላቀኑም። ገና በለጋ እድሜያቸው ወደተቀላቀሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተመልሰው፣ ዳግም ባንኩን በፕሬዚዳንትነት በማገልገል ላይ ናቸው። አዲስ ዘመንም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከልጅነት እስከ እውቀት በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙትን አቶ አቤ ሳኖን ስለ ባንኩ የሥራ ሒደት እንዲገልጹ በማሰብ እንግዳው አድርጓቸዋል። መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ በባንኩ ኢንዱስትሪ ላይ ያመጣው ለውጥ የሚገለጸው እንዴት ነው? በተለይም ሀገሪቱ የገንዘብ ፖሊሲዋን እስከመቀየር ደርሳለችና ምን አዎንታዊ ለውጥ አመጣ?
አቶ አቤ፡– ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀደም ባለው ጊዜ የፊውዳል ሥርዓትን የምትከተል እንደነበረች ይታወሳል፤ ቀጥሎ የመጣው ደርግም ብዙ ነገሮችን ከማፍረሱ በተጨማሪ በተለይ ለቢዝነሱ ምቹ እንዳልነበር ይታወቃል። በጊዜው ተሞክሮ የነበረውም ሌላ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ነው። ከዚያም በኋላ የገባው ኢሕአዴግም ቢሆን ብዙ የተለየ ነገር ማሳየት አልቻለም።
ወደኋላ ተመልሶ ከ1970ዎቹ ሁሉ የጀመሩ ሕጎች የሚሠሩበት ሁኔታ ነበርና ትንሽ የውጭ ምንዛሬ ማኔጅመንት ፖሊሲው ከብዙ ሀገሮች ጋር ሲተያይ የሀገራችን ወጣ ይላል። ስለዚህ ለየት ማለቱ የእራሱ ምክንያት አለው። እንደሚታወቀው ደግሞ ሕጋዊ ገበያ እና ከሕግ ውጭ ባለው ገበያ መካከል ያለው ትልቅ ክፍተት በመሆኑ በሀገር ላይ ችግር ፈጥሯል። በመሆኑም የሀገራችን ኢኮኖሚ የሚለካው በየትኛው ነው? የሚለው ሲጤን የጠራ ነገር የለውም።
በዓለማችን አቅም ያላቸው ሀገራት የውጭ ምንዛሬ እንደ ሀገራት መለኪያ ይሆናል። ብዙዎቹ የሚለኩት በዶላር ነው፤ ወደነው ሳይሆን በግዴታ የተቀበልነው ጉዳይ ነው። አሜሪካ በዓለም ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደመሆኗ ዶላሯም እንደዚያው ነው። ልክ በዓለም ደረጃ ብዙ ቋንቋዎች ቢኖሩም አንዱ ሀገር ከሌላው ሀገር ጋር ለመግባባት በቀዳሚነት የእንግሊዝኛ ቋንቋን እንደሚጠቀመው ሁሉ ማለት ነው።
ሀገራት ሀብታቸውም ሲለካ ወደ ዶላር ተቀይሮ ነው። ሲገበያዩም እንዲሁ ነው። በሀገራችን ውስጥ በብር እንደምንገበያየው ከሀገራችን ወጣ ስንል ያንን ማድረግ አንችልም። በሌሎች ሀገራት ሕጋዊ ገንዘብ ጥገኛ ነን። ይህ ሆኖ ሳለ ግን አንዱ ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራው ጥቁር ገበያ ተብሎ በሚጠራው ምንዛሬ ነው። ከለውጡ በፊት አንድ ዶላር እስከ 115 ብር ድረስ በጥቁር ገበያ ውስጥ ይመነዘር ነበር። በባንኮች ውስጥ ግን ይመነዘር የነበረው 58 ብር ገደማ ነው። ይህ ሁለት አይነት ገበያ ለመፈረጅ አስቸጋሪነቱን የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከዓለም ጋር ለማወዳደር በጥቁር ገበያው ነው ወይስ መንግሥት ተቆጣጥሮ በያዘው ገበያ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በቁጥጥር ስር ያለውን ነገር ደግሞ የገበያ ዋጋ ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው።
ብዙዎች ከሀገራችን ጋር የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተዓማኒ ነው ብለው የሚወስዱት ጥቁር ገበያውን ነው። እሱን እኛ ጥቁር ገበያ እንበለው እንጂ እሱ ገበያ የሚታሰበው በገበያ ኃይል የተፈጠረ ዋጋ ነው ተብሎ ነው። በባንኮች ያለው ዋጋ ግን በቁጥጥር ውስጥ ያለ ነው። ይህን የገበያ አቅም መንግሥታት ተቆጣጥረው ሽባ ያደርጉታል ብለው ያምናሉ። ምክንያቱም ዓለም አቀፍ ባለድርሻዎች ብዙ ናቸው። ስለዚህ ይህ አካሔዳችን ብዙ ችግር አመጣ። ኢትዮጵያን ሲያይዋትም የሚለኳት በ115ቱ ነው? ወይስ በ58ቱ ነው? እሱ ነገር ልዩነቱ ሰፊ ከመሆኑም በተጨማሪ አካሔዱ ጤናማ አልነበረም።
ወደሀገር ውስጥ ስንመጣ ደግሞ፤ ልዩነቱ በአንድ ገበያ ላይ የሚገናኙ ነጋዴዎች አንደኛው በ115 ብር፤ ሌላኛው ደግሞ በ58 ብር እቃ ገዝቶ ማምጣቱ ነው። ሁለቱም ወጥተው የሚሸጡት አንድ ገበያ ላይ ነው። ይህ ደግሞ በብዙ የሀገሪቱ ሲስተም ላይ የሚፈጥረው ሙስናን ነው። ገበያው ጤናማ ካለመሆኑ የተነሳ ነጋዴው የ58ቱን ለማግኘት ሙስና ሰጥቶም ቢሆን ለማግኘት መጣሩ አይቀርም። የ58ቱን ለማግኘት ሰልፍ ሊኖር ይችላል፤ መሰለፍ ደግሞ የሚያቆይና አሰልቺ ነገር እንደመሆኑ ቀድሞ የማግኘት ፍላጎትን ያመጣል፤ ቀድሞ ለማግኘት ሲባል ምንም አይነት ጠንካራ ሥርዓትና ታማኝ ሠራተኞች ቢኖሩም ሥርዓቱና ታማኝነቱ እንዲጣስ የማድረግ ትልቅ ኃይል አለ። ከዚህ የተነሳ ሕግን ማስከበር አይቻልም።
ስለዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን አሠራር አበላሸ፤ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገራችን መግባት የሚኖርበትን የውጭ ምንዛሬ በትክክለኛው መንገድ እንዳይመጣ አደረገ። በተለይ ሐዋላ በሙሉ ተጠልፎ ወደ ጥቁር ገበያው እንዲገባ አደረገ። በሐዋላ ብቻ አላበቃም፤ የወጭ ንግዳችንም ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ ሆነ። ወደውጭ የሚላኩ እቃዎች የሚገዙት እጅግ በጣም በከፍተኛ ዋጋ ነው። ከዚያ በኋላ ላኪው መጥቶ የሚከፈለው በ58 ብር ነው። ይህ አይነቱ አካሔድ የሚያዋጣ ባለመሆኑ የወጪ ንግድ አክሳሪ ነው፤ ኤክስፖርት ለትርፍ የሚሠራ ሥራ ሳይሆን ዶላር ለማግኘት ሲባል የሚሠራ ሥራ ሆነ።
ስለሆነም ትክክለኛ የወጪ ንግድን የሚሠሩ ላኪዎች ጠፍተው የሚሰማሩት የፋብሪካ ባለቤቶች፣ ለጥሬ እቃቸው የግድ የውጭ ምንዛሬን የሚፈልጉ፤ አሊያም የውጭ ምንዛሬውን ለሌላ ንግዳቸው የሚፈልጉ አካላት ሆኑ። ምክንያቱም ባንኮችም ትርፍ የሚያገኙት ከእሱ ስለሆነ በተቻላቸው አቅም ቅድሚያውን የሚሰጡት የውጭ ምንዛሬ ላመነጩት ነው። የውጭ ምንዛሬ ያመጡት እንደሚከስሩም ስለሚያውቁ ጥረት የሚያደርጉት ለእነርሱ ለመስጠት ነው።
መንግሥትም የውጭ ምንዛሬ እንደሚያመጡ ስለሚያውቅ የተወሰነ ልዩ ጥቅም እንዲያኙ ማለትም ከሚመጣው የውጭ ምንዛሬ መልሰው እንዲጠቀሙ ስለሚፈቅድላቸው እሷን ይጠቀማሉ። 100 አምጥተው 40ውን እንዲጠቀሙ ከተፈቀደላቸው በ100ቶው ላይ የከሰሩትን 40ዋ ላይ ጭነው ለመነገድ ይሞክራሉ። በ58 ብርም ዶላር ያገኘው ገበያው ላይ ዋጋ የሚያወጣው ልክ በጥቁር ገበያ እንዳገኘ አይነት ነው። ምክንያቱም እርሱ ያገኛት የዶላር ድርሻ አነስተኛ ናት። ያገኘው መቶው ላይ ከስሮ 40ውን ነው። ሌላውን በ58 ሸጦ ከስሮበታል። በዚህ የተነሳ ንግዱ ጤነኛ መሆን አልቻለም። የነበረው ከገበያ ሥርዓት የወጣ ንግድ ነው፤ ይህን የገበያ ሥርዓት አስተካክሎ (በእርግጥ ገበያ ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም የነበረው ሁለት ገበያ ነውና) አንድ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ግዴታ ነበር።
ለምሳሌ የብሔራዊ ባንክን ብንወስድ፤ የባንኩ ገዥ የእራሱ ምንዛሬ በግማሽ ዋጋ እንዲያጣ መወሰን አይፈልግም፤ አንዱ የቆየበት ምክንያትም ይህ ነው። ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት ክርክር ሲደረግበትም ነበር። ምክንያቱም ለውጥ ካደረግን ብራችን ዋጋ ያጣል፤ እየቀነሰም ይሔዳል። እሱ ደግሞ በሕዝባችን ኑሮ ላይ ጫና ያመጣል። በተለይ ቋሚ ገቢ ላላቸው ፈታኝ ነው። ቋሚ ገቢያቸው ካልጨመረ የብሩ የመግዛት አቅም ሲቀንስ በተለይ ከውጭ የሚመጡ አገልግሎቶች እና እቃዎች ላይ ዋጋው ይለወጣል።
ስለዚህም ይህንን መቋቋም ከባድ ነው በሚል እንዲቆይ ተደረገ፤ ይሁንና የገበያው መፋለስ እየፈጠጠ በመምጣቱ ሀገራችንን እብድ ወይም ሥርዓት የሌላት ናት ሊያስብላት ቻለ፤ ሁለት አይነት ገበያ ብዙዎችም የሚያስቧት ብሔራዊ ባንክም ሆነ ገንዘብ ሚኒስቴር የሌላት ሀገር አድርገው ነው። ይህ ጉዳይ ለሀገራችን ሰዎች ብዙም ላይገባ ይችላል። ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስንታይ የነበረው ምልክት ጤነኛ ያልሆነ ነው። በመሆኑም ለውጡ ለአማራጭ የሚቀርብ ነገር አልሆነም።
በጊዜ ብዛት ሁኔታዎች አጠራቅመውት የተፈጠረ ውጤትና የደረስንበት ደረጃ ሲሆን፣ ከዚያ በላይ ግን ማዘግየት የምንችለው ነገር አልነበረም። ብዙዎች ግን ይህ ለምን ሆነ? ብራችንን ዋጋ አሳጡት፤ በማለት አማራጭ ኖሮ የተከናወነ ነገር አድርገው ማሰብ ጀመሩ፤ ነገር ግን ይህ ምርጫ ሳይሆን ሁኔታዎች አስገድደው የተደረገ ነገር መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው።
ከብር ለውጡ ጋር በተያያዘ በርካታ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ከሪፎርሙ ውስጥ ለውጥ የተደረገበት የውጭ ምናዛሬ ብቻ አይደለም። አጠቃላይ እየተለወጠ የመጣው የፋይናንስ ማኔጅመንት፣ የመንግሥት በጀት አስተዳደር፣ የፊሲካል ማኔጅመንት እና ሥርዓቱ ሁሉ ነው።
በውጭ ምንዛሬ መራራቅ የተፈጠረው የሁለት ገበያ መከሰት ብቻ ሳይሆን ከዚያ ቀድም ብሎ ያለው የገበያ ግሽበት ሌላው ትልቁ ችግር ነው። 34 እና 35 በመቶ ድረስ የምንዛሬ ዋጋው ሲራራቅ ገበያው ከየት ወዴት እንደሚሔድ የማይታወቅ ሆነ። ነገሮችን ሁሉ በዶላር የመለካት አመለካከት ተፈጥሮም ነበር። የዶላር ዋጋ ጨመረ በተባለ ዕለት ሁሉም ነገር ላይ ዋጋ ይጨምርም ነበር። ሀገር ውስጥ የሚመረተው ነገር ሁሉ የዶላር መጨመርን ተከትሎ ዋጋው ይጨምራል። ስለዚህ ምንም ምክንያት በሌለበት ሁኔታ የሚጨመርበትን ነገር መለየት አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
አሁን የተደረገው ለውጥ ግን ምርታማነት እንዲጨምር ነው፤ የውጭ ሀገር ርዳታ ጥበቃ ትተን አምርተን እራሳችን ወደመቻል እንድንሔድ የሚያስገድድ የለውጥ ሒደት ነው። እርግጥ ሰው ወደ ሥርዓቱ እስኪገባ ድረስ ይቸገራል። እንዲያም ሆኖ ግን ለውጡ የማይቀር ነገር በመሆኑ ይመጣል።
በጊዜው የውጭ ምንዛሬ ለውጡ ሲደረግ ዋጋ ከልክ በላይ ወደላይ እንዳይወጣ ብር ከገበያ መቀነስ አስፈላጊ ነበር። ለዚያ ሲባል ጠንካራ የሞኒተሪንግ ርምጃዎች ተወስደዋል። ከአንድ ዓመት በፊት ብሔራዊ ባንክ የብድር መጠን ከዚህ በላይ እንዳያድግ ብሎ ሲናገር ብዙዎች ምክንያቱን ስለማያውቁ አስተያየት ይሰጡ ነበር። ምክንያቱ ግን በቀጣይ የሚመጣ ፖሊሲ ስለሚታወቅ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሰኔ ወር የኢትዮጵያ ብር ልኬቱ ከዜሮ በታች ነጌቲቭ አምስት በመቶ ሆኖ ነበር። በመሰረቱ በየዓመቱ ማደግ አለበት። ነገር ግን አምና የተደረገው ከገበያ ላይ እንዲቀንስ ነው። የባንክ ኃላፊ ሆኜ በ19 ዓመት የሥራ ቆይታዬ ከዜሮ በታች ነጌቲቭ ሆኖ አይቼ አላውቅም። ይህን ያጤንኩት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ይህ የሆነው የገንዘብ አቅርቦቱ እንዲቀንስ በመደረጉ ነው። ይህ ማለት ብር ወደ ማዕከል ተሰበሰበ ማለት ነው። እንዲህ መደረጉ ግን መንግሥትን በጣም የሚፈትን ጉዳይ ነው። ምክንያቱም መንግሥት ብር በገበያ ውስጥ አንሶ እንዲታይ አይፈልግም። ሁሌ ወጪ ማውጣትና ሥራ መሥራት፣ ለሠራተኛ ደመወዝና አበል መክፈል፣ መንገድ መሥራት እና መሰል ጉዳዮችን ለማከናወን ሲባል በርካታ ገንዘብ ይወጣል። በብሔራዊ ባንክ ብር እንዲታተምም የሚያደርጉት መንግሥታት ናቸው። ይህ በመሆኑ ጨክኖ ገንዘብ ከገበያ ውስጥ ወደማዕከል እንዲሰበሰብ ማድረግ ከፖለቲካው አኳያ ሲታይ በጣም ከፍተኛ ውሳኔ ነው። ይህም ለኢኮኖሚ ጤንነት የሚደረግ የፖለቲካ መስዋዕትነት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ብሩ ወደ ማዕከል መሰብሰቡ ያመጣው ለውጥ ምንድን ነበር
አቶ አቤ፡- ብሩ ወደማዕከል እንዲመለስ በመደረጉ ምክንያት እና በተደረገው ውሳኔ 34 እና ከዚያ በላይ ይደርስ የነበረውን የዋጋ ግሽበት ከ20 በመቶ በታች እንዲወርድ አድርጓል። በአሁኑ ወቅት ብሩ ከ58 ወደ 128 ብር ደርሷል።
ገበያው ጤነኛ ሆኗል። በተወሰነ ደረጃ የጨመሩ ነገሮች ቢኖሩም የኑሮ ውድነቱ ጣጣ ቀደም ብሎ ለብዙ ዓመታት ስንቸገርበት የነበረ ፈተና አካል ካልሆነ በስተቀር በለውጡ ምክንያት ችግሩ ተቃለለ እንጂ አልጨመረም። የብራችን የመግዛት አቅም ከ70 በመቶ በላይ አቅም ከማጣት አንጻር ሲታይ ገበያ ላይ የተፈጠረው ጭማሪ የዚያን አምስት በመቶ እንኳ አይሞላም። የሚጠበቁት ብዙ ለውጦችና ጥቅሞች ናቸው። ሁሉንም ጥቅሞች አግኝተናል ማለት ባይቻልም የሚጠበቁ ጠቃሚ ነገሮች አሉ። አሁንም ለውጡ ገና ስላላለቀ ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ፖሊሲው ሪፎርም መደረጉ ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው?
አቶ አቤ፡– ትልቁ ለውጥ የተፈለገው፤ ቁጠባን ለመጨመር አይደለም። በዋናነት የውጭ ምንዛሬ ላይ ነው። ሁለት የነበረውን ገበያ ወደ አንድ ገበያ ማምጣት መቻሉ ተጠቃሽ ነው። ባንኮች የውጭ ምንዛሬውን በራሳቸው እንዲደለድሉ ማድረግ አስችሏቸዋል። እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅግ በጣም ከፍተኛ ጭማሪ አግኝተናል፤ የውጭ ምንዛሬ ገቢያችን በየዓመቱ ይቀንስ ነበር።
ለምሳሌ በዘጠኝ ወር ውስጥ ከወጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ 62 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ከሐዋላ በተለይ ከግሉ ወደ 48 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በዚህ በኩል በግል ባንኮችም ዘንድ ጭማሪ መኖሩን ልብ ይሏል። እንደ ሀገርም በሁሉም እስከ 20 በመቶ ድረስ አለ። በሀገራችን የውጭ ምንዛሬ 20 በመቶ ድረስ እድገት አሳይቶ አያውቅም። ነገሮች እየተስተካከሉ ሲሔዱ ደግሞ የተሻለ ለውጥ ይመጣል። በመሆኑም የውጭ ምንዛሬ ለሚጠይቁ ለመስጠት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህን ለማዝለቅ ግን መሥራት ወሳኝ ሲሆን፣ አንዱ በር ሲዘጋ ሌላ ለመክፈት የሚሞክሩ አሉና ያንን ማስተካከል የግድ ይላል። በአሁኑ ጊዜ ግን የተፈለገው ውጤት መምጣት ጀምሯል።
ለውጡ ተጨማሪ ምርት እንዲመረት ድጋፍ እያደረገ ነው። ከዚህ በፊት በጫካ ውስጥ በመሸሸግ ከሀገር ይወጣ የነበረው ወርቅ፣ በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ለውጥ የተገኘበት ሆኗል። አርሶ አደሩም ምርታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል። መንግሥት በማዳበሪያም ሆነ በነዳጁ በኩል ድጎማ እያደረገ ይገኛል። በጥቅሉ የለውጡ ምልክቶች አመርቂ ናቸው ማለት ይቻላል። ይህን ለማዝለቅ ግን እንቅልፍ አያዋጣም። አንደኛ የወጡ ፖሊሲዎች ስለመሥራታቸው በትጋት መከታተል ያሻል። ይህ በመደረጉ ሀገራችን እራሷን ችላ ከልመናም ከብድርም የምትወጣበት መንገድ ላይ ትገኛለች።
አዲስ ዘመን፡- የብር የመግዛት አቅሙ መውረድ በኢኮኖሚ እድገት ላይም ሆነ በባንኮች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር አይችልም? ይህንን ችግር መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው?
አቶ አቤ፡- የምንለካው በመጣው ውጤት ነው፤ አንዳንዴ ቲዎሪና ተግባሩ ይለያያል። የብር የመግዛት አቅሙ እንደተባለው በጣም ከተጎዳ ቁጠባ ላይ ጉዳት ያመጣል። ይህ ቲዎሪ ነው፤ ይሁንና የኢትዮጵያ ኑሮ የተመሰረተው በዶላር ላይ ብቻ አይደለም። ብዙ ነገር የምናገኘው ከሀገር ውስጥ ነው። ከውጭ የምናመጣቸው ጥቂት ነገሮች አሉ። ከውጭ በምናመጣው ነገር ላይ የተንጠለጠለ ሕይወት ያላቸው የተወሰኑ ዜጎች አሉ። ነገር ግን አብዛኛው ሕዝብ የሚኖረው በዚሁ በሀገር ውስጥ ባለው ነገር ነው፤ በተለይ አርሶ አደሩ ሕዝብ ከውጭ የሚፈልገው ነገር በጣም ጥቂት ነው። በመሆኑም የዶላሩ ነገር ለሁሉም እኩል አይደለም፤ ይለያያል።
ከቁጠባ አንጻር እኛ ብቻ ሳንሆን ጠቅላላ ኢንዱስትሪው በታሪኩ አይቶት የማያውቀው የቁጠባ ማሰባሰብ ሒደት ነበረው። በእርግጥ ባንካችን በዓመቱ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። ይህ ግን ገና ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። አምና በአንድ ዓመት ውስጥ የሰበሰብነው 120 ቢሊዮን ብር ነው። ዘንድሮ በዘጠኝ ወር ውስጥ 416 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነው። አቻምና በዓመት 163 ቢሊዮን ብር ነው፤ ይህ ትልቁ ቁጥራችን የነበረ ነው። ምናልባት የዘንድሮው በዚሁ ከፍታ ከቀጠለ በዓመቱ መጨረሻ ባለፉት አምስት ዓመታት ያሰባሰብነውን ቁጠባ በአንድ ዓመት እየሰራን ስለሆነ ልናሳካ እንችላለን ማለት ነው።
በአሁኑ ጊዜ ወደግማሽ ትሪሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅደን ወደዚያው እየተጠጋን ነው። በዓመቱ መጀመሪያ የያዝነው እቅድ 193 ቢሊዮን ብር ነበረ። እቅዱን ሶስቴ አሻሽለናል። ስለዚህ አሁን ያለን ቁርጠኝነት እስከ ሰኔ መጨረሻ 500 ቢሊዮን ብር ለማምጣት ነው። በአሁኑ ሰዓት ያለን ተቀማጭ ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ብር እየተጠጋ ነው። እንግዲህ አንድ ሶስተኛውን በ83 ዓመታት ውስጥ ያመጣነውን ተቀማጭ (ዲፖዚት) በአንድ ዓመት ውስጥ ልናመጣ ነው። ስለዚህ ቁጠባ እጅግ በጣም የጨመረበት ሁኔታ መኖሩን አመላካች ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ የሆነው እንዴት ነው?
አቶ አቤ፡– ወደ 60 በመቶ በገበያ ውስጥ ያለውን ቁጠባ የሰበሰብነው እኛ ነን። የግል ባንኮችም 40 በመቶ አካባቢ ሰብስበዋል። ቁጠባ ማለት ተጠራቅሞ ለዘላለም የሚቀመጥ አይደለም። ለትንሽ ጊዜ በባንክ ይቀመጣል፤ ያስቀመጠው ደንበኛ ወስዶ እቃ ይገዛበታል። ሰው ገንዘቡን በኪሱ አይዝም፤ ትልቅ ለውጥ ያመጣው ደግሞ ዲጂታይዜሽን ነው። ገንዘቡ የሚንቀሳቀሰው በባንክ ሲስተም ውስጥ ነው። ስለሆነም ቁጠባን የሚጎዳበት ሁኔታ አልተፈጠረም። ከዚህ ጋር ተያይዘው የኢኮኖሚክ ቲዎሪዎች መሻሻል ያለባቸው ናቸው። እነሱ በማኑዋል ዘመን የሚሠሩ ናቸው። ገንዘብን በዲጂታል ማንቀሳቀስና ያንኑ ገንዘብ በኖት ደረጃ ማንቀሳቀስ የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
በዚህ ዓመት የዋጋ ግሽበቱ ወደ 15 በመቶ አካባቢ ወርዷል። በመሆኑም ግሽበቱ እየቀነሰ ነው። የብር የመግዛት አቅም ሲቀንስ ድሮ በሚታሰበው በማኑዋል ዘመን ብዙ ሰው ከባንክ ብር ያወጣና በኪሱ ብዙ ብር ይይዛል። ግብይት ለመፈጸም ትናንት አንድ መቶ ብር ይበቃ ከነበረ ዛሬ እስከ 300 ብር ድረስ ስለሚያስፈልግ ይህን ታሳቢ አድርጎ በኪሱ የሚይዘው ብር እስከ አንድ ሺ ብር ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የብር የመግዛት አቅም ሲቀንስ ከባንክ ብዙ ብር ይወጣና ወደሰው ኪስ ይገባል ማለት ነው።
በአሁኑ ወቅት ሰው ከኪሱ ገንዘብ ማውጣት ግዴታ ስለሌለበት ብሩ እዛው በባንክ ሥርዓት ውስጥ ስለሚዘዋወር ኑሮ ቢወደድም ድሮ የነበረው ቲዎሪ በአሁኑ ጊዜ አይሠራም። ስለዚህ አሁን ቲዎሪያቸውን ማሻሻል ያለባቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ናቸው። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ግን አሁንም እዚያው ድሮ ቦታ ናቸው፤ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ግን ተቀይሯል።
ዲጂታላይዝ በመሆኑ ብርን በኪስ መያዝ አይጠበቅም። ፡ ስለዚህ ለባንኮች ያመጣው ተጽዕኖ የለውም፤ እንዲያውም የጨመረው እድሉ ነው። በእርግጥ እንዲህ ሲባል ኅብረተሰባችን ብር ተርፎት በባንክ ቆጥቧል ማለት አይደለም። ያለችው ብር ሁሉ ከባንክ አትወጣም። የሚዘዋወረው በባንክ ውስጥ ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ቴክኖሎጂ ያመጣው ትሩፋት ነው። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ቲዎሪያቸውን ወደቴክኖሎጂው ከፍ ማድረግ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ባንኮች ወደሀገር እንዲገቡ ከመፈቀዱ ጋር ተያይዞ የሚታየው እንደጸጋ ነው ወይስ እንደ ተግዳሮት? እንደ ተግዳሮት ከሆነ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ አቤ፡- የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ሲገቡ የእኛ ባንኮች እንደሚከብዳቸውና እንደማይችሉ ተደርጎ ከልክ በላይ እየተወራ ነው። ይሁንና ታሪኩ እንዲህ አይደለም። ለምሳሌ ሳፋሪኮም በኬንያ እጅግ በጣም ጠንካራ የሆነ ነው። ከዚያም አልፎ ምስራቅ አፍሪካ ብዙ ሀገሮች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው። ይህ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በብዙዎች ዘንድ ሲነገር የነበረው ኢትዮ ቴሌኮምን በአንድ ጀምበር እንደሚያጣጥፍ ነበር። ይህ የሚያሳየው ለእራሳችን የምንሰጠው ግምት አነስተኛ መሆኑን ነው። ይህ ግን ትክክለኛ አመለካከት አይደለም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገሩን ይወድዳል። የሀገሩንም ተቋም ያምናል። በእርግጥ የተቋማቱ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ባሕልም ወሳኝነት አለው። የእኛ ሀገር ተቋማትም ሕዝቡ እንደሚያወራው ደካሞች አይደሉም። ተቋማቱ እንደ ሌላው ሀገር እራሳቸውን አያስተዋውቁም። ከዚህ የተነሳ ጥንካሬያቸው አይታወቅም፤ ጥንካሬያቸው የሚታወቀው ከሌላው ጋር መወደዳደር ሲችሉ ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም አንዱና ዋና ምስክር ነው። እራሱን በአግባቡ ማሳየት ችሏል። ከየትኛውም ተቋም ጋር ተወዳድሮ መሥራት እንደሚችልም በተጨባጭ አሳይቷል።
የሀገራችን ባንኮች ትልቅ የካፒታል አቅም የላቸውም። እንዲያም ሆኖ በአሠራራቸው ግን ከሌላ ጋር መወዳደር ተስኗቸው በአንድ ጀምበር ደንበኛ የሚያጡ አይደሉም። በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂው ፈተና እየፈጠረባቸው ነው። ጥሩ ቴክኖሎጂ ያላቸው በገበያ ውስጥ ደንበኞቻቸውን በአግባቡ ማስተናገድ የቻሉና እያደጉ የመጡ ሲሆኑ፣ ጥሩ ውጤትም እየሳዩ ነው። ደንበኞች የሚመርጡት ደግሞ የትም ቦታ ሆነው መክፈል የሚችሉትን የአገልግሎት አይነት ነው። እኛን ሳይወዱ በእኛ መሰረተ ልማት ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኛ የትም ቢሄድ የክፍያ ሥርዓቱ “ሲቢኤ” ነው። በዚህ ምክንያት በጣም በፍጥነት እያደገ ነው። በዚህ አይነት መሰረተ ልማት ያላዘጋጁ ባንኮች ይፈተናሉ። አቅሙ የሌላቸው ባንኮች ፈታኝ የሚሆኑባቸው የውጭ ሀገር ባንኮች ብቻ ሳይሆኑ በሀገር ውስጥ ባንክም ጭምር ነው።
ከውጭ ሀገር መጥተው በመጀመሪያ ይወዳደራሉ ብለን የምናስባቸው ሀገራት አሉ። አሁን ለ”ሲቢኢ” ካለን የገቢ ቋት አኳያ ሳየው ሊያመጡብን የሚችሉት ተጽዕኖ በጣም አነስተኛ ነው። እኛም ደግሞ እንቸገር ይሆናል በምንለው ላይ በጣም አተኩረን እየሠራን ነው። ሌላው ላይ ሊወዳደሩን አይችሉም። አንድ ባንክ ከኢትዮጵያውያን ጋር ለመሥራት በጣም በርካታ ኢንቨስትመንት ውስጥ መግባት አለበት። ቴክኖሎጂ ይዞ ብቻ አዲስ አበባ መጥቶ ስለተቀመጠ የሚመጣ ነገር አይኖርም። 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ደንበኛ ወደ እርሱ መጥቶ ሊገለገል አይችልም።
አዲስ አበባ ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬ አመንጪ ተቋማት ላይ ከእኛ የተሻለ ተመራጭ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። በሌላው ዓለም ባላቸው ባንካቸው ምክንያት እኛን ትተው ወደ እነርሱ ሊያዘነብሉ ይችላሉ። እንዲያም ሆኖ ለዚያም ቢሆን ተገቢ ዝግጅት እያደረግን ነው። ደንበኞቻችንንም እንዳይወስዱብን እናደርጋለን። ለዚህ ደግሞ በቂ ዝግጅት አድርገናል። ምናልባትም ከቢዝነሱ ከስረን ደንበኞቻችንን ለማቆየት ልንሠራ እንችላለን። ምክንያቱም እዚያ አካባቢ የምናወጣው ወጪ፤ ካለን አጠቃላይ ገቢ አንጻር ሲታይ ለእኛ በጣም ትንሽ ነው። ስለዚህ የውጭ ባንኮች ሊወዳደሩን በሚችሉበት ዘርፍ ላይ በቂ ዝግጅት አድርገናል። ሊወዳደሩ የማይችሉት 97 እና 98 በመቶ በላይ ይደርሳል። ሌላ ባንክ መጥቶ የትኛውንም ያህል ኢንቨስት ቢያደርግም በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደረሰበት ለመድረስ የማይችለው እስከ 98 በመቶ የሚሆነውን ነው። ከሁለትና ሶስት በመቶ በማይበልጠው ላይ ጠንካራ ውድድር ሊገጥመን ይችላል። እኛ ደግሞ ለዚያ ትኩረት አድርገን እንሠራለን።
በሀገራችን ያሉ አንድ አምስት ስድስት ያህል ባንኮችም በዚህ ደረጃ ከውጭ የሚመጣውን ባንክ መገዳደር ይችላሉ። ከዚያ በታች ያሉ ባንኮች በተወሰነ ደረጃ ሊፈተኑ ይችላሉ። እንዲዚያም ሆኖ ልክ እንደ እኛ ብዙዎቹ ባንኮች አዳዲስ ስትራቴጂዎችን እየቀየሱ ነው። በቴክኖሎጂውም ረገድ ብዙ ኢንቨስት በማድረግ ላይ ናቸው። ምናልባትም እየጣሩና እየተዘጋጁ ያሉት ከሚመጣው በላይ ነው። ዝግጅት እያደረጉ ያሉት ከሚመጣው ጉዳይ በላይ ነው ማለት ይቻላል። ውስን ባንኮች ግን ፉክክሩ ሊከብዳቸው ስለሚችል ሰብሰብ ብለው እራሳቸውን ለማጠናከር ቢሞክሩ መልካም ነው። እነዚህ ከውጭ በሚመጣው ባንክ ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ በሚደረገው ውድድር እራሱ ሊፈትናቸው የሚችል ነው።
ከውጭ የሚመጡ ባንኮች ደግሞ ዘልለው ገበያ ውስጥ መግባት አይችሉም። የሚመጡትም የተወሰነ ነገር ላይ አተኩረውና ገበያውን አጢነው ነው። ሰው እንደሚያስበው በአንድ ጀምበር የሆነ ተዓምር ማምጣት የሚችሉ አይደለም። አንዳንድ ታዋቂ ሰዎች ሁሉ የውጭ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ አላቸው ብለው ሲያወሩ ይደመጣል። የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ሀገር አምጥቶ ለእኛ ሕዝብ የሚሰጥ ምንም አይነት ባንክ የለም። አንድ ባንክ ቢበዛ ይዞ ሊመጣ የሚችለው 40 ሚሊዮን ዶላር ነው። 40 ሚሊዮን ዶላሩን ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ቀን የሚያገኘው ነው። እሱን አምጥተው ለተወሰኑ ሰዎች ገበያ ውስጥ ሊሸጡ ይችላሉ። እሱንም ቢሆን በሙሉ አይሸጡም። ምክንያቱም የተወሰነ ነገር ማቆየት ይፈልጋል።
ለምሳሌ እኛ በአንድ ጊዜ ለደንበኛ 150 እና 160 ሚሊዮን ዶላር እንሰጣለን። እነርሱ ደግሞ 40 ሚሊዮን ዶላር ይዘው መጥተው በዚህች ምን ያህል ደንበኛ ሊስቡ ነው? እዚህ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ለመሰብሰብ ለደንበኞች የሆነ ነገር መስጠት አለባቸው። የሚሰጠው ግን አይኖርም፤ ምክንያቱም ቁጠባ ለመሰብሰብ ጊዜ ይፈጅበታል። ስለዚህም ገበያ ውስጥ ገብቶ ተወዳድሮ የተለየ ነገር ለማምጣት ጊዜ ይወስድበታል። እርግጥ ሲመጡ አዳዲስ ነገር ሊያመጡ ይችላሉ። ምናልባት በተወሰነ ደረጃ ሊወዳደሩ የሚችሉት ከጎረቤት ሀገራት እንደ ኬንያ አይነት ቢሆኑም እነርሱም ኢንቨስት አድርገው በየቦታው ቅርንጫፍ ከፍተው የሚሞክሩ ከሆነ በጣም ዳገት ይሆንባቸዋል።
በተባለው መሰረት አንድ አራት አምስት ባንክ ቢመጣ ከየባንኩ የተሻለ ክህሎት አላቸው የተባሉትን ባለሙያዎች ሊወስዱ ይችላሉ። በጣም የሚያሳስበኝ እሱ ነው። ብዙ ሠራተኛ አይቀጥሩም፤ ጥቂት ይቀጥሩና እነዚያን ከፍተኛ ተከፋይ ያደርጓቸዋል። የሚወስዷቸው ሠራተኞች ደግሞ ጠንካራ ሆነው የባንኩን ኢንዱስትሪ የሚመሩትን ነው። ይህ አንድ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። አንድ ባንክ ደግሞ ሁለትም ሆነ ሶስት ቁልፍ የሆነ ሠራተኛውን ሲያጣ በጣም ከባድ ነገር ነው። ባንኮች፣ አንድ መቶ ሺ አሊያም ሁለት መቶ ሺ የሚከፍሉትን ሠራተኛ እነርሱ ወስደውት አንድ ሚሊዮን ብር ከከፈሉት የቀረው 20 ሺው እና 30 ሺው ሠራተኛ የሚያየው ያንን አንድ ሚሊዮን ብር ደመወዝን ነው።
ሠራተኛው የውጪ ባንኮች ዘንድ መሔድ ይፈልጋል፤ ነገር ግን እርሱ መሔድ አይችልም። ለሁሉም ሠራተኛ ደግሞ ያንን ያህል ደመወዝ መክፈል አይቻልም። እንደዚያም ሆኖ ጉዳዩ የሠራተኛውን አመለካከት የመበጥበጥና ተረጋግቶ መሥራት እንዳይችል የማድረግ ተጽዕኖ አለው። ሠራተኛው ማሰብ የሚጀምረው እንደተበደለና እየተበዘበዘ እንዳለ ነው። ከዚህ የተነሳ ባንኮች ለሠራተኞቻቸው ደመወዛቸውን በማሳደግ ረገድ መገደድ ሊመጣባቸው ይችላል። ይህ ደግሞ የባንኮች ትርፋማነት ላይ በተወሰነ ደረጃ ጫና ሊፈጥር ይችላል። ከዚህ ውጭ ከውጭ ባንኮች ጋር ከሚደረገው ፉክክር ይልቅ የሀገር ውስጥ ባንኮች እርስ በእርስ የሚያደርጉት ውድድር የበለጠ ፈታኝ ነው እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አቤ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም