
ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ በግብርና ዘርፍ ቴክኖሎጂ በማፍለቅ፣ በማባዛት እና ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት ረገድ በመሥራት የሀገሪቱን የምርት እና ምርታማነት አቅም ለማሳደግ የተቋቋመ ወሳኝ ተቋም ነው። ተቋሙ የሀገሪቱን የግብርና ልማት በምርምር የሚያግዙ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማልማት፤ የግብርና ምርምር ሥርዓቱን የማስተባበር ተልዕኮ ተሰጥቶት እየሠራ ያለ ተቋም ነው። ታዲያ ለኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ መዘመንና ምርትና ምርታማነት ማደግ ኢንስቲትዩቱ እስካሁን ምን አበረከተ? እያከናወናቸው ያሉ የምርምር ሥራዎች ምን ያህል ግብርናውን ማዕከል ያደረጉ ናቸው? በሚሉና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የኢንስቲትዩቱን ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ የተጠየቅ ዓምዳችን እንግዳ አድርገናቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እያከናወናቸው ያሉ የሥራ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ የቆየ ተቋም ነው። ዋና ዓላማው የግብርና ዕድገትን ለማሳለጥ ቴክኖሎጂን ማቅረብ ነው። ቴክኖሎጂ ያመነጫል፤ ያባዛል፤ የተባዙትን ቴክኖሎጂዎች ለሚመለከተው አርሶ አደርና አርብቶ አደር እንዲደርስ ያደርጋል። በተጨማሪም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ አዲስ ቴክኖሎጂን በተሻለ ሁኔታ ተጠቅመው ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር ሥልጠና ይሰጣል። የአቅም ግንባታ ሥራ ይሠራል። በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ ቴክኖሎጂ ማመንጨት፤ ማባዛት፤ የተባዙትን ቴክኖሎጂዎች ለሚመለከታቸው አካላት ማድረስ እና ከዚያ በኋላ የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራት ተቀዳሚ ሥራው ነው። ግብርና ለኢትዮጵያ መሰረት ነው። የኢትዮጵያ መሰረት ግብርና ነው። ኢትዮጵያን ከግብርና ውጭ ማሰብ አይቻልም። ግብርና ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ደግሞ አይናወጥም፡፡
የማይናወጥ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚመጣው በግብርናው ዘርፍ በሚመጣ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው። ምንም ነገር አያናውጠውም። እነ ብራዚል፣ አሜሪካ፤ ሕንድና ሌሎች የአደጉ ሀገራት በአብዛኛው ኢኮኖሚያቸው የተመሰረተው በግብርና ላይ ነው። ግብርናቸውን ሲያሳድጉ የማይናወጥ ኢኮኖሚ ስለመሰረቱ ወደኋላ የሚል አይደለም። ስለዚህ ግብርና በጣም ወሳኝ ስለሆነ ኢንስቲትዩቱ ሲቋቋም ምርትና ምርታማነታችን አነስተኛ ስለሆነ ብዙ መሬት ማለትም 13 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደር መሬት ያርሳል። ነገር ግን ከመሬቱ የሚያገኙት ምርት አነስተኛ ነው። ለምሳሌ ለረጅም ጊዜ የጤፍ ምርት በአማከይ 10 ኩንታል በሄክታር ነበር። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር በሠራቸው ሥራዎች በሂደት የጤፍ ምርትና ምርታማነት አሁን ላይ በትንሹ በአማካይ 20 ኩንታል በሄክታር ደርሷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ማንኛውም አርሶ አደር በሄክታር 10 ኩንታል በላይ ምርት ያገኛል። ይህም የሆነው የተለያዩ የተሻሻሉ ዝርያዎች ተሠርተው በመቅረባቸው ነው። የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎች ምርታማነታቸው እየጨመረ ነው። በተጨማሪም ድርቅን መቋቋም ይችላል። የዝናብ እጥረት ሲኖር ሳይደናገጡ ዘርተው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰቭል ዝርያ አይነቶችን ሠርተናል። ይህ ሥራ በስንዴ፣ ባቄላ፣ ምስር፣ ሽምብራ፣ እና መሰል የሰብል ዝርያዎችን በማባዛት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደረገ ነው።
በእንስሳት በኩልም ሲታይ ኢትዮጵያ በእንስሳት ከፍተኛ ሀብት ያላት ሀገር ናት። ነገር ግን ምርትና ምርታማ ከመሆን አኳያ ዝቅተኛ ነው። ይህን ለማሻሻል ተሞክሯል። ነገር ግን በሰብል ላይ የተሠራውን ያህል በእንስሳት ላይ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል። በቅርብ ጊዜ እኛ እየሠራን ያለነው የሌማት ትሩፋት ለመደገፍ በተለይም በዶሮ እና በወተት ከብት ትልቅ ሥራዎች እተሠሩ ናቸው። የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን ከሌላ ሀገር በማምጣት እና በሀገር ውስጥም ያሉትን በማሻሻል እና በመጠቀም የአንድ ቀን እድሜ ያላቸው የዶሮ ጫጩቶችን ለአርሶ አደሩ በማሠራጨት በየቦታው እንዲያረባና እንዲጠቀም ተደርጓል። በተጨማሪም ትንንሽ ኢንተርፕራይዞች እንዲሠሩ በማድረግ ወደ ውጤት ለመቀየር ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ነው።
በወተት ምርት በአማካኝ አርሶ አደሩ ላይ ያለው ከብት የሚሰጠው በቀን አንድ ነጥብ አምስት ሊትር ወተት ነው። ለምንድን ነው ትንሽ ሊትር ወተት የሚሰጡት? ከተባለ አንዱ የምግብ እጥረት ነው። የወተት ላሞች በቂ ወተት እንዲሰጡ በቂ መኖ መመገብ ይኖርባቸዋል። መኖ ካላገኙ በቂ ወተት አይሰጡም። ምክንያቱም የሚሰጡት በተመገቡት ልክ ነው። ሁለተኛው ዝርያ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ዝርያዎች አሉ። ለምሳሌ የቦረና የወተት ላሞች ዝርያ ምርታቸው ከፍ ያለ ነው። የስጋ ምርታቸውም በዚያው ልክ ከፍ ያለ ነው፡፡
አውስትራሊያዎች የቦረና ላሞች ዝርያ ወስደው ዓለም ላይ በወተትና ስጋ አምራችነት ታዋቂ ሆነዋል። የእኛን ዝርያዎች ወስደው እነርሱ አዳቅለው፣ አመቻችተውና አሻሽለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርት እንዲያገኙ አድርጓል። የኦጋዴን ዝርያዎች አሉ። በምዕራብ በኩልም የሸኮ ዝርያ የሚባሉ ደግሞ አሉ። እነዚህ ስሊፒንግ ሲክነስ “sleeping sickness” የሚባል በዝንብ የሚተላፍ በሽታ አለ። በምዕራብ አካባቢ ከብቶች በዚህ ዝንብ ሲነደፉ ይሞታሉ። የሸኮ ዝርያዎች ግን ምንም አይሆኑም፤ ይህ ሀብት ነው። ከዚህ ሌላ ከብት ይዘን ብንሄድ ሲነደፉ ይጎዳሉ። እኛ ያሉን የከብትም ሆነ የበግ ዝርዎች ብዙ ናቸው።
የላም በተመለከተ በቅርብ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሥራዎችን ሥንሠራ ነበር። ዝርያዎችን አዳቅሎ አንድ ዝርያ የተሻለ ማድረግ ይቻላል። ከአንድ ሄክታር መሬት ስንት ኩንታል ምርት ይገኛል? ቢባል በሚሊዮን ዝርያ ይገኛል ሊባል ይችላል። ከዚያ መምረጥ ቀላል ነው። እንደዚሁም የከብቶችን ዝርያዎች ለማሻሻል ሚሊዮኖች ያስፈልጉናል። ከዚህ ውስጥ መርጦና አዳቅሎ የተሻለ ዝርያ መውጣት ይቻላል። ይህ ደግሞ አቅምን የሚጠይቅ ነው። ቴክኖሎጂ ያስፈልገዋል፡፡
እኛ ወደፊት ቴክኖሎጂ በማስፋፋት የዝርያ ማሻሻል ሥራ መሥራት አለብን። አሁን እየሠራን ያለነው የአሜሪካ ላሞች የሚባሉ ቢያንሰ በቀን 15 ሊትር ወተት ይሰጣሉ በተባሉት ላይ ነው። ሕክምናቸው ወጭ ይጠይቃል። ስለዚህ ይህን ለአርሶ አደሩ ብንሰጥ ቀለባቸውንና ሕክምናቸውን ችሎ ለማስቀጠል ይከብዳል። የእኛ ዝርያዎች ደግሞ እንክብካቤ ብዙም አይፈልጉም። ምክንያቱም ተላምደዋል። በሽታም በቀላሉ አያጠቃቸውም። ስለዚህ እነዚህን ሁለቱን ብናዳቅል የሚሰጡት ምርት 75 በመቶ ወይ 50 በመቶ ሊሆን ይችላል፤ በሽታ በመቋቋም፣ ወተት በመስጠት ከሁለቱ መሃል ይሆናል። ለምሳሌ ከስምንት እስከ 10 ሊትር ወተት ማግኘት ያስችላል። እንደዚህ እያደረግን የተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ እያሰራጨን ነው፡፡
ባለፈው ወር ወልቂጤ ላይ ለ26 አርሶ አደሮች አንዳንድ የወተት ጊደር ተሰጥቷል። በቅርቡም ሆለታ ላይ በተመሳሳይ 40 ጊደሮች ለአርሶ አደሮች ተሰራጭተዋል። ይህም የወተት ምርትና ምርታማነትን ይጨምራል። እኛ ወተት በማግኘት በአካልም በአዕምሮም ልናድግ ይገባናል። የምግብ ዋስትና የሚባለው ነገር የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚለውን ውጤታማ ለማድረግ አርሶ አደሩ የተመጣጠነ ምግብ እዲያገኝ በእንስሳት ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በአፈር ማዳበሪያ በኩል ሲጤን የተሻለ እና ከፍተኛ ምርት ሊሰጥ የሚችል የአፈር ማዳበሪያው በምን መልኩ መጠቀም ሲቻል ነው? የሚለው በመጀመሪያ መታወቅ ይኖርበታል። ለምሳሌ ለበቆሎ፣ ለስንዴ፣ ለጤፍና ለሌሎችም የሰብል አይነቶች የሚያስፈልገው ማዳበሪያ የተለያየ ነው። ሰብሉ በምን ደረጃ ላይ ሲሆን ማዳበሪያ እንደሚሰጥ በጥናት ላይ በመመስረት የወጡ ቴክኖሎጂዎች አሉ። ቴክኖሎጂዎችን ለተገልጋዮች እናደርሳለን። እንዴት መሠራት እንዳለበት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እንሠራለን።
ለአብነት ያህል ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከአንድ ሺ 600 በላይ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር አውጥቷል። የሰብል ዝርያ ሲባል እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ባቄላ፣ ምስር፣ አተር፣ ዳጉሳ፣ ተልባ የመሳሰሉትን ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ የተዳቀሉ የቡና ዝርያዎች በምርምር እየወጡ ነው። ቡና ለኢትዮጵያ ትልቁ የገቢ ምንጭ በመሆኑ በመደበኛው ሰባት ኩንታል በሄክታር የሚሰጥ የቡና ዝርያ ነበር፤ በምርምር የወጡ የቡና ዝርያዎች ደግሞ በሄክታር 17 ኩንታል የሚሰጡ ናቸው። እነዚህን የተሻሻሉ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት ሥራ እየሠራን ነው። ስለሆነም ኢንስቲትዩቱ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከፍተኛ በጀት ወጭ ተደርጎባቸው የሚሠሩ የምርምር ሥራዎች ከመደርደሪያ አይወርዱም፤ ወደ ተግባር አይለወጡም የሚል ሀሳብ ሲነሳ ይደመጣል፤ ኢንስቲትዩቱ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ምን ሠርቷል? ውጤታማነቱስ እንዴት ይገለጻል?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- ቅድም እንዳልኩት ጤፍ የምርት መሻሻሉ አነስ ያለ ነው። ለምሳሌ በሄክታር 10 ኩንታል የነበረው ወደ 20 ኩንታል፤ ስንዴ 12 ኩንታል የነበረው አሁን ላይ በአማካይ 36 ኩንታል በሄክታር ደርሷል። ወደ ባሌ ቢኬድ በሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት ይገኛል። አርሲ አካባቢም 70 እና 80 ኩንታል
ምርት ይገኛል። ስለዚህ ስንዴ 12 በሄክታር የነበረው በአማካይ 36 የደረሰበት ምክንያት የምርምር ሥራዎች ወደ ተግባር በመቀየራቸው ነው። ባቄላና አተር እንዲሁ በተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ አተር በሄክታር 14 ኩንታል እየተገኘ ሲሆን፣ ምርቱም በሄክታር ወደ 24 ኩንታል ከፍ ብሏል። ስለዚህ ምርትና ምርታማነት ጨምሯል። ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1966 ነው:: ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ያለው ሥራ እና የዛሬው እኩል አይደለም። ምርምር ለግብርናው ዘርፍ የለውጥ ሞተር ነው። ግብርና ላይ ኢኮኖሚያቸው መሰረት ያደረጉ ሀገራት ምርምር በሰፊው ይሠራሉ። እንግሊዝ፣ ጀርመንና መሰል ሀገራት በግብርናው ዘርፍ ስታኬታማ ሥራ ሠርተዋል። ስለዚህ ኢንቨስትመንት ከተሠራም ግብርና ላይ መደረግ አለበት።
ለምሳሌ በምርምር አንድ የተሻሻለ የሰብል ዝርያ ሲወጣ ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚጠቅመው? አንድ ዝርያ በጣም ጥሩ ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢበዛ 15 ዓመት ነው። ከዚያ በኋላ መታደስ አለበት። ለምሳሌ ስንዴ “ቀቀባ” የሚባል ዝርያ እስካሁን ይመረታል። በሽታን የሚቋቋም ነው፤ ነገር ግን 15 ዓመት ላይሞላው ይችላል። በኋላ ላይ ላይ በሌላ ዝርያ መተካት አለበት። ማዳበሪያ እንኳን በዚህ ደረጃ በዚህን ያህል መጠን ለበቆሎ ይሰጥ ከተባለ ዛሬ መጀመር አለበት። የተሻሻለ ዝርያ ሲኖር ከፍተኛ ምርት ይሰጣል፡፡
ለምሳሌ በሽምብራ የተሻሻለው ዝርያ ከፍተኛ ምርት ይሰጣል። ዝርያዎች ይወጣሉ፤ ይሁንና ዘለዓለማዊ ስላልሆኑ በሌላ ዝርያ ይለወጣሉ። ስለዚህ መሰረት የሆኑ የሰብል ዝርያዎች አይጠፉም። እነሱ ከጠፉ ግብርናችን ይጠፋል። ዝርያዎች ከ10 ዓመት በኋላ በሌላ ዝርያ ሊተኩ ይችላሉ። የአንድ ዝርያ ከፍተኛ የሚቆዩበት ዕድሜ ቢበዛ 15 ዓመት ነው፤ ከዚያ በላይ የሚቆዩ እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ድንችና መሰል ዝርያዎች ናቸው። በማዳቀል የሚገኙት የሰብል ዝርያዎች ግን እያረጁ ይመጣሉ።
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ የሚያከናውናቸው የምርምር ሥራዎች ውጤታማነታቸው የሚለካው በምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- ውጤታማነታቸው የሚለካው በሚሰጡት የምርት ውጤት ነው። በሄክታር ምን ያህል ምርት ይሰጡናል? በሚለው ይለካል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ እንደግብርና ሚኒስቴር፣ ግብርና ባለስልጣን እና መሰል አጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት ከመሥራት አኳያ ውስንነት አለበት የሚል ቅሬታ ሲነሳ ይደመጣልና በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- ኢንስቲትዩቱ በቅንጅት ይሠራል። ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሠራ ነው። አንድ ላይ ሥራዎችን በመሥራት ሥራዎቹን በጋራ ይገመግማል። ከኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣንና ከኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት እንሠራለን። በተጨማሪም ዘርን ከሚያባዙ የግል ድርጅቶች ጋር በጋራ እንሠራለን። ዘር ሲፈልጉ መሰረታዊ ዘር እንሰጣቸዋለን። ይህን ለማስፋፋት ፈቃድ የመስጠት ሥራ ይሠራል። በግል በግብርና የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች በግል ዘርፉ ለማባዛት የሚፈልጉ ከሆነ ይሰጣል። ስለዚህ የግል ባለሃብቶችንም የማሳተፍ ሥራ እየተሠራ ነው።
ከጂአይዜድ እና የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንሠራለን። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ውስንቶች የሉም ማለት አይደለም። የበጀት ውስንትና መሰረተ ልማት ውስንነቶች አሉ። ለአብነት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ላለፉት ስምንት ዓመታት የካፒታል በጀት አግኝቶ አያውቅም። ስለዚህ የምርምር ግብዓቶቻችን ያረጁ ናቸው። ላለፉት ስምንት ዓመታት ብንጠይቅ መልስ አልተገኘም። ነገር ግን ግብርና ምርምር ላይ ኢንቨስት ካላደረግን ግብርናን ማሳደግና ማዘመን አይቻልም፡፡
አንዱ ቁልፍ ተግባር መሆን ያለበት ግብርና ላይ በጀት በመጨመር በሰው ኃይል እና መሰል ግብዓቶች ማደራጀት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ የሚያከናውናቸው የምርምር ውጤቶች ላይ በአርሶ አደሮችና በተቋማት ደረጃ ወይም በድርጅት ደረጃ አግዞናል፤ ቅቡልነት አለው የሚሉ ግብረ መልሶች አሉ?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- በጣም ቅቡልነት አለ። ባለፈው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር ወደ ባሌ ተጉዘን ባደረግነው የመስክ ምልከታ አርሶ አደሮች የስንዴ ዘር ያመርታሉ። ዘሩን ከየት እንዳገኙት ስንጠይቃቸው የሚወዱት ዘር አይነት መሆኑን ገልጸው ነበር። ቅቡልነቱ ትልቅ ነው። ስለሆነም ዋናው ነገር ውጤቱ ነው። የሰብል ዝርያ ሲወጣ ለምሳሌ የድሮ ዝርያ 10 ኩንታል በሄክታር ከሰጠና የተሻሻለው 20 ኩንታል የሚሰጥ ከሆነ ይህ በአርሶ አደሩ በኩል ቅቡልነት አለው። መጀመሪያ ኢንስቲትዩቱ ዝርያ ሲያወጣ መጀመሪያ የአርሶ አደሩ የሚጠቀምበትን እና ኢንስቲትዩቱ በምርምር ያገኘው ጎን ለጎን እንዘራለን። ይህን በማሳያነት ለአርሶ አደሩ ማሳየት ካልተቻለ እንዲሁ ተቀበል ቢባል አያምንም።
አርሶ አደር የሚያየውን ያምናል። የምርቱን ውጤታማነት ካየ በኋላ እንደሚያስፈልገው በማመን ይወስዳል። ስለዚህ በቅቡልነት በኩል ጥያቄ የለም። ነገር ግን የምንሠራው ሥራ በተጨባጭ ከዚህ በላይ መሥራት አለብን። ዲቃላ ዝርያ የሚባል ሁለት አይነት ዝርያ ያለ ሲሆን፣ በተገቢው ሁኔታ በማባዛት የሚገኝ ነው። ሌላው ደግሞ በማዳቀል የሚገኝ ነው። የወንዴና የሴቴ የሚባል ዘርን በማዳቀል የሚሠራ አሠራር አለ። ይህ ማለት የወንዴ የአበባ ብናኝ ሴቴ ላይ በማድረግ የሚከናወን ነው። ዘሩ የሁለቱ ዲቃላ ሲሆን በዚህ የሚገኘው ምርት ከፍተኛ ነው። ያልተዳቀለው 40 ኩንታል በሄክታር ቢሰጥ የተዳቀለው 80 ኩንታል የሚሰጥበት ሁኔታ ነው።
የተዳቀለው ለአንድ ጊዜ ብቻ ምርት ስለሚሰጥ በቀጣዩም በተመሳሳይ መልኩ መዳቀል አለበት። ለምሳሌ የበቆሎ ዲቃላ እስከ 80 ኩንታል ምርት ይሰጣል። ኢንስቲትዩቱ አሁን ላይ እያሰበ ያለው ልክ እንደበቆሎ ዲቃላ የስንዴና የጤፍ ዲቃላ መዝራት ላይ ነው። የጤፍ 20 ኩንታል በሄክታር፤ 40 ኩንታል ስንዴም በሄክታር ሲሆን፣ 30 የነበረው 70 የሚሆንበት ሁኔታ መፍጠር ይቻላል። የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች እንዲኖሩ እንደ ቻይና እና መሰል ሀገራት በአጋርነት እንሠራለን፡፡
ቻይና የስንዴ ዲቃላ የምትሠራ ሲሆን፣ በሄክታር በአማካይ እስከ 70 ኩንታል ምርት ያስገኛል። ይህን ተሞክሮ በሀገራችን ለማስፋት ሥራዎች ተጀምረዋል። ነገር ግን የመሰረተ ልማት እጥረት ስላለ መሟላት መቻል አለበት። መሰረተ ልማቱን ሊያግዘን ተስማምተናል። ታዋቂው የቻይና የደንና የአዝዕርት የምርምር ማዕከል ድጋፍ ለማድረግ ላቦራቶሪ ለመሥራት ቃል ገብቷል።
አዲስ ዘመን፡- ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ከማድረግ አኳያ ኢንስቲትዩቱ ምን አስተዋጽኦ አበረከተ?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች መካከል አንዱ ስንዴ ነው። አሁን ላይ ስንዴ በሀገር ውስጥ አርሶ አደሩ በሚገባ እያመረተ ነው። መንግሥት በያዘው አቅጣጫ መሰረት ስንዴ በመኸርና በበጋ መስኖ በስፋት እየተመረተ ሲሆን፣ በዚህም እራሳችንን ችለናል። ከእራስ አልፎ ወደ ውጭ መላክም ጀምራለች። የሌማት ትሩፋት ውጤታማ እንዲሆን ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በገብስ ምርት ላይ ምርጥ ዘር ለማባዛት በውስጡ ያለው የፕሮቲን መጠን ምን ያህል እንደሆነና ሲባዛ ምን ያህል ማዳበሪያ ቢሰጠው ፕሮቲኑ የተስተካከለ እንደሚሆን በጥናት ተለይቶ ለማባዛት እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በከተሞች አካባቢ ያሉ የኢንስቲትዩቱ የምርምርና ዘር ማባዣ ቦታዎች ለአብነት እንደ ሀዋሳ እና መሰል አካባቢ ያሉ ቦታዎች እየተነጠቁ እንደሆነ ሲነገር ይደመጣል፤ ጉዳዩን እንዴት አያችሁት? ችግሩን ለመቅረፍ ኢንስቲትዩቱ ምን ሠራ? ወደፊትስ ምን ታስቧል?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- እኔ ወደ ተቋሙ ከመጣሁ አምስት ወር በላይ ሆኖኛል። ከመጣሁ በኋላ እንቅልፍ የሚያሳጣኝና እጅግ በጣም የሚያሳዝነኝ ጉዳይ ነበር። አንዳንድ ቦታ የተመራማሪዎችን ቢሮ የማሸግ፤ ሊዝ ክፈሉ የማለት ሁኔታ አለ። እኛ ኢንዱስትሪ አይደለንም፤ ነጋዴም አይደለንም፤ የምንሠራው ምርምር ነው። ለምሳሌ ሰበታ ከተማ ሊዝ ክፈሉ የሚል ደብዳቤ ልከው ቢሮውን አሽገው ነበር። ቅሬታ አስገብተን ቢሮው እንዲከፈት አድርገናል። በአሳ ላይ ለሚደረግ ምርምር ለአሳው ውሃ ያስፈልጋል። ነገር ግን ውሃ መጠቀም አትችሉም ተባልን።
በተመሳሳይ ቢሾፍቱም ደንቢ የሚባል ቦታ ተነጥቀን ለባለሀብት ተሰጥቷል። ለምሳሌ አውሮፓዊቷ ጀርመን ከተማ መሃል ሰፊ ቦታ ላይ የግብርና የምርምር ጣቢያ አለ። ከከተማው በፊት ምርምር ነው የተመሰረተው። ቦታውን ግን አልነኩትም። ምክንያቱም ግብርናቸውን የሚያሳድግና የሚያዘምን ስለሆነ ነው። እንዲህ አይነት የምርምር ስፍራ ከተማ መሀል መኖሩ የተጣራ አየር እንዲኖር የሚያደርግ ነው። ሕንድ ኒውደልሂ በተመሳሳይ ከተማዎች ሲያድጉ የግብርና ምርምር ቦታዎች አልተነኩም። ግብጽ ካይሮ ላይ በተመሳሳይ አልተነካም። በእኛ ሀገር ላይ ግን የመንግሥት የምርምር ስፍራ ስለሆነ የሚነጥቀው አካል ካሳ ስለማይከፍልበት እንዲሁ ተነጥቆ ይወሰዳል። ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመነጋር ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል።
የወንዶገነት የምርምር ቦታ አልተነካብንም። ሲያስቸግሩ የነበሩት ቢሾፍቱ፣ ሆለታ፣ ሰበታና ጅማ ውስጥ ነው። ጅማ መንገድ ይሠራልን ብለው አጋሮ ላይ ቡና ማሳ ውስጥ ገብተው ጨፍጭፈውብናል። ችግሩ ሲብስ ወደ ኦሮሚያ ክልል ርዕሰመስተዳድር በመሄድ አሳውቀን ነበርና ችግሩን አይተው እንዲፈታ ስላደረጉ ምስጋና ይገባቸዋል።
በአስቸኳይ ማንም አካል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርምር ቦታ እንዳይነካ የሚል ሰርኩላር ጽፈው እንዲያቆሙ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- የተነጠቁ መሬቶች ወደ ነበሩበት ተመልሰዋል ማለት ነው?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- ከቢሾፍቱ በስተቀር ሌሎቹ መሬቶች ተመልሰው በነበረበት ቆሟል። ሌላ በአዲስ አበባ አቃቂ ክፍለ ከተማ ላይ ስምንት ሄክታር መሬት ነበር፤ ሰርኩላሩ ከተላለፈ በኋላ ነጻ ተደርጓል። ሸገር ሲቲ ላይ ያለው ደግሞ መሬቱን ለማግኘት ካሳ መክፍል አለባቸው እያሉን ነው። 30 ዓመት ሙሉ ተጠቅመናል። ነገር ግን የእናንተ አይደለም ያለው የሸገር ሲቲ ከተማ አስተዳደር ካርታ አምጡ አሉን ካርታ ሳይሆን ይዞታ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ከምታደርጋቸው ጥረቶች መካከል አንዱ የሌማት ትሩፋት ነው፤ እነዚህንና መሰል ተግባራትን በምርምር ከመደገፍ አኳያ ተቋሙ የሠራቸው ተጨባጭ ሥራዎች ምንድን ናቸው?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- የሌማት ትሩፋት ላይ ከሚሠሩ ሥራዎች አንዱ የሥነተዋልዶ ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ነው። በተለይ በደብረዘይትና ሆለታ እንሠራለን። የአንድ ቀን ጫጩት በማሠራጨት ይሠራል። ይህን ለማሰራጨት መንግሥት የያዘው ዕቅድ አለው። ለዚህ ብሎ ሀዋሳ አካባቢ የገነባው ቦታ ስላለ ለሀገሪቱ የአንድ ቀን ጫጩት ለማሰራጨት እየተሠራ ነው። እኛ በምርምር ሥራ እየረዳን ነው። ዶሮቹ ምን አይነት ቢሆኑ ነው የተሻለ ምርት የሚሰጡት? በሽታን መቋቋም የሚችሉት? ለአርሶ አደሩ ውጤታማ እርባታ የሚሆኑት? በሚለው ምርምር እየሠራን ነው። ይህን ሥራ መሥራት ብቻ ሳይሆን የስልጠና እና የማማከር ሥራ እየሠራን ነው፡፡
የሌማት ትሩፋቱ አንዱ የወተት ምርትን መጨመር ነው። የወተት ምርትንና ምርታማነትን ለመጨመር የወተት ላሞችን መኖ ምን አይነት መሆን እንዳለበት መኖ ላይ የምርምር ሥራ ይከናወናል። ብዙ ጊዜ በጋ ላይ ወተት ይወደዳል የሚል ሀሳብ ሲነሳ ይደመጣል። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? በጋ ላይ መኖን የማምረትና የማስቀመጥ ሥርዓት በአግባቡ መያዝ አለበት። የመኖ አይነት በሙሉ የምርምር ሥራ እየተሠራበት ነው። ለማሻሻል ሙከራ እየተደረገ ነው። ሌሎች ከዚህ ጋር የተያያዙ የአርቲፊሻል ‹‹ሲመሌሽን›› እየተሠራበት ነው። ይህ ማለት በማዘመን ለአርሶ አደሩ አገልግሎት ይሰጣል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ሀብት ቀዳሚ ሀገር ብትሆንም ባላት አቅም ግን ተጠቃሚ እንዳልሆነችና የኢንስቲትዩቱ አበርክቶ ዝቅተኛ ነው የሚል ቅሬታ ሲነሳ ይደመጣል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው? በቀጣይስ ምን መሠራት አለበት ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- የእንስሳት ምርትና ምርታማነት አነስተኛ መሆኑ ይታወቃል። የዋጋ ውድነቱ ከተቋሙ ጋር የሚያያዝ አይደለም። እነሱ ቢሠሩ ኖሮ የሚለው ነገር አይገናኝም። ምክንያቱም የእኛ ተግባር የተሻለ የከብት እርባታ፣ የተሻለ የስጋ አመራረት፣ የወተት አመራረት መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ማውጣት ነው። ነገር ግን እኛ አናመርትም። በምርምር የተገኘው ቴክኖሎጂ ወስዶ ካላመረተ ውጤት አይኖርም።
ስለዚህ ምርት መመረት አለበት። ለማምረት ደግሞ ቴክኖሎጂ መጠቀም ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂው ተቀብሎ በሰፊው መመረት አለበት። ቴክኖሎጂው አለ፤ ማምረት ግን ይፈልጋል። ምርት ደግሞ መሬት ይፈልጋል። የወተት ላም ብዛት መኖር ሳይሆን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የተሻለ መኖ በማቅረብ የተሻለ ወተት እዲሰጡ ማድረግ ነው። ስለዚህ ከወተት መወደድ ጋር የሚያያዝ አይደለም። ሰው ወደ ሥርዓቱ ገብቶ ኢንቨስት ማድረግ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ፕሮፌሰር ንጉሴ፡- እኔም ስለሰጣችሁኝ እድል አመሰግናሁ።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም