በኢትዮጵያውያን ባሕልና እሴት ላይ የተመሰረተ ተቋማዊ መሰረት ያለው ዴሞክራሲ እየገነባን ነው” – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በኢፌዴሪ የሕ ዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር

የዛሬው የዘመን እንግዳችን በሕ ዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ናቸው። ከሚኒስትሩ ጋር ባደረግነው ቆይታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ፣ አሁናዊው የፖለቲካ ምሕዳር፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ተዳስሰዋል፤ መልካም ቆይታ!

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ለውጦች የዴሞክራሲ ጥያቄን በመመለስ ረገድ የነበራቸው አስተዋጽኦ ምን ይመስላል ?

ተስፋዬ (ዶ/ር)፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ አንዱና ዋነኛው ማዕከል የዘመናት የትውልዶችን የዴሞክራሲ ጥያቄ መመለስ እንደሆነ መንግሥት ያምንበታል። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በተለያየ መልኩ እንደምንገነዘበው በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የለውጥ ሙከራዎች ተካሂደዋል። የእነዚህ ለውጦች ዋና ዋና መነሻ የነበሩት ሦስት ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህም የዴሞክራሲ፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የነጻነትና የእኩልነት ጥያቄዎች ናቸው።

ከዴሞክራሲ በቀር ሁለቱ ጥያቄዎች በ1966 ዓ.ም. እና በ1983 ዓ.ም አብዮቶች በተወሰነ ደረጃ ምላሽ አግኝተዋል። ለምሳሌ የእኩልነት ጥያቄን በተመለከተ የተለያዩ ብዙኋን ማንነቶች እኩልነት ሕ ገመንግሥታዊ ዕውቅና ጭምር እንዲያገኝ ሆኗል። ከፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በ1966ቱ አብዮት ጊዜ በዋናነት መሬት ዋነኛ የኢኮኖሚ ማዕዘን ስለነበረ የመሬት ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ ምላሽ አግኝቷል። ነገር ግን በሁለቱም የለውጥ ንቅናቄዎችና ሕ ዝብ በከፈላቸው መስዋዕትነቶች በተሟላ መልኩ ምላሽ ያልተሰጠው የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው። ስለዚህ የዴሞክራሲ ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት የኢትዮጵያውያን የትውልዶች ጥያቄ መሆኑን መንግሥት በደምብ ይገነዘባል።

አዲስ ዘመን፡- ለአምስት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ ባሕ ል እንዴት ይገመግሙታል ?

ተስፋዬ (ዶ/ር)፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሀምሳ ዓመታት የተገነባው የፖለቲካ ሥርዓትና ከዚያ በፊት የነበረው የፊውዳል ሥርዓት እጅግ በጣም ኋላቀር፣ ደካማ እና ከዴሞክራሲ ጋር የማይተዋወቅ የፖለቲካ ባሕ ል ነው የነበረን። የፊውዳሉ ዘመን “ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ” የሚልና ከዴሞከራሲ ጋር የማይተዋወቅ፣ ፖለቲካ ውስጥ ሚና ያላቸው ጥቂት ሰዎች ፈላጭ ቆራጭ የሆኑበት ነው። ከ1966 አብዮት በኋላ የመጡ የፖለቲካ አመለካከቶች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ነጣጣይ፣ በታኝና በነጠላ ትርክቶች ላይ የተመሰረተ ናቸው። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተመሰረተበት አንዱ ነገር ፍረጃ ነው። የጠላትና የወዳጅ የሚባል የተቃርኖ ፖለቲካ ሲራመድ ቆይቷል። በእነሱ መቃብር ላይ ካልሆነ እኛ መለምለም አንችልም፤ የእኛን እሳቤ ተግባራዊ ለማድረግ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያለው አካል መጥፋት አለበት የሚል በፍረጃ፣ በመጠፋፋት፣ በጠላትና ወዳጅ ተቃርኖ የተመላ ፖለቲካ ነው የቆየን፡፡

ሌላው ደግሞ ፍላጎታችንን በኃይል እናስፈጽማለን የሚሉ አካላት ፖለቲካ ሲለማመዱ ነው የቆዩት። ስለዚህ አንድ ሰው የሆነ የፖለቲካ ሀሳብ፣ የሆነ ቡድን ወይም የአንድ ወገን ፍላጎት ካለ ያንን በጠመንጃ ኃይልና በግጭት መጫን እንጂ በሃሳብ የበላይነት እናሸንፋለን የሚል ልምምድ ያልነበረበት ነው።

ፖለቲካችን በእነዚህ ምክንያቶች በከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ጽንፈኝነት መገለጫ ባህሪ ይዞ ነው የቆየው። የፖለቲካ ጽንፈኝነት ማለት ከእኔ ሀሳብ ውጭ ሌላው ሃሳብ በፍጹም ትክክል አይደለም የሚል ነው። የኔን ሀሳብ ሌላው መቀበል አለበት፣ ካተቀበለ በመግደልም፤ በማሰርም፤ በማሳደድም የእኔን ሀሳብ እፈጽማለሁ ብሎ ማሰብ ነው። ይሄ ሰጥቶ መቀበልን የማያውቅ እጅግ ኋላ ቀር የፖለቲካ ባሕላችን ነው።

አዲስ ዘመን፡- በ2010 ዓ.ም. የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት ምን አይነት ርምጃዎች ተወስደዋል ?

ተስፋዬ (ዶ/ር)፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን ብዙም ባልዘለለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተንቀሳቀሱበት መንገድ የራሱ ድክመትና ጥንካሬ የነበረውና አሻራ ትቶ ያለፈ ቢሆንም በብዙ መልኩ ጉድለቶች ያሉበት ነው። ስለዚህ መንግሥት የዴሞክራሲ ሥርዓት ከመገንባት አኳያ ከትናንት የተገኙ ወረቶችን ጠብቆ ይዞ መሄድና በሂደቱም የታዩ ጥፋቶችን ማረም የሚያስችል አቅጣጫ በመከተል ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው። ለውጡ ከመጣ በኋላ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ አንዱ የፖለቲካ ባሕሉን የመቀየር ጉዳይ ነው።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተያያዘ በታሪካችን ውስጥ አንዱ የሚታየው ድክመት የጠላትና ወዳጅ ፖለቲካ ነው። በእነሱ መቃብር እኛ እንለመልማለን ስለዚህ እነሱ ካሉ እኛ መኖር አንችልም በሚል የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት መያዝ በጽንፈኝነት እና አክራሪነት ብሎም በጠላትነት ሲያስፈርጅ ቆይቷል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድ ሀገር ልጆች ሆነው የጋራ መግባባት መፍጠር በሚኖርባቸው ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሠሩ የፖለቲካ ርዕዮት፣ የፖሊሲ እና የፕሮግራም ልዩነቶች ላይ በልዩነት መሥራት ሲገባቸው፣ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ተነስተዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖለቲካ እሳቤን በኃይል በጠመንጃ ለማፈን ተሠርቷል። ይህም ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት ውስጥ እንድንቆይ አድርጎናል። አዎንታዊ የሰላም ባሕል እየገነባን ባለመምጣታችን ሀገራችን የኋላ ቀርነትና የድህነት ተምሳሌት ሆና ቆይታለች።

የለውጡ መንግሥት ዴሞክራሲን በተመለከተ የተለያዩ ርምጃዎችን ወስዷል። እንደሚታወሰው ለውጡ እንደመጣ እስረኞችን መልቀቅ፣ የሚዲያ ምሕዳሩን መክፈት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩ ማድረግ እና ሌሎችም መሰል ርምጃዎች የተወሰዱት የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ምለሽ እያገኘ እንዲሄድ መሰረት ለመጣል ነው።

የለውጡ መንግሥት ዴሞክራሲን በተመለከተ ያለው አቋም ግልጽ ነው። በኢትዮጵያውያን ባሕልና እሴት ላይ የተመሰረተ ተቋማዊ መሰረት ያለው ዴሞክራሲ መገንባት አለበት ተብሎ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት ምክር ቤቶች፣ የፍትህ ተቋማት እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት ሚዲያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እንቧ ጠባቂ እና ሲቪክ ማሕበራት አካባቢ ያሉ የዜጎችን ተሳትፎ የሚገድቡ የፖለቲካ ምሕዳሩን የሚያጠቡ አሠራሮችና አዋጆች ተሻሽለዋል። ሕ ጎች ተቀይረዋል፤ አመራሩ ተጠናክሯል። የዴሞክራሲ ተቋማቱ ነጻ፣ ገለልተኛና ብቁ ሆነው እንዲገነቡ እየተደረገ ነው ያለው።

ስለዚህ በአንድ በኩል የዴሞክራሲ ጥያቄን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያዊ ባሕ ል፣ እሴትና ታሪክ ላይ የተመሰረተ ሕዝባዊ የዴሞክራሲ ባሕል ልምምድ እንዲኖር እየሠራን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ነጻ፣ ገለልተኛና ብቁ የዴሞክራሲ ተቋማቶች ሆነው ሀገርን መሸከም የሚችሉ፣ በጥቂት ቡድኖች፣ ግለሰቦች ወይም ሥልጣን ላይ ባለ መንግሥት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያና የመጪው ጊዜ ትውልድን ማዕከል ያደረጉ ተቋማት እንዲገነቡ እየተሠራ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ረገድ ያሳየውን አዲስ አካሄድ እንዴት ይገልጹታል ?

ተስፋዬ (ዶ/ር)፡- ሌላው ጉዳይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት ነው። ከተፎካከሪ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ምክር ቤት አለ። ምክር ቤቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መሪው ፓርቲ በአጠቃላይ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ልምምድ ውሰጥ የሚታዩ ስኬቶችን፣ ተግዳሮቶችን እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በጋራ የሚወያዩበት መድረክ ነው። በአንድ በኩል በጋራ ምክር ቤቱ ከተፎካካረ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ጥረት ይደረጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በየጊዜው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመገናኘት የምንመካከርበትና የዴሞክራሲ ባሕ ላችን ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ የምንመክርበት አሰራርም ተዘርግቷል። በሀገር ደረጃ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚደንት የሀገሪቱ የለውጥ መንግሥት መሪ እንዲሁም በየክልሎቹ ደግሞ ርዕሳነ መስተዳደሮች በተዋረድ እታች ድረስ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ቁጭ ብለው የሚነጋገሩበትና በመንግሥት ፓርቲ ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቀቃሴ ማነቆ የሚፈጥሩ ነገሮችን በጋራ ተነጋግረው የሚፈቱበት፤ በተመሳሳይ መንገድ ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሲንቀሳቀሱ ሕግና ሥርኣትን አክብረው ከመንቀቀሳቀስ አኳያ ችግር ካለ መንግሥትና መሪው ፓርቲ ከእነሱ ጋር የሚመካከሩበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡

ስለዚህ ይህን ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት ከወሰዳቸው ርምጃዎች ውስጥ አንደኛው ፖለቲካችን አካታች እንዲሆን የተለያዩ አመላካከቶች የሚራመዱበት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት መነሳት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትራችን በበዓለ ሲመት ቀን ባደረጉት ንግግራቸው ውስጥ ይሄ ፍኖተ ካርታ ቁጭ ብሎ ነው ያለው። ብዝኃነትን በአግባቡ የሚያስተናግድ የፖለቲካ ኢትዮጵያዊ መሰረት ያለውን የዴሞክራሲ ባሕል ከፍ የሚያደርግ መሰረት እንገነባለን ባሉት መሰረት አዲስ መንገድ ተከትለናል።

አንድነት ማለት አንድ አይነትነት አይደለም።

መንግሥት አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ አንድ እየሆንን፣ በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ እየዳኘን የምንሄድበት የፖለቲካ ሥርዓት እንገነባለን ብሎ ቃል በገባው መሰረት ተንቀሳቅሷል። በ2013 ዓ.ም ምርጫ ሕ ዝቡ ለብልጽግና ፓርቲ መንግሥት መመሥረት የሚያስችል ከፍተኛ ድምጽ ማግኘቱ ይታወሳል። ብልጽግና ፓርቲ አሸናፊ ቢሆንም እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ ለውጥ መንግሥት በሀገራችን ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ የመሥራት ልምምድ የሌለን እንደመሆናችን መጠን አብሮ ለመሥራት ያለንን ቁርጠኝነት በቃላት ብቻ ከማውራት ባለፈ በተግባር ማረጋገጥ አለብን የሚል አቋም ይዘናል። በዚህ መሰረት ከፌዴራል መንግሥት ካቢኔ እስከታችኛው ወረዳ ድረስ ያሉ የመንግሥት አመራር አካላት ከተፎካካሪ ፓርቲዎችም ጭምር እንዲዋቀሩ ለማድረግ ተሞክሯል።

የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያሳተፍነው ሦስት አራት መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ነው። አንደኛው የተለያየ የፖለቲካ እምነት ኖሯቸው የፖለቲካ ፓርቲ የመሰረቱ ሰዎች ኢትዮጵያዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት ይችላሉ። በአመለካከት መለያየት በአንድ ሀገር ውስጥ የዘመናዊነት ምልክት እንጂ እንዳለፈ ታሪካችን አንዱ ሌላውን እንዲጠፋ የሚደረግ የጠላትነት ምልክት አይደለም የሚለውን ነገር ለማሳየት ነው። ሁለተኛ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኋላ ቀሩን የፖለቲካ ባሕላችንን መቀየር አለብን የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። ሦስተኛው ዴሞክራሲን ለመለማመድ አይነተኛ መሳሪያ ይሆናል ተብሎ ነው ርምጃው የተወሰደው።

ስለዚህ ከዚህ አኳያ የብልጽግና ፓርቲም ሆነ የመንግሥት ቁርጠኝነት አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ባልተሄደበት መንገድ በመሄድ በኢትዮጵያ ተቋማዊ መሰረት ያለው የዴሞክራሲ ባሕል ልምምድ እውን ለማድረግ የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ትልቅ ርምጃ ነው ብለን እናምናለን።

በአጠቃላይ እኛ እንደ መንግሥት ብልጽግና ፓርቲም እንደ መሪ የፖለቲካ ድርጅት የሚያምንበት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የምናደርገው ግንኙነት በፉክክር ላይ ብቻ ሳይሆን በትብብር ላይም የተመሰረተ መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት የወሰዳቸው ርምጃዎች ምን አይነት ውጤት አስገኝተዋል ?

ተስፋዬ (ዶ/ር)፡- እኛ ኢትዮጵያውያ አንድ ማወቅ ያለብን ነገር የዴሞክራሲ ባሕ ል መገንባት የሂደት ጉዳይ ነው። መንግሥት አንድ ጊዜ ይሄን አቋም ስለወሰደ ሁሉ ነገር ይስተካከላል ማለት አይደለም። በተወሰነ ደረጃ እስካሁን በተወሰዱት ርምጃዎች የመጣ እድገት አለ። ሆኖም ግን በተሟላ መልኩ ሁሉንም ነገር በሀሳብ የበላይነት በሰለጠነ ፖለቲካ ሃያ አንደኛውን ክፍለዘመን በሚመጥን መንገድ ፖለቲካችንን ማራመድ እንችላለን የሚል አመለካከት ገና የሁሉም የፖለቲካ ተዋንያን አመለካከት ስላልሆነ ማሕበረሰቡ፣ ምሁራን እና የሚዲያ ሰዎች ከዚህ አኳያ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል። ምክንያቱም ባለፉት ዘመናት ሁላችንም በጋራ እብደት ውስጥ ነው የቆየነው። ከዚህ እብደት ውስጥ ለመመለስ የሀሳብ መሪዎች የሚባሉ አካላት ጫና መፍጠር አለባቸው። ሕዝቡ ትልቅ ትግል እያደረገ አሁንም መስዋዕትነት እየከፈለ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሰላማዊ ትግልን ብቸኛ አማራጭ የሚያደርግ የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲጎለብት ከማን ምን ይጠበቃል ?

ተስፋዬ (ዶ/ር) የሆነ አመለካከት አለን ብለው በየጫካው የገቡ ሽፍታዎች የኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባሕላችን ውጤቶች ናቸው ብለን ነው የምናምነው። ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባሕላችን በጽንፈኝነት የተመላ ስለሆነ የዛ ጽንፈኝነት ሰለባዎች ናቸው። የሰላም አማራጭ የማይቀበሉ አካላትን ሃሳብ የሚደግፉት ጽንፈኛ ሚዲያዎች ናቸው። ስለዚህ ተያይዘን ነው ወደ ገድል እየገባን ያለነው ማለት ነው። እንደዚህ አይነት ነገሮችን ማረም ይፈልጋል።

ፖለቲካችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ትናንትን ነው ማዕክል የሚያደርጉት። ከትናንት ትምህርት ብቻ ነው መወሰድ ያለበት። እይታችን ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን አስተሳስረን መመልከት የምንችልበት የፖለቲካ አመለካከቶች ከፍ እያሉ መሄድ አለባቸው። ለሰላማችን ጠንቅ የሚሆኑ ጉዳዮችን ወደ መስመር በማስገባት መሥራት ይኖርብናል፡፡

በሀገር ደረጃ ከትናንት ታሪካችን እና ከትርክት ጋር የተያያዙ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚጠይቁ እንደ ባንዲራ እና ሕገመንግሥት ባሉ ጋዳዮች ላይ የሚኖሩ ቅሬታዎችን እንዲሁም ትናንት ተፈጸሙ የሚባሉ በደሎችን በተመለከተ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመፍታት እንደ ሀገር ትናንት በሆነ ነገር ዛሬ ሒሳብ እያወራረድን የምንሄድበትን ነገር በማቆም ትውልዳችን የራሱን አዲስ ታሪክ እንዲሠራ ማድረግ አለብን የሚል አቋም ይዘናል። ስለዚህ ከትናንት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎችን እና ጥፋቶችን በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና በሽግግር ሥርዓት እያከምን ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ ከትናንት ትምህርት ወስዶ ዛሬን የተሻለ ለማድረግ መንቀሳቀስ አለበት።

አዲስ ዘመን፡- እያንዳንዱ ሰው ፖለቲከኛ የሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ይህ ሁኔታ ወዴት ይወስደናል?

ተስፋዬ (ዶ/ር) ፡ ከማሕበራዊ ሚዲያ እና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አብዮት ጋር ተያይዞ አንዱ ትልቁ ችግር ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ መሆኑ ነው። ፖለቲካን ፖለቲከኞች ናቸው እንጂ መሥራት ያለባቸው ሁሉ ሰው ፖለቲከኛ ሊሆን አይችልም። ሁለት ነገሮች ናቸው ያሉት። ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ የመሆን ዝንባሌ እና ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ ለመሆን የሚሄድበት መንገድ ስሜትን፣ ጊዜያዊ የሆኑ ኮርኳሪ ነገሮችን ይዞ መጓዝና በዚያ ዙሪያ ላይ የተለያዩ ውዥንብሮችን መንዛትን ማዕከል አድርጎ መንቀሳቀስ እየበረከተ መጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የሀሳብ መሪ የሆነው ኃይል በዚህ ነገር ውስጥ ገብቶ መስመር ማስያዝ አለበት። ምክንያቱም ሀገርና ዴሞክራሲ የሚገነባው በዜጎች የነቃ ተሳትፎ ነው። ሁለት ነገሮች ሚዛን መጠበቅ አለባቸው። የትም ዓለም ላይ ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ ሊሆን አይችልም። ኢንጂነር፣ ሐኪም፣ አስተማሪ እና የሌላ ሙያ ባለቤት የሚሆን ሰው እንዳለሁ ሁሉ ፖለቲከኝነት እንድ መስክ ነው። እኛ ሀገር ነው እንጂ አስቸጋሪ የሆነው ፖለቲካ ሳይንስ ነው። እንደማንኛውም ማሕበራዊ ሳይንስ አንድ የሙያ ዘርፍ ነው። እኛ ሀገር የፖለቲካን ትርጉምን ሁላችንም እየሰማን ያደግንበት መንገድ ችግር ስላለበት መስተካከል አለበት፡፡

ሁሉ ሰው ፖለቲከኛ ሊሆን አይችልም ነገር ግን ሁሉም ሰው የሀገሩ ጉዳይ ያገባዋል። በተለይ የሰላም ጉዳይ ችግር ውስጥ ስንገባ ትክክል አይደለም ይቁም ማለት አለበት። ምክንያቱም መንግሥት በፖለቲካ አጀንዳ ምክንያት ግጭት ውስጥ መግባት አያስፈልግም የሚል አቋም ይዞ እየሠራ ነው የሚገኘው። ትናንት የተፈጠረው ነገር መፈታት ካለበት የሚፈታበት መንገድ ቀይሰናል። በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ፕሮግራም ተቀርጾ እየተሠራ ይገኛል። ስለዚህ ሰላምን፣ ልማትን፣ ሉአላዊነትን እንዲሁም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና አብሮነታችንን በተመለከተ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴታችንን የሚሸረሽሩ ነገሮች ሲኖሩ ትክክል አይደለም፤ ማንኛውም ሀሳብ ካለ በሰላማዊ መንገድ መሄድ አለበት ብሎ ሕ ብረተሰቡ መገሰጽ፣ መንገድ ማሳየት እና የራሱን ተጽዕኖ ማሳረፍ አለበት።

ይሄ ማለት ሁሉም ዜጋ ፖለቲከኛ መሆን አለበት ሳይሆን በፖለቲካ ዙሪያ ከሕዝብ የሚጠበቀውን ሚና ይጫወት ማለት ነው። የሀሳብ መሪዎች ቀና ቀና መንገዱን ማሳየትና ሀገርን ማዕከል በማየት ጊዜያዊ ስሜትን መተው አለባቸው።

አሁን ማሕበራዊ ሚዲያ ያመጣው አንድ ጣጣ ፖለቲካን የየዕለት ዕቅድ ነው ያደረገው። ፖለቲከኞችና ሀገር መሪዎች ለዛሬ ብቻ ሳይሆን የዛሬ ሠላሳ፣ ሃምሳ እና መቶ ዓመት ጭምር የት እንደርሳለን የሚለውን ነው።

በማሕበራዊ ሚዲያ እንደምናየው ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ ሆኖ የሚያብድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በሀገር ጉዳይ ላይ ምን አገባኝ ብሎ ነገር አለሙን እርግፍ አድርጎ መቀመጥም ትክክል አይደለም። በተለይ ሕዝቡ በሰላም፣ በሀገር እድገት እና ሰላም ዙሪያ ላይ በጋራ መቆም አለበት። በአመጽና መጠፋፋት ለውጥ እናመጣለን ብለው የየራሳቸውን ጠባብ የቡድን ፍላጎት ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ትክክል አይደለም እረፉ ማለት መቻል አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ትክክለኛ እና ጤናማ የሚባል የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዴት ያለ ነው ?

ተስፋዬ (ዶ/ር) ፡ የዜጎች የፖለቲካ ሥራ ጤናማ ነው የሚባለው ምን ሲሆን ነው የሚለው ጥያቄ በጣም ሰፊ ሀሳብ የያዘ ነው። እኛ እያልን ያለነው ኢትዮጵያውያን ከነብዝኃነታችን አንድ ሀገር ናትና ያለችን በአንድ በኩል የሲቪክ ማሕበረሰብ ግንባታን እያጠናከርን በሌላ በኩል ደግሞ የማሕበረሰብ ወይም የማንነት መብቶችን በማስከበር ሕብረብሔራዊ አንድነት ያላት ጠንካራ ሀገር ሆና መገንባት አለባት ነው። መምህሩ የትምህርትን ሥራ፣ ሀኪሙ የሕክምናን ሥራ፣ አርሶ አደሩ የእርሻን ሥራ፣ ባለሀብቱ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራ እየሠራ እያንዳንዱ አካል በተሰማራበት ዘርፍ በቅንነት፣ በታማኝነትና በኃላፊነት ስሜት ለሀገሩ ለሕዝቡ ሲሠራ ነው ጤናማ ፖለቲካ የሚኖረው።

ለምሳሌ ሚዲያዎቻችን መሥራት ያለባቸው ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባስብ የጋራ ትርክት መገንባት ነው መሆን ያለበት። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የነበሩን ትርክቶች ነጣጣይ ሆነው ነው የቆዩት። ሕብረብሔራዊ ማንንትን ኢትዮጵያዊ ማንነት ውስጥ ያሉ በጣም ብዙ እሴቶችን አጉልቶ አውጥቶ ሀገራዊ አንድነትን የሚገነቡ ሥራዎችን መሥራት አለባቸው። እያንዳንዱ ማሕበረሰብ የራሱ ማንነትና መብቱ ተጠብቆ በኢትዮጵያዊነቱ በዕኩልነት የሚኖርባት ምድር እንደሆነች ማሳየት አለባቸው። በሚዲያ ተቋም ውስጥ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን መሥራት ጤናማ ነው። ነገር ግን እከሌ አንተን በድሎሃል ተነስ ግደል ጨርሰው ማለት፣ የሰላም ጥሪ ሲቀርብም የሰላም ጥሪ የሚባል አይሠራም አራት ኪሎ ልትገባ ይህን ያህል ጊዜ ቀረህ እያሉ የሚቀሰቅሱትን ለሀገር እደማይበጁ ማሳየት ያስፈልጋል።

ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ እየሠራ በፖለቲካው መስክ የተሠማሩ አካላት ሲሳሳቱ በመረጃ ላይ በመመስረት ሕጋዊነት የተመላ ትችትና ተግሳጽ በማቅረብ ተጠያቂነት እንዲኖር እያደረጉ መሄድ ጤናማ ፖለቲካ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ዋናው ነገር ሀገርን ከፍ እድርጎ መመልከት ነው። ከጽንፈኝነት ከግለሰብ ፍላጎትና ከነጻ ትርክት በተላቀቀ መንገድ የኢትዮጵያን የወደፊት ትውልድ ማዕከል እድርጎ መሥራት ጤናማ ፖለቲካ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ምስጋና አቀርባለሁ፡፡

ተስፋዬ (ዶ/ር) ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

በተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You