የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት በምህጻረ ቃሉ ኢጋድ እአአ በ1986 በኢትዮጵያ፤ በኬንያ፤ በሱዳን፤ በሶማሊያ፤ በጅቡቲና ኡጋንዳ አማካኝነት ተመሰረተ:: ድርጅቱ ሲመሰረት ዋነኛ ዓላማው የነበረውም በምስራቅ አፍሪካ በተደጋጋሚ እየተነሳ የበርካቶችን ህይወት የሚቀጥፈውን ድርቅንና ጦርነትን ለመግታት፤ ቀጣናውንም ሰላምና ልማት ወደ ሰፈነበት ቀጣና ለመለወጥ ነው::
ይህንኑ ዓላማ ወደ ተግባር ለመቀየርም ኢጋድ በየአባል አገራቱ በርካታ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል:: ጦርነትና አለመረጋጋት የሚስተዋልባቸውን የቀጣናውን አገራት ፊታቸውን ወደ ሰላም እንዲመልሱ የማግባባት፤ ግንዛቤ የመፍጠርና ዘላቂ ሰላም የሚገኝበትን ስልት ሲነድፍ ቆይቷል::
በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚስተዋለውን የትምህርት እና የጤና ተቋማት ተደራሽነት ውስንነትን ለመቅረፍ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግም አገራቱ የተሻለ የማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል:: ለዚህም እንደ አብነት በደቡብ ሱዳን፤ በሱዳንና በሶማሌያ ያደረጋቸው ጥረቶች ተጠቃሾች ናቸው:: አሁንም የሰሜን ሱዳን ተፋላሚዎችን ወደ ሰላም ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኢጋድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው::
በተመሳሳይ መልኩ በጎረቤት አገራት የሚነሱ አለመግባባቶች ቶሎ እንዲፈቱና አገራቱ በፍጥነት ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለችው ሚና መተኪያ የሌለው ነው:: የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ጀምሮ በደቡብ ሱዳን፤ በሱዳንና በሶማሊያ ወደ ግጭት የገቡ ኃይሎችን በመሸምገል ውጤታማ ተግባራትን አከናውነዋል::
ግጭት ባልቆመባቸው በሱዳን የአብዬ ግዛትና በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ለአባል አገራቱ ጥላና ከለላ መሆን ችላለች:: ከሰሞኑም በቀውስ የምትገኘውን ሱዳንን ወደ ሰላም ለመመለስ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎች ከጀነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር እንደሚወያዩ አስታውቀዋል::
ውይይቱ በሱዳን ተባብሶ የቀጠለውን ጦርነት ማስቆም፣ ሁሉም አይነት ግጭቶች እንዲቆሙ እና ወታደራዊ አመራሮቹም ጦርነቱን ለማቆም ቁርጠኛ አቋም እንዲወስዱ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል::
በሌላም በኩል ላለፉት አርባ ዓመታት በድርቅ የሚጠቃውን የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን ለእርሻና ለኑሮ ተስማሚ ወደ ሆነ አካባቢ ለመቀየር ኢጋድ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል:: በዚህ ረገድ በተለይም ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢጋድ ያስቀመጣቸውን ዋና ዋና አላማዎች በማሳካት ረገድ ተጠቃሾች ናቸው::
ኢትዮጵያ በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ በበርካታ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በቀጠናው የሚታየውን ድርቅ በዘላቂነት ለመቋቋም አበክራ በመስራት ላይ ትገኛለች:: ከዚያም ባሻገር የአካካቢ መራቆት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ዋነና ችግር መሆኑን በመረዳት የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከኢትዮጵያ አልፎ በኢጋድ አባል አገራት ዘንድ እንዲተገበር የመሪነት ሚናውን ወስዳ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች::
ኢትዮጵያ የቀጠናውን አገራት ልማት በማቀራረብ ረገድ እየተጫወተችው ያለችው ሚና በአካባቢ ጥበቃ ብቻ የተገታ አይደለም:: በተለይም ከአባይ ግድብና ከጊቤ ሶስት ግድቦች የሚመነጭ ኃይልን ለጎረቤት አገራት በተመጣጣኝ ዋጋ በማዳረስ ቀጠናው በኃይል እንዲተሳሰር በማድረግ ላይ ትገኛለች:: በመንገድና ባቡር መሰረተ ልማቶች ላይ እያከናወነች ያለው ተግባርም የዚህ ሌላው መገለጫ ነው::
በድርቅና ርሃብ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ዛሬ ስንዴን በማምረት ኤክስፖርት የማድረግ ደረጃ ላይ ደርሳለች:: ይህ የአካባቢውን አገራት ከማነቃቃቱም ባሻገር አባል አገራቱ በቅርበት ስንዴን እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሮላቸዋል:: በቀጣይም ጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ ሩዝና መሰል ሰብሎችን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት አሰራር ተዘርግቷል::
የኢጋድ አንዱ ዓላማ አባል አገራቱ የተሻለ የንግድ ልውውጥ እንዲኖራቸው ማስቻል ነው:: በተለይም በአባል አገራቱ መካከል ነጻ የንግድ ቀጠናን ዕውን በማድረግ ሸቀጦች ያለምንም መሰናክል በሁሉም አገራት ገበያ እንዲገኙ ዕድል መፍጠር በኢጋድ በኩል በትኩረት እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው:: ይህንኑ ዕውን ለማድረግም ኢትዮጵያ በድሬዳዋ አካባቢ ነጻ የንግድ ቀጠና ኮሪደር በመክፈት የኢጋድን አላማ ወደ መሬት ለማውረድ እየሰራች ነው::
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በኢጋድ ጥላ ስር ሆና በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሰላምና ደህንነት፣ በመሰረተ ልማት እና ሌሎችም መስኮች የማይተካ ሚናዋን እየተወጣች፤ የምስራቅ አፍሪካ አባል አገራት በልማትና በሰላም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩሏን ሚና እየተጫወተች ትገኛለች:: ይሄው ተግባሯም ኢጋድ በቀጣናው የያዘውን ግብ እንዲያሳካ የሚያግዝ እንደመሆኑ፤ ቀጣይነት ባለው መልኩ ትስስርና ትብብሩን በሚያጠናክር መልኩ ኃላፊነቷን ትወጣለች::
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2015