የንብረት ግብር አንድ ግለሰብ አሊያም ሕጋዊ አካል ለሚጠቀምበት ንብረት ለመንግሥት የሚከፍለው ገንዘብ ማለት ነው። በአብዛኛዎቹ የዓለም አገራት የንብረት ግብር የሚለካው ንብረቱ በየዓመቱ ተተምኖ የሚኖረውን ዋጋ መሠረት በማድረግ ነው።
የንብረት ግብር ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግሥት እንደሆነ መዛግብት ያሳያሉ። አብዮቱን ተከትሎ የመጣው ደርግ ባወጣው አዲስ ሕግ መሠረት የመሬት እና የጣሪያ ግብር ዜጎች እንዲከፍሉ ማድረግ ጀመረ። በዚህ ወቅት መሬት ግብር የሚጣልበት ንብረት ሳይሆን ዜጎች ከመንግሥት የሚከራዩት ነበር። ቢሆንም ዓመታዊ ግብር መክፈል ግድ ይል ነበረ። በ1983 ዓ.ም ወደ ሥልጣን የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት ጊዜ ያለፈበት ያለውን የንብረት ግብር እንደ አዲስ ከልሶት ተግባራዊ ቢያደርገውም ዘላቂ ሊሆን አልቻለም።
በርካታ የዓለማችን ከተሞች የንብረት ግብር ጥለው በሚሰበስቡት ገንዘብ ራሳቸውን ይደጉማሉ። አብዛኛውን ጊዜ የንብረት ግብር የሚጣልበት መሬት እና ሕንፃ ቢሆንም ተሽከርካሪዎች ላይም ግብር የሚጥሉ አገራት አሉ። የንብረት ግብር(ፕሮፐርቲ ታክስ) ከሌሎቹ የግብር ዓይነቶች የሚለየው በቀላሉ የሚደበቅ አለመሆኑ ነው። መንግሥት በሚሠራው የዋጋ ግምት መሠረት የአንድ ንብረት ዓመታዊ ዋጋ ተሰልቶ የሚጣል በመሆኑ ግለሰቦች ይህንን ግብር የሚደብቁበት መንገድ እንደማይኖራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ::
የንብረት ታክስ በሌሎች አገሮች ከፍተኛ ወይም ትልቅ የገቢ ምንጭ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ይህም በአጠቃላይ የንብረት ግብር ተብሎ የሚጠራ የግብር ዓይነት ነው:: የንብረት ግብር በኢትዮጵያ ሁኔታ የጣራና ግድግዳ ግብር በሚል በደርግ ጊዜ በወጣ አዋጅ እስካሁን ድረስ የሚከፈልበት እንደሆነ ይነገራል፣ ሆኖም የክፍያ መጠኑ እጅግ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ብዙዎች ያነሳሉ:: በደርግ ጊዜ የወጣው ሕግ መሻሻል እንደሚገባው ብዙኃን የሚስማሙበት ጉዳይ ሲሆን፣ ንብረት የራሱ የሆነ የግመታ ሥርዓት ሊኖረው እንደሚገባም ይነገራል። በተጨማሪም የታክስ ሥርዓቱ መሻሻል እንዳለበት እና ይህንንም መነሻ በማድረግ በረቂቅ ደረጃ ሕግ እንደተዘጋጀለት እየተገለጸ ይገኛል::
የምጣኔ ሀብትና ኢኮኖሚክስ ባለሙያው ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ እንደሚናገሩት፤ ንብረት ላይ ሆነ ገቢ ላይ ታክስ የሚጣልበት የራሱ ዓላማ አለው:: በአንፃራዊነት ሃብት ካለው ሰው ግብር በመሰብሰብ ዝቅተኛ ኑሮ ላለው ሆነ እንደ መንግሥት የልማት ሥራዎችን ለመሥራት እና ተገቢ የሃብት ክፍፍል በማድረግ ከድህነት ወለል በታች ያሉ ዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚተገበር የግብር ሥርዓት ነው ይላሉ።
በተለይ የንብረት ግብር ሲባል በእግሊዝኛ አጠራሩ Trickle down የሚባል የኢኮኖሚ ሥርዓትን የሚመለከት ሲሆን ማለትም አንድ ሀገር እያደገች ስትሄድ እና ሀብት እየተከማቸ ይሄዳል የሚለውን ጥቅል አባባል የሚመለከት ነው:: ሀብት ካለው ወደ ሌለው ጠብ እያለ መሄድ አለበት፤ በዚህ ሂደት ድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎች ከድህነት ለመውጣትና ኑሯቸውን ለመደጎም ያስችላቸዋል:: ይህንን መነሻ በማድረግ ሀገር ግብር በሚከፍሉ ዜጎች እንድትደጎም ትደረጋለች:: ለዚህም ገቢ በሚያገኙ ዜጎች ላይ የሥራ ግብር ፣የንግድ ትርፍ ግብር ፣በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ንብረት(ፕሮፐርቲ) ላይ ግብር ይጣላል::
ስለ ንብረት ግብር ስናወራ ትክክለኛነት ወይም ፍትሐዊነትን ከማስፈን አኳያ አንድ ሰው ካለው ላይ ነው ግብር የሚከፍለው ይላሉ ዶክተር ዳዊት፤ እንደ ምሳሌ ሲያነሱ ትልቅ ሕንፃ ኖሮት ብዙ ኪራይ ከሚሰበስብ ግብር ሳይቆረጥ በወር አራት ሺህ እና አምስት ሺህ ከሚያገኝ አንድ ግለሰብ ግብር እየሰበሰቡ በርካታ ሃብት እና ንብረት ካለው የንብረት ግብር አለመሰብሰብ በራሱ ፍትሐዊ አይደለም ብለዋል።
የሀገራችንን ሁኔታ ስንመለከት ሃብት ያለው ሰው ግብር ሳይከፍል የሚያልፍበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑን ምሑሩ ይናገራሉ:: በሌላ በኩል ደግሞ ንብረት ማፍራት ከግብር ለመሸሽ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል፤ አንድ ሰው በየጊዜው ትናንሽ ገቢዎች ላይ ኢንቨስት አድርጎ ትርፍ ከማግኘት ይልቅ (fixed asset) ቋሚ ነገር ላይ አውሎ ሃብት የማካበት ሁኔታ አለ ፤ይህ ደግሞ ግብር ወደ መሰወር የሚያስገባ ነው ብለዋል።
መንግሥት በማወቅ ሆነ ባለማወቅ ወይም ወቅቱ አልደረሰም በማለት ሳይሰበስብ የቀረው በጣም ከፍተኛ የሆነ ግብር አለ፤ ስለዚህ ይህንን የንብረት ግብር በተገቢው ሁኔታ መሰብሰብ ከተቻለ በአሁኑ ጊዜ በእጅጉ እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ከማስፈን አኳያ ሰፊ ድርሻ የሚጫወት ይሆናል ብለዋል።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘካሪያስ ምኖታ በበኩላቸው፤ የንብረት ግብርን በተገቢው ሁኔታ መሰብሰብ የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ለዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት አይነተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ይላሉ::
በመሠረቱ ታክስ የሚሰበሰበው መልሶ ለሕዝብ ጥቅም ለማዋል እንደሆነና በመሠረተ ልማት ላይ ማለትም በመንገድ፣ በውሃ፣ በመብራት እና መሰል ዘርፎች ላይ ከዋለ ደግሞ የዜጎችን ሕይወት የመለወጥ አቅሙ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ:: ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለሀገር እድገት አስተዋፅዖ የጎላ ይሆናል:: ኢንቨስትመንት መሳብ ከተቻለ ደግሞ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ፤ይህ ደግሞ ለኢኮኖሚው ዕድገት አጋዥ ነው ብለዋል።
ነገር ግን የንብረት ግብር አሠራሩን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ የሕግ ማሻሻያ ይፈልጋል የሚሉት አቶ ዘካርያስ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ከመንግሥት እና ከሕዝብ ከሚለው ወጥቶ የግል መሆንን እንደሚጠይቅ ይጠቁማሉ:: በመጀመሪያ በተገቢው ሁኔታ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እናውለው ካልን ከሕግ አንፃር ብዙ የግድ መሻሻል ያለባቸው የመሬት እና የንብረት ነክ ጉዳዮች አሉ ይላሉ።
ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ በበኩላቸው ሲናገሩ፤ አፈፃፀሙ ላይ ችግር እንዳይፈጠር በተለይ የዋጋ ግመታ ላይ አሠራሩ የግለሰቦች ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ:: መስፈርቶችን ማዘጋጀት እና የሚተገበርበትን መንገድ ግልጽ እና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለመሥራት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ካልሆነ አንድ ሰው በትንሽ ንብረት ትልቅ ግብር በሌላ መልኩ ደግሞ ትልቅ ንብረት ይዞ ጥቂት የንብረት ግብር የመክፈል ሁኔታዎች ሊያጋጥም እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ያስቀምጣሉ::
በሌላ በኩል የታክስ ጫናው ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ እንዳያርፍ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግና የንብረት ግብር ዋነኛ ዓላማ አቅም ካለው ግብር ከፋይ በመውሰድ ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል መደጎም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ይላሉ::
ነገር ግን በዚህ ሂደት አብዛኛው ዜጋ የራሱ ቤት የሌለው እና በኪራይ ቤት የሚኖር እንደመሆኑ ይህንን ምክንያት አድርጎ ሌላ ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ሂደቱ በጥንቃቄ መመራት አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ቀድሞ መከላከሉ እንዳለ ሆኖ ይህንኑ ሰበብ በማድረግ በተከራዮች ላይ ዋጋ ጨምሮ በተገኘ ሰው ላይ ሲገኝ ተጨማሪ ግብር በመጨመር መቀጣጫ በማድረግ ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ እንዳይኖር መደረግ እንዳለበት ያስረዳሉ:: እንደ ምሳሌ ሲያነሱ፤ አንድ ሺህ ብር የሚያከራይ ሰው በዚህ ምክንያት አምስት መቶ ብር ከጨመረ ያንኑ ብር ለመንግሥት እንዲከፍል ከተደረገ አከራይ የመጨመር ፍላጎት አይኖረውም:: ከዚህ በተጨማሪ ጠንከር ያለ ቅጣት ከተጣለም የኪራይ ዋጋ ለመጨመር አይነሳሳም:: ይህንን አሠራር የሚያስጠብቅ አካል ግልፅነት የሰፈነበት መሆን አለበት :: አንዳንድ ሀገራት ላይ እንደተስተዋለው ለሙስና እና ማጭበርበር በር ከፋች እንዳይሆን መንግሥት አሠራሩን በጥንቃቄ እና ግልፅ በሆነ መንገድ መምራት አለበት ብለዋል ዶክተር ዳዊት።
ታክስ ሲጣል ሁለት መርሆዎች ታሳቢ መደረግ አለባቸው የሚሉት አቶ ዘካሪያስ፤ የመክፈል አቅም እና የተጠቃሚነት መርሐ በዋናነት መሠረት ተደርጎ እንደሚተገበር ዶክተር ዳዊት ያስረዳሉ:: ስለዚህ እነዚህ ሁለት ነገሮች ቀጣይነት ባለው መልኩ ታሳቢ ተደርገው መያዝ እንዳለባቸው ያብራራሉ::
የመሬቱ ወይም የንብረት የአካባቢ የገበያ ዋጋ በትክክል መጠናት እንደሚኖርበትና ከብዙ ዓመታት በኋላ ይህ ቦታ ምን ያህል ዋጋ ያወጣል የሚለውን በማስላት የዛሬው ተመን ሊወጣ እንደሚገባም ይጠቁማሉ:: ይህ እንዲሆን ደግሞ በመላው ሀገሪቱ ዳታ ቤዝ ተዘጋጅቶለት ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። አሠራሩም በመላው ሀገሪቱ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መመራት እንዳለበትና አካታች የሆነ ፍትሐዊ የሆነ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ያገናዘበ መሆን ይገባዋል ይላሉ:: በተጨማሪ የንብረት ግብር የማይክሮ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት በማይጎዳ መልኩ እና ለዋጋ ግሽበት ተጨማሪ መንስኤ በማይሆን መልኩ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ።
እንደ ዶክተር ዳዊት ገለጻ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በባለሙያ የተደገፈ አሠራር ሊኖር ይገባል:: ተጠያቂነት ያለው ተቋም የሚመራው ሆኖ ያለውን የመሬት ሁኔታ የመኖሪያ ፣የንግድ ፣የኢንዱስትሪ አካባቢያዊ መስተጋብር በአግባቡ በመለየት መሠራት አለበት:: የንብረት ግብር የምጣኔ አግባቡ ደግሞ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ተራውን ዜጋ ሆነ ባለሀብቱን በማይጎዳ መልኩ ሊሠራ ይገባል ።
አቶ ዘካርያስ በበኩላቸው አንዳንድ ሀገራት የንብረት ግብር ያስከፍላሉ ነገር ግን ከአጠቃላይ ግብር ተቀናሽ ያደርጋሉ:: አሁን ከኢትዮጵያ አንፃር ይህ አሠራር ሰለሌለ ተደራራቢ ታክስ እንዳይፈጥር እና ለዜጎች ወይም በኢንቨስትመንት ለተሠማሩ ሰዎች ወይም ለባለሀብቶች የምሬት ምንጭ እንዳይሆን እና ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ማነቆ ሆኖ እንዳይመጣ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ይላሉ።
ንብረቱ ያለበት ቦታ ሌላው ወሳኝ ነገር ነው የሚሉት አቶ ዘካሪያስ ልየታ ሲደረግ የተለያየ ደረጃ ያላቸውን ቦታዎች እኩል መታየት እንደሌለባቸው ይጠቁማሉ:: አሁን እየተተገበረበት ያለው ሁኔታ በጥናት እና በተደራጀ መልኩ ወደ ትግበራ የገባ ስላልሆነ በተለይ በዋጋ ትመና ወቅት በጥቅም በመመሳጠር ለሙስና እና ብልሹ አሠራር ተጋላጭ እንዳይሆን ያላቸውን ስጋት ገልፀው ጉዳዩ ቀለል ተደርጎ ሊታይ የማይገባው ትልቅ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ አመልክተዋል።
በአጠቃላይ አቶ ዘካሪያስ እንደተናገሩት፤እውነተኛ የንብረት ግብር ዳታ ቤዝ ወይም የመረጃ ሲስተም መተግበር አለበት:: ይህም ዲጂታላይዝ ሊሆን ይገባል:: ምክንያቱም ማን? የት? ምን ያክል መሬት ወይም ንብረት አለው የሚለውን ሰንዶ ስለሚያስቀምጥ ግልፅነት ለማስፈን ያግዛል ብለዋል።
ምሑራኑ እንደተናገሩት፤የንብረት ግብር ተግባራዊ ሲደረግ የመጨረሻ ጫናው ሄዶ በደሃው ዜጋ ላይ እንዳይወድቅ ይህንን የሚቆጣጠር አካል በተደራጀ ሁኔታ መፈጠር አለበት:: ተቋማዊ እና ተጠያቂነት ያለበት የሕግ ከለላ ያለው፤ በባለሙያ የተደራጀ፤ የማስፈፀሚያ አቅም ያለው ተቋም ተመሥርቶ እጅግ ከፍ በለ ጥንቃቄ ሊከናወን ይገባል::
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2015