ከአፍ የሚወጡ ክፉ ቃላት፣ ከእጅ የሚወረወሩ ፍላጻዎች ወደ ጨለማው ጦርነት ሲያስጉዞ፤ ቀና ንግግሮች፣ መልካም ተግባራትና እሳቤዎች ደግሞ ከጨለማው ጦርነት ወደ ብርሃናማው ሰላም ያደርሳሉ፡፡ ጦርነት ደግሞ ሃብት ንብረትን ያወድማል፤ የተሰራን ያፈርሳል፤ የተዋደደን ይነጥላል፤ ክቡሩን የሰው ልጅ አካልና ሕይወት ይነጥቃል፡፡ በአንጻሩ ሰላም ሰርቶ ሃብት ማፍራትን፣ ገንብቶ መቋጨትን፣ ወልዶ መሳምና አሳድጎ ለቁምነገር ማድረስን፣ ወዳጅነትና ወንድማማችነትን አጠንክሮ በፍቅር ማጽናትን የመሳሰሉ ከፍ ያሉ በረከቶችን ያድላል፡፡
ቀና ሃሳብ፣ መልካም ቃላትና ንግግሮች ከበጎ ምግባር ጋር ሲዳመሩ ደግሞ፤ ድቅድቅ ጨለማ የሆነውን አውዳሚ ጦርነት አስወግደው በቦታው ለሰው ልጆች ብሩህ መንገድ የሆነውን ሰላም ያስገኛሉ፤ ያጸናሉም፡፡ ኢትዮጵያም በተለያዩ ምክንያቶች በጨለማው ጦርነት ውስጥ አልፋ አያሌ ዜጎቿን ተነጥቃለች፤ በትሪሊዮን የሚቆጠር አንጡራ ሃብቷን ለእሳት ዳርጋለች፤ በወንድማማቾች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት ያሻገር ክፉ ጠባሳንም አዝላለች፡፡
ከእነዚህ ሁነቶች መካከል ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህም ከፍ ያለ ቁሳዊም፣ ሰብዓዊም ጉዳት ደርሷል፤ ሥነልቡናዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኖውም የገዘፈ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሌ በጨለማ መራመድ፣ በድቅድቅ ውስጥም መዳከር መጨረሻው ጫፍ የሌለው ጥፋትን የሚያስከትል እንደመሆኑ፤ ከጦርነት ለመውጣት እና ብርሃናማውን ሰላም እውን ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
ጥረቶቹም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰ የሰላም ስምምነት ወደ ፍሬነት የተሸጋገሩ ሲሆን፤ ይሄንን ፍሬ ዜጎች እንዲያጣጥሙት ለማድረግም ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህ ረገድ ቀዳሚው ተግባር ቁጭ ብሎ መነጋገር እና ከጦርነት ወደ ሰላም በሚያሸጋግሩ ጉዳዮች ላይ መልካም ውይይትን ማድረግ ነበር፡፡ በዚህም በመንግስት እና በሕወሓት አመራሮች እንዲሁም የጦር አዛዞች መካከል የተደረጉ ንግግሮች ዜጎች ከሰላም ስምምነቱ ፍሬ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ያስቻለ ነበር፡፡
ይሄንን የበለጠ ከማጠናከር አኳያም በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተመራ እና የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችን እንዲሁም የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችንና ሚኒስትሮችን የያዘ ልዑክ ወደ መቐሌ ተጉዞ ዜጎችን ከሰላም ስምምነቱ የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ በሚቻልበት ሂደት ላይ መክሯል፡፡ ይሄም ጦርነትን ወደ ሰላም መቀየር ብቻ ሳይሆን፤ ሰላምን የበለጠ ማጽናት የሚቻልበትን ሕዝባዊ አቅም የፈጠረ ነበር፡፡
ይሄም ሰላም እንደ ፀብ ምክንያት የማይፈልግ፣ ይልቁንም ስለ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከሚጨነቅ ስብዕና እንደሚመነጭ፤ ሰላም ግጭትን ለመፍጠር እንደሚደረግ ዝግጅት የተለየ ጊዜና ሁኔታንም እንደማይፈልግ፤ ይልቁንም ሰላም የሚፈልገው ቀና ሃሳብ እና የይቅርታ ልብ መሆኑን ያሳየ ነው፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሰላም እውን መሆን የተጉና የለፉ አካላትን የማመስገኛ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “ፀብ አቁሞ ሰላም ለመፍጠር በቂ ያልሆነ ምክንያት፤ ትክክለኛ ያልሆነ ጊዜም የለም፤” ሲሉ የተናገሩትም ይሄንኑ የሚያረጋገጥ ሃቅ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መልዕክታቸው ሰላምን ማጽናት ትልቅ ጀግንነት፣ የልብን ቆራጥነት እና ለሕዝብ መሰጠትን የሚጠይቅ ስለመሆኑ አስገንዝበውም ነበር፡፡ በወቅቱም ሦስት ዓመት ከመዋጋት 20 ዓመት መነጋገርና መወያየት እንደሚገባ፤ ኢትዮጵያውያንም በውይይትና በምክክር ችግሮቻችንን መፍታት መለማመድ እንዳለብን፤ ከምክር ይልቅ መከራ የሚመክረን እንዳንሆንም አስገንዝበው ነበር፡፡ በመነጋገርና በመወያየት በይቅርታና እርቅ ከተበላሸው ትናንት ይልቅ የተዋበ ነገን ለመፍጠር መስራት እንደሚገባም አሳስበው ነበር፡፡
ከዚህ አኳያ በጦርነቱ ከፍ ያለ ጉዳት የተከሰተባቸው አካባቢዎች (ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች) አብነት ሆነው እንዲገለጡም አስገንዝበው ነበር፡፡ ለአብነትም፣ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ወደ አማራ ክልል እና ወደ ትግራይ ክልል ተጉዘው ተቃቅፈው ይቅርታን፤ ተቀራርበውም መወያየትን በመግለጽ ለህዝቦች የሰላምን ልዕልና እንዲገልጡ ነግረውም ነበር፡፡
ይሄን መነሻ በማድረግም ከሰሞኑ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ባህርዳር ተገኝተው ይሄንኑ አሳይተዋል፡፡ በቀጣይም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ይሄንኑ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ይሄን መሰሉ ወንድማማችነትን እና ቁጭ ብሎ መነጋገርን መርሁ ያደረገ የሰላም ሂደት ደግሞ፤ በአመራሮች ጥረት እና በሕዝቦች የጸና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ መጓዙ መልካም ቢሆንም፤ ሂደቱ በሁሉም የፖለቲካ ልሂቃን እና ፖለቲከኞች ሊታገዝ ካልቻለ በሚፈለገው ልክ ሊጓዝም ሆነ ውጤታማ ሊሆንም አይችልም፡፡
በመሆኑም በየደረጃው ያለው አመራር፣ የሕዝብ እንደራሴ፣ እና ሕዝቡም የቀደመ ሰላምና አንድነቱን፣ ወንድማማችነትና አብሮነቱን ለመመለስ ሊሰራ ያስፈልጋል፡፡ በሁሉም ወገን ያሉ አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃንና ፖለቲከኞችም ዳር ቆሞ ከመተቸት፣ ሂደቱን ከማጠልሸትና ወደኋላ ከመጎተት እሳቤ መውጣትም ይኖርባቸዋል፡፡ የሆነውን እያሰቡ ከመቆዘምና ቂም ቋጥሮ ከመኖር ተወያይቶ በፍቅርና ይቅርታ ተሻግሮ የወደፊት ብልጽግናን መተለምና ለዚሁ በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ እንዲሆንም የሰላሙን ሃሳብና ጉዞ እንዲጸና ሁሉም ሊደግፈው ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2015