ዶክተር ገመዶ ዳሌ ተቀማጭነታቸው በኮትዲቯር አቢጃን ሲሆን፣ በዓለም አቀፉ የአረንጓዴ እድገት ኢንስቲትዩት ውስጥ የአፍሪካ የደንና የተፈጥሮ ሀብቶች አያያዝ መሪ ሆነው ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ፤ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በጀርመን አገር በኢኮሎጂ ሰርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችንም ሲያስተምሩም ቆይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የተቋሙ ስራ አስኪያጅ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴርን ደግሞ በሚኒስትርነት መርተዋል፡፡ ከሚኒስትርነት ከተነሱ በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል በዓለም አቀፉ የአረንጓዴ እድገት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ኢንስቲትዩት የመንግስታቱ ድርጅት ሲሆን፣ በአባልነት የያዘውም 45 አገራትን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ መስራች ከሚባሉት አስር አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ተቋሙ የተቋቋመው በ2012 ሲሆን፣ ሐሳቡን ያቀረቡትም ሆነ በወጪም በኩል ድጋፍ ያደረጉት የወቅቱ የደቡብ ኮሪያ መሪ ነበሩ፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ የተከፈተው በዚያው ዓመት ነው፡፡ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ከመደገፍ እስከ ትግበራው ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት የተቀበለችው ከመሆኑም ሌላ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ እንዲካተት እስከማድረግ ድረስም ሁኔታውን ስታስኬደው ነበር፡፡ የዛሬው ወቅታዊ ከዚሁ ከአረንጓዴ አሻራና ከብዝሃ ሕይወት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ አዲስ ዘመንም በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው ከዶክተር ገመዶ ዳሌ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ተከታዩን አጠናቅሯል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ ያልዎ ልምድ የካበተ ነውና ተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ የሚገኘውን ፋይዳ በተመለከተ ካለዎት አተያይ ጥያቄያችንን ብንጀምር?
ዶክተር ገመዶ፡- የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው የሚለውን ስንመልስ በዚህ ውስጥ የአገር በቀል ዝርያዎች ጉዳይ ይመጣል፡፡ የተፈጥሮ ሀብትን የምንጠብቀው ለሰው ልጅ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ መንፈሳዊ ብሎም ባህላዊ አገልግሎቶች ሁሉ ከተፈጥሮ ሀብት ሰለሚገኙ ነው፡፡
አንድ ሰው ጤናማ እንዲሆን ከተፈለገ ከተፈጥሮ ሀብት ጋር መታረቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም የአዕምሮም ጤና ጭምር በተፈጥሮ ሀብት ይታከማል፡፡ ሁሉም ምግቦቻችንን ብንወስድ ሁሉም ማለት በሚያስደፍር መልኩ በተፈጥሮ ሀብት የመጡ የብዝሃ ሕይወት ሀብቶቻን ውጤቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ጤፍን ብንወስድ የኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ሀብት ነው፡፡
አገር በቀል ዝሪያዎችን መጠበቁ ግድ የሚለን ውሃን፣ ንጹህ አየርን፣ የዳበረ አፈርን እንዲሁም ምግብንም ጭምር ለማግኘት ነው፡፡ እዚህ አገር በቀል በራሳቸው የሥርዓተ ምህዳር መስተጋብር ውስጥ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ በመሆናቸው የውጪውን አምጥተን ከምናስገባ የመጀመሪያ መስተጋብር ጤነኛ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረጉ የተፈለገውን አገልግሎት ማግኘት ያስችለናል፡፡ ለዚህም ነው የተፈጥሮ ሀብቶች በተፈጥሮ ቦታቸው መገኘት አለባቸው የምንለው፡፡
ይህን ስንል ግን በዓላማ፣ ለተለየ የኢኮኖሚ ፍላጎት፣ ለተለየ የኢንዱስትሪ ፍላጎት የውጪዎቹን ችግኞች አንጠቀምም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ባህር ዛፍን ብንወስድ የቀደሙ መሪዎቻችን ባህር ዛፍን ወደኢትዮጵያ እንዲገቡ አድርገው ባይተከል ኖሮ እንጦጦ ዛሬ ባዶ ሆኖ አዲስ አበባ ከተማ በጎርፍ መጥለቅለቅ በቸገረው ነበር። ለዚህም ነው በዓላማ ተክለን የምንጠቀምበት ከሆነ አገር በቀል ብቻ መሆን አለበት ተብሎ አይደመደምም፡፡ በመሆኑም እንደየሁኔታው የሚወሰን ይሆናል፡፡
እስካሁን ከተሰሩት ውስጥ ለአብነት ያህል የወዳጅነት አደባባይን ብንወስድ በዚህ የወዳጅነት አደባባይ ላይ የተሰራውን ስራ ሲጤን ችግራችን የቦታ ጥበት ሳይሆን የአስተሳሰብ ጉዳይ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ በከተማ ውስጥም እንደ ወዳጅነት አደባባይ አይነት ግቢ ሰርቶ ማሳየት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ገጠር ሲሆን ሁሉም ነገር ለእርሻ፣ ከተማ ሲሆን ሁሉም ነገር ለግንባታ ከማድረግ የተመጣጠነ ተፈጥሮ እና ልማትን ያገናዘበ ተግባር ታቅዶ መከናወን እንዳለበት አንድ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን በተወሰነ ጊዜ በዘመቻ አይነት ሳይሆን በስርዓት መመራት አለበት፡፡
ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት እያለን አገር በቀል ዝሪያዎች እየጠፉ ስለሆነ ለተፈጥሮ ሀብት መጥፋት ግንባር ቀደም ጠር ወይም ጠላት ግብርና ነው እንል ነበር። ይህን ነገር በአንድ ወቅት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ባሉበት በተቻለኝ አቅም ለማስረዳት ሞክሬ ነበር፡፡
አሁንም ግልጽ ለማድረግ ግብርናን የእኛ አመራር የተረዳበት ቅኝት ትክክል ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እርግጥ ነው ግብርና አብዛኛውን ሕዝባችንን የሚመግብ ነው፡፡ ከስራ አንግለልም ሲታይ ብዙውንም ሕዝብ ቀጥሮ የያዘ ዘርፍ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ዘርፍ ስለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ግብራችን ግን አሁን ያለውን ፍላጎት አርክቶን ለቀጣዩም የአገር ምጣኔ እድገት ለማረጋገጥ ከተፈለገ ሁሉንም አጥፍቶ ግብርናን በማድረግ ሳይሆን ለግብርና ራሱ መሰረት የሆነውን መሰረት ላይ አተኩሮ መስራት ግድ ይላል፡፡
ለምሳሌ በአሁን ወቅት የማዳበሪያ ግዥ በጣም ጨምሯል፡፡ የመሬታችንን ለምነት በአግባቡ መንከባከብ ሲገባን በማዳበሪያ ኃይል ምርት እንዲሰጠን እያደረግን ነው፡፡ ይህ መሬታችንን ጭምር የሚበክል ነው፡፡ ግብርና ያለ ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ማስኬድ ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ በግብርና ዙሪያ ከፍ ያለ ምርት አምራች አገር ናት፡፡ ለአብነት በኦቶዋንና በሚሽጋን አካባቢ ያለው የመሬት አቀመጣጥ ሲታይ ለጥ ያለ ነው፡፡ ስፍራውም ሲታይ የግብርና ማሳው ደን እንጂ የግብርና ውጤት አይመስልም፡፡ በማሳው ዙሪያ የሚታየው ደን ነው፡፡ ያደጉ አገሮች የሚያርጉት እንዲህ ነው፡፡
ወደእኛ አገር ሲመጣ ዛፍና ግብርና ጠላት ይመስል ደኑ ሁሉ ይጠፋና ማሳው ባዶውን እንዲቀር ይደረጋል፡፡ ዝርያዎች የተሻለ ምርት ለመስጠት ምቾት የሚሰማቸው አካባቢው ቀዝቀዝ ያለውን ነው፡፡ አብዛኛው የግብርና ምርቶቻችንን የምናገኘው የወንዴውና የሴቷ አካል በተለያየ ቦታ ላይ ሆነው ነው፡፡ እነዚህ አካላት ምርት እንዲሰጡን ከተፈለገ መዳቀል አለባቸው፡፡ ያንን የማዳቀል አገልግሎትን የሚሰጡት ቢራቢሮ፣ ንብ እና ሌሎች ነፍሳት ናቸው፤ እነዚህ ነፍሳት ደግሞ ላገለገሉን አገልግሎት በደረሰኝ ጠይቀውን ቢሆን ክፍያቸው ከባድ ይሆንብን ነበር፡፡ እኛ እያደረግን ያለው ጸረ አረም መድሃኒትም ሆነ ሌላው ሌላው በመርጨት እነዚህ ነፍሳት ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ እንቅፋት እንፈጥርባቸዋለን፡፡ ስለሆነም የአዳቃይ ነፍሳትን ጤናማነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ የግብርና ቦታዎች ዛፎችን መትከል ይበጃል፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን የተጀማመሩ ነገሮች አሉ። ስለዚህ አንዱ ዘንድ የሚሰራው ተፈጥሮ ሀብት በብዙ መልኩ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ላቅ ያለ ፋይዳ አለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በአረንጓዴ አሻራ እየተከናወነ ያለው ተግባር ለዚህ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው ማለት አይቻልም? አሰራሩንስ እንደምን አዩት?
ዶክተር ገመዶ፡- በአሁኑ ወቅት ያለው አመራር እያከናወነ ያለው ተግባር ለሪከርድ ያለመ የችግኝ ተከላ በመርህ ደረጃ እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ጉድለቶች አሉበት ወይ? ከተባለ አዎ ጉድለቶች አሉበት፡፡ ይህ ስራ በራሱ በተቋም ደረጃ እየተመራ ነው ቢባል መልሴ አይደለም ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆኖ ግን እየተሰራ ያለውና የተወሰደው እርምጃ ‹‹ይቻላል›› የሚለውን በሚገባ ያመላከተ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁርጠኝነት ሌሎቹን ሚኒስትሮች እንዴት እንዳንቀሳቀሰ ማጤን ተችሎበታልና በጥሩ ሁኔታ ቀጥሏል የሚል አተያይ አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፤ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ የልማት ስትራቴጂን ከመተግበር አኳያስ ያበረከተችወን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ገመዶ፡– በዚህ ስራ ግልጽ አቋም አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ የልማት ስትራቴጂን የዓለም ማኅበረሰብ ገና በጉዳዩ ላይ የጋራ መረዳት ሳይኖራቸው ያንን ማድረግ ይቻላል ብላ ብቻ ሳይሆን የስትራቴጂዋ አካል አድርጋ የገለጸች አገር ናት፡፡ ይህም የሆነው እኤአ 2011 ላይ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአገሪቷ መሪ ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት የተለመደው መንገድ ሳይሆን የአረንጓዴ እድገት አማራጭ ነው በሚል በመንቀሳቀሳችንን ነው ዓለም የሚያውቀን፡፡ ከዚያ በኋላ ስትራቴጂው የአገሪቱ ሰነድ ሆኖ ከጸደቀ በኋላ ወደአተገባበር ስንመጣ ደግሞ የሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲታቀድ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የእቅዱ አካል ሆኖ ነው የታቀደው፡፡
ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በወሰዱት እርምጃ ያንን በተሻለ መልክ በተግባር ለመግለጽ ችለዋል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ እና ኃይለማርያም የየራሳቸውን ጥረት አድርገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ የዶክተር ዐቢይን ለየት የሚያደርገው ግን ስራውን ራሱ የእርሳቸው ስራ አድርገው እያስኬዱት መሆኑ ነው፡፡ እርሳቸው የስራው ባለቤት በመሆን መስራታቸው ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ግን በአሁኑ ወቅት እየተሰራ ያለው ስራ በእጅጉ የሚያስመሰግንና ውጤቱም ያማረ መሆኑን ሳልናገር ማለፍ አልፈልግም፡፡ ለምሳሌ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት በወዳጅነት ፓርክ የተያዘው የተፈጥሮ ሀብት ሲታይ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በዚህ መልክ የተሰሩ በርካታ ስራዎች በመሆናቸው ለዓለም ማኅብረሰብ በአግባቡ የተገለጹ አይመስለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ መተከል የጀመረው ሁለተኛ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አለ፤ በመጀመሪያው ዙር በተካሄደው መርሃግብር ምን የተገኘ ስኬት አለ ይላሉ? ከዚህስ በኋላ ምን መደረግ አለበት?
ዶክተር ገመዶ፡- የአንደኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ በጣም በተሳካ ሁኔታ የማኅበረሰብ ንቅናቄ ተፈጥሮ ተሰርቷል፡፡ ይህ ንቅናቄ በሌሎች አገሮች አይገኝም፡፡ አጋጣሚ ሆኖ አሁን ከምሰራበት ከከኮትዲቯር አቢጃን ወደ ዛምቢያም እና ዑጋንዳ በስራ ምክንያት በሔድኩበት ወቅት ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ሁለቱም ዘንድ ያለው አሰራር ከእኛ ጋር የሚመሳሰል አይደለም፡፡ እኛ ዘንድ ልዩ የሚያደርገው የተፈጠረው ንቅናቄና ይህ ንቅናቄ ደግሞ የተመራበት አግባብ ጥሩ ነው፡፡ ይህ የተፈጠረው የሕዝብ ንቅናቄ መቀጠል አለበት ባይ ነኝ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ሁሉም አመራር ፕሮግራሙን የራሱ እንዲያደርግ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በኋላ ፕሮግራም በራሳችሁ ስሩ ቢሉ ስንቱ ሚኒስትር፤ ስንቱ የክልል መሪና ሌላውም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ጉዳዩን ሊያስኬደው ይችላል? ቢባል በአግባቡ ስለመሰራቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ይህ ሊጤን የሚገባው ነው፡፡
ሶስተኛው ደግሞ ጥሩነቱ በርካታ ችግኞች መተከላቸው ነው፤ እዚህ ላይ መተኮር ያለበት ጉዳይ ግን በጣም ብዙ ችግኝ የተተከለው የት ነው? የተተከሉትስ ለምን ዓላማ ነው? የሚለውን ነገር የምናጠራበት ታማኝ የመረጃ ስርዓት የለንም፡፡ ሲጀመር እየተከልን ያለነው አገር በቀል ዝርያዎችን ነው የሚባል ከሆነ ሐሳቡ ጉድጓዱ ከመቆፈሩ በፊት አገር በቀል ዝርያዎችን ከዘር ለቀማው ጀምሮ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
ለምሳሌ አገር በቀል ዝርያ ለአዲስ አበባ እና ለሞጆ ተመሳሳይ መሆን የለትም፡፡ ስለዚህ የትኞቹ ዝርያዎች የት? እና ለምን? ዓላማ መተከል አለባቸው? የሚለው ነገር እየተሰራ ያለው መጤን አለበት፡፡ በእኔ አተያይ እንዲህ አይነቱ ክፍተት በሁለተኛው ዙር ላይ ይስተካከላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዘር መስብሰብ እስከ ችግኝ ማፍላትና ቦታ መርጦ መትከል ድረስ ጥንቃቄ ይደረጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ መልኩ ሰርተን ኢትዮጵያውያን ችግኝ ተክለው የጠፋውን የደን ሽፋን በዚህ ያህል መጠን አሳደጉ፤ ሕዝባቸውንም ተጠቃሚ አደረጉ የሚል የተደራጀ መረጃም ሊኖረን ይገባል፡፡
አንድ ችግኝ፤ ዘር ከመምረጥ እስከ ማፍላት ያለው ሒደት በገንዘብ ሲሰላ እስከ አንድ መቶ ብር ድረስ ወጪ ይወጣበታል፡፡ ይህ ለአንድ ችግኝ ሲሆን፣ የሁሉም ሲሰላ ወጪው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አይከብድም፡፡ ያ የተተከለው ችግኝ አልጸደቀም ማለት ደግሞ ምን ያህል ወጪ እንደወጣበት ማስላቱ ከባድ ነው። እንኳን ይህ ሁሉ ገንዘብ ወጥቶበት የሚባክን ነገር ቀርቶ ኢትዮጵያ እንዲሁም ሀብት የሌላት አገር ናት፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነቱ ክፍተት በሁለተኛው ዙር እንዳይደገም ማድረጉ ትልቅ ብልህነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን የመንግስትን ዩኒቨርሲቲዎችን ብቻ ስንወስድ 46 ያህል አሉን። በእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በትንሹ እስከ 10 ሺ ተማሪዎች አሉ እንበል፡፡ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ተማሪዎቻቸውን ይቀልባሉ፡፡ የሚያበስሉት ደግሞ በእንጨት ነው፡፡ የምግብ ማብሰያ እንጨት የሚመጣው ደግሞ ደን እተጨፈጨፈ ነው፡፡ የደን ሳይንሱን በአግባቡ ያውቃል የሚባለው የወንዶ ገነት የደን ኮሌጅ ራሱ የሚያበስለው ከደን በሚሰበሰብ ማገዶ ነው። ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚያበስሉት አብዛኞቹ በማገዶ ነው፡፡ ገጠርም ከተማም ያሉ እንዲሁ የሚያበስሉት በማገዶ ነው፡፡
ይህን ሊቀለብስ የሚችል ነገር ደግሞ የታቀደ ኮሜርሻል ፕላንቴሽን ወይም ለንግድ የታቀደ ሰው ሰራሽ ደን ነው፡፡ ይህ በልዩ ትኩረት መታቀድ አለበት፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት ተጀምሮ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮ ሀብቱን መጠበቅ እንደተጠበቀ ሆኖ ጎን ለጎን ለማገዶም ሆነ ለኮንስትራክሽን ለምሳሌ ለኤሌክትሪክ ምሰሶ ከሚያስፈልገው ጀምሮ የሚያገለግል ተብሎ ታቅዶ መተከል አለበት፡፡ እስካሁን ይህ የለም፡፡ ነገር ግን ታቅዶ መሰራት አለበት፡፡ ይህን ለመስራት ደግሞ የባለሙያም ችግር የለብንም፡፡ ልምዱም አለን፡፡ በዚህ ላይ በሁለተኛው ዙር በትኩረት ቢሰራበት የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አረንጓዴ አሻራ ሲባል ችግኞች እንዲተከሉ የሚታሰቡት ገላጣና በጣም የተጎዳ መሬት ላይ ነው፤ ለም በሆነ መሬት ላይስ ለምን አይተከልም?
ዶክተር ገመዶ፡– የምንሰራው የማዳበር ስራ ከሆነ በገላጣ ቦታ ብንተክል ችግር የለውም፡፡ በተፈፈጥሮ የግጦሽ አሊያም የሳር መሬት የሆነውን ወደግጦሽ መቀየር ስህተት ነው፡፡ ይህ ሆነ ማለት ጤናማ በሆነ መሬት ውስጥ ባዕድ ነገር እንደማስቀመጥ ይቆጠራልና እሱ ደግሞ ሲሆን ስርዓቱን አናጋናው ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ በተፈጥሮ የእርሻ መሬት የሆነው ላይ ባህር ዛፍ መትከል ወይም በሌላ አገላለጽ ማሳን ወደባህር ዛፍ በታ መቀየር በጣም አደገኛ ነው፡፡ ሲሆን ሲሆን ተዳፋት የሆነ መሬት ላይ ችግኞችን ብንተክል ተመራጭ ነው፡፡ ዋናው አገራዊ ችግራችን የደን፣ የሳር፣ የእርሻ መሬት እያልን አለመለየታችን ነው፡፡ በዚህ መልክ ያለመለየታችን የአቅም ችግር አይመስለኝም፡፡ አሁንም ቢሆን ምርታማነቱ እንዲቀጥል ከተፈለገ ይህ መስተካከል አለበት፡፡
ከዚህ አኳያ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲም ሕግም የለንምና እሱን በማውጣት ደኑ ወደግብርና ሲሄድ መከልከል፤ ግብርናም ወደ ደኑ ሲሄድ መከልከል ያስፈልጋል፡፡ የደኑን መሬት ግብርናው ጨፍጭፎ ወደአዝርዕትነት ለመቀየር ሲታገል ሕግ ሊኖር ይገባል ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አገር በቀል ችግኞችን ለማግኘት ዋጋ እንደሚያስከፍል ይነገራል፤ ከዚህም የተነሳ የውጪው ላይ ርብርብር ሲደረግ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር ገመዶ፡- ለዚህ ችግሩ ችግኝ ስለመተከሉ ሩጫ የሚጀመረው ሰኔ ሲቃረብ መሆኑ ነው፡፡ አገር በቀል ዝርዎች አብዛኛዎቹ በመደብ ላይ ከአንድ ዓመት በላይ መቆየትን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ የበጀት ዓመቱ በሚጀምረው ሐምሌ ላይ እቅዱ ሲታቀድ ከነሐሴ ጀምሮ ዘሮቹ ካሉበት ተፈልገው መፈላት መጀመር ግድ ይላቸዋል፡፡ ስለዚህ አገር በቀል ዝርያዎች ነው የምንተክለው ብሎ ያቀደ አመራር በየችግኝ ጣቢያዎች እንዲፈሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
የግል ችግኝ ጣቢያ ያሏቸው ተቋማት የውጭ ዝርያዎች ፈጥነው እስከ ስድስት ወር ድረስ ስለሚደርሱላቸው የሚያዘጋጇቸው እነርሱን ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆንና የተሻለውን ውጤት ለማምጣት መልፋት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ግን አገር በቀል ችግኞችን ብቻ መትከል የተሳሳተ ስለሚሆን ያንን ብቻ ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የችግኝ ተከላውን ወደቀጣናው አገር በማስፋት ላይ ትገኛለች፤ ይህንን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዴት እያስተዋለው ነው?
ዶክተር ገመዶ፡- ሁለት ነገሮችን መለየት አለብን፤ በፖለቲካው በኩል የታየነው እንዴት ነው የሚለው ነገር ሲጤን የታየነው በጣም በመልካም መንፈስ ነው። ለምሳሌ ኮትዲቯር የራሳቸው የግሪን ሌጋሲ ኢኒሼቲቭ አላቸው፡፡ ሩዋንዳን ስናይ ደግሞ በተለይ በጽዱነቷ ለዓለም አቀፉም ማኅበረተሰብ ምሳሌ የሆነች አገር ናት፡፡
በዚሁ ግለት ግን ኢትዮጵያ አንድ ለየት ያለ እድል ያላት እና ያልተጠቀመችበት ብዬ የምለው ተራራዎችን ወደማሳነት ቀይሮ ስርዓት ምህዳሩን ለአደጋ ከማጋለጥ መቻል አለብን፡፡ እንደሚታወቀው ጎረቤቶቻችን ስናይ ዝቅ ያሉ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ኢትዮጵያ ከፍ ያለች አገር ናት፡፡ አረብ አገሮችን ጨምሮ ደኖቻችንን በአግባቡ አድምተን እንዲሁም የውሃ መገኘትን ጨምረን ውሃን ኤክስፖርት የማድረግ እቅድ ቢያዝ ትልቅ የኢኮኖሚ ትርጉም ያለው ስራ መስራት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ የአረብ አገራት፣ ሁለቱም ሱዳኖች ውሃን የሚያኙት ከየት ነው? ኢትዮጵያ የውሃ መገኛነቷ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህን ምቹ እድል መጠቀም ያለብን በሐሳብ ሳይሆን ታቅዶ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ስናደርግ ጉዳዩን ከቢዝነስ ጋር ማገናኘት ቻልን ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ውሃንም አልምተን ለውጪ ገበያ ማቅረብ እንችላለንና ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የአካባቢውን አገራት ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አገር ውስጥ ያሉ ዝርያዎችን በተመለከተ ከብዝሃ ሕይወት አኳያ ሲታያይ ምን ያህል አቅም አለ ማለት ይቻላል?
ዶክተር ገመዶ፡- የውጭ ዝርያዎችንም ሆነ የአገር ውስጥ ዝሪያዎችን የምንተክለው በአግባቡ ባህሪያቸውን ተረድተን ቢሆን ተጠቃሚዎች እንሆናለን። በውጭ ቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ማተኮር አገራዊ ልማትን አያረጋግጥም። አገራዊ ልማት የሚሳለጠው አንድም ከራስ በመነጨ አቅም ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አንደኛ ዝርያዎቻችንን በአግባቡ መለየት አለብን፡፡
ኢትጵዮያ በብዝሃ ሕይወት ሀብቶቻቸው በጣም የበለጸጉ ናቸው ከተባሉ 25 አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ይህ መታደል ነው፡፡ ይህ በየትኛውም መስፈርት ኢትዮጵያ ጥሩ አገራት ናት ተብሎ የሚሰጠን አሊያ የተሰጠን ነገር ሳይሆን በተፈጥሮ የታደለች አገር ሆና ያገኘችው ነው፡፡ የብዝሃ ሕይወት መገኛ ደግሞ ደንና ረግራጋማ (ዌትላንድ ወይም የመሬት ኩላሊት) አካባቢዎችን በአግባቡ በመያዝ ነው፡፡ ረግራጋማ አካባቢዎች ደግሞ በርካታ የብዝሃ ሕይወት ሀብቶቻችን መገኛ ናቸውና እያንጣፈፉ ወደማሳነት መቀየር ኪስራ ነው፡፡ ይህን አሰራር ትልልቅ የመንግስት ኃላፊዎች እንደስኬት የሚያወሩት መሆን የለበትም፡፡
እያንዳንዱ የብዝሃ ሕይወት ሀብት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው፤ ከመድሃኒት አኳያ ሲታይ ወደ ስድስት ሺ 29 አካባቢ ዝርያዎች አሉን፤ ከዚያ ውስጥ 10 ከመቶ የመድሃኒት እጽዋዕት ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሳ የመድሃኒት ፋብሪካዎችን እንገንባ ብንል እንኳ በአግባቡ ከለየንና ከተጠቀምንበት አቅማችን ብዙ ሊያስኬደን የሚችል ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ያሉ ተመራማሪና በመንግስት በኩል ጥሩ የሆነ ተግባቦት መኖር አለበት፡፡ ተመራማሪው ሁሌ ተቺ መሆን የለበትም፤ መንግስትም ተመራማሪውን ከቁምነገር የማይቆጥር መሆን የለበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቀጣናው ያለው የአካባቢያዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እውን የሚሆነው የተፈጥሮ ሀብቶችንና ድንበር ተሻጋሪ ስነ ምህዳሮችን በጥንቃቄ በማስተዳደር ነው ይባላል፤ ይህን እንዴት ያዩታል
ዶክተር ገመዶ፡– ይህ የግድ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከፍተኛ ደረጃ የፈጠሩት ድባብ በጣም ምቹ ነው። ኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እየጎላ ነው፡፡ እኛ ብቻ እየጠበቅን በሌላው አገር የሚኖር ተነሳሽነት የማይኖር ከሆነ ግን ትርጉም የለውም፡፡ በጋራ ለማደግ ድንበር ተሻጋሪ የተፈጥሮ ሀብት ማኔጅመንት (ትራንስባውንደሪ ናቹራል ሪሶርስ ማኔጅመንት) በደኑም ሆነ በውሃ መሰረታዊ ጉዳይ ነውና እሱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ኢትዮጵያ ደግሞ በሁሉም አቅጣጫ እድሉም አላት፡፡
ጥሩ ነገሩ ኢጋድ ይህንን እንደ አንድ ትልቅ አንኳር ጉዳይ ይዞ እየተነሳ መገኘቱ ነው፡፡ በኢጋድና በሌሎች ተቋማት ቅንጅት የተሻለ ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡ የተጀመረውም ችግኞችን የማጋራት እና አብሮ የመትከል ነገር ይህንን የበለጠ የሚያጠናክር ያደርጋልና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቆጣጠር ምን ያህል ጥረት እያደረገች ነው?
ዶክተር ገመዶ፡– ኢትዮጵያ በሁሉም መልክ ጥሩ የሚባል ስራ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ አንደኛ እያደጉ ያሉ አገራት አፈ ጉባኤ ሆና ስታገልግል ቆይታለች፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ምሳሌ በመሆን እየመራች ትገኛለች፡፡ ለተፈጥሮ ሀብት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ለመከላከል በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራ ነው ያለው፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ የተከሰተ እና የቆየ ስለሆነ ዛሬ በምንተክለው ችግኝ ልንቀለብሰው የምንችለው ሳይሆን ጊዜ የሚፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በዚህ ላይ ስትራቴጂ አውጥታ እየሰራች ነው፡፡ በማላመድና በማሻሻል ላይ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ይህ ደግሞ ጥሩ ምሳሌ የሚያደርጋት ናት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ከከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ገመዶ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2015