የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር የስነ ዜጋና ስነምግባር ትምህርት ለማስተማሪያነት ባቀረበው መፅሐፍ ምዕራፍ አራት ላይ እንዳስቀመጠው፤ ሥነምግባር ማለት፡- በምንኖርበት ማኅበረሰብና አካባቢ ተቀባይነትን ያገኘ መልካም ባሕርይን መላበስና መተግበር ማለት ነው።
ሥነምግባራችን ከአስተዳደጋችን፣ አኗኗራችንና ሥነልቦናችን ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው። ሥነምግባር ፍላጎታችንና ምርጫችን፣ በጎና ጸያፍ ሥራዎቻችን የሚመነጩበት የማንነት መገለጫ ነው። የሰው ልጅ በተፈጥሮው እንደሚኖረው አስተዳደግ ማኅበራዊ ገጠመኝ፣ መልካም ወይም መጥፎ ሥነምግባርን ሊላበስ ይችላል።
የሰው ልጅ በልጅነት ዘመኑ መልካም የሚባሉ ዓለማዊና መንፈሳዊ ሥነምግባሮችን እንዲያውቅና እንዲተገብር በሚያበረታታ ቤተሰብና ማኅበረሰብ ውስጥ ካደገ ሐቅንና መልካም ነገርን የመውደድና መጥፎ ነገርን የመጥላት ባሕርይን ያዳብራል። መልካም ባሕርይ አንድን ሰው በጎ ተግባራትን ያለማንም አስገዳጅነት እንዲያከናውን ያደርጋል።
እንዲህ ዓይነት ባሕርይ የተላበሰ ሰው የመልካም ሥነምግባር ባለቤት ነው ሊባል ይችላል። ሥነምግባር ከሰው የሚመነጭና ካለማንም አስገዳጅነት የሚፈፀሙ ተግባራት መገለጫ ነው። ለምሳሌ ሆደ ሰፊነትና እርጋታ፣ ታጋሽነትና ቻይነት፣ ቸርነትና ጀግንነት፣ ፍትሐዊነትና በጎነት፣ ወዘተ፣ የመልካም ሥነምግባር መገለጫዎች ናቸው።
በተቃራኒው የሰው ልጅ የባሕርይ ማስተካከያ አሊያም የቤተሰብ ክትትል ካልተደረገለት፣ ወይም በመጥፎ አስተዳደግ ካደገ፣ መጥፎውን መልካም፣ ቆንጆውን ደግሞ የሚያስጠላ አድርጎ የመመልከት ባሕርይ ሊኖረው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሰው አስነዋሪ ተግባራትን ያለምንም እፍረት ይተገብራል፤ ይናገራል። አንድ ሰው፣ አንድን መጥፎ ሥራ በንግግርም ሆነ በተግባር ያለምንም እፍረት የሚናገርና የሚተገብር ከሆነ፣ መጥፎ ሥነምግባርን የተላበሰ ነው እንለዋለን።
ከመጥፎ ሥነምግባር መገለጫዎች ውስጥ ተንኮል፣ ሐሰት መናገር፣ ግልፍተኝነት፣ ስግብግብነት፣ እብሪተኝነት፣ ተሳዳቢነት፣ ወዘተ፣ ይገኙበታል። የሥነምግባር መርሆዎች በጋራ የሚኖሩ ወይም የሚሠሩ ህዝቦች፣ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች በጋራ የሚመሩበት የሚከተሉትና የሚተዳደሩበት ራሳቸውንና ሥራቸውን ለመቆጣጠር የሚያግዙ የሥነምግባር መመሪያዎች ናቸው።
የሥነምግባር መርሆዎች እንደ አገሩ፣ እንደ ባህሉ፣ እንደ ሙያው ወዘተ.. ሊለያዩ ይችላሉ። ሆኖም በብዙ ሕዝቦች፣ ባህሎችና ሙያዎች ተቀባይነት አላቸው፡፡መልካም ሥነምግባር ያለው ዜጋ ለአገር እድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ዛሬ የአገራችንን እድገት ወደ ኋላ እየጎተቱ ላሉ እንደ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም በስልጣን መመካት ዋነኛ መንስኤ የሥነምግባር ጉድለት ነው። ለማኅበራዊ ሕይወት ጠንቅ የሆኑ እንደ ሌብነት፣ ሱሰኝነት፣ አጭበርባሪነት፣ ስግብግብነት፣ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ወዘተ የመብዛታቸው ምስጢርም የሥነምግባር ጉድለት ነው፡፡
ስለዚህ መልካም ሥነምግባር ያለው ዜጋ ማፍራት ለጤናማ ማኅበራዊ ሕይወትና ለአገር ብልጽግና ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ መልካም ዜጋ መሆን የሚፈልግ ሰው የማኅበረሰቡንና የሙያውን የሥነምግባር መርሆዎች አውቆ ማክበርና መተግበር ይጠበቅበታል። ይህንን ከሚያስፈጽሙና የዕውቀት ምንጭ ከሆኑት መካከል ደግሞ ትምህርት ቤቶች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
በአባባል ደረጃ እንደሚገለጸው፤ እውነተኛ ትምህርት ‹‹ልብንና አዕምሮን ያርቃል››፡፡ ለዚህም ትምህርት ቤቶች በስነምግባርና ስነዜጋ ትምህርታቸው ከእውቀት ባሻገር ያለውን እውነታ ለትውልዱ ያሳዩበታል፡፡ ምክንያቱም ስነምግባር እውቀት ብቻ ሳይሆን ኑሮም ነው፡፡ በስርዓተ ትምህርት ተካቶ በመምህራን ብቻ የሚሰጥ የነበረ የአቅም ማጎልበቻ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቃል፡፡ ውልደቱ አካባቢ መድረሻው ደግሞ ስኬት ነው። ብልሃት፣ እውነት፣ እውቀትና ልቀትን የምናገኝበት አገራዊ ልምድና ጥበብ ነው፡፡ ስነምግባር የነገዋን አገር የምናይበት መነጽርም ነው፡፡
በፉክክሩ ውስጥ ጥበብን የምናገኝበት ኃይል፡፡ ጥበብ ደግሞ አስተዋይነት፤ ከእኔነት ይልቅ ለሌሎች መትረፍ፤ የእኛነት ባህል ነው፡፡ እናም እንደ አገር የተያዘውም አቅጣጫ ይህንን በመመርኮዝ መሥራት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እውቀትና እውነታዎችን በትምህርት ለማገናኘት መሞከር ሲሆን፤ በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ተብሎ በአንድነት ይሰጥ የነበረውን ለየብቻ በማድረግ ትኩረት እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡
የዜግነት ትምህርት ለብቻው የስነምግባር ትምህርት ላይ ያተኮረውን ደግሞ ግብረገብ በሚል እንዲሰጥ ሆኗል። መማር ሽምደዳና ለቁጥር ከፍታ ከሆነ ከምረቃ በኋላ ነገሮች ያከትማሉ፡፡ ከሰዎች ጋር በትብብር ለመስራት፣ ሰርቶ ለመደሰትና የፈለጉት ስኬት ላይ ለመድረስም አያስችልም፡፡
መማር ከስርዓት መያዝና ግብረገብ ከመሆን ጋር ተያይዞ እንዲቀጥል ለማስቻል ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ተግባሩ እንዲከወን እድሎች ተመቻችተዋል፡፡ በእርግጥ ሰሚ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ወጥተው የተማሩትን ልምድ እንዲያደርጉ ማበረታታትም ይገባል፡፡ በተጨማሪም ወላጅና የአካባቢው ሰው ነባር ባህሉንና ወጉን እያሳወቃቸው በመልካም ስነምግባር እንደያድጉ ማገዝም ይኖርበታል፡፡
ከትምህርት ቤት ውጪ ያሉ ተቋማትና ድርጅቶችም እንዲሁ ተግባሩን ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክያቱም ዜጋን በመልካም ምግባር ማነጽ ለአንድ አካል የሚተው አይደለም፡፡ ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ተቋማት በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው የድርሻቸውን ሲወጡ የምንመለከተው፡፡
ድርጅቱ ቅን ኢትዮጵያ ይባላል፡፡ ቅንነትን፣ መተባበርንና መከባበርን እንዲሁም መደናነቅን ባህል ያደረጉ ዜጎችን መፍጠር ዋነኛ አላማው ነው፡፡ እናም ይህ ድርጅት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን አገር አቀፋዊ የማመስገንና የመደናነቅ ቀንን በየዓመቱ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ቀኑን ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ “ተማሪ ለአገር ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ አክብረውታል፡፡
በዓመታዊው አገር አቀፍ የመመሰጋገንና የመደናነቅ ቀን ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ባደረጉት ንግግር፡- ትናንት የነበረንን መልካምነትና አመስጋኝነት ባህል እያጣን በመምጣታችን አንድ ከሚያደርጉን እልፍ እሴቶች ይልቅ ልዩነታችን ላይ በማተኮራችን ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገናል። ስለሆነም እንደ አገር ቅንነት፣ መልካምነትና አመስጋኝነትን ባህሉ ያደረገ ተተኪ ትውልድ ማፍራት ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ለአንድ አካል የምንተወው ሳይሆን ሁሉም ተረባርቦ የሚያመጣው ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን የመደናነቅና የመመሰጋገን ባህላችን ከፍ ያለ ነበር ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አገራዊ ጀግኖቻችንን ዓለም እንዲያውቃቸው ሆኗል። ይህ መልካም እሴት እንዲጠናከር በትኩረት መሥራት ግን በብዙ መልኩ ይቀረናል። እናም ልዩ ትኩረታችን ሆኖ ልንሰራበት ይገባል፡፡ በዚህ ደግሞ የቅን ኢትዮጵያ ማህበር ያሳየው ቁርጠኝት የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ከመደበኛ መማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ አገር ተረካቢው ትውልድ በሥነምግባር የታነጸና መከባበርና መመሰጋገንን እሴቱ ያደረገ ሆኖ እንዲቀረጽ የግብረ ገብ ትምህርትን የመደበኛ ትምህርቱ አንድ አካል አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሆኖም ሁሉም ባለድርሻ አካላት አመስጋኝነትን፣ መደናነቅንና ቅንነትን እሴት ያደረገ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት መሥራት ይገባዋል፡፡
ምክንያቱም አሁን ላይ የአብሮነታችን ቱባ የተተረተረው ከሚያቀራርቡን በርካታ እሴቶች ይልቅ ጥቃቅን ልዩነታችን ላይ በማተኮራችን ነው፡፡ እናም አሁን የደበዘዘውን መልካም እሴት መልሰን የምናጠናክርበትና ቅንነት፣ መመሰጋገንና የመደናነቅ ባህላችንን የምናሳድግበት ጊዜ ነውና እድሉን መጠቀም ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ይህንን መልካም እሴት ባህሉ ያደረገ ዜጋ ማፍራት ላይ ግድ መስራት አለብን፡፡
ዶክተር ፋንታ እንደገለጹት፤ በቅርቡ ዜጎች ትምህርት ቤታቸውን በተለየ መልኩ የሚያግዙበት ሕጻናትም ከማመስገን ባለፈ የሚያስመሰግን ተግባር ምን እንደሚመስል የሚማሩበት መርሐ ግብር ይፋ ይደረጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መላው ኢትዮጵያውያን በቅንነት ከሚኒስቴሩ ጎን በመቆም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው አገራዊ ንቅናቄ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የቅን ኢትዮጵያ ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ካሣሁን አበሩ በበኩላቸው፤ እየደበዘዘ የመጣውን የአመስጋኝነት ባሕል ለመመለስ ከአገር ተረካቢ ልጆች መጀመር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከትምህርት ቤቶች እንዲጀመር ተደርጓል። ለዚህ ደግሞ ከቤተሰብ ቀጥሎ ልጆችን ኮትኩቶ በማሳደግ አገር ተረካቢ ትውልድ እያፈሩ የሚገኙ መምህራን ከፍ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል። ምክንያቱም ነገ መልካም እሴት የተላበሱ ዜጎች እንዲኖሩ እየሰሩ ነውና፡፡ ዛሬ ላይ መምህራን መልካም ዘር እየዘሩ ይገኛሉ፡፡ ድንግል መሬት ላይ የተዘራ ዘር ደግሞ ፍሬው ውጤታማ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡
የቅን ኢትዮጵያ መሥራችና የሀሳቡ ባለቤት ዶክተር ቶሎሳ ጉዲናም የሚሉት ሕጻንነት የነገ አገር ተረካቢ ዜጎች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ወላጆች፣ መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እነዚህ ሕጻናት ከመለያየትና ዘረኝነት ርቀው የአመስጋኝነት፣ የመደናነቅና ቅንነትን መልካም እሴቶችን ተላብሰው እንዲያድጉ መረባረብ አለባቸው፡፡
የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ አገራዊ አንድነት ለማጠናከርና ዜጎችን በሙሉ የሚያሳትፍ እንዲሆን መከባበርና መደናነቅ ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡ መመሰጋገን፣ መከባበርና መተባበር አንድነታችንን ይበልጥ ያጠናክራል። በዚህም ኢትዮጵያውያን ጠንካራ የመመሰጋገን ባህል ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን ለትውልዱ ማስተማርና እንዲኖረው አርአያ እየሆኑ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆንላቸው ደግሞ ለተደረገላቸው ብቻ ሳይሆን ለሚደረግላቸው ጭምር አመስጋኝ ይሆናሉ፡፡
ምስጋና የመከባበርና መተባበር መገለጫ ነው። መደናነቅና መከባበር እንዲሁም አመስጋኝ መሆን አንድነትን አጠናክሮ ትልቅ የመስራት ኃይልን ያጎናጽፋል። ለነገሮች ልዩ ትኩረት መስጠት፤ መተባበርና ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራት ይዳብራል፡፡ ለአገሩ ብሎ የሚሰራ ትውልድን ያበዛል፡፡ ተስፋን ስንቅ አድርገው ገና ከጅምሩ ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑም ያግዛል፡፡
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ተቋቁማ በአሸናፊነት እንድትቀጥልም ያስችላል፡፡ ስለሆነም እጅ ለእጅ ስንያያዝ ኢትዮጵያዊነት ውበታችን ይጎላልና ራሳችንን አድምቀን ለዓለም ጭምር ብርሃን እንሁን እንላለን፡፡ ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2015