ኢትዮጵያ የምታስመዘግበውን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ተከትሎ እንዲሁም ዕድገቱን ለማስመዝገብ በምታከናወናቸው ተግባራት በኮንስትራክሽን ዘርፉ በኩል ለውጦች ሲመዘገቡ ቆይተዋል። ይህም ስኬት አገሪቱን ግንባታ እንደ አሸን የፈላበት በመባል በውጭው ዓለም ጭምር እስከመታወቅ አድርሷትም ነበር፤ ይህን ግንባታ የሚያከናውነው የኮንስትራክሽን ዘርፉም እንዲሁ በተለይ በተቋራጮች፣ በአማካሪዎችና በባለሙያዎች በኩል በተሰጠው ልዩ ትኩረት ከቁጥር አኳያ ከፍተኛ ስፍራ ላይ መድረሱንም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ይመስክራሉ።
በአገሪቱ በመንግሥት ባለቤትነት የሚገነቡት የኃይል ማመንጫዎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የፍጥነት መንገድን ጨምሮ የሚገነቡ ሌሎች የመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ አየር ማረፊያዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የጤና ተቋማት፣ የባቡር መስመሮች፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች፣ ወዘተ እንዲሁም የከተሞች መስፋፋትና አዳዲስ ከተሞች መፈጠር ሲታሰብ አገሪቱ በርግጥም ኮንስትራክሽን የተስፋፋባት ስለመሆኗ ጥሩ ማሳያዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። በዚህ ላይ የግሉ ዘርፍ የሚያካሂዳቸው የሪል ስቴት፣ የሆቴል፣ የኢንዱስትሪና የመሳሰሉት ግንባታዎች ሲታከሉ ሁኔታው በርግጥም ኮንስትራክሽን እንደ እንጉዳይ የፈላባት ያስብላታል።
ይህ ዘርፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባጋጠሙት ተግዳሮት ለመቀዛቀዝ ተዳርጓል። እንደ ሲሚንቶ ባሉ የግንባታ ግብአቶች እጥረት፣ በፋይናንስ እጦት፣ በተወዳዳሪነት አቅም ማነስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃና በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ እንዲሁም በሰላም እጦት ሳቢያ የግንባታው ኢንዱስትሪ በሚጠበቅበት ስፍራ ላይ አይደለም፤ ተጎድቷል። ግንባታዎች ክፉኛ መጓተት፣ የግንባታ ወጪዎች በየቀኑ መናር፣ የአገር ውስጥ ተቋራጮች በዘርፉ ውስጥ ራሳቸውን ማቆየት እየተሳናቸው መምጣትም ይህንኑ ያመለክታሉ።
እየተቀዛቀዘ ያለው ደግሞ በፍጹም መቀዛቀዝ የሌለበት ግዙፍ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ነው። ለአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 19 በመቶውን ያበረከተ፣ ከአገሪቱ የካፒታል በጀት ከ60 እስከ 65 በመቶውን የሚያንቀሳቅስ እንዲሁም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከግብርናው ቀጥሎ ትልቁን ድርሻ የያዘ ዘርፍ ነው የተቀዛቀዘው።
የዚህን በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወት ግዙፍ ዘርፍ ችግሮች ከስር ከስር መፍታት በተገባ ነበር። ግን ያን ማድረግ አልተቻለም፤ በተቋራጮች በኩል ተወዳዳሪ ተቋራጭ ለመገንባት ዕቅድ ቢያዝም ተቋራጮች ተወዳዳሪ መሆን አይደለም ራሳቸውን ዘርፉ ውስጥ ማቆየት እየተቸገሩ መሆናቸው እየተጠቆመ ነው። በአጠቃላይ ይህ ኢንዱስትሪ መታመሙ፣ ያለተተኪ እየቀረ መሆኑ እየተገለጸ ነው።
ስለሆነም ኢንዱስትሪውን መታደግ የግድና የግድ ይሆናል። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርም የዘርፉን ችግሮች እያዳመጠ ለመፍትሄ እየሠራ ይገኛል። አዲስ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለመቅረጽ እየተዘጋጀ ነው። ለዚህ የፖሊሲ ሰነድ ግብዓት ለማሰባሰብም ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ሚኒስቴሩ በቀጣይ የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎችን እንደሚተገብርም ይጠበቃል።
የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት በፖሊሲ ማሻሻል ጭምር እያከናወነ ያለው ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው። አሁን የፖሊሲ ሰነዱን ለማዳበር ግብዓት እያሰባሰበ ያለበት ሁኔታ ባለድርሻዎችን በማሰባሰብ ጠንካራ የጥናት ሰነዶችን በማዘጋጀትና በማወያየት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
አገር እንዳለፉት ወቅቶች ሁሉ በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ትገኛለች። ይህንንም ዓለም አቀፉ ተቋም አይኤም ኤፍ ጭምር አረጋግጦታል። በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትና በአገሪቱ እየሰፈነ የመጣው ሰላም የምጣኔ ሀብት ዕድገቱን ዘላቂነት ይጠቁማሉ። በዚያው ልክ የግንባታው እንቅስቃሴም ይቀጥላልና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለዚህ በሚመጥን መልኩ ዝግጁ ማድረግ ይገባል። ዘርፉን ለመታደግ የሚከናወነው ተግባር ችግሮቹን ብቻ የሚፈታ ሳይሆን ቀጣይ ኃላፊነቶችን ለመወጣት የሚያስችል መሆን ይኖርበታል።
በተለይ በአገር በቀል ተቋራጮች ተወዳዳሪነት እንዲሆኑ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። በአስር ዓመቱ መሪ ዕቅድ የአገር በቀል ተቋራጮችን የተወዳዳሪነት አቅም በመገንባት ከዘርፉ ገበያ ድርሻ 75 በመቶውን፣ ከምሥራቅ አፍሪካ የዘርፉ ገበያ ደግሞ 25 በመቶውን እንዲይዙ መታቀዱ ይታወቃል። ይህን ዕቅድ ለማሳካት ተቋራጮችን ተወዳዳሪ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል።
አሁን ያለው የተቋራጮች የተወዳዳሪነት አቅም ቀጣዩን ኃላፊነት መሸከም የሚችል ስላለመሆኑ በቂ ግንዛቤ ተይዞበታል። የውጭ የግንባታ ተቋራጮች ወደ አገሪቱ እንዲመጡ ከተደረገበት ሁኔታም ይህንኑ መገንዘብ ይቻላል። አገሪቱ በፍጥነት የሚሠራ ግዙፍ ፕሮጀክት ይዛ ብትመጣ ይህን ሊሠራ የሚችል የአገር ውስጥ ተቋራጭ መገኘት መቻሉ አጠራጣሪ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው። ይህ ትልቅ ክፍተት መሆኑ ሊታወቅ የግድ ይሆናል።
ዘርፉን የሚመራው አካል አሁን የተቋራጮችን ተወዳዳሪነት አቅም ለመገንባት ቁርጠኛ ሆኗል። የአገሪቱ ተቋራጮች ግዙፍ የሚባሉትን የግንባታውን ዘርፍ ፕሮጀክቶች ለመገንባት ጭምር ዝግጁ መሆን አለባቸው። የበይ ተመልካች ሆነው መቆየት የለባቸውም። ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የተወዳዳሪነት አቅምን በማጎልበት ነው።
ትላልቆቹ ተቋራጮች የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሥርዓታቸውን በመቀየር የኮርፖሬት ባህል እንዲገነቡ መንግሥት እየጠየቀ ነው። ትናንሾቹን ተቋራጮች ደግሞ እየደገፈ ለማብቃት እንደሚሠራ አስታውቋል። የተወዳዳሪነት አቅም መጎልበት ከአገርም አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ ጭምር መቀጠል እንዳለበት ታምኖበት እየተሠራ ነው። ተቋራጮች ይህን የመንግሥት ቁርጠኝነት ለመጠቀም ዝግጁና ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2015