አስታዋሽ ያጣ የጥበብ ባለውለታ መሆን የኮይሻ ሴታ ዕጣ ፈንታ ይመስላል። በባሕል ሙዚቃ ውስጥ ያልታየውን እንዲታይ፣ ያልተደመጠውንም እንዲደመጥ ያደረገ፤ ብዙ አሳይቶ እርሱ ግን ምንም ሳይታይ አሳዛኝ በሆነ የሕይወት መስመር ውስጥ አልፎ እስከወዲያኛው ሄደ። እነዚህ ከኮይሻ ሴታ የሕይወት ማኅደር ውስጥ የተቀነጨቡ እውነታዎች ናቸው። ኮይሻ ሴታ ተወልዶ ያደገው በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በወላይታ ዞን በዳሞት ዳሌ ወረዳ አደ ዳሞት ቀበሌ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ በሙዚቃ ውስጥ የመኖርና ሙዚቀኛ የመሆን ትልቅ ሕልም ነበረው። ሕልሙ ሕልም ሆኖ ብቻም አልቀረም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአካባቢው በስተቀር እምብዛም የማይታወቀውን የወላይትኛ ሙዚቃን ተወዳጅና ተደማጭ ለማድረግ በቃ።
ኮይሻ አሃዱ ብሎ የሙዚቃ መሠረቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የጣለው በተወለደባት አካባቢ በነበረው የቀበሌ የኪነት ባንድ ውስጥ ነበር። በ1971 ዓ.ም ባንዱን በመቀላቀል በሌሎች ሙዚቀኞች ሥራ ቢጀምርም፣ የኋላ ኋላ ግን የራሱን ሥራዎች እያቀረበ መጫወትም ጀመረ። የነበረው ተቀባይነትም ከባንዱና ከአከባቢው እየወጣና እየሰፋ ሄደ። በየመድረኩ ሁሉም ሰው ‘ኮይሻ’ ማለትና የእርሱን የሙዚቃ ጨዋታ መናፈቅ ጀመረ። ከደቡብ ምንጭ የፈለቀው የኮይሻ የሙዚቃ ጥበብ፣ ከደቡብ ወደ ምሥራቅና ምዕራብ እንዲሁም መስመሩን ሰንጥቆ ወደ ሰሜን በረዥሙ ፈሰሰ። ከሙዚቃ መድረኮች አልፎ በየእግር ኳስ ሜዳው የደጋፊዎች ማዕበል ኃይል ሆነው የሚጨፈርባቸው የሞራል ስንቅም ጭምር ናቸው።
ኮይሻ ሙዚቃዎቹ ተወዳጅ እንዲሆኑ ያደረገው በድምፅ ብቻ ሳይሆን ከድምፅ ጋር አጣምሮ በሚያሳያቸው የዳንስ ስልቶችም ጭምር ነው። ሙዚቃዎቹ በብዛት ቀድመው የነበሩ የሕዝብ ሙዚቃዎች ቢሆኑም በሙዚቃዎቹ ውስጥ የወላይታ ማኅበረሰብ ባሕልና ትውፊቶችን አስሶ በማውጣት በሀገር ደረጃ እንዲታወቁ አደርጓል። ከምንም ነገር በላይ ኮይሻ ለዚህ ማኅበረሰብ ባሕል ትልቅ ባለውለታ ነው። ዛሬ ላይ እንደ አሸን የፈላው የወላይታ ብሔር ተወዳጅ ሙዚቃና ሙዚቀኞች የኮይሻ ሴታ አሻራዎች ያረፉበት ናቸው።
‘አሊ ጀናው’ በ1984 ዓ.ም የሠራው የኮይሻ ሴታ የበኩር አልበሙ ነበር። ይህ አልበም የመጀመሪያ የሆነው ለኮይሻ ብቻ ሳይሆን በአልበም ደረጃ የተሠራ የመጀመሪያው የወላይትኛ ሙዚቃም ጭምር ነበር። ሙዚቃው በአምባሰል ሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት የተሠራ ሲሆን በዚህ አልበም ኮይሻ ትልቅ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር። ማተሚያ ቤቱ ለኮይሻ 5 ሺህ ብር ሊከፍለው በመስማማት ከድምፃዊው ጋር ውል ይገባል። መጨረሻ ላይ በድምፃዊው እጅ የገባው ገንዘብ ግን 5 መቶ ብር ብቻ ነበር። ምንድነው ሲል በነገሩ ግራ የተጋባው ኮይሻ ይጠይቃል። የፈረምከው 5 መቶ ነው ተባለ። የት እንደገባች ያልታወቀቸው በ5 መቶና በ5 ሺህ መሐል ያለችው ይህቺ አንዲት ዜሮ ወደ ሌላ ችግር አመራች። በኋላ ላይ ግን ኮይሻ ቀጥ ብሎ ወደ ማተሚያ ቤቱ ባለቤት በመሄድ ጉዳዩን ያስረዳል። የማተሚያ ቤቱ ባለቤትም ነገሩን ካጤኑ በኋላ የተስማማውን 5 ሺህ ብርና በካሳ መልክ ደግሞ 1 ሺህ ብር ጨምረው እንደሰጡት ይናገራል።
አልበሙ ከወጣና አድማጭ ጆሮ ከደረሰ በኋላ የነበረው ተቀባይነትና ተደማጭነት ከተጠበቀው በላይ ሆነ። በየሙዚቃ ቤቱ የሚደመጠው የኮይሻ ሙዚቃ ነበር። ብዙ ነገሮች ለኮይሻ ቀና እየሆኑ የመጡ መሰሉ። ከወላይታ ተነስቶ አልበሙን ለመሥራት አዲስ አበባ የገባው ኮይሻ፣ አዲስ አበባን በጣም ወደዳት። የሙዚቃ ሥራውንም በተሻለ ለመሥራት በማሰብ እዚሁ አዲስ አበባ ከተመ። ነገር ግን ሁኔታዎች እንደጠበቀው አልሆንልህ አለው። የወደዳት አዲስ አበባ እርሱን ለመውደድ ተሳናት። በጉጉት ቢቀበላትም እርሷ ግን ጀርባዋን አዞረችበት። የትውልድ ቀዬውን ጥሎ፣ ልቡን በተስፋ ሞልቶ የነገ የሙዚቃ ትልሙን በአዲስ አበባ ቢመለከትም ሁሉም ነገር ግን የተገላቢጦሽ ሆነበት። ኑሮ በአዲስ አበባ ለእርሱ የዋዛ አልነበረችም። በሯ በምንም የማይከፈትና የማይገፋ ሆነ። ግራ መጋባቱ ከእለት ወደ እለት እየጨመረና ተስፋው እየተመናመነ መሄዱንም ቀጠለ። ሕይወቱ የጉዞ መስመሯን ስታ ወዲህና ወዲያ እንደምትናውዝ የባሕር ላይ መርከብ ሆነች። በወቅቱ እንዲህ እንዲሆን ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች ነበሩ።
1980ዎቹ መባቻ ስሙ ገኖ የወጣበት ወቅት ነበር። ነገሩ ግን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንዲሉ የኮይሻ ሕይወት እንደስሙ አልነበረም። ስሙ ገኖ ሙዚቃውም ከጫፍ ጫፍ ማድመቂያ ሆኖ ሳለ የእርሱ ሕይወት ግን የደበዘዘና በማይነጋ ሌሊት ውስጥ እንዳለች ጨለማ ነበር። ብዙዎች የእርሱን ሙዚቃ አሳደው ሲያደምጡ፣ እርሱን ግን ከወዴት አለህ ብሎ የሚፈልገው አንድም ሰው አልነበረም። የኮይሻ ሙዚቃ እንደሻማ እያበራ፣ ኮይሻ ግን እንደሻማ ሲቀልጥ ነበር። በሀገር ውስጥ ከነበሩ ከተለያዩ ባንዶች ጋር በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት እየተዘዋወረ ሥራዎቹን ቢያቀርብም ሕይወቱ ግን ከችግርና ስቃይ ለማምለጥ አልቻለችም። ብዙ ሰዎች የኮይሻን ግሩም ሙዚቃዎች ያውቃሉ ነገር ግን ሙዚቃው ምን አይነት ነው ከማለት በቀር ሙዚቃው የማነው ብለው አይጠይቁም።
ከዚህም የባሰው ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ድምፃውያን የእርሱን ሙዚቃ እየወሰዱ ከፊትና ኋላ ግጥምና ዜማ እየለጣጠፉበት የመታወቅ አባዜአቸውን አርክተውበታል። ‘በጨው ደንደስ በርበሬ ትወደስ’ ሆነና የሙዚቃው ባለቤት የሆነው ኮይሻ ተቀብሮ በእርሱ ሙዚቃ ሌሎች ተወደሱበት፤ ተከብረው ነገሡበት። “ሁል ጊዜ ሙዚቃዎቹን በሰማሁ ቁጥር እንባ ይተናነቀኛል” ይላል ኮይሻ፤ ያለ እርሱ ፈቃድ ሙዚቃዎቹን ሰርቀው መኖሩን እንኳን ስለረሱት እያሰበ። በእርግጥም ሠርተው ምንም እንዳልሠሩ ልፋት መና ሲቀር በእጅጉ ልብን ይሰብራል። ከኮይሻ ሙዚቃዎች ተወስደው በጣም ተደማጭነትን ካተረፉ ሙዚቃዎች መሐከል ለአብነት ያህል እስቲ ሁለቱን እንመልከት።
‘መቼ ትመጪያለሽ ሰኞ
ልጠብቅሽ ወይ ማክሰኞ
……. ……. ……
የዚህ ሙዚቃ ግጥሙ የተሠራው በአማርኛ ቢሆንም ዜማው ግን ሙሉ ለሙሉ የተወሰደው ‘ጋሼ ወላሎሜ ሀያ’ ከሚለው የኮይሻ ሙዚቃ ላይ ነው። ሌላው ሁለተኛው ሙዚቃ ደግሞ ‘ቡሌ ኢያቡሌ’ የተሰኘው ሙዚቃ ነው። በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭ ሙዚቃ ነበር። ለረዥም ጊዜያትም ተደማጭነት ነበረው። ይህን ሙዚቃ ከኮይሻ በመውሰድ ይዘቱን ጥቂት ለወጥ አድርጎ የሠራው በሕዝብ ዘንድ በጣም ተቀባይነትና ተወዳጅነት ያለው ድምፃዊ ቢሆንም ለዚህ ሙዚቃ መሠረት ከሆነው ከኮይሻ ፈቃድ ካለመጠየቁም ውጭ ምንም አይነት እውቅና አለመስጠቱ ፍጹም ስህተት ነው። እነዚህን ሁለት ሙዚቃዎች የማያውቅ አለ ብዬ አላስብም። የሙዚቃ አድማጭ ባንሆን እንኳን ሁኔታና አጋጣሚዎች እንድናውቃቸው ያደርጉናል። ብዙዎቻችን በሙዚቃዎቹ ስለመዝናናታችንም አልጠራጠርም፤ ቅሉ የሙዚቃዎቹን አባት ኮይሻን ባናስበውም።
የአሳዛኙ ድምፃዊ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት በእጅጉ ቅስምን የሚሰብሩ ነበሩ። ወደ ኋላ ወደ ትውልድ መንደሩ መመለስም ሆነ በሚገኝባት አዲስ አበባ ወደፊት አንድ እርምጃ መሄድ ተስኖት በተስፋ መቁረጥ የደመነብስ ኑሮ መምራቱን ቀጠለ። ከሚኖርባት የቀበሌ ቤት ውስጥ ከመግባትና መውጣት ውጭ ሕልሙን የሚኖርባትን የሙዚቃ በር ግን አሁንም ለማግኘት አልቻለም። የእነዚያ ጣፋጭና ተወዳጅ ሙዚቃዎች አባት የሆነው ኮይሻ ሴታ ስም በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ቢገኝም ከእርሱ ጋር ግን ማንም አልነበረም። ኑሮው ቁልቁል እየተምዘገዘገ ሄዶ ከችግር ዋሻ ውስጥ ተፈጠፈጠ። የሚበላውን እንኳን እስከማጣት ደረሰ። ካገኘ ቀምሶ ካጣም ጾሙን ውሎ ማደር ጀመረ። በዚያች ቤት ውስጥ ሲኖር አጠገቡ ከነበሩት ጎረቤቱ በስተቀር ጎራ ብሎ የሚጠይቀውም ሆነ ከወዴት አለህ ብሎ የሚፈልገው ሰው አልነበረም።
ብዙ ጊዜ እየታመመ ለብቻው በተዘጋ ቤት ውስጥ እያቃሰተ ማንም ሳያውቅለት ለቀናት የማቀቀባቸው ጊዜያት ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም። አቅሉን ከሳተበት አልጋ ላይ አንስተው የሰፈሩን ሰው በማስተባበር ሕክምና እንዲያገኝ ያደርጉ እንደነበርም ጎረቤቱ የነበሩት ሰው ከአንድ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ገልጸው ነበር። ያለበት ሁኔታ ሁል ጊዜ ፍርሃትን ስለሚያጭርባቸው ጠዋትና ማታ ከቤቱ ጎራ እያሉ ይጎበኙታል። ከእለታት በአንደኛው ምሽት እንደልማዳቸው ወደ ኮይሻ ቤት ብቅ በማለት ቢመለከቱ በሩ ተዘግቷል። ኮይሻ ከቤቱ አልገባም። መጥፎ ስሜት ከውስጣቸው እያንዣበበ ሁኔታው አላምር ያላቸው እኚሁ ጎረቤቱ ይመጣል እያሉ ምሽቱን ሙሉ ቢጠብቁም ሳይመጣ ቀረ። ከቤቱ ውጭ አድሮም ሆነ ሳይነግራቸው የትም ሄዶ የማያውቅ በመሆኑ አንዳች ነገር ሳይሆን እንዳልቀረ በመጠርጠር በነጋታው ለፖሊስ ጣቢያ አመለከቱ። የፈሩት አልቀረም ነበር ኮይሻ እራሱን ስቶ ከመንገድ ላይ ወድቆ እንደነበር፣ እንዲሁም ወደ ሆስፒታል ስለመወሰዱ ሰሙ።
በሆስፒታል ውስጥ ከአፉ ላይ ኦክስጂን ተጠምዶ፣ ከችግር ጋር ሲታገል የከረመው ነፍስና ሥጋው አሁን ደግሞ ከሞት ጋር ፍትጊያ ተያያዘ። በዚህ ወቅት የብሔራዊ ቲያትር አባል የነበሩት ድምጻዊ አረጋኸኝ ወራሽና ፀጋዬ እሸቱ ወደ ሆስፒታሉ በመምጣት ኮይሻ ዳግም ቆሞ እንዲሄድ ጥረት ቢያደርጉም የኮይሻ ሁኔታ ግን እርሱን ለመርዳትና አለሁልህ ብሎ ከጎኑ ለመቆም ዳግም ዕድል የሚሰጥ አልነበረም። ኮይሻ ሌላ አልበም ለመሥራት እየተፍጨረጨረ በነበረበት በዚህ ጊዜ እቅዱ ሁሉ መና ቀረና በዚያው ወደ ማይመለስበት የሞት ዓለም ነጎደ። የአሳዛኙ ድምፃዊ ፍጻሜ በሚያሳዝን መልኩ ተጠናቀቀ። በ2010 ዓ.ም ኮይሻ በ50 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ኮይሻ በሕይወት ሳለ በሠራቸው የሙዚቃ ሥራዎች ያበረከተው በጣም ብዙ ቢሆንም፣ ነገር ግን ለምን ምንም ዓይነት ሽልማት ሊበረከትለት እንዳልቻለ የብዙ ሰዎች ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። ሌላው ቀርቶ የወላይትኛ ሙዚቃ በመላው ሀገሪቱ ተወዳጅ እንዲሆን ባደረገበት የትውልድ መንደሩ እንኳን ከሚገባው ጥቂቱን አለማግኘቱ ኮይሻ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ውለታው ተቀብሮ የቀረ አሳዛኝ ድምፃዊ ያደርገዋል። በመላው ኢትዮጵያ እየዞረ ሥራዎቹን ያላቀረበበትም ሆነ ያልረገጠው መሬት አልነበረም። ጣፋጭ የሆኑ ሙዚቃዎችን አበርክቶ መራራ ሕይወትን የኖረ አሳዛኝ የጥበብ ሰው ኮይሻ ሴታ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም