በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሰፋ ያለ ስፍራ ይዘው ከተቀመጡ ክስተቶች መካከል ከጣሊያን ጋር የተደረጉ ሁለት ጦርነቶች ዋነኞቹ ናቸው። ኢትዮጵያ በነጮች ዐይን ውስጥ ብትወድቅም ከክንዳቸው በታች ልትሆን አልወደደችምና፤ በሁለቱም ጦርነቶች ባለድል ሆናለች። ቀዳሚው የአፍሪካውያን ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል ሲሆን፤ ሁለተኛው ይኽኛው ዛሬ መታሰቢያቸውን የምናደርግላቸው አርበኞች አሸናፊ የሆኑበት የድል በዓል ነው።
ይህ የአምስት ዓመታቱ የጦርነት ታሪክ፤ ኢትዮጵያ እንደ አገር ብዙ ያየችና የተፈተነችበት፤ «መቼም ከዛ የባሰ አይመጣም!» ብለው እንደሚያነጻጽሩበት ቀን የመሰለ ዘመን ነው። ጣሊያን ከዓድዋ ጦርነት በበረታ የተዘጋጀችበት፣ ኢትዮጵያ የለውጥ ሽግግር ላይ በመሆኗ ዝግጁ ያልነበረችበት፣ መሪዋ የዓለም አገራትን «ጣሊያንን ተይ በሏት!» ይሉ ዘንድ ስደት የወጡበትና ሕዝብን አንድ አድርጎ የሚመራ ያልነበረበት፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ፣ እያዩ እንዳላዩ የዓለም መንግሥታት ሁሉ ጀርባቸውን ያሳይዋት ጊዜ ነበር።
ከዚህ የባሰ ይኖራል? ይሁንና ግን ከአምስት ዓመታት ጦርነት በኋላ፤ አንድም ቀን ተረጋግታ መግዛት ያልቻለችው ጣሊያን እስከ መጨረሻው ወጥታለች። ይህንኑ እንዲሁም ስለአርበኝነትና በጥቅሉ ስለዚህ የአምስት ዓመት ጦርነት ታድያ የተለያዩ መጻሕፍት በተለያየ እይታ ብዙ ታሪኮችና መረጃዎችን አጋርተውናል። ዛሬ በዚህ የኪነጥበብ አምድ እነዚህን እየጠቀስን አርበኝነትን፣ ዘመኑን እና የአምስት ዓመቱን ጦርነት እጅግ በጥቂቱ እናወሳለን።
የአምስት ዓመቱ መጀመሪያ
ጳውሎስ ኞኞ «የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት» በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ስለኢትዮጵያና ጣሊያን ጠብ መነሻና ቀጥታ ወደ ጦርነቱ ስላስገባው የወልወል ግጭትም አትቷል። በዚህም ላይ ራሱ ወልወል የት ነው? ምንድንስ ነው? እንዴት ለግጭቱ መነሻ ሆነ? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። በእርግጥ ይህ የወልወል ግጭት አውሮፓውያኑ Immediate cause እንደሚሉት ወይም መደበኛ ባልሆነ አተረጓጎም የተመቸ ሰበብ ሆናቸው እንጂ በውስጠ ታዋቂነት ሌላ ዓላማ ነበራቸው።
በዚሁ የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው፤ ወልወል በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሃገር በኦጋዴን ውስጥ የሚገኝ የኢትዮጵያ መሬት ሲሆን እያንዳንዳቸው 50 ሜትር ርዝመት ያላቸው 359 የውሃ ጉድጓዶች ያሉበት ስፍራ ነው። እነዚህን ጉድጓዶች ያስቆፈሩት ደግሞ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንደሆነ በታሪክ ይነገራል።
ታዲያ የጸቡ መነሻም የፋሽስት ጦር ወሰን አልፎ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ወልወል መገኘቱ ነው። እንደውም ከዛ አልፎ ከሮም አንድ ትእዛዝ ተላለፈ ተባለ። ትእዛዙ እንዲህ ይላል፤ «ማንኛውም የኢጣልያ ወታደር የረገጠው መሬት ሁሉ የኢጣልያ ቅኝ ግዛት መሆን አለበት። የምኒልክ ጊዜ በ1898 ዓ.ም. እና ግንቦት 16 ቀን 1908 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የወሰን ስምምነት መፍረሱን የኢጣሊያ ሹማምንት ሁሉ እንዲያውቁት»
በዚህ መሰረት ወልወል ላይ የሰፈረው የጣሊያን ጦር እና የኢትዮጵያ ሠራዊት ተፋጥጠው ቆዩ። ጳውሎስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል አስፍሮታል፤ «ህዳር 26 ቀን ረቡዕ ልክ ከቀኑ 9 ሰዓት ተኩል ሲሆን በድንገት ባንዳዎቹ በኢትዮጵያ ወታደር ላይ አደጋ ጣሉ። ወዲያው በሰማይ አውሮፕላኖች፤ በምድር ታንኮች ደርሰው በጣሊያኖቹ መድፍና ቦምብ መሬቷ ተርገበገበች። ኢትዮጵያውያኑም ያሉበትን ስፍራ ሳይለቁ ባላቸው አሮጌ መሳሪያ እስከ ሌሊቱ 5 ሰዓት ድረስ በጀግንነት ተዋጉ። በዚያም ጦርነት 94 ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ሲወድቁ 45 ቆሰሉ።» መጽሐፉ ቀጥሎ የሆነውን ሲያብራራም፤ ይህ ከሆነ በኋላ በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ብላቴን ጌታ ሕሩይ የጣሊያንን ድርጊት ተቃውመው አዲስ አበባ ከተማ ላለው የኢጣሊያ መንግስት ጉዳይ ፈፃሚ ደብዳቤ ላኩ። ነገር ግን በዚህም የተሻለ ነገር አልነበረም፤ ጭራሽ «… ጥፋቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ወታደሮቻችሁ 30 ኢጣሊያውያን ወታደሮች ገድለውብናል። የኢጣሊያ መንግስትም ከኢትዮጵያ መንግስት ካሳ ይጠይቃል። ካሳውን ብቻ ሳይሆንም ይቅርታ እንድትጠይቁን እንፈልጋለን።» ብለው አረፉት። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ይህን ሃሳብ የተቀበለ ባለመሆኑ ጦርነቱ እንደማይቀር እርግጥ ሆነ።
ከላይ እንዳልነው ታድያ በዚህ ላይ የጦርነቱ መነሻ ይህ የወልወል ግጭት ይሁን እንጂ፤ ለጣሊያን መነሻ ምክንያት የሆናት ዝርዝር ነጥብ መኖሩን የጥላሁን ጣሰው «የኢትዮጵያና የጣሊያን ሁለተኛው ጦርነት» መጽሐፍ ይነግረናል። ከዚህም አንደኛው የአርባ ዓመታት የጣሊያን ቂም ነው። ይህንንም በርካታ ኢትዮጵያውያን ጸሐፍት የሚያምኑበትና የጻፉት ነው። አልፎም በጦርነቱ መጀመሪያ ሰሞን ጣሊያናውያን ኢትዮጵያ እንደተወረረችና እንደተያዘች ብሎም እንደተሸነፈች አምነው በእጅጉ ደስታን ማድረጋቸው አስቀድሞም ቂም ይዘው እንደነበር ያሳብቅባቸዋል።
በሌላ ወገን ለጦርነቱ የጣሊያን መነሻ በዘመኑ የነበረውን የዓለም ስርዓት የማፍረስ ሀሳብ ነው ሲሉ በአውሮፓ የሚታተሙ ጋዜጦች መጥቀሳቸው ይነሳል። በዘመኑ የነበረው የዓለም ስርዓት መገለጫ የነበረው ደግሞ የዓለም መንግሥታት ማኅበር ነውና ያንን የማፍረስ ዓላማ ነበረው ይላሉ። ይህም ኅብረት ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ የተመሠረተው የዓለም መንግሥታት ማኅበር በእንግሊዝና ፈረንሳይ የበላይነት የሚመራ ነበር።
አርበኛና አርበኝነት
አርበኛ ወይም አርበኝነት የሚለው ቃል የተገኘው «ሀርብ» ከሚለው የግእዝ ቃል መሆኑን ግዛው ዘውዴ በ«ዝክረ አርበኝነት እና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ማኅበር አጭር ታሪክ» በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል። «ሀርብ» ማለት ትርጉሙ ሲሆን አርበኛ ማለት ጦረኛ ወይም ተዋጊ ማለት ነው።
በዚሁ መጽሐፍ የግርጌ ማስታወሻ ላይ፤ አርበኝነት የሚለው ቃል በፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትርጉሙ አገልግሎት ላይ መዋል የጀመረው በ1888ዓ.ም የዓድዋ ድል ጀምሮ መሆኑን ይጠቅሳል። ከዛም ቀደም ሲል ቢሆንም በየዘመናቱ የአርበኝነት ሥራ መሠራቱ በመጽሐፉ ተገልጿል። ታድያ ከትላንት ለዛሬ እያደረ እየበረታ ሄዶ ኢትዮጵያ የውጭ ወራሪዎች በተፈታተኗት ወቅት በተለይም በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ እና በአጼ ዮሐንስ አራተኛ ጊዜ የበለጠውን እመርታ አሳይቷል ይላሉ። በስፋት ለቃሉ መገለጫነት ያገለገለው ደግሞ የአምስቱ ዓመት የጣሊያን ወረራ እና የኢትዮጵያውያን ትግል ነው።
መጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል፤ «ከዓድዋ ድል ወዲህ በነበሩት የተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች አርበኝነት ለአገር የነጻነት ቤዛነት፣ በዓለም ዙሪያ ደግሞ የአይበገሬነት ተምሳሌት የበቃ መሆኑ ታይቷል። በተለይ ከ1928-1933 ዓ.ም ድረስ በዘለቀው በአምስቱ ዓመታት የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ የተስተዋለው ወኔና ተጋድሎ ግን ከዚህ ታሪካችን የወረደ የጋራ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሀብታችን በገሃድ በሥራ ላይ የዋለበትን ገድል ያመላከተ ነበር።»
ይህ የአምስት ዓመት ጦርነት የአርበኝነት ብቸኛው መጠሪያ እስኪመስል ድረስ የሆነው በአንድ ምክንያት ነው። ይህም በጊዜው ተደራርበውና ተከታትለው የመጡት ችግሮችና ፈተናዎች፤ ስለአገራቸው የሚታገሉ ኢትዮጵያውያንን እጅ እንዲሰጡ በብዙ የሚገዳደራቸው ስለነበር ነው። እንዲህ ነው፤ በመጀመሪያ ደረጃ ጣሊያን ከዓድዋ በሽንፈት ከተሰናበተች አርባ ዓመታት በኋላ ጦር ይዛ «የወልወል» ስምምነትን ምክንያት አድርጋ ነገር ግን በበቀል ስትመልስ፤ ኢትዮጵያ የዛን ያህል ተለውጣና አድጋ አልጠበቀቻትም።
ይህም በመጽሐፉ እንደሚከተለው ተጠቅሰዋል፤ «ኢትዮጵያ…ከዓድዋ ድል በኋላ በቀጣይ 40ዓመታት ከመጠነኛ መሻሻል በቀር መንጠቅ ነጠቅ ያለ ለውጥ ሳታስመዘግብ የአምስት ዓመታቱ ጦርነት ዕዳ ከደጃፏ ደርሶባታል።» ከዚህም አልፎ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሞት በኋላ የነበረው የስልጣን ፍትጊያ፤ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት እያዳከመው የሄደ ነበር። መጽሐፉ እንደሚያትተው፤ አጼ ኃይለሥላሴ በ1923ዓ.ም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ስልጣናቸውን ለማደላደልና ባሰቡት መንገድ ዘመናዊነትና ማዕከላዊ አስተዳደርን ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት፤ የራሳቸው ጦር የነበራቸውንና አገር ሲገዙ የቆዩ መሳፍንትና መኳንንትን ስልጣን ገድበው ነበር።
በዚህም ምክንያት ይላል መጽሐፉ፤ «በዘመቻ ወቅት እንደ ዘማች፤ በሰላም ጊዜ ደግሞ ግብረ በላ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ጦርና ሎሌ ጭፍራነቱን እየተወ፣ ከየጌታው እየተለየ ማደሪያ ፍለጋ መበተን ጀመረ። ዘመናዊ ውትድርናም በቅጡ ተደራጅቶ ተሰናድቶ ሳይደርስ ሁሉ ነገር ገና በሽግግር ላይ እንዳለ የከፋው የፋሽት ኢጣሊያ ጦር አንዣበበ።»
በዚህ ሁሉ ምክንያት የ1928ቱ ጦርነት ላይ አምስት ዓመት መጠበቅ ሳያስፈልግ በአንድ ጊዜ ወራሪን ማስወገድ ሳይቻል ቀረ። መጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው ጦሩን ከየግዛቱ ማሰባሰብ ቢቻልም እንኳ በሚገባ የተዘጋጀውን የጣሊያንን ጦር ማሸነፍ ቀርቶ መመከት እንኳን አልተቻለም። «የንጉሡ ከአገር መውጣት ደግሞ መሪ ለለመደ ሕዝብ እንደገና እስኪደራጅ ድረስ ጉዳቱ ከፍቶበታል።» ሲል መጽሐፉ ያክላል።
ይህ ነገር መሆኑ እንግዲህ በዚህ የአምስት ዓመት ጦርነት ወቅት የነበረውን አርበኝነት ያገዝፈዋል። ዓድዋ ሕዝብ በአንድ መንፈስ፣ በአንድ ልብ፣ ስለአንድ አገሩ በአንድ መሪው ቀስቃሽነት አንድ ሆኖ የወጣበት ነው። ያም ብቻ አይደለም፤ የፋሽስት ሠራዊትም ቢሆን ያኔ ኢትዮጵያን ለመውረር ሲሞክር ፈጽሞ እረታለሁ ብሎ አያስብምና ሠራዊቱን ያደራጀበት መንገድ እንደ ሁለተኛውና የአምስት ዓመቱ ጦርነት እንደማይሆን ግልጽ ነው።
በጥላሁን ጣሰው የተዘጋጀው ሌላው ስለዚህ የድል በዓልና የአምስት ዓመት ጦርነት የሚያትተው «የኢትዮጵያና የጣሊያን ሁለተኛ ጦርነት ታሪክ» የተሰኘውን መጽሐፍ ደግሞ እንመልከት። በዚህ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው አርበኝነት በተለያየ ጊዜ የተለያየ ትርጓሜ ተሰጥቶት እንደነበር ነው። ከዚህም አንዱ አርበኝነት ያለመንግሥት መሪነት ሕዝብ በየመንደሩ እየተሰባሰበ ያካሄደው አመጽ ተደርጎ መተርጎሙ ነው። ይህም የተሳሳተ እይታ ይሁን እንጂ በተለይ ጣሊያኖች እንደ ፕሮፖጋንዳ ይጠቀሙበት ነበር።
የአምስት ዓመቱ ጦርነት መጀመር አስቀድሞ፤ ሐምሌ 11 ቀን 1927ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ ለዓለም መንግሥታት በጻፉት ደብዳቤ ስለአርበኝነት ካሰፈሩት በጥቂቱ ተጠቅሶ ይገኛል፤ «…እስከ መጨረሻው ድረስ ሰላም እንዲሆን እንጣጣራለን። ነገር ግን ድካማችንና መልካም አሳባችን ፍሬ ያላገኘ እንደሆነ ሕሊናችን አይወቅሰንም። የኢትዮጵያ ሕዝብም በእምነት ተባብሮ ለአገራችን ነጻነት በእውነተኛ ነገር ለመከላከል እግዚአብሔር የአርበኞቻችንን ኃይል እንዲያጸና እጁን ወደ እግዚአብሔር ይዘረጋል።»
አምስቱ ዓመታት
አምስቱ ዓመታት የጦርነትና የመከራ ጊዜ ከማለት ይልቅ የአርበኝነት ወቅት ማለቱ ሳይቀል አይቀርም። በበኩሌ ይህን የምለው ከምናነባቸው ታሪኮችና ከዛም ከምናገኘው የዛን ጊዜ ፈተና አንጻር፤ ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ላይ ካደረጉትና ከፈጸሙት ግፍ በላይ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ለአገራቸው አድርገዋል በማለት ነው። ታዲያ በአምስቱ ዓመታት ውስጥ የሚያባራ የማይመስል መከራን ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው ላይ ስለነጻነታቸው በመሟገታቸውና ባርነትን በመጥላታቸው ብቻ ተቀብለዋል።
በእነዚህ ጊዜያት ከተደረጉ ዋና ዋና ጦርነቶችና አይረሴ ክስተቶች መካከል አንደኛው የማይጨው ጦርነት መሆኑ በጥላሁን «የኢትዮጵያና የጣሊያን ሁለተኛው ጦርነት» መጽሐፍ ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። ይህም መጀመሪያ አካባቢ የተደረገውና ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው የተሳተፉበት ነው። ይህም ግን ሳይሳካ ነው ወታደሩ የተበተነው።
የአሸንጌ ሐይቅ እልቂትም በተመሳሳይ በዚህ ይነሳል። ይህንንም ራስ ካሳ እንደሚከተለው ገልጸውታል ሲል ጥላሁን በመጽሐፉ አስፍሮታል፥ «በሰሜን በኩል አርባ የሚሆኑ አይሮፕላኖች ከመስመሩ መጨረሻ ጀምረው በአንድ ጊዜ ሰልፈኛው ላይ ኤፕሪት ጋዝና የቦንብ መብረቅ ያወርዱበት ጀመር።… እንደገና ጋዙን ሊሞሉ ሲሄዱ ሌሎች ደግሞ ወዲያውኑ እነርሱን የሚተኩ ጋዝ የሞሉ አውሮፕላኖች በቦታቸው ይመጣሉ።…በጥቂት ሰዓታተ ቆይታ የአንድ ትልቅ ሰልፍ ሙሉ ወታደር ድምጥማጡ ጠፍቶ አፈር ለበሰ።
…በማግስቱ ጎህ ሲቀድ የአሸንጌን ሐይቅ ባየነው ጊዜ የሚያሰቅቅ ትዕይንት ተደቅኖ አገኘን። የሐይቁ ዙሪያ በሬሳዎች መቀነት ተከቧል። የሴት የወንድና የእንስሳት ሬሳ አብሮ ተደባልቋል።…ከሬሣው ብዛት የተነሳ ሐይቁ ትልቅ የመቃብር ቦታ ይመስላል…»
ሌላው ደግሞ የካቲት 12 ቀን 1929ዓ.ም ነው። ይህም በየዓመቱ የካቲት 12 ላይ የምናስባቸው የሰማዕታት ቀን ነው። በዚህም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገ ሙከራ መነሻነት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ሁሉ ሲገደሉና መከራ ሲቀበሉ ነበር። እንዲሁም አቡነ ጴጥሮስን እዚህ ላይ መርሳት አንችልም። እኚህም ቅዱስ አባት ለአገራቸውና ለወገናቸው እስከ ፍጻሜው ድረስ ቆይተው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ተደምረው ነው ዛሬ ላይ መለስ ብለን የምናስበው የድል በዓል መሰረት ሆነው ያነጹትና ያቆሙት።
ድልና የድል በዓል
«በምድር ላይ የሚያስደንቅ ነገር አለ ቢባል የኃይለኞች ጉልበት ለደካሞች እየታደለ፤ ተሸናፊ አሸናፊው፤ ተጠቂ አጥቂ ሲሆን ከማየት የበለጠ ዕፁብ ድንቅ ትርዒት የለም።» ይላሉ፤ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ የአርበኞችን ታሪክ ባኖሩበት «ቀሪን ገረመው» መጽሐፋቸው ላይ። በጊዜው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ለአምስት ዓመታት ያህል በጽናት ተዋግተው ነጻነታቸውን ለትውልድ አቆይተዋል፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቅቃ ለመውጣቷ በእርግጥ ተጨማሪ ግፊቶችና ኃይሎች መኖራቸው ይታወቃል።
በዛው በ«ቀሪን ገረመው» መጽሐፍ ካለው ጨምረን እናንሳ፤ «ድል አድራጊነት በቀልድና በዋዛ የሚገኝ ነገር አይደለም። ከብዙ ችግርና ፈተና በኋላ የሚገኝ የአርበኞች ዕድል ነው። ለአንድ አርበኛም በአጭሩ ሦስት ነገሮች ያስፈልጉታል። እነዚህም ሦስት ነገሮች ጀግንነት፣ የጦር መላና የጦር መሣሪያ ናቸው። ከሦስቱም የበለጠ የሚያስፈልጉት ጀግንነትና ስልት በመሆናቸው አንድ አርበኛ እነዚህን ነገሮች ከሚጎድሉበት የጦር መሣሪያ ቢያንሰው ይቀላል።» ይላል።
አርበኝነት ሲባል ታዲያ በውጪ ተዋጊነት ብቻ ሳይሆን በውስጥም ጭምር ነው። በዚህም ለጠላት ወራሪ ታማኝና ወዳጅ መስሎ መረጃ በማቅረብና ውስጥ ለውስጥ በማጥቃት የሚገለጥ ነበር። ይህም ቀላል የሚባል ነገር አልነበረም። ይሁንና እናትና አባት አርበኞች ስለአገራቸውና ስለልጆቻቸው ነጻነት ሲሉ ከዚህ ጽዋ ሊጠጡና ሰማዕትነትን ሊቀበሉ ቆርጠው ነበር።
«ቀሪን ገረመው» መጽሐፍ ላይ እንደ ሚገኘውም፤ የፋሽስት መንግሥት አምስት ዓመት ሙሉ ዘመናዊ መሣሪያ ከሌለው ሕዝብ ጋር እየተዋጋ ድል ይሆን የነበረው የውስጥ አርበኞች ከውጭ አርበኞች ጋር በሚያደርጉት ምስጢራዊ ግንኙነት ነው።
እናም ስለዚህ ሁሉ ምክንያት የድል ነገር ሲታሰብ አርበኛና አርበኝነት፤ አርበኛ ሲነሳ ደግሞ ድል የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ሆነዋል። ከላይ የጠቃቀስናቸው መጻሕፍትና ያላነሳናቸው ሌሎችም መጻሕፍት የዚህን የአምስት ዓመቱን የፋሽስት ወረራና የኢትዮጵያውያን አርበኞችን ትግል ይገልጣሉ። እነዚህን መጻሕፍት ለታሪክና ለታሪክ ማጣቀሻነት ይዘን በኪነጥበቡ ዘርፍ ይህን ታሪክ ምን ያህል ተጠቅመናል ብንል መልሱ «አንዳች እንኳ!» የሚል ይሆናል።
ከዓመታት በፊት በጳውሎስ ረጋሳ የተዘጋጀውና ለእይታ ቀርቦ ተወዳጅነትን ያገኘው «አሸንጌ» ፊልምን የተመለከተው የሚረሳው አይደለም። ከዛ በተረፈ ግን ታሪክን በዛ መልክ እያነሱና ታሪካዊ ስፍራዎችን መቼት ያደረጉ፤ እውነተኛ አርበኞችን በገጸ ባህሪነት ያካተቱ የጥበብ ሥራዎችን አንመለከትም። በተፈጥሮ ከታደልነው ጸጋ በተጨማሪ እነዚህ አገራችንን ያቆዩልን አርበኞች ታሪክና እውነታቸው ከመጽሐፍ አልፎ በሚገኙ የጥበብ ክዋኔዎች ሁሉ ታትመው ለተመልካችና ለሰሚ ቢተላለፉ መልካም ይሆናል።
ሁሉም ዘመን የራሱ አርበኝነትን የሚጠይቅ ተጋድሎና አርበኛ አላቸው። ይህ የእኛ ዘመን በአንድ ወገን የኋላን በሚገባ በማወቅ በተጓዳኝ ደግሞ የወደፊትን ለትውልድ እንዲሆን አድርጎ በማቆየት መካከል የሚደረግ ትግል ነው። ይህ ትግል ለሁሉም ኢትዮጵያውያን በድል የሚጠናቀቅ እንዲሆን እንመኛለን። ለአርበኞች እናቶችና አባቶቻችንም ሕይወታቸውን ከፍለው ባቆዩልን አገር መሬት ላይ በኩራት ሆነን፤ ስለክብራቸው ዝቅ ብለን እናመሰግናቸው ዘንድ ይገባል፤ እናመሰግናለንም። ሰላም!
ሊድያ ተስፋዬ