የአምራች ኢንዱስትሪው በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ውስንነት መቅረፍ የሚችል አቅም ማዳበር ይኖርበታል

አዲስ አበባ፡- የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪው በትራንስፖርት ዘርፍ ያለው ውስንነቶች በቀላሉ መቅረፍ የሚችል አቅም ማዳበር እንደሚኖርበት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያበቁ ተሽከርካሪዎች መልሶ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እና የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፉን ለማሳደግ ያለመ የባለድርሻ አካላት የጋራ መድረክ ትናንት ተካሂዷል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) በዕለቱ እንደገለጹት፤ የትራንስፖርት ዘርፍ ለማሳደግ እንዲሁም አገልግሎቱን ለማሻሻል የአምራች ኢንዱስትሪው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ይህን ሚናውን ለመወጣትም አቅሙን ማጎልበት ይጠበቅበታል፡፡

በኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎች፣የተሽከርካሪ ቦዲዎችንና መለዋወጫዎች በሀገር ውስጥ በብዛት የማይመረቱ በመሆኑ በትራንስፖርቱ ዘርፍ በርካታ ክፍተቶች እንዲኖር አድርጎታል ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ የተሽከርካሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተኬደ ያለበት ርቀት ችግሩን በቀላሉ መፍታት የሚችል ነው ብለዋል፡፡

ከውጭ የሚገባ ምርት በሀገር ውስጥ መተካት ለኢኮኖሚያዊ እድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤በርካታ ሀገራት በሚፈለገው ፍጥነት ማደግ ያልቻሉት የሀገር ውስጥ አቅም ማዳበር ስላልቻሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያም ይህ እጣ ፈንታ እንዳይገጥማት ከወዲሁ የሀገር ውስጥ አቅም ማሳደግ እንዳለባት አመልክተው፤የመንግሥት ተቋማት በሀገር ውስጥ የሚመረት ምርት እያለ ከውጭ እንዳይገዙ ተብሎ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በዘርፉ እውቀቱና አቅሙ ያላቸው ተቋማትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ነው ሚኒስትሩ የጠቆሙት፡፡

እንደ አለሙ (ዶ/ር) ገልጻ፤ የሀገር ውስጥ ምርት ማሳደግ የመለዋወጫ ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም ብልሽት ሲገጥም የባለሙያ እጥረት እንዳያጋጥም የሚያደርግ ነው፡፡

በቅርቡ የተጀመረው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም በርካታ ሀብት ከማፍራት በተጨማሪ በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት አስችሏል፡፡በቀጣይም በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች ድጋፍና ክትትል ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ዘሩ በበኩላቸው፤ ፌዴሬሽኑ በትራንስፖርት ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንዲገኝና ኢትዮጵያ ታምርትን በማጠናከር የሀብት ብክነት እንዳይከሰት አገልግሎት ጨርሰው የቆሙ ተሽከርካሪዎችን እያደሰ ዳግም ወደ አገልግሎት እያስገባ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ከ500 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ዳግም ወደ ስራ ለመመለስ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ብርሃኔ፤ይህም የውጭ ምንዛሬ ለማዳንና ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

ዳግም ወደ አገልግሎት የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ከአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም ከጥራት አኳያ ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው ለሚለው ከአምራቾቹ እንዲሁም ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተውጣጡ አካላት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተለያዩ የመኪናና የመኪና ቦዲ አምራቾች፣ የነዳጅ መኪናዎችን ወደ ኤሌክትሪክ የሚቀይሩ ድርጅቶች፣ የታክሲ ማህበራት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You