የልጅየው ታሪክ በለጠና የአባትየው ታሪክ የተዋጠ ይመስላል። እኝህ ሰው የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አባት የሸዋው ንጉሥ ኃይለመለኮት ሣሕለ ሥላሴ ናቸው። ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጋር ጦርነት ሊገጥሙ በአንኮበር ቶራ መስክ ላይ ዝግጅት እያደረጉ ከ169 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 30 ቀን 1848 ዓ.ም ያረፉት ንጉሥ ኃይለመለኮት ሣሕለሥላሴን እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው የዚህ ሳምንት ክስተት የሆኑ ሌሎች ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ታሪኮችን እናስታውስ።
ከ24 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 26 ቀን 1993 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ፣ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በክብር ተፈጸመ። ነሐሴ 20 ቀን 1967 ዓ.ም ሕይወታቸው ያለፈው ንጉሠ ነገሥቱ የሞቱበት ምክንያት አሁንም ድረስ አከራካሪነቱ ቀጥሏል። በደርግ በኩል ታመው እንደሞቱ ሲነገር፤ ደርግን አናምነውም የሚሉ ወገኖች ደግሞ ራሱ እንደገደላቸው ይገምታሉ። ደርግን አስወግዶ ሥልጣን የያዘው ኢሕአዴግ ጥቅምት 26 ቀን 1993 ዓ.ም የክብር ሥርዓተ ቀብራቸውን አስፈጽሟል።
ከ12 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 26 ቀን 2005 ዓ.ም ስመ ጥሩውና አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ አረፈ።
‹‹… ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ ገብሬ! ገብሬ የመታውን የዚምባብዌው 2 ቁጥር በራሱ ግብ ላይ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … ››
‹‹ … አሁን ዳኛቸው ነው የሚመታው … አሁን ዳኙ ሊመታ ነው … አሁን ይገላግለናል … ወይኔ! ወይኔ ዳኙ! ዳኙ አገባ! ዳኝሻ አገባ! በጣም አስደናቂ ግብ ነው ዳኝሻ! ቀኙን አሳይቶ ግራውን፤ ግራውን አሳይቶ በቀኙ … አሁን ተጨዋቾቻችን ደስታቸውን እየገለጹ ነው! … ሕዝቡ ወደ ሜዳ እየገባ ነው … ተመልካቹም ‹እንደተመኘኋት አገኘኋት› እያለ ነው … ችቦ በራ! ስታዲየሙ ተንቀለቀለ…›› ደምሴ ዳምጤ በዚህ የደስታ ሲቃ ድምፁ በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል።
ከ135 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ.ም ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ አስተዳደር መቃናትና ስኬት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ባለቤታቸው ጣይቱ ብጡል ‹‹እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ›› ተብለው፣ ምኒልክ በነገሡ በሦስተኛው ቀን፣ የእቴጌነት ዘውድ ደፉ። እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‹‹እቴጌ ጣይቱ›› በመባል ይታወቃሉ።
ከ88 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 27 ቀን 1929 ዓ.ም ስመ ጥሩው አርበኛ፣ የጦር መሪና ግዛት አስተዳዳሪ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ) አረፉ።
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ
የሚለው ስንኝ ዓድዋ በመጣ ቁጥር የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ማድመቂያ ነው፤ የጋዜጣና መጽሔቶች ጽሑፍ መግቢያ ነው። ይህኛው ነጥሮ የወጣ የባልቻ አባ ነፍሶ ውዳሴ ይሁን እንጂ ሌሎች ስንኞችም አሉ።
እንደ ደጋ ገብስ እንዲያ ኮስሶ
ያስቆረጥማል ጠላቱን ኮሶ
የዳኘው ጀግና ባልቻ አባ ነፍሶ
ማን እንዳንተ አርጎታል የእርሳሱን ጉትቻ
የዳኘው አሽከር አባ ነፍሶ ባልቻ!
ስለባልቻ አባ ነፍሶ ብዙ ተዘምሯል። ይቺኛዋን ግን እናስታውስ፤ የዓድዋው ጦርነት ስመ ጥሩ ጀግናው ባልቻ አባ ነፍሶ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያ በድጋሚ ስትወረር ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጋር ፀብ ስለነበራቸው ባልቻ ከጣሊያን ጎን ይሰለፋሉ ብለው ጣሊያኖች አስበው ነበር። ደጃዝማች ባልቻ በንጉሡ ላይ ቅሬታ ቢኖራቸውም በሀገር ጉዳይ ላይ በፍፁም ሌላ ድርድር ውስጥ መግባት አልፈለጉም። ጦራቸውን ማሰባሰብ ጀመሩ እናም ከነ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ፣ አበበ አረጋይ፣ በላይ ዘለቀና አቡነ ጴጥሮስ ጋራ ስለ ጦርነቱ የምስጢር ደብዳቤ መለዋወጥ ጀመሩ። ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ አምስት ሺህ ጦራቸውን ይዘው ከትውልድ መንደራቸው ከአገምጃ ሶዶ ተነስተው አዲስ አበባ ደረሱ፤ ከዚያምም ረጲ ተራራ ላይ ሆነው መድፋቸውን ጠምደው የሌሎችን አርበኞች መልዕክት ይጠባበቁ ጀመር። ሺህ የባልቻ ሰላይ የነበሩት በባንዳ ተይዘው ሲገደሉ ጣሊያን በአውሮፕላን ሆኖ የደጃዝማች ባልቻ ጦርን እየተከተለ ብዙ ጉዳት ቢያደርስባቸውም በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ወኔ የሠሩት ሥራ ፍሬ አፍርቶ የሀገራቸውን ነፃነት አስጠብቋል። እርሳቸውም ይሄው በጀግንነት ይታወሳሉ።
ከ55 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 27 ቀን 1962 ዓ.ም የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ተመርቆ ተከፈተ። ፋብሪካው የተገነባው በኢትዮጵያ እና በኔዘርላንድስ መንግሥታት ትብብር ነበር።
ከ35 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 30 ቀን 1982 ዓ.ም (ኖቨምበር 9, 1989) በርሊንን ‹ምሥራቅ› እና ‹ምዕራብ› አድርጎ ከፍሏት (ለያይቷት) የነበረው ‹‹የበርሊን ግንብ›› ፈረሰ። ሁለቱን ጀርመኖች ከማዋሓዱም ባሻገር የኮሚኒዝም ሥርዓትን ያፈረሰ ነው ተብሎ ይነገርለታል።
አሁን በዝርዝር ወደምናየው የንጉሥ ኃይለመለኮት ሣሕለሥላሴ ታሪክ እንለፍ።
የታሪክ ፀሐፊው ፍስሐ ያዜ ‹‹የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ ከኖህ እስከ ኢሕአዴግ›› በሚለው ቅጽ 1 መጽሐፉ በ81ኛው ምዕራፍ ላይ እንዲህ ይለናል።
‹‹… ልጅ ምኒልክ የአፄ ልብነ ድንግል ልጅ ከሆኑት ከአፄ ያዕቆብ ትውልድ 13ኛ የዘር ሐረግ ላይ ይቀመጣሉ። አያታቸው ሣሕለሥላሴ የሸዋውን ንጉሥ ኃይለመለኮትን ይወልዳሉ…..›› እያለ ይቀጥላል። ስለዚህ ንጉሥ ኃይለመለኮት ከአፄ ልብነ ድንግል ዘር 12ኛ የዘር ሐረግ ላይ ይቀመጣሉ።
ንጉሥ ሣህለሥላሴ (የንጉሥ ኃይለመለኮት አባት) ለ33 ዓመታት ከ 5 ወራት ያህል ሸዋንና በሸዋ ዙሪያ ያለውን ቦታ ሲያስተዳድሩ ቆይተው ጥቅምት 12 ቀን 1840 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ ዙፋኑን የወረሱት ልጃቸው ንጉሥ ኃይለመለኮት ናቸው።
ንጉሥ ኃይለመለኮት በሰውነታቸው ግዝፈትና ጥንካሬ እንዲሁም በልባቸው ቀናነት በሸዋ ዘንድ የታወቁና የተወደዱ ንጉሥ ነበሩ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚነግሩን፤ ንጉሥ ኃይለመለኮት ከጥንካሬያቸው የተነሳ ዒላማ ተኩስ በሚተኩሱ ጊዜ መሣሪያውን አጠንክረው በመያዛቸው ምክንያት ጥይቱ ሲወጣ ጠመንጃቸው ለሁለት ተሰብሮ እጃቸው ላይ ቀርቶ ያውቃል።
ንጉሥ ኃይለመለኮት ሸዋን ለ8 ዓመታት ያህል አስተዳድረዋል። በሥልጣን ላይ ሳሉም ተቀናቃኝ ሊሆኑባቸው የሚችሉትን ወገኖቻቸውን እንዲያስሯቸውና እንዲያስወግዷቸው ሰዎች ሲመክሯቸው፣ ‹‹ተዉ! ይሄን አላደርገውም! እግዚአብሔር የወደደውን ነው የሚያነግሠውና የሚያስገዛው›› የሚሉ ቀና ሰው እንደነበሩ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በመጽሐፋቸው ጠቅሰውታል።
የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ እንደሚነግረን፤ ካሣ ኃይሉ የዘመነ መሳፍንትን የየአካባቢ መስፍኖች ሁሉ አሸንፈው፣ ‹‹ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ሆነው ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ጀመሩ። በዚህን ጊዜ ታዲያ ራስ ዓሊ ተቀናቃኛቸው ነበሩ። የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ተቀናቃኝ የሆኑት ራስ ዓሊ የሸዋ ንጉሥ በነበሩት በንጉሥ ኃይለመለኮት ሣሕለሥላሴ እየተደገፉ አልያዝ አሉ። ይህ ሲሆን ሸዋ ለአፄ ቴዎድሮስ እየገበረ አልነበረም። አፄ ቴዎድሮስ በነገሱ በዓመቱ (በ1846 ዓ.ም ማለት ነው) ትግራይን እና ወሎን አስገብረው ሸዋ ገቡ።
አፄ ቴዎድሮስ ሸዋን አስገብረው ግሼ ሲደርሱ የግሼው ሹም አቶ ሀብተማርያም ተዋግተዋቸው ነበር፤ ሆኖም ሀብተማርያም ድል ሆኑ። አፄ ቴዎድሮስ መንዝ ሲደርሱ የይፍራታና ግድም ሕዝብ መገበር ጀመረ። ጉር ሥላሴ ሲደርሱ ግን ብዙ ሕዝብ መዋጋት ጀምሮ ነበርና ንጉሠ ነገሥቱ ብዙ ሰው አለቀባቸው። ይህ ከሆነ በኋላ ነው እንግዲህ የሸዋው ንጉሥ ኃይለመለኮት ሣሕለ ሥላሴ ከሚኖሩበት ከተማ አንኮበር ወጥተው ቶራ መስክ ላይ አፄ ቴዎድሮስን ለመዋጋት የተዘጋጁት። በመሐል ባሉ አካባቢዎች ውጊያዎች ሲደረጉ ቆይተው ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ እና ንጉሥ ኃይለመለኮት ሣሕለሥላሴ ሳይገናኙ ኃይለመለኮት ያደረባቸው ሕመም ጠንክሮ ጥቅምት 30 ቀን 1848 ዓ.ም ሌሊት ማረፋቸው ተሰማ።
በዚሁ በጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ ላይ እንደተጻፈው፤ ንጉሥ ኃይለመለኮት የሞቱት ከአፄ ቴዎድሮስ በተላከ መልዕክተኛ ተመርዘው ነው የሚል ሐሜት ነበር። በአንኮበር የሚገኙ የውጭ አገር ሰዎች እንደጻፉት ግን ኃይለመለኮት የሞቱት በንዳድ (ወባ ማለት ነው) በሽታ ነው።
ከንጉሥ ኃይለመለኮት ሞት በኋላ የሸዋ ሰዎች ንጉሣቸውን ቀብረው፤ የ11 ዓመት ልጅ የሆነውን ምኒልክን (በኋላ አፄ ምኒልክ) ይዘው ሸሹ። ይህን የሰሙት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከደብረ በግዕ ተነስተው ጠራ ገቡ። ጠራን ካስደበደቡ በኋላ ምኒልክን እያባረሩ ወደ መገዘዝ እንደደረሱ ራስ እንግዳ የሚያዝዙትን ጦር ወደ በረኸት ሰደው አፄ ቴዎድሮስ ወደ ምንጃር ተሻገሩ። ሕጻኑን ምኒልክን ይዘው ይሸሹ የነበሩ የሸዋ ሰዎች ከአረርቲ ቆላ ቆላውን ሄደው፣ ከሰምን ተሻግረው፣ በረኸት ብቅ ሲሉ ከራስ እንግዳ ጦር ጋር ተጋጠሙ። በዚያ ቦታ ጦርነት ተደርጎ ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰው ሞተ። ከምኒልክ ጋር ብዙ ሰዎችም አብረው ተሰደው ነበር። በዚያን ጊዜ በመኳንንቱ እንዲህ ተብሎ ተገጠመ።
ቁርጡን አወቁና አለመኖርህን
በረኸት አገቡት ጌታዬ ልጅህን
የዚህ ግጥም መልዕክት ለሟቹ ንጉሥ ኃይለመለኮት ሣሕለሥላሴ ይመስላል። የእርሳቸውን አለመኖር ልጃቸው ምኒልክ በስደት ተንከራተተ ማለት ነው።
ከጦርነቱ በኋላ የንጉሡ ልጅ የሆኑት ምኒልክ ተመለሱ። ምኒልክን ይዘው የሚሸሹት ሰዎች የአፄ ቴዎድሮስን ሠራዊት ብዛት፣ የጦርነቱንም ብርታት አይተው ነበርና ምንጃር ሆነው ሲማከሩ፤ ግማሾቹ ምኒልክን ይዘን ወደሌላ ቦታ እንሂድ ብለው ተማከሩ። ሌላው መካሪ ደግሞ ሕጻኑን ይዘን ሀገር ለሀገር ከመንከራተትና አፄ ቴዎድሮስም ተከታትለው ከሚወስዱብን በፈቃዳችን ብንሰጣቸው ይሻላል ብለው መከሩ። የጉባኤው ሀሳብ ለሁለት በመከፈሉ ምንም እንኳን ሕጻን ቢሆንም የምኒልክ ሀሳብ ይጠየቅ ተባለ። ሕጻኑ ምኒልክ ለአፄ ቴዎድሮስ ከሚሰጥ እና ወደ ሌላ ቦታ ከሚወሰድ ምርጫ ቀርቦለት ወደ ሌላ ቦታ መወሰድን መርጧል።
ይህ ሁሉ ሲሆን አፄ ቴዎድሮስ አንኮበር ነበሩ። አንኮበር ሆነውም ‹‹አባት ያለህ የአባትህን እሰጥሃለሁ መርቅ፤ አባት የሌለህ ግን አባትህ እኔ ነኝና ደጅ ጥናኝ›› የሚል አዋጅ ስላስነገሩ ብዙ የሸዋ ሰዎች የአባታቸውን ሀገርና ሹመት እናገኛለን በማለት ለአፄ ቴዎድሮስ መግባታቸው ተሰማ። ይህን ጊዜ አቶ አንዳርጋቸው የተባሉ ከምኒልክ ጋር ተሰደው የነበሩ ወደ ምኒልክ ጠጋ ብለው ‹‹ይህን የመሰለ አዋጅ ተነገረ፣ ንጉሡ ቃልኪዳናቸውን የማያፈርሱ ቆራቢ ናቸው፣ አቡነ ሰላማም ደግ ጳጳስ ናቸው ይባላልና የአባትህን አልጋ አይነጥቁህም›› በማለት ለምኒልክ አስረድተውና አግባብተው ወደ አፄ ቴዎድሮስ ይዘዋቸው ገቡ። ይህ የምኒልክ በአፄ ቴዎድሮስ መያዝ በታሪክ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። ምኒልክ በአፄ ቴዎድሮስ ከተማረኩ በኋላ እንደ እስረኛ ሳይሆን እንደ ልጅ ተንከባክበው ይዘዋቸው እንደነበር በታሪክ ተጽፏል።
አፄ ምኒልክ ለዚህ ሁሉ የበቁት የንጉሥ ኃይለመለኮት ልጅ መሆናቸው ነው።
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የንጉሡን ልጅ ምኒልክን እንደ ልጃቸው ማየት ብቻ ሳይሆን፤ የንጉሥ ኃይለመለኮት ሞት አሳዝኗቸው ነበርና አስከሬናቸው እንደገና ወጥቶ በንጉሣዊ የቀብር ሥርዓት እንዲቀበሩ አድርገዋል። ከዚያ በኋላ ያለው ታሪክ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እና የንጉሥ ኃይለመለኮት ልጅ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም