በኢንተርናሽናል የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ታሪክ በርካታ ፍልሚያዎች በሰፊ የግብ ልዩነት ሲጠናቀቁ ታይተዋል። በትልቁ ዓለም ዋንጫ መድረክ ሳይቀር በሰፊ የግብ ልዩነቶች የተጠናቀቁ በርካታ ጨዋታዎች በታሪክ ተመዝግበው ይገኛሉ።
በአጠቃላይ በእግር ኳስ ታሪክ በሰፊ የግብ ልዩነት የተጠናቀቁ በርካታ ጨዋታዎች ቢኖሩም በብሔራዊ ቡድኖች መካከል በተካሄዱ ጨዋታዎችን በተመለከተ በሰፊ የግብ ልዩነት የተጠናቀቁ ብሎ ፊፋ ከመዘገባቸው ውጤቶች መካከል ዋነኛ የሆነው ከ24 ዓመት ነበር የተመዘገበው።
እግር ኳስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነ በዓለም ላይ የተፎካካሪ ቡድኖች ደረጃ ጎልቶ በማይታይበት በዚህ ዘመን ከደርዘን በላይ ግቦች በአንድ ጨዋታ ሲመዘገቡ ማየት ከባድ ነው፡፡ በክለብም ይሁን በብሔራዊ ቡድኖች ደረጃ እግር ኳስ ከልምድ ወጥቶ በሳይንስ እየተመራ ከመጣ ወዲህ የአሠልጣኞች የታክቲክ ብስለት እየተቀራረበ መምጣቱን ተከትሎ በጣት የሚቆጠሩ ግቦችን ብቻ በአንድ ጨዋታ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ የአሠልጣኞች፣ ቡድኖችና የተጫዋቾች ደረጃ ፍፁም የተራራቀ በሆነባቸው ፍልሚያዎች እንኳን አንድ ቡድን ብቻ ከደርዘን በላይ ግቦችን ሲያስቆጥር ማየት እየቀረ መጥቷል፡፡ አንድ ብሔራዊ ቡድን በአንድ ጨዋታ ላይ ከ30 በላይ ግብ አስቆጥሮ ያሸነፈበት አጋጣሚ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የተፈጠረ መሆኑ ግርምት ይፈጥራል፡፡
ይህ ታሪካዊ ጨዋታ በአውስትራሊያ 31 ለ 0 ድል የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ከባዱ ሽንፈት የደረሰባት ደግሞ በእግር ኳስ ስሟ ሲጠራ የማትታወቀው የኦሽኒያዋ አሜሪካን ሳሞአ ናት። ጨዋታው የኦሽኒያ ሀገራት የ2002 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ነበር። በመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታዋን ቶንጋን 22 ለ 0 ያሸነፈችው አውስትራሊያ፣ በፊጂ 13 ለ 0 የተሸነፈችው ሳሞአ ጋር በኮፍስ ሀርበር ስቴድየም ተገናኘች።
በሦስት ሺ ተመልካቾች ፊት የተካሄደው የአውስትራሊያና ሳሞአ ጨዋታ ገና ከአስረኛው ደቂቃ ጀምሮ ግብ ቢያስተናግድም ታሪክ የማይረሳው ውጤት ይመዘገብበታል ብሎ ያሰበ አልነበረም። የአውስትራሊያው አማካኝ ኮን ቦትሲያኒስ ሀገሩን ገና በጊዜ መሪ አደረገ። ኋላ ላይም በ50ኛው እና 84ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው ግቦች ሐትሪክ ሠርቷል።
ታሪካዊ ውጤት በተመዘገበበት ጨዋታ ግን ቀዳሚዋን ግብ ከመረብ አሳርፎ ሶስታ ከሠራው ተጫዋች በላይ አርቺ ቶምሰን የተባለውና ሌሎችም የአውስትራሊያ ተጫዋቾች የጨዋታው ኮከብ ነበሩ። ቶምሰን የተባለው ተጫዋች ለማመን በሚከብድ ሁኔታ (12′, 23′, 27′, 29′, 33′, 37′, 42′, 45′, 56′, 60′, 65′, 85′, 88′) ደቂቃዎች በጨዋታው አስራ ሦስት ግቦችን በተጋጣሚ መረብ ላይ በማዝነብ ታሪክ ሠርቷል።
የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ዴቪድ ዝሪሊችም ብዙ አልራቀም፣ (13′, 21′, 25′, 33′, 58′, 66′, 78′, 89′) ደቂቃዎች ስምንት ግቦችን ከመረብ አዋህዷል። ሌሎቹን የአውስትራሊያ ግቦች ኦሬሊዮ ቪድማር በ (14′, 80′) ደቂቃ፣ ቶኒ ፖፖቪች (17′, 19′) ደቂቃዎች፣ ሳይመን ኮሎሲሞ (51′, 81′) እና ፉስቶ ደ ኤሚሲስ በ55ኛ ደቂቃ ማስቆጠር ችለዋል።
ይህ የአውስትራሊያ የ31 ለ 0 ድል በብሔራዊ ቡድኖች ኢንተርናሽናል ጨዋታ ክብረወሰን ሆኖ ከ24 ዓመት በፊት ቢመዘገብም፣ በአጠቃላይ የእግር ኳስ ታሪክ አፈታሪክ ከሚመስለው የ 149 ለ 0 ውጤት ጋር ሲነፃፀር በብዙ ርቆ ይገኛል።
ብዙዎች የማያምኑት የ 149 ለ 0 ውጤት በእግር ኳስ ታሪክ ትልቁ ተብሎ ይታወቃል። ይህ ውጤት የተመዘገበውም በአፍሪካዊቷ ደሴት 2002 ላይ በማዳጋስካር ሊግ AS Adema የተሰኘ ክለብ S.O. l’Emyrne የተባለውን ክለብ የረታበት መሆኑ በብዙ የመረጃ ምንጮች ተጠቅሶ ይገኛል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም