የአሜሪካ መንግሥት ዶናልድ ትራምፕ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመመረጣቸው በፊት ኢራን ለመግደል አሲራለች ካለው ጋር በተያያዘ ተሳታፊ ተብሎ የተጠረጠረ አፍጋኒስታናዊ ላይ ክስ መሠረተ። የፍትህ ሚኒስቴር ትራምፕን ለመግደል “እቅድ የማቅረብ” ኃላፊነት ተሰጥቶት ተሳትፏል ሲል በወነጀለው የ51 ዓመቱ ፋርሃድ ሻኬሪ ላይ የመሠረተውን ክስ ይፋ አድርጓል።
የአሜሪካ መንግሥት ሻኬሪ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን ገልጾ፣ ኢራን ውስጥ ይኖራል ተብሎ እንደሚታመን ገልጿል። በማንሃተን ፍርድ ቤት በቀረበው በዚህ የወንጀል ክስ፣ አቃቤ ሕግ በኢራን የአብዮታዊ ጥበቃ ባለሥልጣን የሆነ ግለሰብ ሻኬሪ ትራምፕን እንዲሰልል እና የግድያ ዕቅድ እንዲያቀርብ በመስከረም ወር ላይ መመሪያ መስጠቱ ተብራርቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሆኑት ሜሪክ ጋርላንድ በሰጡት መግለጫ “የፍትህ መሥርያ ቤቱ የኢራንን መንግሥት አካል ላይ ክስ የመሠረተው፣ አስተዳደሩ የወንጀል ተባባሪዎችን የኢራንን የግድያ ሴራ በዒላማዎቹ ላይ፣ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ እንዲፈጽሙ በመታዘዛቸው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የፍትህ መሥርያ ቤቱ ኢራንን በመተቸት የሚታወቅ አሜሪካዊ ጋዜጠኛን ለመግደል ተመልምለዋል ያላቸውን ሁለት ሌሎች ግለሰቦችም ላይ ክስ መሥርቷል። በፍትህ መሥርያ ቤቱ ክስ የተመሠረተባቸው ሌሎቹ ግለሰቦች ካርሊስሌ ሪቬራ በመባል የሚታወቀው የ49 ዓመት ጎልማሳ ከብሩክሊን እና የ36 ዓመቱ ጆናቶን ሎድሆልት ከስታተን አይላንድ እንደሆኑ አብራርቷል።
ሁለቱ በኒውዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል። ትራምፕ በዚህ ዓመት ሁለት የተለያዩ የግድያ ሙከራዎች አጋጥሟቸዋል። በሐምሌ ወር ላይ አንድ ታጣቂ የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ በፔንስልቬንያ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ ተኩሶባቸው ጆሯቸውን ጨርፏቸዋል።
በመስከረም ወር እንዲሁ ሌላ ግለሰብ ትራምፕ በዌስት ፓልም ቢች በሚገኝ መኖርያ ቤታቸው ጎልፍ ሲጫወቱ ጦር መሣርያ በማነጣጠሩ በቁጥጥር ስር ውሏል። አፍጋኒስታናዊው ሻኬሪ ትራምፕን በሰባት ቀናት ውስጥ የመግደል እቅድ እንዲያወጣ ተጠይቆ ነበር ሲል ያትታል በአሜሪካ አቃቤ ሕግ የቀረበው ክስ።
እንደ አቃቤ ሕግ ገለጻ፣ ሻኬሪ ትራምፕን ለመግደል በሰባት ቀናት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሃሳብ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ባለሥልጣናት እቅዱን ለጊዜው ገትተውታል።አቃቤ ሕግ ሻኬሪን ጠቅሶ እንዳለው የኢራን መንግሥት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው ይሸነፋሉ ብሎ በማመኑ ከምርጫው በኋላ ለመግደል መሞከር ቀላል እንደሚሆን መወሰናቸውን ገልጿል።
አቃቤ ሕግ ሻኬሪን በልጅነቱ ወደ አሜሪካ የመጣ አፍጋኒስታናዊ ዜግነት ያለው ሲል ገልጾታል። በአውሮፓውያኖቹ 2008 ለ 14 ዓመታት ከስርቆት ወንጀል ጋር በተያያዘ በእስር ካሳለፈ በኋላ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ተደርጓል። አቃብያነ ሕጎች እንዳሉት የ51 ዓመቱ ጎልማሳ፣ የኢራን መንግሥት ዒላማ የሆኑ ግለሰቦች ላይ ክትትል ለማድረግ በእስር ቤት የሚገኙ “የወንጀል ተባባሪዎች መረብ”ን ሪቬራ እና ሎድሆልትን የሚባሉ ግለሰቦችን ጨምሮ ተጠቅሟል።
ሻኬሪ ለሪቬራ እና ሎድሆልት የኢራንን መንግሥት የሠብዓዊ መብት ረገጣ እና ሙስና የዘገበውን አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ለመግደል 100 ሺህ ዶላር ቃል ለመክፈል ቃል ገብቷል ሲል አቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አመልክቷል። ስሙ ያልተጠቀሰው ጋዜጠኛ ከዚህ ቀደምም ዒላማ ተደርጎ ነበር ሲል አቃቤ ሕግ ተናግሯል።
አርብ ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መቀመጫዋን ብሩክሊን ያደረገች ማሲህ አሊነጃድ የተባለች ጋዜጠኛ ኤፍቢአይ እርሷን ለመግደል ያሴሩ ሁለት ሰዎችን ማሰሩን ጽፋለች። ገዳዮቹ ብሩክሊን በሚገኘው ቤቷ ፊት ለፊት እንደመጡ ተናግራለች። አሊነጃድ “ወደ አሜሪካ የመጣሁት በሕግ ላይ በግልጽ የተቀመጠውን የመናገር ነፃነቴን ለመጠቀም ነው፤ መሞት አልፈልግም” ስትል ጽፋለች። በተጨማሪም “አምባገነንነትን መዋጋት እፈልጋለሁ፤ እናም ደህንነቴ ሊጠበቅ ይገባል” ብላለች።
ከአሜሪካዊው ጋዜጠኛ እና ትራምፕ በተጨማሪ የኢራን መንግሥት በማህበራዊ ሚድያ ላይ እስራኤልን የሚደግፉ እና ኑሯቸውን በኒውዮርክ ከተማ ያደረጉ ሁለት የአይሁድ ዝርያ ያላቸው አሜሪካውያን ነጋዴዎችን ለመግደል ማቀዱን ክሱ ያስረዳል። ሻኬሪ ለአቃቤ ሕግ ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰ ከአንድ ዓመት በኋላ በጥቅምት 2024 በስሪላንካ የእስራኤል ቱሪስቶች ላይ በጅምላ ጥቃት ለማድረስ እንዲያቅድ የኢራን አካላት እንደጠየቁት ተናግሯል።
ሻኬሪ፣ ሪቬራ እና ሎድሆልት ሁሉም የተከሰሱት ግድያ ለመፈጸም በመመልመላቸው ሲሆን ይህም የ10 ዓመት እስራት ያስቀጣቸዋል። በተጨማሪም እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ በሚችለው ገንዘብ ለመሰወር በማሴር እንዲሁም ለግድያ ተግባር በሦስተኛ ወገን ተመልምለው በማሴር ወንጀሎችም የሚቀጡ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም