አዲስ አበባ :- የአቪዬሽን ዘርፉ ለግል አልሚዎች ክፍት መደረጉ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል እንደሚፈጥር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በድህረ-ምረቃ ፣ በቅድመ-ምረቃ፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በሰርተፊኬት ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 974 ተማሪዎች ትናንት አስመርቋል።
በወቅቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ተሻለ በሬቻ እንደገለጹት፤ የአቪዬሽን ኢኮኖሚው ለግሉ ዘርፍ ክፍት መደረጉ ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አይነተኛ ሚና አለው።
መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለግሉ ዘርፍ ክፍት በማድረጉ በአቪዬሽን መስክ በርካታ ተቋማት ተሰማርተው ኢኮኖሚውን ከማንቀሳቀስ ባለፈ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል።
ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅም በገበያው ላይ የሚፈለጉ የትምህርት መስኮችን በማስተማር በተለይም በአቬሽን ዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት በመቅረፍ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዕውቀት በተግባር ካልተደገፈ ውጤታማ ስለማይሆን ወጣቶች አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ ለዓለም አቀፍ የሥራ እድሎች ያላቸውን ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
መመረቅ በራሱ ግብ አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ምሩቃኑ ለቀጣይ እራሳቸውን ብሎም ሀገርን ለመለወጥ መዘጋጀት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በርካታ የሥራ እድሎች ማመቻቸቱን ገልጸው፤ ከሀገር ውጭ መሥራት ለሚፈልጉ የውጭ የሥራ ስምሪት መኖሩን ፣ በግል ለሚሰሩ ደግሞ የቦታ፣ የብድርና መሰል እድሎች መመቻቸታቸውን አመላክተዋል።
የናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚና መስራች የሆኑት ካፒቴን አበራ ለሚ፤ ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በቅርቡ ዩኒቨርሲቲ የመሆን ዓላማ ሰንቆ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኮሌጁ በተሟላ ግብዓትና የስልጠና ዘርፎች ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገዛኸኝ ብሩ በበኩላቸው፤ በአቪዬሽን፣ በሆቴልና በቱሪዝም መስኮች እያደገ የመጣውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ከማሟላት አኳያ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ተናግረዋል።
ከኮሌጁ ሰልጥነው የሚወጡ ተማሪዎች በተመረቁበት የትምህርት ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ስልጠናዎች ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ኮሌጁ ከሲቪል አቬሽን ባለስልጣን እውቅና ባገኘበት በአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሽያንነት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማሰልጠን የጀመረ ብቸኛ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ የናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባል እና የናሽናል አየር መንገድ እህት ኩባንያ ነው።
በወዳጅነት አደባባይ በተካሄደው የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ የክብር እንግዶች፣ የኮሌጁ ከፍተኛ አመራሮች፣ ተመራቂ ተማሪዎችና የተመራቂ ቤተሰቦችን ጨምሮ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም