አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ አረንጓዴ ስፍራዎች በዘላቂነት ለመንከባከብ ከአራት ሺህ 600 በላይ የአረንጓዴ ልማት ሠራዊት ወደ ስራ ማሰማራት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ እየተሰሩ ያሉ የአረንጓዴ መሰረተ ልማትና የኮሪደር ልማት ስራዎችን በዘላቂነት ለማስቀጠልና የለሙ ቦታዎችን ባለቤት ለመስጠት ያለመ የንቅናቄ መርሀ ግብር ትናንት ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ በወቅቱ እንደገለጹት፤የኮሪደር ልማት ዘርፍ አንዱ በሆነው የአረንጓዴ መሰረተ ልማት ስራ ከተማዋን በተፈጥሮ የበለጸገችና ለመኖር ተስማሚ የአፍሪካ ግንባር ቀደም ከተማ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ አረንጓዴ ስፍራዎች በዘላቂነት ለመንከባከብም ከአራት ሺህ 600 በላይ የአረንጓዴ ልማት ሠራዊት በዘርፉ በማሰልጠን የስራ ስምሪት መስጠት ተችሏል፡፡
የከተማዋን አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ደረጃዋን የሚመጥን ዘመን ተሻጋሪ ከተማ ለመገንባት በሚ ያስችለው የኮሪደር የአረንጓዴ ልማት ብዙ በተጨባጭ የሚታዩና የሚቆጠሩ ድሎች መመዝገቡን ገልጸው፤እነዚህን የአረንጓዴ ስፍራዎች ውበታቸው እንደተጠበቀ ለማስቀጠል ከአራት ሺህ 600 በላይ የአረንጓዴ ልማት ሠራዊት በዘርፉ በማሰልጠን የስራ ስምሪት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የከተማውን እድገትና መስፋፋት ተከትሎ በሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ከ603 ሄክታር መሬት በላይ አረንጓዴ ቦታዎችን ማልማት መቻሉን አመልክተው፤ 60 ሄክታር መሬት በኮሪደር አረንጓዴ ልማት የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም ከ70 በላይ የሚሆኑ የህዝብ መናፈሻዎች እና 38 የውሀ አካላት መልማታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮሪደር አረንጓዴ ልማትና ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማዋ በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ስራዎች ተከትሎ የአዲስ አበባ አረንጓዴ ሽፋን ከ2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 20 በመቶ ከፍ ማድረግ እንደተቻለ አስታውቀዋል፡፡
ለዓይን የማይመቹ አካባቢዎችና ለአፍንጫ የሚሰነፍጡ ወንዞች የከተማዋ መለያ እስኪመስል ድረስ የከተማዋን ገጽታ አደብዝዘው እንደነበር አንስተው፤ በተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራም በአረንጓዴ በተዋቡ ሰፈሮች ተቀይረዋል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ይመኙሻል እንደገለጹት፤ አረንጓዴ ከተማ ግንባታ ሲባል በአካልና በአዕምሮ የዳበረ የነገዋን ኢትዮጵያ ተረካቢ ጤናማ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ ለዚህም በሁሉም መዳረሻዎች ዘመኑን የዋጁ የተለያዩ የህጻናት አዕምሮ ማጎልበቻና አረንጓዴ ቦታዎች ተገንብተዋል፡፡እነዚህ የለሙ አረንጓዴ ቦታዎች በዘላቂነት በእንክብካቤ ለማስቀጠልም ከ4 ሺህ 600 በላይ የአረንጓዴ ልማት ሠራዊት በዘርፉ በማሰልጠን የስራ ስምሪት መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለከተማዋ ሌላኛው የቱሪዝም የገቢ ምንጭ መሆን የቻሉ የህዝብ መዝናኛዎችን ገንብቶ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከተማዋን አረንጓዴ ከተማ ገንብቶ ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀው፤ ሁሉም አካል በኮሪደር ልማቱ ውጤቶችን በዘላቂነት ለማስቀጠል ኃላፊነት መወጣት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡
በህዝብ ንቅናቄ መድረኩ ከ11ዱም ክፍለ ከተሞች ለተመረጡ ተጽእኖ ፈጣሪና ታዋቂ ግለሰቦችም የአረንጓዴ ልማት አምባሳደርነት ተሰጥቷል።
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም