ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ትልቅ ሳንካ ሆኖ የቀጠለ የኢትዮጵያ ችግር ነው። አሁንም ድረስ በርካቶች ሕጋዊ መንገዶችን በመተው በሕገ ወጥ መንገድ ጥሪታቸውን አሟጠው ገንዘባቸውን ለሕገ ወጥ ደላሎች ሲሳይ አድርገው ባህር አቋርጠው ወደ ተለያዩ አረብ ሀገራት ይጓዛሉ። ከነዚህ ውስጥ ታዲያ ጥቂቶች ብቻ ናቸው በለስ ቀንቷቸው ወደሚፈልጉበት ሀገር የሚደርሱት። እዛም ደርሰው ግን በሕገ ወጥ መንገድ እንደመግባታቸው ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አይሆኑላቸውም።
አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ በተለይ የአረቡ ዓለም መናወጥ ለስደተኞች አስተማማኝና ቋሚ ስራ ለማግኘት አዳጋች አድርጎታል። ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ብዙዎቹ አረብ ሀገራትም በርካታ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ወደሀገራቸው መልሰዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ወደነዚህ ሀገራት የሚደረገው ሕገ ወጥ ጉዞ አሁንም አልቆመም። መንግስት በሕገ ወጥ መንገድ ወደነዚህ ሀገራት ተጉዘው እንግልትና ስቃይ ሲደርስባቸው የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲመለሱ አድርጌያለሁ፤ ወደዛ የምልካቸውም የሰለጠኑና ሕጋዊ መስመርን የተከተሉ ናቸው ቢልም አሁንም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አልተገታም። ስለዚህ ምን ይደረግ?
ዘ ፍሪደም ፈንድ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጀምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የአቅም ግንባታ ስራዎችን የሚያከናውን ምግባረ ሰናይ ድርጅት ነው። አቶ ዳንኤል መለሰ ደግሞ የዚህ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እጅግ የተወሳሰበ፣ ከገጠር ቀበሌ እስከ ትልልቅ ከተሞች ድረስ የተሳሰረና በርካታ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች የሚሳተፉበት የወንጀል ድርጊት ነው።
ችግሩም ያን ያህል የገዘፈ ሲሆን በአመቱ 100 ሺ ያህል ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ወደተለያዩ ሀገራት እንደሚሄዱ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ አንፃር ይህን ችግር ለመቅረፍ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ይጠይቃል። ለአብነትም ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን በሚመለከት ፍትህ ሚንስቴር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ሕግና አዋጆችም ወጥተዋል። እነዚህን አዋጆች ደግሞ ፖሊስ፣ አቃቢ ሕግና ፍርድ ቤቶች ግንዛቤው ኖሯቸው ማስፈፀም ይኖርባቸዋል።
ከሕግ አግባብ አንፃር የሕግ ሰዎች፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚሰሩ ስራዎች አንፃር በማህረሰቡ ውስጥ የሚሰሩ አካላትና የሚዲያ ሰዎችንና ሌሎችም ተቀናጅተው ሲሰሩ ነው ጉዳዩን እልባት ማስገኘት የሚችሉት። ስለዚህ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት አንዱና ዋነኛው የሚታየው ችግር የባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ መስራት አለመቻል በመሆኑ ተቀናጅቶ መስራቱ ወሳኝ ነው።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ የሚሰራውን ስራ ከማስተባበር አንፃር የተጀመሩ ጥረቶች አሉ። ይሁንና ስራው ከችግሩ ጋር የሚመጣጠን አይደለም። ስለዚህ ከመንግስት፣ ከሲቪል ማህበራትና ከግለሰቦች ኃላፊነት አንፃር ብዙ የሚቀሩ ስራዎች አሉ።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ፍሪደም ፈንድ ከሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተገናኘ ፍሪደም ፈንድ ከፍትህ ሚንስቴርና ተያያዥ ከሆኑ ተቋማት ጋር ይሰራል። ለአብነትም ከክልል የፍትህ ቢሮዎች፣ ከስራና ክህሎት ሚንስቴር ጋርና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ቢሮዎች ጋር በቅርበት ይሰራል። ከሌሎች ሃያ አምስት ድርጅቶች ጋርም ተመሳሳይ ስራዎችን ያከናውናል።
በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ያለውን ችግር ለመቀነስ በምክክር የሚሰሩ ስራዎች አሉ። ድርጅቱም እየሰራው ያለው ስራ እነዚህን ምክክሮች በማብዛትና ከመንግስት ጋር በመወያየት ችግሩን ለመቅረፍ ነው። ይሁንና አንዳንድ የፖለቲካ ይሁንታን የሚጠይቁ ጉዳዮች በመንግስት በኩል መፈቀድ አለባቸው። መንግስትም ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት መስራት አለበት።
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጄ ተግይበሉ በበኩላቸው እንደሚገልፁት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በአንድ ሀገር ብቻ ሳይሆን በርካታ ሀገራትን የሚያሳትፍ ነው። ከዚህ አንፃር ችግሩን ለማስቆም የአንድ ሀገር ስራ ብቻ ሆኖ የሚቆጠር ባለመሆኑ የሁሉንም ሀገራት ትብብር ይጠይቃል። ችግሩን ለመፍታት ደግሞ በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠነ ሰፊና ቅንጅታዊ ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች ትገኛለች። ለዚህም የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርማለች። የጠረፍ አስተዳደር ስራዎችን ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የቁጥጥር ስራዎችንም ታከናውናለች። ይሁንና ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና የአፍሪካ ቀንድና የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች ከፍተኛ ግጭት ያለባቸው፤ በዚሁ ምክንያት ሰዎች ከአንዱ ሀገር ወደሌላው ሀገር የሚፈልሱባቸው ሁኔታዎች አሉ። በጎርፍ፣ ድርቅና ሌሎች ተፈጥሯዊ ችግሮችና በጎሳ ግጭቶች ምክንያቶች ዜጎች ከአንዱ ወደሌላው ሀገር ይሰደዳሉ።
ኢትዮጵያም የበርካታ ሕዝቦች መገኛ እንደመሆኗ ዜጎች በህጋዊም ሆነ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደተለያዩ ሀገራት ይሄዳሉ። የበርካታ ሀገር ዜጎች ስደተኞች ተቀባይ ሀገርም ናት። የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መሸጋገሪያም ጭምር ነች። ከዚህ አኳያ የሚፈፀመው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ውስብስብ ከመሆኑ አንፃር በአንድ ጊዜ መግታት የሚቻል አይደለም። በቀጣይ ግን ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ትብብር በማጠንከር ችግሩን ለመቀነስ ይሰራል።
ስራ አስፈፃሚው እንደሚሉት በዚህ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተለያዩ አካላት ሊሳተፉ ይችላሉ። ከፍተኛ ሀብትም የሚፈስበት በመሆኑ ከታች ካለው ማህበረሰብ ጀምሮ እስከላይኛው የመንግስት አካላት ድረስ ያለውን መዋቅር ሊነካ ይችላል። ከዚህ አንፃር አዘዋዋሪዎቹ ከእስር ቤት የሚያመልጡባቸውና እንዳይያዙ የሚደረጉበት ሁኔታ ስለሚኖር የሕግ ስርዓቱን በማጥበቅ መከላከል ያስፈልጋል።
ዜጎችም ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን እንዲያጋልጡ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን መስጠት ይገባል። የመንግስት የፀጥታ ኃይሎችም ስራቸውን በተገቢው ሁኔታ መስራት አለባቸው። በዚሁ ሁኔታ ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በህግ የሚጠየቁበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ከጉዳዩ ስፋት አኳያ ግን አሁንም ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን በመከላከል ዙሪያ ሰፊ ስራ መስራት ይጠይቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2015