አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ጣሊያን የዓድዋ ሽንፈቷን ለማካካስ ስትል ለዳግም ወረራ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰችበት እና አባት አርበኞች አምስት መራራ የትግል ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ የተቀዳጁትን ድል ተከትሎ፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ድሉን በማስመልከት፣ “…ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ ነው፤” ሲሉ ካስተላለፉት መልዕክት ውስጥ “አዲስ ዘመን” የምትለውን ሃሳብ በመውሰድ ስያሜው አድርጎ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም አንድ ብሎ ለሕትመት በቃ።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ልደትና እድገትም ከዚሁ የታሪክ ዐውድ ከሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ውልደት ተነጥሎ አይታይም። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሲወሳ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሲታወስም ታሪክ ሰናጁ አዲስ ዘመን ጋዜጣ አብሮ መነሳቱ የግድ ነው። በዚሁ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታነታቸው 83 ዓመታትን በዘመን ውስጥ የታሪክ ሁነቶችን እየከተቡ፤ ወቅታዊ መረጃዎችን በታማኝነት ለሕዝብ እያደረሱ፤ ትውልድን እየገነቡ እና ከፍ ያለ አገራዊ ኃላፊነትን እየተወጡ ዛሬን ደርሰዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በዘመናት ጉዞው ውስጥ በይዘት፣ በአቀራረብ፣ በቅርጽና በቀለም የተለያዩ መገለጫዎች ያሉት ቢሆንም፤ 82 ዓመታትን ሳይቆራረጥ የዘለቀ ብቸኛው አገር አቀፍ የሕዝብ ጋዜጣ መሆን የቻለ ነው። በዚህም አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመረጃ ምንጭ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ክስተቶች፣ ሁነቶችና ውጣ ውረዶች በጽሑፍም፣ በፎቶም ተደግፈው የሚገኙበት እንደመሆኑ የታሪክ ማጣቀሻ መሆን የቻለበትን እድል ፈጥሮለታል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በዚህ መልኩ የመረጃም የታሪክም አውድ ሆኖ እንዲዘልቅ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል፣ ጋዜጣው የሕዝብ እንደመሆኑ የሕዝብን ጉዳይና አጀንዳ ከፍ አድርጎ ለማስረጽ የሚችልበትን አሰራር በመዘርጋትና እንደየ ወቅቱ እና ሥርዓቱ ራሱን በማስማማት፤ ከቆሞ ቀር እሳቤ ራሱን በማላቀቅ አዳዲስ አሰራርና እሳቤዎችን በመተግበር፤ ሕዝብ እና መንግሥት ለአገር ሁለንተናዊ ለውጥ አንድ ሆነው የሚሰሩበትን ሃሳብ የሚለዋወጡበት መድረክ መሆን የቻለ ነው። ይሄንኑ ሃቅም በርካቶች ይመሰክራሉ።
በዚህ መልኩ የአንድ ወገን ተገዢ ሳይሆን የሕዝብ ጥቅምና ፍላጎትን ማዕከል አድርጎ በመያዝ መራመድ መቻሉ ደግሞ፤ ጋዜጣው በዘመናት ጅረት ውስጥ የማይነጥፍ የመረጃ ምንጭ፣ ያልተዛባ የታሪክ ሰነድ ሆኖ ከመዝለቁም በላይ፤ በሥነ ጽሑፉ ዓለም አንቱታን ያተረፉ (እንደ እነ ሀዲስ አለማየሁ፣ በዓሉ ግርማ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ስብሃት ገብረእግዚኣብሔርን የመሳሰሉ) አንጋፋ ደራስያንን ለአገር ማበርከት ችሏል። ይሄ ደግሞ በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ታሪክና እድገት ውስጥ ተኪ የሌለው አብርክቶውን ያሳያል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የመረጃ ምንጭ፣ የታሪክ ሰነድ፣ የሥነጽሑፍ እድገት መሰረት ብቻ ሳይሆን፤ በሚያስተናግዳቸው ይዘቶች ትውልድን በአመለካከት፣ በእውቀትና ሞራላዊ ሥነምግባት ማነጽ የቻለም ነበር። ለዚህም ኢትዮጵያውያን እንደየእድሜ ደረጃቸውና እንደ ማህበራዊ መሰረታቸው (ለልጆች፣ ለወጣቶች፣ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣…) የተለያዩ አምዶችን በመክፈት የየፍላጎታቸውን እንዲያገኙ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። የንባብ ባህልን ከማሳደግ አኳያም የተጫወተውና እየተጫወተ ያለው ሚናም የሚዘነጋ አይሆንም።
ከዚህ በተጓዳኝ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሕዝብን ስሜትና ፍላጎት ከአገራዊ ፋይዳው አንጻር የሚዳስስባቸው፤ ለዚህ እንቅፋትና ፈተና የሆኑ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን ነቅሶ የሚያወጣባቸው፤ አጥፊዎች እንዲጠየቁ፣ መልካም ያደረጉም እንዲመሰገኑ ግብራቸውን የሚገልጥባቸው አምዶችን በማዘጋጀትም አንቱ ያስባሉትን ተግባራት ፈጽሟል። በዚህም የተወላገደው እንዲቀና፣ የተበላሸው ተፈትሾ እንዲታረም፣ በግፍ የፈሰሱ እንባዎች እንዲታበሱ፣ አጥፊዎችም በሕግ እንዲዳኙና የሕዝቦች ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ በማድረግም በዘመናት ጉዞው ውስጥ የሚታወስባቸውን ተግባራት ፈጽሟል።
ዛሬም ቢሆን አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሚገለጥባቸው የሕትመት ውጤቶቹ ተኪ የሌለው አበርክቶ ያለው ነው፤ ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ ከፍ ወዳለው የልዕልናቸው ማማ እንዲራመዱ በማድረጉ ሂደት ከፍ ባለ ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል። በተለይም ለአገርና ሕዝብ ሰላም፣ አንድነት፣ እኩልነትና መከባበር እውን መሆን በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሊተገበሩ የሚገባቸውን ተግባራት በልካቸው ተገንዝቦ እየተወጣ ያለ፤ ተገቢ የመረጃ እና የሃሳብ መለዋወጫ መድረክ ሆኖም እያገለገለ ያለ ነው።
ይሄ ተግባሩ ተግሞ ጋዜጣው (በንጉሡ ዘመንም፣ በደርግ ሥርዓትም፣ በኢህአዴግ የአገዛዝ ወቅትም ሆነ ዛሬ ከለውጡ ማግስት ባለው አውድ ውስጥ) ሳይዋዥቅ የቀጠለ፤ ስለ አገርና ሕዝብ ተግተው በሚሰሩ የተቋሙ ብሎም የጋዜጣው አመራሮችና ባለሙያዎች ብርቱ ጥረት ውስጥ የሚገለጽ ነው። ምክንያቱም አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደ ስሙ ሁሉ በየዘመኑ አዲስ እና የማይሰለች ሆኖ ለመቀጠሉ፤ በሕዝብ ዘንድ አስተማማኝና ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ስለመዝለቁ፤ ያልተዛቡ የታሪክ ክስተቶችን እየሰነደ ለመራመዱ፤ የሕዝብ ልሳንና ጆሮ ሆኖ ለማገልገሉ እነዚህ አመራሮችና ባለሙያዎች በየዘመናቱ ዋጋ እየከፈሉ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ አልፈዋልና ነው።
ዛሬም ከ82 ዓመት ልደቱ ማግስት በሚኖረው ያልተቆራረጠ ብቻ ሳይሆን በየዘመኑ እየታደሰ የሚራመደው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጉዞ፤ እንደ ትናንቱ ሁሉ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭነቱ፣ የሕዝብ እንባ አባሽነቱ፣ የሃሳብ መለዋወጫ አውድነቱ፣ የታሪክ ሰነድነቱ ተጠብቆ፤ ከፍ ያለ አገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየተጋ ይገኛል፡፡ ለዚህም የ82 ዓመታት የጉዞ ልምዱን ቀምሮ፣ ከዘመኑ የተጣጣሙ አሰራሮችን ነድፎ፣ ከአቻ የሕትመት ውጤቶች አሰራሮችን ተመልክቶ ሁሉን አቀፍ ተራማጅነቱን የሚያረጋግጥበትን አሰራር በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ እንዲሆንም ከውስጥም አሰራሩን፤ ከውጭም ተደራሽነትና ሕዝባዊ ተቀባይነቱን በየጊዜው እየፈተሸ ዘመናዊነትን እየተላበሰ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ተቋም የተያዙ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ከፍ ያለ ውጤት እየታየባቸው መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ቢሆኑም፤ እነዚህን መልካም ጅምሮች አልቆና መሰረታቸውን አስፍቶ ከመሄድ አኳያ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያለውን አቅም በእጅጉ መጠቀም አሁንም እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ይሄ ሲሆን አዲስ ዘመን ጋዜጣ በቀጣይ ዘመናትም እንደ ስሙ አዲስነትን እና አስተማማኝ የመረጃ ምንጭነቱን አስጠብቆ መጓዝ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የለውጥ ጉዞ አሳላጭነት ተልዕኮ መወጣት ያስችለዋል፡፡
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2015