ሰብዓዊነት የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ አጀንዳ ነው። ከዚህ የተነሳም የሰው ልጆች መንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች በአንድም ይሁን በሌላ ለሰብዓዊነትና ለሰብዓዊ እሴቶች የተገዙ ናቸው ።
በተለይም መንፈሳዊ እሴቶቹ ሰብዓዊ እሴቶች ላይ መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው፤ የሰብዓዊነት ጉዳይ ሁሌም ቢሆን የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ጉዳይ ስለመሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ለዚህም ዘር፣ ሃይማኖት፣ የቆዳ ቀለም ወዘተ የሚፈጥሩት ትርጉም ያለው ለውጥ የለም።
በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት መስተጋብር ውስጥ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች የሰብዓዊ መብቶችን በማክበርና በማስከበር ረገድ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶች ይኖራሉ፤ እነዚህ ክፍተቶች በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ናቸው።
አሁን ላይ ራሷን የሰብዓዊ መብት ቀዳሚ ተቆርቋሪ አድርጋ ከምታስበው አሜሪካ ጀምሮ ሰለጠነ በሚባለው ዓለም በግልጽም ይሁን በስውር የሚደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ስንመለከት ችግሩ ዓለም አቀፍ ይዘት እየተላበሰ ስለመምጣቱ አስረጅ የሚያስፈልገው አይሆንም።
ከሁሉም በላይ አንዱ ከሳሽ ሌላው ተከሳሽ ሆኖ ለሕሊና፤ ለሞራል ፍርድም ሆነ ለውግዘት የሚዳረግበት ተጨባጭ እውነታ ሊኖር አይችልም፤ በተለይም ካለንበት ዘመን ዓለም አቀፍ የሴራ፤ የራስ ወዳድነትና የጽንፍ ፖለቲካ አንጻር እውነታው አዲስ ዕይታ የሚፈልግ ነው።
የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ሰብዓዊ አጀንዳ መሆኑ እየቀረ፤ ለዘመኑ ፖለቲካ ስትራቴጂክ አቅም መግዣ እየሆነ ባለበት ሁኔታ፤ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የተቋቋሙ ዓለም አቀፍ ተቋማትንም ሆነ፤ ተቋማቱ የሚያወጧቸውን የተዛቡ ሪፖርቶች መነሻ ምክንያት በአግባቡ መቃኘት ተገቢ ነው።
ግለሰቦች ሳይሆኑ ሃገራት እንደሃገር እየፈረሱ ሕዝቦቻቸው ከፍ ላሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሲዳረጉ፤ ሃገር ከማፍረስ በስተጀርባ ያሉ ኃይሎች በአደባባይ በየሀገራቱ ስለሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አፋቸውን ሞልተው ሲያወሩ ሃይ ለማለት ድፍረት የሚያጡ ተቋማት በየወቅቱ የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ፋይዳ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመትም የሚከብድ አይሆንም።
በተለይም እነዚህ ተቋማት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስም የሚያወጧቸው ሪፖርቶች፤ በሕዝቦች መካከል ያሉ ዘመናትን ያስቆጠሩ ተቻችሎና ተባብሮ የመኖር እሴቶችን የሚጎዱና ሕዝቦችን ወደግጭት የሚያመሩ እየሆኑ የመምጣታቸው እውነታ ብዝኃነት ውበታቸው ሆኖ ለኖሩ ሕዝቦች አዲስ የስጋት ምንጭ በመሆን ላይ ነው።
ለዚህ ደግሞ እ.ኤ.አ. ጁን 1 ቀን 2023 (ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም) ሂዩማን ራይትስ ዎች ያወጣው ሪፖርት ተጨባጭ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው። ሪፖርቱ በተለመደው መንገድ በሃገራችን የተወሰነ አካባቢ ጉልህ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል ይላል።
እንደሚታወቀው፤ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የነበረው ግጭት በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጉዳት ያደረሰና ይሄም ለመላው ዓለም የተገለጸ የአደባባይ ሚስጥር ነው። እውነታው ደግሞ ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተደበቀ አይደለም ።
ድርጅቱ ይህንን የአደባባይ እውነታ እንዳላየና እንዳልሰማ በመሆን የተወሰነ አካባቢን መርጦ በልዩ ሁኔታ ደጋግሞ ሪፖርት በማዘጋጀት በሰብዓዊ መብት አጀንዳ ሽፋን በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮውን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
የሰሞኑ ሪፖርቱ ከሁሉም በላይ፣ ለዘመናት አብረው የቆዩ ሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚያጠለሽ፣ ግጭት ቀስቃሽ የሆነና ሀገራችን እያደረገች ያለውን የእርቅ እና ምክክር ሂደት ለማደናቀፍ የሚጥር፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሀገሪቱ ስላለው ተጨባጭ እውነታ የተዛባ ዕይታ እንዲኖረው ለማድረግ የሚሞክር ነው።
መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሞ የማይታገስ ስለመሆኑ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ግጭት ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት እንዲያጣሩ አስፈላጊውን ሁኔታ በማመቻቸት በተግባር አሳይቷል።
የተቋማቱ የጋራ ሪፖርት ሲወጣም በሪፖርቱ የተሰጡ ምክረ-ሃሳቦችን ለመተግበር የሚኒስትሮች ጥምር ግብረ-ኃይል በማቋቋም ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም፣ ተፈጸሙ የተባሉ የመብቶች ጥሰቶች ምርመራ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።
ከዚህ በተጨማሪም በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል የነበረውን ግጭት ለማቆም በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማስፈጸም ብሎም በሀገራችን የሚታዩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮችን በማዘጋጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ ወገኖች ላይ ተገቢው ማጣራትን በማድረግ ተጠያቂነትን ማስፈንን ጨምሮ እውነትን የማፈላለግ እና ተጎጂዎችንም መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ማዕቀፍ እንደሚፈጥር ይታመናል።
ይህ እንደ ሃገር እየተከናወነ ባለበት ሁኔታ ሂዩማን ራይትስ ዎች አንድ አካባቢን ታሳቢ በማድረግ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው የተዛቡ፤ በተጨባጭ መረጃ ያልተደገፉ ሪፖርቶች፤ ድርጅቱ የቱን በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ በመግባት የችግር ምንጭ ለመሆን እያደረገ ያለውን ያልተገባ እንቅስቃሴ አመላካች ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2015