የህፃን ልጇም ሆነ የእሷ ልብስ ሁሌም የፀዳ ነው። እናትና ልጅ በመልክ ብስል ይሉት ቀይ ናቸው። ሁለቱንም አስተውሎ ላያቸው የፊታቸው ገጽታ በሰም እንደተቀባ ወለል ያንፃባርቃል፡፡ ውብ መልክና ቁመና ይዘው ካልታሰበ ቦታ መገኘታቸው ሁሉንም ያስደነግጣል፡፡ ሁለመናቸው አበባ ቢመስልም የዕጣ ፋንታ ነገር ከማይሆን ቦታ ጥሏቸዋል፡፡
ቅዳሜና እሁድ ሙሉ ቀን፤ ከሰኞ እስከ ዓርብ ደግሞ ከዘጠኝና ከአስር ሰዓት በኋላ አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አጥር ስር በአሳዛኝ ሁኔታ ተኝተው ሲለምኑ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል፡፡
ብዙ ጊዜ ህፃን ልጇ የትምህርት ቤት ዩኒፎርሙን እንደለበሰ ጋቢ ተከናንባ መሬት በምትተኛው እናቱ ላይ ጋደም እንዳለ እንቅልፍ ወስዶት ሲታይ ይበልጥ የአላፊ አግዳሚውን አንጀት ይበላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ያያቸው ማንም መንገደኛ ስለነሱ ምንም ሳይነግረው የቻለውን እየመፀወተ ያልፋል፡፡ እነሱን የሚያዩ አብዛኞች በሀዘኔታ ከንፈራቸውን እየመጠጡ፣ ራሳቸውን እየነቀነቁ ያልፋሉ። ሁኔታቸውን ልብ ብሎ ላጤነ የእናትና ልጁ ገጽታ ከማሳዘን አልፎ የማማሩን እውነት ይረዳል፡፡ ይህኔ ‹‹መልክ ገንዘብ አይሆን አይበላ›› ማለቱ አይቀርም፡፡
እርግጥ ነው እናትና ልጁ ውብ ናቸው፡፡ ልብሳቸውም ለልመና የወጣ ሰው አይነት አይደለም። ፀአዳና ንጹህ ነው፡፡ እናም ‹‹ለምን ጎዳና ላይ ወጥተው ልመናን መረጡ ? የሚለው የበርካታ ሰዎች ጥያቄ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡
መቼም አንዲት እናት ፈጣሪ ጤና ከሰጣት ልጇን ሰርታ ማሳደግ ምርጫዋ ይሆናል፡፡ አካሏ ጎድሎ መስራት የሚያስችላት ጤናማ ሁኔታ ላይ ካልሆነች ግን ለልጇ ስትል የማትከፍለው መስዋዕትነት አይኖርም፡፡ የዚች ወጣት እናትም ሁኔታ ይህንኑ እውነታ ያሳያል። ጤናዋ በፍፁም ሰርቶ ልጅ ማሳደግና ማስተማር የሚያስችላት አይነት አይደለም፡፡
ይህች እናት ድህነት ከሴትነት ተዳምሮ ጫናው በርትቶባታል፡፡ የዕለት ጉርስ የሚሆን ቁራሽ ማግኘት አልቻለችም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የዕድሜ አለመብሰል ሲታከልበት የሕይወት አቅጣጫዋን አስቶ ከህይወት ፈተና ጥሏታል፡፡
ከሃያ ዓመቷ ወጣት ፍሬህይወት አድማሱ /ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስሟ የተቀየረ/ ጋር የተገጣጠመውም ዕጣ ፈንታ እንዲህ ያለው እንደሆነ እራሷ ባለ ታሪኳ በምሬት ትናገራለች፡፡ ወጣት ፍሬህይወት ውልደትና ዕድገቷ በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ከተማ ‹‹አጅባር›› ከተሰኘ አካባቢ ነው፡፡ ለቤተሰቦቿ አምስተኛና ብቸኛዋ ሴት ልጅ ስትሆን አራት ታላላቅ ወንድሞች አሏት፡፡
ስለ አባቷ ማንነትና ታሪክ የምታውቀውም ሆነ ከእናቷ የሰማችው ባይኖርም እናቷ የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸው ምስኪን ደሀ መሆናቸውን ትናገራች፡፡ እናት አምስት ቤተሰብ ቀርቶ ራሳቸውንም የሚያኖር አንዳች ገቢ የሌላቸው እንደሆኑ ስታወሳ እንባዋን ማዘዝ መቆጣጠር ይሳናታል፡፡
ወንድሞቿ እና እሷ ብዙ የሚባል የዕድሜ ልዩነት የላቸውም፡፡ ምን አልባት እናት በላይ በላዩ ሳይወልዷቸው አልቀሩም፡፡ ይህ አይነቱ እውነት ረዳትና አጋዥ እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ ወይዘሮዋ ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ በተፈለጉበት ስፍራ ሁሉ ጉልበት ከፍለው፣ በየሰው ቤት ሰርተው ነው፡፡
እናት ሌት ተቀን በሥራ ይባዝናሉ፡፡ የጉልበት ስራ የሚባል አይቀራቸውም፡፡ እንዲሁም በስራው አምሽተው ሲገቡ ለልጆቻቸው ራት፣ ቁርስና ምሳ ማዘጋጀት ግድ ይላቸዋል፡፡ ሲነጋ ደግሞ ማልደው ወደተለመደው ውሏቸው ይበራሉ፡፡
ፍሬህይወት እድሜዋ ከፍ እያለ ሲመጣ የእናቷን ድካም ተረድታ ለማገዝ ሞክራለች፡፡ ትምህርቷን ትታ እናቷ ለመደገፍ ጥራለች፡፡ ‹‹እናቴ ልብስ ስታጥብ አብሪያት አጥብ ነበር፡፡ እንጀራ ስትጋገርም እየጋገርኩ ድካሟን ላቀልላት እጥራለሁ›› ትላለች ወጣት ፍሬህይወት እናቷን ለመርዳት የነበራትን ጥረት ስታስታውስ፡፡
ይህ የኑሮ ልምድ ግን እንደነበረው አልቀጠለም፡፡ አዲስ አበባ ሀብታም የሚባሉ ዘመዶች ባሏት አንዲት ጓደኛዋ ሰበብ የህይወት አቅጣጫዋ ሊቀየር ግድ ሆነ። ባልንጀራዋ ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ ቢሄዱ በተሻለ ሥራ እናቷን እንደምትለውጥ ስትነግራት ፍሬህይወት አላንገራገረችም። ሀሳቧን በሙሉ ዕምነት ተቀብላ ለመንገዷ ጓዟን ሸከፈች፡፡
ፍሬ ህይወት እናቷን ከድህነት የማውጣት ቢቻላትም ታላላቅ ወንድሞቿን የማስተማር ህልም አላት፡፡ ይህን ዕቅድ በልቧ ሰንቃለች፡፡ አሁን ሀሳቧ ዕውን እንዲሆን ከጓኛዋ ጋር ጉዞ ጀምራለች፡፡ የትራንስፖርት ችላ ካገሯ ያወጣቻት አብሮ አደጓ አዲስ አበባ ሲደርሱ ካሰበችው ደርሳ ከደላላ አገናኘቻት፡፡ ደላላው ሰው ቤት በሰራተኝነት ሲያስቀጥራት አልዘገየም፡፡
የተቀጠረችበት ቦታ ካዛንቺስ አካባቢ ከሚገኝ መኖሪያ ነበር፡፡ ቤቱ ፎቅ እንደነበር ትዝ ይላታል፡፡ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በዚህ ቤት በሰራተኝነት ስትቀጠር የአስራ ሁለት ዓመት ታዳጊ ነበረች፡፡ ቀጣሪዎቿ ባልና ሚስት ሁለቱም ስራ ውለው ማታ ወደቤታቸው ይመለሳሉ። ሦስት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጅ አለቻቸው፡፡ ከወንዶቹ ልጆች ትልቁ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አይኑን ጣል አድርጎ ያያታል። ሁሌ ቢያተኩርባትም እሷ ቀና ብላም አታየውም።
አጋጣሚ ቀና ካለች ግን ዓይኑን ሳይሰብር እንደሚያያት ታዝባለች፡፡ በወቅቱ ልጅነት ፤ እፍረትና ድንጋጤ ተደራርበውባት ነበርና ምክንያቱን ለመጠየቅ አልደፈረችም። ብዙን ጊዜ የልጁን ዕይታ አንገቷን ደፍታ፣ በፍርሃት ታሳልፈዋለች። ልጁ ግን በዚህ ብቻ አላቆመም። ወላጆቹ ሥራ ሲሄዱና እህት ወንድሞቹ ሳይኖሩ አጋጣሚውን ይጠቀማል፡፡ ምግብ የምታበስልበት ማዕድ ቤት ድረስ እየመጣ ያያታል፡፡
ሁኔታው ሁልጊዜ ግራ ያጋባታል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከልጁ ጋር አንዳች ዓይነት ንግግር አልነበራቸው፡፡ ‹‹ምን ፈልገህ ነው እኔ ዘንድ የምትመጣው?›› ብላም ጠይቃው አታውቅም። በዚህ ሁኔታ ዓመታት አለፉ፡፡ ከእሱ በቀር የቤቱ ብቸኛዋ ሴት ልጅና ሁለቱ ወንዶች እንዲሁም ወላጆቻቸው በብዙ ነገር ቁጥብ ነበሩ፡፡ ከእርሷ ጋር ቀርቶ እርስ በእርሳቸውም ሲጫወቱ አይታይም፡፡
ፍሬህይወት አብዛኛውን ጊዜ ልብስ ካጠበች፤ ቤት ካፀዳችና ምግብ ካበሰለች በኋላ ከማዕድ ቤት አትወጣም። እንደ አብዛኞቹ የቤት ሰራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጋር እየተሳሳቁ ቴሌቪዥን ማየት ቀርቶ ያበሰለችውን ምግብ ደፍራ አታቀርብም፡፡ ቤተሰቡ የሚመገብ፣ የሚስተናገደው በሴቷ ልጅ አማካኝነት ነበር፡፡
ቡናም ቢሆን ተቀምጣ አታፈላም፡፡ ከሰል አቀጣጥላ ካቀራረበች በኋላ እናትዬዋ ያፈላሉ፡፡ እሷ በየምትጠራው የተበላበትና የተጠጣበትን እቃ ለማንሳትና ለማጠብ ነው። በዚህ ሁኔታ ከቤተሰቡ ጋር አንድ ዓመት ከሦስት ወር አሳለፈች፡፡ አሰሪዎቿ ግን የወር ደሞዝ ከፍለዋት አያውቁም። እሷም ብትሆን ፍፁም ጠይቃቸው አታውቅም።
ከቀናት በአንዱ ሁሌም በአትኩሮት የሚያያት ትልቁ ልጅ በቤቱ ማንም ያለመኖሩን ያረጋግጣል፡፡ እንደ ልማዱ ወደ ማዕድ ቤት ይመጣና ጥቂት ሲመለከታት ይቆያል፡፡ ምግብ እየሰራች፣ በስራ እየተጣደፈች ነው። ሳታየው ከኋላዋ ይደርስና እንዳትጮህ ያፍናታል። አንገቷን አንቆም አስገድዶ ይደፍራታል። ጎረምሳው ያሻውን ከፈፀመ በኋላ ከወደቀችበት ጥሏት ከቤት ወጥቶ ይሄዳል፡፡
ደፋሪዋ ድርጊቱን ፈፅሞ ጥሏት ሲሄድ የተናገረውን አትረሳም። ድርጊቱን ለወላጆቹም ሆነ ለእህት ወንድሞቹ ትንፍሽ ብትል እንደሚገላት ዝቶባታል፡፡ ጆሮዋ ይህን ቃል ስቃይ በተሞላበት ህመም ውስጥ ሆና አድምጧል። ኃይል የተሞላበት የጎረምሳ ጉልበቱ አቅሟን አዳክሞ፣ ያልፀና ሰውነቷን ጎድቶ ነበርና ከወደቀችበት ልትነሳ ብትሞክርም አልቻለችም፡፡
ከወደቀችበት ሳትነሳ ለአራት ሰዓታት ከመሬት ወድቃ ቆየች። ልብሷ በደም ተነክሮ በወደቀችበት እንቅልፍ ወሰዳት። ስትነቃ ግን ነገሩ ህልም ነው የመሰላት። የተፈጠረውን ነገር ማመን አቃታት። ትንሽ አሰበች፡፡ አሰሪዎቿና ልጆቹ የመምጫቸው ሰዓት መቃረቡ ትውስ አላት፡፡ እነርሱ ሳይደርሱ እንደምን ራሷን አጠንክራ መነሳት አለባት፡፡ ጥርሷን ነክሳ ተነሳች ገላዋን ታጠበች። ልብሷን አጸዳች።
ህመሙ ቢፀናባትም አመመኝ ብላ አልተኛችም ምንም እንዳልተፈጠረ ራሷን አረጋግታ የተለመደ ሥራዋን ቀጠለች። ድርጊቱ ተሸፋፍኖ ለአራት ወራት ዘለቀ። ውሎ አድሮ ግን ሆዷ እየገፋ፣ ሰውነቷ ይለወጥ ያዘ፡፡ አሰሪዋ የሰጠቻት ሰፋፊና ረጃጅም ቀሚስም ሆዷን መደበቅ አቃታው፡፡ አምስተኛ ወር ሲቃረብ የሆዷ መጠን እየጨመረ መጣ፡፡
ደግነቱ አብዛኛውን ጊዜ አሰሪዎቿ ቤት ሲኖሩ እሷ ከማዕድ ቤት አለመውጣቷ የሆዷን መግፋት ለመደበቅ ጠቅሟታል፡፡ ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ነገር አይታ ስለማታውቅ እርግዝናው ውፍረት መስሏት ነበር፡፡ በሂደት ግን ስሜቱም ድካሙም እየተጫጫናት ጭራሽ አላሰራት አለ፡፡ ፍሬህይወት ግራ አጋቢውን ጉዳይ ማወቅ ፈልጋለች። ደርሶ የሚረብሽ የሚያስጨንቃትን ስሜት እያሳሰባት ነው፡፡ አንድቀን አሰሪዎቿ ሥራ ሲሄዱ ጠብቃ በአቅራቢያው አለ ሲባል ከሰማችው ጤና ጣቢያ አቀናች፡፡ የአምስት ወር ተኩል ነፍሰ ጡር መሆኗ ተነገራት፡፡
‹‹የአሰሪዎቼ ጎረምሳ ልጅ ከደፈረኝ በኋላ ወደ ማዕድ ቤት ሊመጣ ቀርቶ የት እንደገባ አይቼውም አላውቅም›› የምትለው ፍሬህይወት፤ የማርገዟን እውነት ከጤና ጣቢያው እንደሰማች ብርክና ድንጋጤ ያዛት፡፡ ተመልሳ አሰሪዎቿ ቤት ለመግባት ፈራች። ልብሷን ለመውሰድ እንኳን ሳትደፍር እንደወጣች ቀረች፡፡
የት እንደምትሄድ ባታውቅም ቀኑን ሙሉ እያለቀሰች ስትጓዝ ውላ አመሻሹን ሽሮ ሜዳ አካባቢ ራሷን አገኘችው። ሁኔታዋን የተመለከቱ አንዲት ሴት አዝነው ቤታቸው አሳደሯት፡፡ የተወሰነ ቀንም ከእሳቸው ጋር ቆየች። ሴትዬዋ ደሃ ናቸው፡፡ እሷን ተንከባክበው ማኖር ማሳደር አይችሉም፡፡ ቀኗ እስኪደርስ ድረስ ሰርታ የዕለት ጉርሷን እንድትችል መከሯት፡፡ ጎንበስ ቀና እያለች ልብስ ማጠብ የጉልበት ሥራ በመስራት ያዘች፡፡ ሁለት ወራት በዚህ መልክ አለፉ፡፡
‹‹ከጉልበተኛው ጎረምሳ የተረገዘው ልጅ እንደምንም ዘጠኝ ወር ሞልቶት ተወለደ›› ትላለች ወጣት ፍሬህይወት በትካዜ ግዜውን እያስታወሰች፡፡ ሆኖም ልጁን የወለደችው እንዲህ በቀላሉ አልነበረም፡፡ የወለደችው ሽሮ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ሲሆን ለሰባት ጊዜ ቀዶ ህክምና እንደተደረጎላት ታስረዳለች፡፡
በወቅቱ የአራስ ወግ አላየችም ‹‹እንኳን ማርያም ማረችሽ ››አልተባለችም፡፡ ጠያቂ ወዳጅ ዘመድ አጥታ ለሶስት ወራት በሆስፒታሉ ተኝታ በበረታ ስቃይና ህመም ማሳለፏን አትረሳም፡፡
ፍሬህይወት የታዳጊነት ጉልበቷ ሳይጠና ተደፍሮ ማርገዝ ዛሬን ስቃይ ውስጥ እንደከተታት አሁን ያለችበትን ሁኔታ ያሳያል፡፡ ከመውለዷ ባለፈ ሃያ ዓመታት በበሽታ ውስጥ ሆና ጎንበስ ቀና ብላ እንዳትሰራ ሆናለች። ‹‹ሆዴ ሰባት ጊዜ እዚህም እዛም እየተቀደደ በመሄዱ ጎንበስ ቀና ብዬ ሥራ መሥራት አልችልም። ከባድ ዕቃ ማንሳትም አይታሰብም። መቀመጥ እንኳን አይሆንልኝም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ተኝቼ የማሳልፈውም ለዚህ ነው›› ትላለች መልከኛዋ፣ ዓይነግቡዋ የልጅ እናት ወጣት ፍሬህይወት፡፡
ባትድንም ከሆስፒታል በቃሽ ተብላ ስትወጣ ምርጫዋ ህፃን ልጇን ይዛ በረንዳ መውደቅ ነበረ፡፡ ልጇ ሁለት ዓመት እስኪሞላው ከአንዱ በረንዳ አንዱ በረንዳ እየተዘዋወረች አሳደገችው፡፡ በዚህ መሃል ሽሮ ሜዳ አካባቢ የምትኖር አንዲት ወጣት ሴት ተዋወቀች፡፡ ጓኛም ሆኑ፡፡ ወጣቷ ራርታ አስጠግታት ልጇን ለማሳደግና ትምህርት ቤት ለማስገባት ችላለች፡፡
ሆኖም መሥራት ባለመቻሏ ላስጠጋቻት ወጣት ሴት ለምና ያገኘችውን ሳንቲም ስትሰጣት እንደነበር ትናገራለች። ‹‹ይህቺ ሴት ካስጠጋችኝ በኋላ ልጄን ትምህርት ቤት በማስገባቴ አሁን ኬ ጂ ሁለት ደርሶልኛል፡፡ ምግብም እዛው ትምህርት ቤት ስለሚመገብ ሃሳብ አይገባኝም፡፡ ዩኒፎርምም ያለበሰው ትምህርት ቤቱ ነው፡፡ በመጪው ነሐሴ ወር ስድስት ዓመቱን ይይዝልኛል›› ትላለች፡፡
በደባልነት አብራት እንድትኖር በመፍቀድ አስጠግታት የነበረችው ወጣት ቤቷ በመፍረሱ ፍሬህይወት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማደሪያ በማጣት ከህፃን ልጇ ጋር ጎዳና ላይ ለመውጣት ተገድዳለች።
‹‹ልጄን በአባቴ ስም ነው የማስጠራው›› የምትለው ወጣት ፍሬህይወት፤ የደፈራትን ወጣት ፈልጋ አባትህ ይሄ ነው ለማለት እንደማትፈልግና ልፈልግ ብትልም ቦታውን ማስታወስ እንደተሳናት ታስረዳለች፡፡ በጊዜው እውቀቱም ስላልነበራት ለመክሰስ እንዳልቻለች ትግልፃላች፡፡ ስለዚህም ስቃዩዋን ይዛ የተፈጠረውን ነገር በውስጧ ይዛ እህህህ! ብላ ትኖራለች፡፡
‹‹ልጄ ትምህርቱን ሳያቋርጥ እንዲማርልኝ እፈልጋለሁ። መጠለያ ባገኝም ደስ ይለኛል›› የምትለው ወጣት ፍሬህይወት፤ አግዙኝ የሚል ጥሪ ታስተላልፋለች፡፡ እኛም ይህን ፅሁፍ የተመለከቱ ሁሉ ወጣት ፍሬህይወትን ለመርዳት ምላሻቸው ፈጣን እንደሚሆን እንገምታለን፡፡ በየሰዉ ቤት ተቀጥረው ሲሰሩ በአሰሪ ልጆች፤ አባወራዎችና በተለያዩ የቤተሰብ አባላት በመደፈራቸው ዕጣ ፈንታችው እንደ ወጣት ፍሬህይወት የሆኑ ወጣቶች በርካታ ናቸውና ጩኸታቸው ሊሰማ፣ እምባቸው ሊታበስና ከልመና የሚወጡበት መንገድ ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015