የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በትውልድ አካባቢዋ የቀድሞው ባሌ ክፍለ አገር፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ አዲስ አበባ አቃቂ አድቬንቲስት አዳሪ ትምህርት ቤት ተከታትላለች። የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን ባጠናቀቀች ማግስት ስደት አጓጉዞ ከባህር ማዶ ከሆላንድ አገር አደረሳት። በባዕድ አገር የብቸኝነት ኑሮ በሕይወት ትግል ውስጥ ብዙ ተምራለች። ከስደት ሕይወት የቀሰመችውን ትምህርት፣ በመውጣት በመውረድ ውስጥ ያካበተችውን ልምድና ተሞክሮ ቀምራ ረጅሙን ጉዞ በአገሯ ለማድረግ ሌት ተቀን ተግታለች።
ከላይ ታች የመውጣት የመውረዷ ትጋትና ጥድፊያዋ ሁሉ አገሯ ገብታ አዳዲስ ሥራዎችን ለመሥራትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደነበር ታስታውሳለች። አገሯ ገብታ ሰርታ ለማሰራት በነበራት ጥድፊያና ጉጉትም ብዙ ደንቃራዎች ገጥመዋት ሁሉንም በጽናት አልፋለች። ከስደት ለመመለስ በተሰናዳችበት ወቅት ‹‹አገሬ ጎደሎዋ ምንድን ነው?›› በማለት ራሷን ጠይቃለች። ለጥያቄዋ ምላሽ ብዙ ጎዶሎዎችን መመልከት ብትችልም ‹‹ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፤ ለሃምሳ ሰው ጌጡ›› እንዲሉ፤ እርሷ በአቅሟ የምትችለውን ለማድረግ መውተርተር ጀመረች። የዕለቱ የስኬት አምድ እንግዳችን ወይዘሮ እመቤት ታደሰ።
ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ስደት ደህና ሰንብት በማለት ከሆላንድ ወደ ትውልድ አገሯ ኢትዮጵያ ተመልሳለች። የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን ባጠናቀቀች ማግስት ስደት የወጣችው ወይዘሮ እመቤት፤ በውጭው ዓለም ስትኖር ሕይወት ብዙ እንዳስተማረቻት ትናገራለች። በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ብዙ ያሳለፈች ቢሆንም፣ ‹‹እችላለሁ›› የሚል ጠንካራ እምነት የነበራት በመሆኑ ያሰበችውን ሁሉ በከፍተኛ ጥረትና ትጋት ማሳካት ችላለች። ‹‹ምንም ሳይኖረኝ በሆላንድ አገር ሬስቶራንት ለመክፈት አቅጄ ከፍቻለሁ›› የምትለው ወይዘሮ እመቤት፤ ወደ ትውልድ አገሯ በተመለሰች ጊዜም በተለያዩ የሥራ ዘርፎችን ለመሥራት ስትሞክር ‹‹ተይ አይሆንልሽም›› በማለት ወደ ኋላ የሚጎትቷት ብዙዎች ነበሩ።
እርሷ ግን ያሰበችውን ሳታሳካ እንቅልፍ የማይወስዳት በመሆኗ፤ አይሆንም የተባለውን እንዲሆን በማድረግ ሁለት ያልተለመዱ የሥራ አማራጮችን ይዛ ብቅ ብላለች። በሆላንድ አገር ስትኖር የምግብ ጥበቃና እንክብካቤ ትምህርትን በዲፕሎማ የተማረችው ወይዘሮ እመቤት፤ በአገረ ሆላንድ የአፍሪካውያን ሬስቶራንት ከፍታ ሠርታለች።
በውጭው ዓለም ማንኛውም ሰው ገንዘብ ስላለው ብቻ ተነስቶ ማንኛውንም ሥራ መሥራት አይችልም። ስለሚሠራው ሥራ ዕውቀት ሊኖረው የግድ ነው የምትለው ወይዘሮ እመቤት፤ የምግብ ጥበቃና ክብካቤ ትምህርት እንደመማሯ የመጀመሪያ የሥራ አማራጭ አድርጋ የጀመረችው ሥራ ፈጣን ምግብ (Fast Food) ማዘጋጀትን ነው።
በወቅቱ ሥራው አገር ውስጥ የተለመደ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ድካም እንደነበረው የምታስታውሰው ወይዘሮ እመቤት፤ በምግብ ዘርፍ ብዙ ክፍተት እንዲሁም ብክነት ስለመኖሩ አጫውታናለች። ሆቴሎች የሚሰጡት አገልግሎት በቂ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ክፍተቶችን ተመልክታለች። በተለይም አትክልትና ፍራፍሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚውለው ይልቅ ተበላሽቶ የሚጣለው ይበልጣል በማለት ቀደም ባለው ጊዜ ፒያሳ የነበረውን አትክልት ተራ በማስታወስ ሰፊ ብክነት እንደነበር ታዝባለች። ይህን መነሻ በማድረግም አትክልቶች ሳይበላሹ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆዩ የማድረግ ሥራ እንደጀመረች ትገልጻለች።
ከሁለት አስርት ዓመታት የውጭ ቆይታ በኋላ ወደ አገሯ ጠቅልላ የመጣችው ወይዘሮ እመቤት፤ የሚታጠብ ዘላቂ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ምርት ለማምረት እንዲሁም የምግብ ሥራን ለመሥራት የወሰነች ቢሆንም አስቀድማ የጀመረችው ግን የምግብ ሥራውን ነው። የምግብ ሥራው አትክልቶች ተልጠው፣ ተከትፈውና ለምግብነት ተዘጋጅተው ረዘም ላለ ጊዜ በማቆየት መጠቀም የሚቻልበት ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ በውጭው ዓለም ተግባራዊ ሲደረግ ከማየት ባለፈ ሥራዋ እንደነበር ያነሳችው ወይዘሮ እመቤት ሥራውን ለመጀመር አላመነታችም።
ድንች፣ ካሮት፣ ፎሶሊያና ሌሎች አትክልቶችም ታጥበው፣ ተልጠውና ተከትፈው ረዘም ላለ ጊዜ በማቆየት ለምግብነት ማዋል በውጭው ዓለም የተለመደ ቢሆንም፤ በአገር ውስጥ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ትንሽ ተፈትናለች። በወቅቱ የነበሩ ጥቂት ሱፐርማርኬቶችም ቢሆኑ በራቸው ክፍት አልነበረም። ይህም ገበያ ውስጥ ለመግባት ብዙ አታግሏታል። ያም ቢሆን ለችፕስ አገልግሎት የሚውለው ድንች ከውጭ የሚገባ እንደሆነ ከእነዚህ ከሱፐርማርኬቶች በሰማች ጊዜ ‹‹ኢትዮጵያ ድንች ለምን ከውጭ ታመጣለች›› የሚል ቁጭት ገብቷታል። ቁጭቷን በሥራ በመወጣት አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ድንችን አዘጋጅታ ለሱፐርማርኬቶች የማቅረብ ሥራዋን አንድ ብላ ጀምራለች።
ከሱፐርማርኬቶች በተጨማሪም ወደ ሸራተን አዲስ እና ሂልተን ሆቴል በመሄድ ድንች በተገቢው እንክብካቤ አዘጋጅታ ለማቅረብ ተስማማች። ድንቹ የሚጨመርበት ምንም አይነት ግብዓት አለመኖሩን ያነሳችው ወይዘሮ እመቤት፤ በሚፈለገው የሙቀት መጠን በስሎና በአግባቡ ታሽጎ ማቀዝቀዣ ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ እንደሚችል ነው ያስረዳችው። በትላልቅ ሆቴሎች የሚቀርቡት የድንች ጥብስ (ችብስ) በዚህ መልኩ የሚዘጋጁና ከውጭ አገር የሚገቡ እንደነበርም አጫውታናለች። “እርግጥ ነው ከውጭ የሚመጣው የድንች አይነት ይለያያል” የምትለው ወይዘሮ እመቤት፤ በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ ያለው የድንች ዝርያም እየተሻሻለ መሄድ የቻለ በመሆኑ ከውጭ የሚገባው የተቀቀለ ድንች እየቀረ መሆኑን ተናግራለች።
ለዚህም አንድ ምክንያት ነኝ የምትለው ወይዘሮ እመቤት፤ ተቀቅሎ ለችፕስ የተዘጋጀ ድንች ሸራተንና ሂልተንን ጨምሮ በተለያዩ ሆቴሎች ተደራሽ እያደረገች እንደሆነም አጫውታናለች። ከድንች በተጨማሪ ሌሎች አትክልቶችንም በአግባቡ አጥቦ፣ ከትፎና አስፈላጊውን ክብካቤ አድርጎ በማቀዝቀዣ ማስቀመጥና ረዘም ላላ ጊዜ መጠቀም እንደሚቻልም ነው የገለጸችው።
ከዚህ በተጨማሪ ሁለተኛ ዕቅዷ የነበረውን የሚታጠብ ሞዴስ ወይም ዘላቂ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርት ለማምረት ከላይ ታች ያለችው ወይዘሮ እመቤት፤ ከብዙ ድካም በኋላ “ማሪዮድ የሚታጠብ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ” በሚል የንግድ ስያሜ ወደ ማምረት መግባቷን ገልጻለች።
ዘላቂ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያን ለማምረት መነሻ ምክንያቶቿ ብዙ ስለመሆናቸው በማንሳት፤ ‹‹የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ/ሞዴስ/ ድህነት ሴት ተማሪዎችን ወደ ኋላ የሚጎትት ነው›› ትላላች። ሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያውን በቀላሉ ማግኘት ባለመቻላቸው ከትምህርት ገበታ ከመቅረት ጀምሮ የተለያዩ ግፍና በደል ይደርስባቸዋል ስትል ገልጻ፤ ይህን ችግር ለመከላከል የሚወስዱት መፍትሔ ደግሞ ወደ ኋላ የሚጎትታቸው ከመሆኑም በላይ ያልተገቡ ግብአቶችን እንዲጠቀሙ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግራለች። ይህም ከፍተኛ ለሆነ የጤና ቀውስ የሚዳርጋቸው መሆኑን በመገንዘብ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቷን ትናገራለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ/ሞዴስ/ ድህነት ስለመኖሩ ያነሳችው ወይዘሮ እመቤት ከስደት መልስ ትኩረት ሰጥታ የሠራችውም በዚሁ ምክንያት ነው ትላለች። ዘላቂ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያን በአገር ውስጥ ለማምረት ስትነሳ ሃሳቡ አዲስና የመጀመሪያ እንደመሆኑ ተቀባይነትን ለማግኘትና ጠቀሜታውን ለማስረዳት ብዙ ታግላለች። በትግሎቿም ወደኋላ ለሚጎትቷት ደንቃራዎች ሳትበገር ውጥኗን ከዳር ለማድረስ ተግታለች። የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደነበረች በማስታወስም ችግሩ አንገብጋቢና ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻው እንደሆነ ትናገራለች።
‹‹የሚታጠብ አልያም ዘላቂ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ላምርት ብዬ ስነሳ ብዙ ሰው ስቆብኛል፤ እንዴት በዚህ ዘመን ስለሚታጠብ ሞዴስ ታወሪያለሽም ተብያለሁ›› የምትለው ወይዘሮ እመቤት፤ ችግሩን ተቸግራ የኖረችበት በመሆኑ ከሃሳቧ አልቀረችም። አስፈላጊውን ሁሉ አሟልታ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረተችውን ዘላቂ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ አስቀድማ ለራሷ ተጠቅማዋለች። በአገልግሎቱ እርካታ ማግኘት እንደቻለች የምታስታውሰው ወይዘሮ እመቤት፤ ወደ ሥራው ከገባች አስራ አራት ዓመታት ቢቆጠርም አሁንም ድረስ ምርቱን ለሁሉም ሴቶች ተደራሽ ማድረግ እንዳልተቻለ ነው ያስረዳችው።
እሷ እንደምትለው፤ ምርቶቹን ለሁሉም ሴቶች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ የማስታወቂያ ሥራ እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ምርቶቹ መንግሥታዊ ባልሆኑ የውጭ አገር ለጋሽ ድርጅቶች አማካኝነት በገጠሪቷ ኢትዮጵያ እየደረሱ ይገኛሉ። የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ /ሞዴስ/ ድህነት በከተሞች ሳይቀር ስር የሰደደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰፊ ሥራ ሊሠራበት ይገባል፤ ምርቱ ተኪ ምርት እንደመሆኑ በአገር ውስጥ በስፋት ቢመረትና ገበያ ውስጥ እንደልብ ቢገባ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ ስለመሆኑም አጽንኦት ሰጥታ ተናግራለች።
በውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት በሚደረገው ጥረት መንግሥትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ ያስገነዘበችው ወይዘሮ እመቤት፤ ምርቱ ለሁለት ዓመታት የሚያገለግል በመሆኑ ለተማሪዎች አይነተኛ መፍትሔ ነው። በተለይም ተማሪዎች በንጽህና መጠበቂያ ምርት እጥረት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይጎድሉ ከማድረግ ባሻገር የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት ረገድም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ትገልጻለች። ለተደራሽነቱ በብርቱ እንትጋ ስትልም ነው ያሳሰበችው።
ስደት ደህና ሰንብት በማለት በሁለት ያልተለመዱ የሥራ ዘርፎች ተሰማርታ እየታገለች ያለችው ወይዘሮ እመቤት፤ በሁለቱም ዘርፎች 70 ለሚደርሱ ዜጎች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች። በቀጣይም ፈጣን ምግቡንም ሆነ ዘላቂ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በስፋት አምርቶ ወደ ገበያው የመግባትና ተጨማሪ የሥራ ዕድል የመፍጠር ሰፊ ዕቅድ አላት።
‹‹ትልቁ ትኩረቴ ዘላቂ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያው ላይ ነው›› የምትለው ወይዘሮ እመቤት፤ በተለይም ‹‹የአካል ጉዳት ያለባቸው ሴቶች ያሳስቡኛል›› ነው የምትለው። ለዚህም አመቺ ነው ያለችውን የንጽህና መጠበቂያ በቀላሉ መጠቀም እንዲችሉ በማድረግ ሰርታለች። ዊልቸር ላይ የዋሉ አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች የማንም እርዳታ ሳያሻቸው በቀላሉ በራሳቸው መጠቀም የሚያስችላቸውን የውስጥ ሱሪና የንጽህና መጠበቂያም አምርታለች። ከዚህ በተጨማሪም ለሆስፒታሎች የሚያገለግል አንሶላን ጨምሮ ሴቶች በሚወልዱበት ወቅት የሚጠቀሙትን እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች አልጋ ላይ ለዋሉ ሰዎች የሚያገለግል የአዋቂዎች ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያም ታመርታለች።
የንጽህና መጠበቂያ ምርቶቹ ኮተን በሆኑ ጨርቆች የሚመረቱ መሆናቸውንም ጠቅሳ፣ ቆዳ ላይ ምንም አይነት የማሳከክ ችግር የማይፈጥር እንደሆነም ነው የገለጸችው። ለዚህም ከጤና ሚኒስቴር የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘት ችላለች። ኮተን ከሆነው ጨርቅ በተጨማሪ እንደ ቁልፍና ውሃ የሚይዘውን ፕላስቲክ ከውጭ በማምጣት የሚመረተው ዘላቂ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ምንም አይነት ኬሚካል የሌለው መሆኑን ጠቅሳ፣ ከውጭ ከሚገባው ይልቅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ስለመሆኑም አስረድታለች።
ምርቱን አጥበው መልሰው መጠቀም የሚችሉት በመሆኑ ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ያስቀራል። ነገር ግን ከውጭ የሚገባው የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ወይም ሞዴስ በየአካባቢው ተጥሎ አካባቢን ሲበክል ይስተዋላል። በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን በመዝጋት ቀዳሚ የሆነው ይኸው የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ መሆኑን ያመላከተቸው ወይዘሮ እመቤት፤ የህጻናት ዳይፐርም ሌላው ችግር እንደሆነ በመጠቆም በአገር ውስጥ ተኪ ምርት ላይ ሰፊ ሥራ ቢሠራ መልካም እንደሆነ ትመክራለች።
የህጻናት ዳይፐርም ሆነ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መጠቀም የሚኖረው አበርክቶ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ በመግለጽ፤ ሴቶች አቅማቸው ፈቅዶ ሞዴስ ቢገዙም በየቦታው የሚጣል በመሆኑ አካባቢን ከመበከል ባለፈ እንስሳት እንዲበሉት ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ጉዳቱ የትየለሌ ነው ስትል ትገልጻለች። ስለዚህ ከውጭ የሚገባውን የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ በአገር ውስጥ በሚመረተውና መልሶ ጥቅም ላይ በሚውለው ምርት በመጠቀም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ እንሁን የምትለው ወይዘሮ እመቤት፤ በተለይም ሁሉም ሴቶች ምርቱን በቀላሉ ገዝተው መጠቀም እንዲችሉ ግንዛቤ በመፍጠር ለማስተዋወቅና ለመጠቀም እንበርታ ብላለች።
‹‹በአገር ውስጥ ያለውን የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ/ሞዴስ/ድህነትን ከማንም በላይ እኔ አውቀዋለሁ›› የምትለው ወይዘሮ እመቤት፤ በተለይም በትምህርት ቤቶችና በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ችግሩ የከፋ እንደሆነ ነው ያነሳችው። ምርቱን በስፋት ገዝተው በገጠራማ አካባቢዎች ተደራሽ የሚያደርጉት የውጭ ድርጅቶች ሲሆኑ፤ በከተሞች አካባቢ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ምርቶቹን በመለገስ ማህበራዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች እንደሆነም አጫውታናለች። በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮችና በጦርነት ምክንያት ጉዳት ላይ ላሉ ሴቶች ምርቱን እያቀረበች መሆኑን በመጥቀስ፤ የሚታጠብ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርት ከውጭ የሚገባውን መተካት የቻለ ተኪ ምርት እንደመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ እንዲውል እንሥራ የሚል መልዕክቷ አስተላልፋለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015