ዓለማችን በከባድ የአየር ንብረት መዛነቅ ተወጣጥራለች፤ ድርቅ እና እርሱን ተከትሎ የሚከሰት ሰደድ እሳት፣ ረሃብና ተያያዥ ችግሮች፤ ከባድ ዝናብ እና ይሄንን ተከትለው የሚከሰቱ ጎርፍ፣ ከባድ ወጀብና የመሬት መንሸራተትን የመሳሰሉ ምስቅልቅሎሾችም ዓለማችንን ዕረፍት ነስተዋታል። ዓለም ግግር በረዶዎቿ እየቀለጡ ወደ ውሃነት፤ ውሃዎቿም ወደ ተንነት እየተለወጡባት፤ አያሌ ወንዞቿ ውሃ ርቋቸዋል፤ ውቅያኖሶቿ ገጽታቸውን ለውጠው፤ ወጀብና አውሎንፋስ ኅብረት ፈጥረው በሱናሚና መሰል አደጋዎች አስጨንቀዋታል።
ባለ ብዙ መገለጫው ይሄ የአየር ንብረት ለውጥ ታዲያ በዋናነት የሰው ልጆች የእጅ ሥራ ውጤት ሲሆን፤ በተለይ የበለጸጉት አገራት ወደከባቢ አየር በሚለቅቁት በካይ ጋዝ ምክንያት የተፈጠረ ስለመሆኑ ዓለም የተስማማበት ሃቅ ነው። እናም ዓለም በሰው ልጆች የተጋረጠባትን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ፈር ከማስያዝ አኳያ ወደከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን ከመቀነስ በተጓዳኝ፤ እነዚህን በካይ ጋዞች መጥጦ ጠቃሚ አየርን የሚያድለውን የደን ልማትን እውን ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መስራት ትልቁ ተግባር ሊሆን እንደሚገባው አቅጣጫ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያም ምንም እንኳን ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር መከሰት ይሄ ነው የሚባል ጉልህ ሚና ባይኖራትም፤ የዚሁ ሰለባ ከሆኑ የዓለም አገራት አንዷ እንደመሆኗ ችግሩን ከመከላከል አኳያ የበኩሏን ለመወጣት የሚያስችላትን ከፍ ያለ ተግባር እያከናወነች ትገኛለች። ለዚህ ደግሞ በአንድ በኩል ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን በመቀነስ ረገድ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን (በተለይ የውሃ፣ የእንፋሎትና የፀሐይ ኃይል ልማትን) አልምቶ የመጠቀም ቁርጠኛ ርምጃ ውስጥ ገብታለች።
በሌላ በኩል በአካባቢ ጥበቃ ስራን በልዩ ትኩረት እየሰራች ትገኛለች። በዚህ ረገድ በተለይ ከ2010ሩ አገራዊ ለውጥ ማግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሃሳብ አመንጪነት ኢትዮጵያን ልምላሜ የማልበስ ዓላማ ተይዞ ላለፉት አራት ዓመታት እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከፍ ያለ ውጤት የተገኘበት ነው።
በዚህ ተግባር ስኬታማ ጉዞ አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ በተሰራበት የመጀመሪያው ዓመት እንደ አገር በአንድ ቀን ከ354 ሚሊዮን ችግኞች በላይ መትከል መቻሉ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለመርሃ ግብሩ መሳካት ያላቸውን ከፍ ያለ መሻት ያረጋገጠ ነበር። በዚህም በአራት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 25 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል።
ይሄ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከመትከል ባለፈ የተተከሉ ችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ማድረግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ የተሰራበት ነው። በዚህም ውጤታማ መሆን የተቻለ ሲሆን፡ ለአብነትም በአራት ዓመታት ውስጥ ከተተከሉት ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ከ85 በመቶ በላይ የጽድቀት ምጣኔ ተመዝግቧል። ይሄም ሥራው ከዘመቻነት ወደ የሕዝብ ባለቤትነት የተሸጋገረ መሆኑን ያሳየ ነው።
በዚህ መልኩ የደን ሽፋንን የማሳደግ፣ የውሃና የአካባቢ ብክለትን የመከላከል፣ የአካባቢ ጥበቃን ሥራን የማጠናከርና ሌሎችም ግቦች ተቀምጦለት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፤ በዋናነት ለደን እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች ላይ ያተኮረ ነው። በሂደቱ የአገር በቀል ዝርያዎች ሰፊ ድርሻ እንዲይዙ ተደርጓል። በመሆኑም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ለደን ሽፋን መጨመር፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለምግብነት፣ ለእንስሳት መኖነት፣ ለገቢ ምንጭነት፣ ለመድሃኒት እና ውበትና መዓዛን የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎቹ ጎልተው የታዩበት ነበር።
ይሄንን ስኬታማ ተግባር ከአገር አልፎ ወደ ጎረቤት አገራት ጭምር የማስፋት ዓላማ ተይዞ የተሰራ ሲሆን፤ በዚህም ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና እስከ ሩዋንዳ ጭምር ችግኞችን ወስዶ መትከል የተቻለበት ዕድልም ተፈጥሯል።
ይሄ የኢትዮጵያ መልካም ጅምር ደግሞ ከአገር አልፎ ለቀጣናው፤ ከቀጣናው አልፎ ለአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት መዛባት ተገቢውን ምላሽ በመስጠት የራሱን ጡብ ያስቀመጠ ሆኗል። ጅምሩም በአህጉር ደረጃ የሚገታ ሳይሆን፤ ዛሬ ላይ ዓለም የተደቀነባትን የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ከመከላከል አኳያ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ እንደመሆኑም ኢትዮጵያ በዘርፉ ላከናወነችው ተግባር ዓለማቀፍ እውቅናን ተችሯታል። የአረንጓዴ አሻራ ተግባር የአንድ ወቅት ተግባር እና እውቅና እስከማግኘት ተጉዞ የሚቆም ተግባር አይደለም። ይልቁንም በኢትዮጵያ በሁለተኛው ምዕራፍ ዘንድሮም ለአምስተኛ ጊዜ ከስድስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ችግኝ በላይ ለመትከል እቅድ የተያዘ ሲሆን፤ እስከ አሁንም ለዚህ ተግባር የሚውሉ ስድስት ቢሊዮን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ ሆነዋል።
የዚህ ዓመት የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም ‹‹ዛሬ ነገን እንትከል››በሚል መርህ ትናንት በአፋር ክልል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በይፋ ተጀምሯል። ይሄም እንደ ቀደሙት ሁሉ ከዕቅዱ ከፍ ያለ አፈጻጸም የሚመዘገብበት ስለመሆኑ የዝግጅት ሥራዎች አመላካች ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያን ልምላሜ የማልበስ ቃል በተግባር እየተገለጠ ያለበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ስኬታማ ጉዞ በላቀ ውጤት ታጅቦ እንዲዘልቅ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2015