ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ አገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብለን ከተደመጥንባቸው እና ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እንደ አንድ ትልቅ ተሞክሮ እየወሰዳቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ነው።
የመረሐ ግብሩ ዋንኛ አላማውም አገሪቱን አረንጓዴ ገጽታ በማላበስ ለዓለም ስጋት እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም አረንጓዴ መልክዐ ምድር መገንባት ቢሆንም፤ እውነታው ግን ከዚህም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት የሆነውን የካርቦን ልቀት ስጋት ለመቀነስ ሊኖረው የሚችለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። የታሪክ መዛግብት እንደሚያመልክቱት፤ አገራችን ቀደም ባሉት ዘመናት በደን ሃብቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ነበረች። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የህዝብ ቁጥር ለእርሻና ለግጦሽ የሚሆን ተጨማሪ መሬት በመጠየቁ የደን ሀብቱ ለከፋ ጭፍጨፋ ተዳርጎባታል። በዚህም አሁን ላይ ለበረሀማነት ተጋላጭነቷ እየጨመረ ስለመምጣቱ በመስኩ ያሉ ምሁራን ይናገራሉ።
አሁናዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ፤ አሁን ላይ ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት በደን የተሸፈነው 15 በመቶ /17 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥም 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ የተፈጥሮ ደን፤ የተቀረው ደግሞ በችግኝ ተከላ የተሸፈ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ በደን ምንጠራ የተራቆተ እና ለደን ልማት ምቹ የሆነ 18 ሚሊዮን ሄክታር ባዶ መሬት አለ። ይህንን ለአገርና ለህዝብ ሁለንተናዊ ስጋት የሆነውን ችግር በዘለቄታው ለመፍታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የክረምቱን መግባት ተከትሎ በሐምሌ 2011 ዓ.ም ተጀምሯል። በወቅቱም አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ አራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችልዋል።
በዚህም ህዝቡ ለአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ የነበረው ግንዛቤ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ በቀጣዮቹ ዓመታት ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል። ለምሳሌ፣ በ2013 ዓ.ም ሰባት ቢሊዮን፤ በ2014 ዓ.ም ስድስት ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል። በአጠቃላይም በመረሀ ግብሩ የመጀመሪያ ምእራፍ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከእቅዱ በላይ 25 ቢሊዮን መትከል ተችሏል።
በ2011 ዓ.ም ሐምሌ ወር በተጀመረውና በውጤት በተጠናቀቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ወቅት በአንድ ቀን 354 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ መስበር፤ በዚህም እንደ ሀገር የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የመነጋገሪያ ርዕስ ለመሆን ችለናል። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ አገር ይዘነው ለተነሳነው የይቻላል መንፈስ ከፍ ያለ የአቅም ምንጭም ሆኖናል።
የአካባቢ የአየር ብክለት ችግር ካለው ዓለም አቀፍ ገጽታ ጋር በተያያዘም፤ ጎረቤት አገራት የፕሮግራሙ አካል እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ፤ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን ወደ ጎረቤት አገራት በመላክ እንዲተከሉ ተደርጓል። መርሃ ግብሩን ወደ ጎረቤት አገራት የማስፋፋቱ ስራ በድንበር አካባቢዎች በግጦሽ መሬት፣ በውሃና በደን ሃብት እጥረት የሚፈጠረውን ግጭት በማስቀረት፤ ስደትንና ከመኖሪያ ቀዬ መፈናቀልን የሚያስቀር እንደሆነ ይታመናል።
መርሃ ግብሩ እንደ አገር በምግብ እህል እራሳችን ለመቻል እያደረግነው ላለው ጥረት እንደ አንድ ትልቅ አቅም የሚወሰድ ሲሆን፣ የውሃ ሃብትንና የብዝሃ ህይወት ጥበቃን በማረጋገጥ ዘላቂ አገራዊ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የግሪን ሀውስ ጋዝን ለመቀነስ እየተደረገ ካለው ጥረት ለዚህ ጥረት ስኬት ኢንቨስት ከሚደረገው ሀብት አገርን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፤ ይህም ለመርሀ ግብሩ ማስፈጸሚያ ለሚያስፈልገው ገንዘብ ተጨማሪ ምንጭ በመሆን ሊያገለግል ይችላል። ከዚህም ባለፈ የከተሞችን ውበት በመጠበቅ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል፤ ለነዋሪዎችም የተሻለ የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍያለ ነው።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው አምራች ኃይል ያለስራ በተቀመጠባት አገራችን፣ መርሀ ግብሩ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር የሚኖረው ጠቀሜታ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ችግኞችን ከማፍላት ጀምሮ በመንከባከብ ሂደት ውስጥ ሰፊ ቁጥር ያለው ሰራተኛ ይፈልጋል። ይህንን ኃይል በጠንካራ ዲሲፕሊን መምራት ከተቻለ ከራሱ አልፎ ለአገር የሚጠቅም ዜጋ አድርጎ መግራት ይቻላል።
በትናንቱ እለት የተጀመረው ሁለተኛው ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እነዚህንና ሌሎችንም ከመርሀ ግብሩ የሚገኙ ጥቅሞችን ለዘለቄታው ለማስቀጠል ዓላማ ያደረገ ነው ።
በሁለተኛው ምእራፍ አምስተኛው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 6.5 ቢልዮን ችግኝ የሚተከል ሲሆን፤ ለመትከል ከተዘጋጁት ውስጥም አብዛኞቹ የፍራፍሬ ዛፍ ችግኞች ናቸው።
የፍራፍሬ ዛፍ ችግኝ ተከላው አገርን አረንጓዴ በማልበስ ከአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ከመታደግ በላፈ፤ አገርና ህዝብ ለመርሀ ግብሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው። ይህም ዜጎች መርሃ ግብሩን ከቀደመው በተሻለ መልኩ የራሳቸው አድርገው እንዲሄዱ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው።
መላው ዓለም የአየር ፀባይ ለውጥ ብዙ ዋጋ እየከፈለና ከፍ ባሉ ስጋቶች ውስጥ እየተናጠ ባለበት በዚህ ወቅት፤ የጀመርነው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ባለፉት አራት ዓመታት ካስገኘልን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት አንጻር መርሀ ግብሩን አቅደን ስኬታማ ስለመሆናችን ከሁሉም በላይ ለራሳችን እውቅና ልንሰጥ ይገባል።
የመረሀ ግብሩ ስኬት ለመጭው ትውልድ የተሻለ የመኖሪያ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ፤ የተፈጥሮ አካባቢን የመጠበቅና የመንከባከብ ባህልን ማውረስ የሚያስችል በመሆኑ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ልንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ትናንት የጀመርነው ሁለተኛ ምእራፍ፣ አምስተኛው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደቀደመው ምእራፍ ስኬታማ እንዲሆን ወገባችንን አጥብቀን፤ ብሩህ ነገዎችን ታሳቢ ባደረገ ቁርጠኝነት‹‹ዛሬ ነገን እንትከል››በሚል መርህ እንቀሳቀስ። ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነትም እንፍጠር።
ከመርደቂዮስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2015