አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የምጣኔ ሀብት ባለሙያና የቀድሞ ዲፕሎማት
የኢትዮጵያ እድገት የሚያባንናቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ አንድ ርምጃ ወደፊት ሄደች በተባሉ ቁጥር እነርሱ አስር ያህል ርምጃ ወደኋላ ያፈገፈጉ ያህል የሚሰማቸው ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሳም ውስብስብ የሆነ ሴራቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ይሯሯጣሉ፡፡ ከሰሞኑንም የግብጻውያኑን አካሄድ ላስተዋለ አካል እየተስተዋለ ያለው ይኸው እንደሆነ መረዳት አይከብደውም፡፡
ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በተለይም በግብጽ በኩል እየተሸረበባት ያለው ሴራ እንዴት መታለፍ ይችላል? በቀጣናውና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ምን ይመስል ነበር? እንዴትስ መሆን አለበት በሚሉና በመሰል ጥያቄዎች ዙሪያ ከቀድሞው ዲፕሎማትና የምጣኔ ሀብት ምሁር ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ አድርጎ ተከታዩን አቅርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው ጭምር ትልቅ ፋይዳ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬታማ እንዳይሆን ግብጽ በብዙ መንገድ ስትጥር ቆይታለች፤ ጥረቷ አልሰምር ሲላት ደግሞ ጦሯን ይዛ ወደሱማሊያ ሄዳለችና ይህንን እንዴት አዩት? ግብጽስ ኢትዮጵያን የምትፈታተናት እስከ መቼ ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ተቃርኖ ዛሬ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ላለፉት መቶ ዓመታት አብሯት የኖረ ነው፡፡ ግብጽ እንዲያ በማድረጓ ብዙ ጊዜ ተሳክቶላታል፡፡ ግብጻውያን ኢትዮጵያ እንዳትበለጽግና እንዳታድግ በተለይም ጎስቋላ ሀገር ሆና እንድትኖር ብዙ ለፍተዋል፤ ሰርተዋልም፡፡ በዚህም ተግባራቸው ብዙ ጊዜ ስኬትን አግኝተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትገነጠልና ምንም መብት እንዳይኖራት በብዙ ጥረው ተሳክቶላቸዋልም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎችን በመፍጠር ረገድ በብዙ ሲደክሙ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ድርጊታቸው ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ትልልቅ ሴራ ሸርበዋል፡፡ አሁንም እንደዚያ ዓይነት ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲያውም ይህንን ተግባራቸውን ምናልባት አጠናክረው ሊቀጥሉ ይችላሉ የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ምክንያት ቢባል የግብጽ ፖሊሲ የተነደፈው ‹‹ኢትዮጵያን አድክመን ባለችበት ካልቆየናት ሕልውናችን ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል» ከሚል ፍራቻ የተነደፈ ፖሊሲ አለ፡፡ ይህ በጣም መጥፎ የሚባል ፖሊሲ ነው፡፡
ፖሊሲዋ “ግብጽን ጠንካራ ለማድረግ ኢትዮጵያን ማዳከም” የሚል መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዚሁ መርህ የሚቀጥል መሆኑ ነው፡፡ ይህን አቋሟን የምትለውጠው መቼ ነው ከተባለ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም አካሄዷ ሲጤን የምትለውጥ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ነገር በዚህ ዓይነት ጉዞዋ ለመቶ ዓመታት መዝለቋ ነው፡፡
ግብጻውያን ብዙ ጊዜ ውጊያቸውን የሚያደርጉት በእጅ አዙር ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ጠንክራ እስከተገኘች ድረስ ፊት ለፊት ሊጋፈጧት አይደፍሩም። ከዚህ የተነሳ በእጅ አዙር ካልሆነ ወርረን እንይዛታለን የሚለውን አመለካከት የተውት ይመስላል፡፡
ግብጻውያን ሁለት ሶስት ጊዜ ተዋግተዋል፡፡ ይሁንና ከውጊያው የወጡት ተሸንፈው ነው፡፡ ስለዚህ ፊት ለፊት መጋፈጡ አዋጭ እንዳልሆነ የተረዱት ግብጻውያኑ፤ ኢትዮጵያውያኑን ከኢትዮጵያውያኑ ጋር በእጅ አዙር ማዋጋትን ቅድሚያ ሰጥተው እየሰሩበት ሲሆን፣ በአሁን ወቅትም ይህን የሴራ አካሔዳቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዓይነት ሂደት ውስጥ ማለፍ ፈታኝ መሆኑን ተገንዝበን ከተግዳሮቱ ውስጥ ለመውጣት ስንል አንድነት ላይና ትብብር ላይ ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል፡፡ ለሌላ ተገዝቶ መሥራት እና ተገዝቶ መዋጋት አሸማቃቂ በመሆኑም እንዴት እናስወግዳለን በሚለው ላይ በጣም ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡
በሕግም፣ በኃይልም በፍቅርም በፖለቲካም በሰብዓዊ መብት በመጠበቅም ረገድ ሥራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል፡፡ በእነዚህ ላይ ተግተን ብንሰራ በውስጥ ገብታ ልታዳከመንም ሆነ ያላትን ኃይል በመጠቀም ልትከፋፍለን አትችልም ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህ ከውስጥ ያለውን ኃይል እሷ እናዳትጠቀም የማድረግ ሁኔታ ላይ በከፍተኛ ትጋት መሰራት የግድ ይለናል፡፡ ያለበለዚያ ግብጽ ይህን የምታቆም አይመስለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ የቀድሞ ዲፕሎማት ግብጽ ወደሱማሊያ ያጓጓዘችው የጦር አውሮፕላኖች ከነሙሉ ትጥቃቸው እንደሆነ ታውቋልና ይህን የሚያዩት እንዴት ነው? በኢትዮጵያስ በኩል ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– እንግዲህ ግብጽ የቱንም ያህል ብንልምናት እሺ የምትል አይመስለኝም፤ ከዚህ ተግባሯ የምታፈገፍግ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን መደረግ ያለበት ምንድን ከተባለ ሱማሊያዎች የግብጽን አካሄድ በበጎ የተመለከቱ አይመስለኝም፡፡ ራሳቸው እየወሰዱ ያለ ርምጃ መኖሩን እሰማለሁ፡፡ ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማሲና ከፍተኛ የሰው ለሰው እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ እንደሰራችና ውጤትም እየሰጣት መሆኑን አመላክች ነው ባይ ነኝ፡፡
አሁን የሱማሊያ ፌዴራል መንግሥቱ ግብጽን አስገባለሁ፤ ኢትዮጵያን አስወጣለሁ፤ ኢትዮጵያን እወጋለሁ በሚልበት ጊዜ የሱማሊያ አካል የሆኑ ሌሎች ደግሞ “አይ! አይሆንም፤ ግብጽን አታስገቡ፤ ኢትዮጵያንም አታስወጡ፤ እኛ ወዳጃችን ኢትዮጵያ ናት፤ ያውም በመከራና በመጥፎ ጊዜ የደረስችልን ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ግብጽ በአሁኑ ወቅት እየመጣች ያለችው የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው ማለት ጀምረዋል፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህ ትልቅ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው። ይህ ግድብ ሕዝብ ለሕዝብ ያለው ግንኙነት ምን ያህል እንደጠነከረ የሚያሳይ ነው፡ ፡ እንግዲህ መንግሥት ብቻ አይደለም ይህን መሥራት ያለበት፡፡ በዚህ ረገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ሌላው ለዓለም አቀፍ መንግሥታት በተለይ እንደ አሜሪካ ላሉ ሀገሮች ይህንን የግብጽን ፍላጎት በተከታታይነት ማስረዳቱ ተገቢ ነው፡፡ የግብጽ ሁኔታና ፍላጎት ኢትዮጵያን ማዳከም እንደሆነና ይህም ደግሞ ለአፍሪካ ካላት መልካም ያልሆነ አመለካከት የመነጨ መሆኑን ግንዛቤ በአግባቡ ማስጨበጥ መልካም ነው፡፡
ግብጽ፣ በአሁኑ ወቅት የምትፈልገው ቀደም ሲል የነበራትን በተዘዋዋሪ የማጥቃት አካሄዷን ነው፤ ጥረት እያደረገች ያለውም ያንን ሙከራዋን ይበልጥ ለማደስ ነው፡፡ እኔ ማለት የምፈልገው ለጥቁር አፍሪካውያን፣ ለወገኖቸቻችን፣ ለወንድሞቻችን ይህን የግብጽን አካሔድ በተከታታይ ለሚመለከተው ማስረዳትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆም ማድረግ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ መሰራት አለበት የሚል ነው፡፡ ግብጽ፣ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤትም ቀድማ ሄዳ ሁልጊዜ ከምታስረዳ እኛ ቀደም ብለን ማስረዳት አለብን እላለሁ፤ ምክንያቱም ቀድሞ መገኘት በዲፕሎማሲው ረገድ ጥሩ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር በተጠናቀቀው ዓመት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ምን ያህል ስኬታማ ነበረች ይላሉ? በቀጣይስ እንደ ሀገር ምን መሰራት አለበት?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- ተሳክቶልና ወይ ካልሽኝ፤ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ተሳክቶልናል ብዬ የምወስደው የተጠናቀቀውንና ያለፈውን ጊዜ ነው። ያለፈው ዓመት ከዲፕሎማሲው አንጻር በጣም ደስ የተሰኘሁበት ዓመት ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ስኬት ያገኘንበት ዓመት ነው፤ ነገር ግን እሱም ቢሆን አይበቃም፡፡ ምክንያቱም ጠላቶቻችን ጠንካራዎች ናቸው፡፡ ጠንካራ ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎችም ጭምር ናቸው፡፡
ጠላቶቻችን፣ ጥቁር ሕዝብ ወደላይ መውጣት የለበትም የሚል እሳቤ ያላቸው አሉ፡፡ ይሁንና በእኛም በኩል የውስጥ ድክመት አለ፤ ድህነታችንን መቅረፍ ተስኖናል፤ እንደሚታወቀው ደግሞ ድህነት ለሌሎች በገንዘብ እንድንገዛ የሚያደርግ ነው፡፡ ጠላቶቻችን ይህን ድህነታችንን በመጠቀም በገንዘብ እየገዙ ሀገራችንን እንድናዳክም ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ይሰራሉም። ድሃ ስለሆንን ትንሽ ገንዘብ ስናገኝ ለሚከፍለን ሀገር እንሰራለን፡፡ የዚያ ሀገር ሕልም እንዲሟላላቸው እናደርጋለን፡፡ በዚህ ተግባራችንም ሀገራችን እንድትጎዳ እናደርጋለን፡፡ ይህ ዓይነት አካሔዳችን የሚመነጨው ከድህነት ነው፡፡
በዚህ ረገድ ደግሞ ለወጣቱ ሥራ መፍጠር ያስፈልጋል፤ እንዲህም ሲባል ለወጣቱ ሕይወት ትርጉም የሚሰጥ ሥራ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወጣቱ በኑሮው ዙሪያ ትርጉም ካጣ በገንዘብ ለመግዛት ለሚፈልጉ አካላት መሳሪያ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ድህነትን መቅረፍና ለወጣቱ ሥራ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት ሀብታም እየሆንን ነው የሚል አተያይ አለኝ፡፡ ድሮ እኔ ትምህርት ቤት ሳለሁ ኢትዮጵያ ትልቅ ናት ሲባል እሰማለሁ፡ ፡ እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ትልቅ ሆና ያየሁት ግን አሁን ነው፡፡ እኔ በአሁኑ ወቅት እድሜዬ ወደ 80 እየተጠጋ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ሁሉ እድሜዬ ያየሁት ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ጥሩ ሆና የተገኘችው በአሁኑ ወቅት ነው ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ ለዚህ ምክንያትህ ምንድን ነው ብለሽ ብትጠይቂኝ አንደኛ ከሁሉ በፊት ልጠቅሰው የምፈልገው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚው እያደገ ነው በሚለው ነው፡፡
በተለይ ባለፉት በአምስት ዓመት ውስጥ ኢኮኖሚው እጥፍ አደገ ማለት ህልም ነው፡፡ በዚሁ ከቀጠልን፣ ሕዝባችንን ከድኅነት ማላቀቅ ከቻልንና ለወጣቱ ሥራ ከሰጠን ግብጽና ሌሎች ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚያደርጉትን ጥረት ዋጋ ቢስ እናደርገዋለን ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግብጽ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን የማዳከም ስትራቴጂ ተክናበታለችና በቀጣይ የውስጥ ሰላማችን ይጠበቅ ዘንድ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ? መንግሥትስ ማድረግ ያለበት ምንድን ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- የውስጥም የውጭም ሰላማችን ይጠበቅ ዘንድ ሁላችንም መሥራት አለብን እላለሁ፡፡ እኔ የተፈጠረው የሰላም መታጣት መንግሥት ብቻ በፈጠረው ጥፋት የመጣ ነው የሚል አተያይ የለኝም፡፡ የመንግሥት ብቻ ጥፋት ነው የሚሉ አካላት አባባላቸው የሞኞች ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ለሀገር ውስጥ ሰላም መደፍረስ የውጭው ሁኔታ አለ፡፡ ግብጽ እንኳን የኢትዮጵያን ድሃ ይቅርና የአሜሪካንን ሴናተር በገንዘብ ገዝታ ዓለም እስኪያውቅ ድረስ ሰውዬው ፍርድ ቤት ቀርበው እስራት እንዲፈረድባቸው እየታቀደ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህን የአሜሪካንን ሴናተር በወርቅ እና ዶላር እየደለለች የመግዛት አቅም ያላት ከሆነ የእኛን ድሃ ደግሞ ምን ያህል እንደገዛች መገመት አያቃትም፡፡
ውጭ ሀገር ያሉት የእኛዎቹ ተወላጆች ደግሞ እንደሌላው አፍሪካዊ ዝቅ ብሎ መሥራት፣ መነገድና ካሉበት ሀገር ሕዝብ ጋር ተባብሮ መሥራት ብዙም የሆነላቸው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከዚህ የተነሳ ለመሸጥ በቀላሉ የሚገኙ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ጠንክሮ መሥራትን የማይፈልግ ከሆነ ሀገሩን በቀላሉ ጎድቶ ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ ለመፈለግ ቅርብ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ግብጻውያን፣ አሜሪካ እኛን እንድትጎዳንና እንድታጠፋን ያን ያህል ገንዘብ የሚሰጧት ከሆነ ለእኛዎቹ ደግሞ ምን ያህል ከዚያ የበለጠ እንደሚሰጡ መገመት አያቅትም፡፡ ግን ይህ ጉዳይ እምብዛም ግልጽ አልሆነም፡፡ ሕዝቡም መንግሥትም ይህን ማወቅ አለበት፡፡
ከዚህ ሌላ መንግሥት አስቀድሜ ለማለት እንደሞከርኩት ለወጣቶቹ ሥራ መፍጠር፣ በሕዝብና በሕዝብ መካከል የሚደረገውን ተቃርኖዎችን ማስወገድ እና የሕግ የበላይነት በጣም እንዲጠነክር ማድረግ ይጠበቅበታል፤ ከሕግ ውጭ በሰው ላይ የሚደረግ ያልሆነ ነገር እንዲወገድ ማድረግና ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
ሕዝቡ ደግሞ በውጭ ተቀምጦ ችግር እየፈጠረ ያለ ኃይል እንዳለ አጢኖ መንግሥትን መርዳት መቻል አለበት፡፡ መንግሥትም እንደ እሱ ዓይነት ችግር መኖሩን ለሕዝቡ ማስረዳት አለበት፡፡ ይህንን ችግር በውል ሲያስረዳ አላስተዋልኩም፡፡ በዚህ ረገድ ምሁሩም ያለውን ሁኔታ በአግባቡ ለሕዝቡ ማስረዳት ይጠበቅበታል ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም የውጭው ግፊት ምን ያህል እንደሆነ ሕዝቡ በአግባቡ የሚያስረዳው አካል ይፈልጋልና ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ባለፈው ጊዜ የነበራት ዲፕሎማሲያዊ አካሔድና በቀጣይም ደግሞ አጠናክራ መቀጠል አለባት የሚሉት የትኛው ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– በበኩሌ ባለፉት ዓመታት ሲካሔዱ የነበሩት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች በጣም የሚያረካ ነበር እላለሁ፡፡ በጣም በከፍተኛ ደረጃ የረካሁት በጣም ብዙ ሀገሮች እነ ቱርክ ጭምር ሲሯሯጡለት እና ለመግባት ሲለምኑ የነበረው የብሪክስ አባልነታችን ጉዳይ ላይ ነው፡፡ እኛ በርግጥ ምን ያህል እንደለፋን ባላውቅም ግን አባል ሆነን ተገኝተናል።
ይህ በወቅቱ ግብጽ፣ እንደ እኛው አዲስ አባልነትን ያገኘች መሆኗ ቀርቶ ቀድማን ገብታ ቢሆን ኖሮ፤ እኛ ወደብሪክስ እንዳንገባ የማትፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም ነበር፡፡ ነገር ግን እኩል ስለገባን በአሁኑ ወቅት ልታደርገው የምትችለው ነገር አይኖርም፡፡ እናም ብዙዎቹን ቀድመን ለብሪክስ አባልነት መብቃታችን በጣም በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው ብዬ እወስደዋለሁ፡፡ ይህ አንደኛ ጉዳይ ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ አፍሪካን አስተባብሮ በናይል ምክንያት እኛ ብቻ ስንታገል ቆይተን አሁን ሌሎች አፍሪካ ሀገሮችም ጭምር አብረውን ከእኛ ጋር ለመተጋል የሚያበቃ ኮሚሽን ለማቋቋም የበቃንበት ሂደት ሲሆን፣ ይህ እጅግ በጣም የሚያኮራ ነው፡፡ እነዚህ የተሰሩ ሥራዎች ዘላቂዎች እንጂ ጊዜያዊ አይደሉም፡፡
ሶስተኛው ደግሞ አሁን የባህር በር ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ይህ የተደረገው ጥረት በጣም ደስ ከሚያሰኘኝ ውስጥ በመሆኑ ስሜትህን እንዴት ትገልጸዋለህ ብለሽ ብትጠይቂኝ ሜዳ ላይ ወጥተህ ዝለል ዝለል የሚያስብልኝ ጉዳይ ነው ልልሽ እችላለሁ። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን የባህር በሩን ማግኘት ከቻልን ትልቅ መሆናችንና ወደተመኘነውም ከፍታ መውጣታችን አይቀርም ብዬ አምናለሁ፡፡
አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ባለፉት ስምንት አስርት ዓመታት በውስጡም አልፌያለሁ፤ ከታሪክ ድርሳናትም አንብቤ ተረድቻለሁ፡፡ እኛ አሁን ለመውጣት የምንፈልገው ያህል ከፍታ የወጣንበት ወቅት መኖሩን ከዚህ ቀደም አላውቅም፡፡ በታሪክም አላነበብኩም፡፡ እንዲህ ስል ከአክሱም ጊዜ በኋላ ማለት ነው፡፡ አክሱም ደግሞ በጣም በጣም የቆየ ታሪክ ነው፡፡ አሁን ወደምንመኘው ከፍታ ላይ ለመውጣት የባህር በር ያስፈልገናል፡፡ አሁን የሚያስፈልገን ወደብ አይደለም፡፡ ወደብ እቃ ማጓጓዣ ነው፡፡ ጸጥታችንን የምንጠብቅበት የራሳችን የምንለው ነገር እንዲኖረን የሚያደርግ፤ ጠላት በአንድ ወገን ቢመጣ ቀድመን የምንከላከልበት፤ ኃያል ለመሆን፤ ከሌሎችም ጋር እኩል መታየት እንድንችል የሚያስችለን የባህር በር ነው፡፡ ይህን የባህር በር ደግሞ በአሁኑ አካሔዳችን ሂደት ከቀጠልን እናገኘዋለን ነው ለማለት እወዳለሁ፡፡
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሶስቱ ነገሮች በእኔ አስተያየት በጣም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው። ይህን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ሥራ ደግሞ ሁሉ ነገር አለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁሉ ነገር በምልበት ጊዜ የመጀመሪያው በጣም ጠንካራ የሆነ ሕዝብ አለ፡፡ በገንዘብ የሚገዙና የሚያወናብዱ ጥቂቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይሁንና 90 በመቶ ያህሉ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እንዲህ በምልበት ጊዜ ከልዩ ስሜት ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነው ስልም ነፃነታቸውን በሚያጡበት ጊዜ ነፃነቱን ጠብቆ የቆየ ሕዝብ ነው፡፡ እኛ ማለት ይህኛው ዓይነት ሕዝብ ነን፡፡ ይህ ዓይነት ኩሩ ሕዝብ ዛሬም አለ፤ በቁጥር ደረጃም ብዙ ነው፡፡ በአካባቢው ኃይል ለመሆን የሚያስችል አቅም የሚፈጥር ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የመሬት ሀብትም ባለቤት ነን፡፡ ያለን መሬት ደግሞ ምቹ የሆነ ነው፡፡ ያንን ከተጠቀምን ማንም በፈለገው ልክ ተጽዕኖ ሊያደርስብን አይችልም፡፡ ከጥንካሬያችን የተነሳ ድምጻችንን ከፍ አድርገን ለመናገር የሚያስችል ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ለዚህ ሁሉ ዋና የሆነና አቀነባብሮ የሚወስድ አመራር የሚባለው አካል አለ፡፡ እኔ ሥራ ላይ እያለሁም ስለ አመራር ተናግሬ አላውቅም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ያለው አመራር እንዳስተዋልኩት ከሆነ ባለራዕይ፣ አርቆ የሚያስብ፣ ደፋር፣ ሩህሩህ፣ ሀገርን በጣም ከሁሉ አብልጦ የሚወድ ነው ባይ ነኝ፡፡ ይህ በራሱ አንድ ትልቅ ሀብት ነው፡፡ እናም ይህ ሁሉ በተሟላበት ሁኔታ የምንመኘውን ለማከናወን እንችላለን ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የምጣኔ ሀብት ባለሙያም እንደመሆንዎ ኢትዮጵያ በቀ ጣይ ኢኮኖሚዋ እንዲያድግ ማተኮር የሚጠበቅባት የትኛው ዘርፍ ላይ ነው ይላሉ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– ወደ ውጭ ሀገር በምንልከውና ከውጭ ሀገር በምናስገባው እቃ መካከል ያለው ልዩነት የሰማይ እና የምድር ያህል የተራራቀ ነው፡፡ ይህ በታዳጊ ሀገሮች መካከል ሀገራቱ እድገት በሚጀምሩበት ጊዜ ከውጪ የሚመጣው እያደገ መሄዱ ጤነኛ አካሄድ ነው፡፡ ነገር ግን አላስፈላጊ የሆነ የገቢ ምርት ላይ ብቻ መመርኮዝ የለብንም፡፡
እናም በገቢና በወጪ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ መደረግ ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እኛ ለምርት አገልግሎት የሚውሉ ነገሮች (capital goods) የለንም፡፡ እሱ ከሌለ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት አይቻልም፡፡ ስለዚህ እድገታችን በጣም በፈጠነ ቁጥር ‘capital goods’ ከውጭ በብዛት እናመጣለን፤ እና እሱ ደግሞ ለእድገት አስፈላጊ ነው፡፡
ነገር ግን በጣም መጥፎ የሚሆነው መቼ ነው ከተባለ የምግብ ፍጆታንም ጭምር ከውጭ ሀገር ስናመጣ ነው። በአሁኑ ወቅት ስንዴ ከውጭ ማስገባት አቁመናል። ስኳር ግን ማምጣት አላቆምንም፡፡ ስንዴ ብናቆምም ስንዴን ለማምረት የሚያስችሉ ግብዓቶችን ከውጭ ሀገር ማስገባት አላቆምንም፤ ለምሳሌ እንደ ማዳበሪያ፣ ጸረ አረም መድኃኒትና መሰል ግብዓት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላ መልኩ ለዚሁ ስንዴ ማምረት ማቀላጠፊያ የሆኑ ማሽነሪዎች እንደ ትራክተር፣ ኮምባይነር የመሳሰሉትን የምናመጣው ከውጭ ሀገር ነው፡፡
እሱ ሁሉ ግብዓት ከውጭ ከመጣ እዚህ የጨመርነው የሰው ጉልበት ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ለዚህ መፍትሔ መፈለግ አለብን፡፡ የአፈር ማዳበሪያ እዚህ ማምረት አለብን፤ ትራክተር እዚህ ማምረት መቻል አለብን፡፡ ኬሚካሎችንም እዚሁ ማምረት መቻል አለብን፡፡ እንደዛ ማድረግ የማንችል ከሆነ ራሳችንን በምግብ ቻልን ማለት አንችልም፡፡
ስለሆነም ይህን አድርገን ቢያንስ በምንበላው ረገድ ራሳችንን መቻል አለብን፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን እሱን እያደረግን አይደለም፡፡ እናም በእኔ አተያይ በማኑፋክቸሪንግ መስክ የሚደረገው ጥረት ደካማ ነው፡፡ ለምሳሌ በቱሪዝም፣ በሰርቪስ ረገድ እና በሌሎች ዘርፎች የሚደረገው ጥረት በጣም ከፍተኛ የሚባልና ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ልክ በእሱ ደረጃ ግን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተደረገ አይደለም። በቴክኖሎጂ ረገድም ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ሰዎቹ የደረሱት ለመድረስ ጥሩ ትግል እየተካሔደ ነው፡፡ ዝም ብሎ ከማየት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡
ነገር ግን ትኩረት መደረግ ያለበት በማኑፋክቸሪንግ ረገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ነው፤ ይህ በጣም ደካማ እንደሆነ መናገር እሻለሁ፡፡ እኔ በዚህ እድሜዬ ሐሰት መናገር አልሻም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የማይመራመሩት ለምንድን ነው? ለአርሶ አደሩ የሚሆን እንደ ትራክተር ትልልቁን ዓይነት እንኳ ባይሆን አነስተኛ መሳሪያን ስለምን በምርምር አያመርቱም? እሱ ዓይነት ቴክኖሎጂ ሲመረት አላይም፡፡
በሌሎች ሀገራት ግን ወደወስብስቡ ማሽኖች ከመምጣታቸው በፊት አነስተኛ መሳሪያዎችን በማምረት ነው ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉት፡፡ ለምሳሌ ቻይና የዛሬ ሃያ ዓመት አካባቢ በሔድኩበት ጊዜ ያስተዋልኩት ነገር፤ ሲረባረቡ የነበረው ትራክተር ላይ አይደለም፡፡ ትኩረት አድርገው ሲሰሩ የነበረው አነስተኛ መሳሪያዎች ላይ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አካሔድ ስገመግም አሁን የማየው ነገር ጉድለት አለው እላለሁ፡፡ ስለዚህ ይህን ጉድለት ለመሙላት መሥራት አስፈላጊ ነው ባይ ነኝ፡፡
ከዚህ ውጭ ግን ኢኮኖሚው እጅግ በጣም እያደገ መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡ ይህ በመሆኑም እንደ ሀገር የሚያኮራ ነው፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ረገድ ያለውን ችግር ከፈታንና በወጪ እና ገቢ ምርት ላይ ያለውን ስፋት ማጥበብ ከቻልን ኢኮኖሚያችንም ጤናማ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሁልጊዜ ትብብርዎ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ፡- እኔ በጣም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም