በየትኛውም የዓለም ክፍል የተካሄዱ የለውጥ ንቅናቄዎች በብዙ ተግዳሮቶች የተፈተኑ ናቸው። ለውጥ በራሱ በአሮጌ፤ በዕለት ተዕለት የማኅበረሰብ መስተጋብር ውስጥ የባሕል ያህል ስርጸት ባገኘ አስተሳሰብ እና እሱን በሚጻረር አዲስ/ተራማጅ አስተሳሰብ መካከል የሚደረግ የማይቀር ትግል ነው። ይህም በመሆኑ ለተቃርኖ ሕግ ተጋላጭ እና ተገዥ ነው።
በለውጥ ሂደት ወስጥ የሚፈጠሩ ተቃርኖዎች ሊያስከፍሉ የሚችሉትም ዋጋ እንደየማኅበረሰቡ የንቃተ ሕሊና ደረጃ የሚሰላ ቢሆንም፤ ይብዛም ይነስም በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ ማኅበረሰብ ሊከፍለው የሚገባ ዋጋ ስለመኖሩ ግን ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ።
ይህንን ተጨባጭ እውነታ ካለመረዳትና የለውጥ ፈተናዎችን አቅልሎ የማየት፤ የለውጥ ሂደትን አልጋ በአልጋ አድርጎ የመመልከት የተዛባ እሳቤዎች ይስተዋላሉ። ይህም በለውጥ ፈላጊው ማኅበረሰብ ውስጥ መዘናጋትን ከመፍጠር ባለፈ፤ በለውጡ ያለውን ተስፋ ፈጥኖ እንዲደበዝዝ ሊያደርገው እንደሚችል ይታመናል።
ከዚህም ባለፈ የለውጡ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ራሱን አግባብ ባለው መልኩ የለውጥ ኃይል አድርጎ እንዳያሰልፍ፤ ለውጡን የሚያጋጥሙት ፈተናዎችም ሆነ ቡድን ወይም ግለሰብ አድርጎ እንዲያስብ ያደርገዋል፤ በዚህም በአሮጌው አስተሳሰብ ተጠልፎ ወደ ቀደመው የቁዘማው ሕይወት መመለሱ የማይቀርበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በርግጥ አሁን ያለንበት ዘመን ከቀደሙት ዘመናት ለውጥንና የለውጥ አስተሳሰቦችን በተሻለ መንገድ ለለውጡ ኃይሉ /ለማኅበረሰቡ በማድረስ ተናቦ ውጤታማ መሆን የሚያስችሉ ሰፋፊ አማራጮችን የያዘ ነው፤ አማራጮችን በጥንቃቄ በመጠቀም ፈጥኖ መንቀሳቀስ ካልተቻለ ግን የተገላቢጦሽ የስጋት ምንጭ መሆኑ የማይቀር ነው።
በእኛም ሃገር የሕዝባችንን የለውጥ መሻት ተከትሎ የለውጥ ኃይሉ ሥልጣን ከያዘበት ማግስት ጀምሮ፤ እንደሀገር አላራምድ ያሉንን፤ በየዘመኑ ብዙ ዋጋ ያስከፈሉንን ያረጁ አስተሳሰቦችን ከታሪክ በመማርና በሰከነ መንፈስ፤ በዕውቀት፣ በጥበብ፣ ጊዜንና ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ ስሌት በአዲስ ተራማጅ አስተሳሰብ ለመቀየር ሰፋፊ ጥረቶች አድርጓል፤ ዛሬም እያደረገ ነው።
ከቀደመው የለውጥ ታሪኮቻችን ልንማር እንደምንችለው፤ ለውጥ ስሜታዊነት በሚፈጥረው ሞቅታ፤ በለውጥ ወቅት የሚፈጠሩ ተቃርኖዎችን በኃይል ለመፍታት በመሞከርም ሆነ ከፍ ብለው በሚሰሙ የፕሮፖጋንዳ ድምጻች ስኬታማ መሆን አይችልም። ከዚህም የለውጥ ኃይሉ ብዙ ተምሯል።
በተለይ እኛ ይዘናቸው የመጣናቸው የተዛነፉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰቦች፤ እንዲሁም በይደር ያስቀመጥናቸው ችግሮቻችን፣ ለውጡ እንደሃገር ከፈጠረው መነቃቃት ጋር ተያይዞ ከመጣው የውጭ ተጽዕኖ ጋር ተዳምረው ለውጡን በተረጋጋ እና በሰከነ መንፈ ስ መምራት የግድ አድርጎታል ።
አሁን ላይ የለውጡን ገፊ ምክንያቶች በአግባቡ ባለመረዳት የተፈጠረው ለውጡን አቅልሎ የማየት ሁኔታ፤ የለውጡን ሂደት አልጋ በአልጋ አድርጎ የመመልከት፤ መንግሥት ለለውጡ ስኬት ዋነኛ አቅም ለሆነው መዋቅራዊ ለውጥ ለሰጠው ትኩረትና እየተመዘገበ ላለው ውጤት ተገቢውን ዋጋ የመንፈግ ስጋት ፈጥሯል።
ከዚህም ባለፈ ከተዛቡ ታሪኮች ላይ የሚነሱ የጥፋት ትርክቶች የብሔርና የኃይማኖት ቀለም እየያዙ የመምጣታቸው እውነታ ፤ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን ተቻችሎ በአንድ ሃገረ-መንግሥት ጥላ ስር በልበ ሙሉነት የመኖርን ትልቁን ብሔራዊ እሴታችንን በብዙ መልኩ እየተፈታተነ ይገኛል።
ይህም ሕዝቡን/የለውጥ ኃይሉን ለአሉባልታ እና ከአሉባልታ ለሚፈጠሩ የጥፋት ትርክቶች ተጋላጭ አድርጎታል፤ በለውጡ ላይ ያለውን እምነት በመሸርሸር፤ ትናንቶችን ናፋቂ እንዲሆን፤ ከነገ ብሩህ ተስፋዎቹ እንዲፋታ እየፈጠሩት ያለው ግራ መጋባት፤ በለውጡ ሂደት ላይም እያስከተሉ ያለው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
የለውጥ ኃይሉ ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ፤ ትልቁን የለውጥ ግብ ታሳቢ ያደረገ፤ በሰፊ ትዕግስት እና ሆደ ሰፊነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑ፤ ችግሮቹ እንደ ሕዝብ ሊያስከፍሉን ይችሉ የነበረውን ከፍ ያለ ዋጋ ትርጉም ባለው መልኩ ቀንሶታል ፤ አዲስ የችግር አፈታት ተሞክሮ ጅማሬም ሆኗል።
ይህንን በየትኛውም የለውጥ ሂደት ሊያጋጥም የሚችልን ፈተና ተሻሮ ለመሄድ የመንግሥት አካሄድ እንዳለ ሆኖ፤ በሃገራዊ ለውጡና በለውጡ ገፊ ምክንያቶች ዙሪያ ችግሮቻችን በአዋጅና በመመሪያ የምንሻገራቸው ሳይሆኑ መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ የሚፈልጉ ስለመሆናቸውም ተገቢውን ሕዝባዊ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።
የሚፈለገውን የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት በቅድሚያ በሀሳብ የበላይነት ማመንና ለዚህ የሚሆን በጎ ሕሊና እና ቅን ልቦናን መሠረት ያደረገ ዝግጁነት ይፈልጋል። ከራስ ጋር በብዙ ታግሎ ራስን አሸንፎ መውጣትንም ከሁሉም በላይ ይጠይቃል!
አብዛኞቹ ችግሮቻችን ብዙ ትናንቶቻችንን በልተው በይደር ሲንከባለሉ ዛሬ ላይ የደረሱ፤ በተረጋጋ መንፈስና በሰከነ አዕምሮ ቁጭ ብለን ተነጋግረን የምንፈታቸው፤ ከትናንቶች ይልቅ ነገዎች ላይ ባለን ብሩህ ተስፋ በቀላሉ ልንሻገራቸው የምንችላቸው መሆናቸውንም በሕዝቡ ውስጥ ማስረጽን ይጠይቃል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015