ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገት ወሳኝ መሳሪያ ነው:: የአንድ ሀገር በዕድገት መገስገስ ወይም ወደኋላ መቅረት ቀጥታ የሚያያዘው ከትምህርቱ ዘርፍ ውጤታማነት ጋር ነው:: የትምህርት ስርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ደግሞ በበቂ አቅርቦት መጠናከር ይኖርበታል::
ከዚህ አንጻር በ2015 የትምህርት ዘመን ከገጠሙ ችግሮች ውስጥ ዋነኛው የተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍት እጥረት ነው:: በ2014 ዓ.ም ትምህርት ዘመን በሙከራ ደረጃ እንዲሁም በ2015 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ የተገባበት አዲሱ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓትም በመጽሐፍት እጥረት ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖበታል:: ተማሪዎችም ለአንድ አመት ያህል ያለ በቂ መማሪያ መጽሐፍት ለመማር ተገደዋል::
የተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍት ለደረጃው የሚገባው መሰረታዊ የዕውቀት፤ ክህሎትና ዝንባሌ ማስጨበጫ ይዘቶችን የያዙ ስለሆኑ ተማሪዎች በቂ እውቀት ጨብጠው ወደሚቀጥለው ደረጃ እንዲሸጋገሩ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ:: የመማሪያ መጽሐፍት በሌሉበት ሁኔታ ተማሪዎች በደረጃቸው ሊይዙት የሚገባቸውን እውቀት እንዳይዙ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ የትምህርት አቀባበላቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው::
የ2015 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር የተካሄደው ያለ በቂ መጽሐፍት አቅርቦት ነው:: ይህም በተለያዩ ወቅቶች በዘገባ መሸፈኑ የሚታወስ ነው:: በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ አስተያየት ሲሰጥ እንደሚሰማውም በመጽሐፍቱ እጥረት ምክንያት ለማካካስ የታቀደው በኢንተርኔት አማካኝነት ነው:: ሆኖም ከተማሪዎቻችን አቅም፤ ክህሎትና እንደሀገር ካለው የኢንተርኔት አቅርቦት ችግር ጋር ተያይዞ ውጤታማነቱ በቅድሚያ ሊፈተሽ የሚገባው ነው::
አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ እንኳን የኢንተርኔት አገልግሎት ተዘርግቶ የሚገኘው በከተሞች አካባቢ መሆኑና በገጠሩ ክፍል ተደራሽ አለመሆኑ ሰፊ ቁጥር ያለውን ተማሪ ከትምህርት ማዕዱ በሚፈለገው መጠን እንዳይገለገል ያደረገ መሆኑን ታሳቢ ማድረግ ይገባል::
የኢንተርኔት አቅርቦት አለባቸው በሚባሉ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች እንኳን በጉዳዩ ዙሪያ ተማሪዎች ሲጠየቁም ከአስተማሪዎቻቸው የቤት ሥራና ሌሎች የትምህርት ይዘቶች በቴሌግራም አማካኝነት አልፎ አልፎ እንደሚደርሳቸውና ሆኖም የተሳለጠ የኢንተርኔት አገልግሎት ባለመኖሩ ምክንያት ለማንበብና ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም እንደተቸገሩም ተናግረዋል። በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያትም ኢንተርኔት መጠቀም የማይችሉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም:: ስለዚህም የዘመኑን ትምህርት በኢንተርኔት አማካኝነት ለማዳረስ የተደረገው ሙከራ በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ እንዳልሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል::
በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ላይ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጀው የስምንተኛና የስድስተኛ ክፍል መማሪያ መጻሕፍት ተደራሽ አለመሆናቸው የስድስተኛና ስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ተፈታኞች በአግባቡ እንዳይዘጋጁ እክል እንደፈጠረባቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል::
በአጠቃላይ ያለ በቂ የመማሪያ መጽሐፍት አቅርቦት የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት መፍጠር አዳጋች ነው:: በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ የትምህርት ጥራት ባለባቸው ሀገራት የመማሪያ መጽሐፍት በበቂ ሁኔታ በወቅቱ አለማዳረስ በቋፍ ላይ ያለውን የትምህርት ጥራት ወደ ከፋ ደረጃ ውስጥ መክተት ስለሚሆን ሳይውል ሳያድር ችግሩን የሚመጥን መፍትሄን መፈለግ ግድ ይላል::
በቂ የሆነ ግብዓት ባልተዘጋጀበት ሁኔታም ከተማሪዎች ውጤት መጠበቅም ብዙ ርቀት የሚያስኬድም አይደለም:: በተለይም አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይተገበራል በተባለበት ዓመት ላይ ይህን መሰል የመጽሐፍት አቅርቦት ችግር መፈጠሩ እንደ ሀገር በርካታ ዕውቀትና ሀብት የፈሰሰበትን ፖሊሲን ውጤታማ እንዳይሆን የሚያደርገው ይሆናል::
የተማሪዎች የመማር መጽሐፍት ጉዳይ ቀጣይነት ያለውና የመማር ማስተማሩ ሂደት አንዱ አካል በመሆኑ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግን ይጠይቃል:: ችግሩ ሰፊና ውስብስብ በመሆኑን ከመንግስት ባሻገር በህትመት ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ አካላትን በሀገር ውስጥ ማሳተፍና ማጠናከርን ግድ ይላል::
በአጠቃላይ ግን በ2015 የትምህርት ዘመን ያጋጠመው የተማሪዎች የመጽሐፍት እጥረት ተማሪዎች ተገቢውን እውቀት እንዳይጨብጡ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ የትምህርት አቀባበላቸውም ላይ የራሱን የሆነ ተጽዕኖ ማሳደሩ ሊሰመርበት ይገባል:: ስለሆነም በ2015 የትምህርት ዘመን የተፈጠረው የመጽሐፍት አቅርቦት ችግር ወደ 2016 የትምህርት ዘመን እንዳይሻገር ትምህርት ሚኒስቴርና በየክልሉ የሚገኙ የትምህርት ቢሮዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ የቤት ሥራቸውን በኃላፊነት መንፈስ ሊወጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2015