የሀገሪቱን ሕገመንግሥት (አንቀፅ 86) ስንመለከትና የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሰነድ ስናገላብጠው፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት ጋር ሊኖራት ስለሚገባት ግንኙነት እንዲሁም የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት መርሕና ሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ምን ይመስላሉ? የሚሉትን ዐብይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በግልፅ ያመላክታል።
እነኝህ ከፍተኛ የሕግ ማዕቀፎች ኢትዮጵያ በርካታ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ትርፎችን እንድታገኝ ረድተዋታል። በቅርቡ እየሆነ ያለውን ብቻ ብናነሳ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በእጅጉ እየተሻሻሉ ስለመሆናቸው ብዙ መረጃዎችን አንስቶ መነጋገር ይቻላል። ከነዚህ ውስጥ ለዛሬ አማርኛ ቋንቋን በተለያዩ ሀገሮች በትምህርት ደረጃ መሰጠት የተጀመረበትን እውነታ ለመቃኘት ልሞክር ።
እንደሚታወቀው ቋንቋ በውስጡ ሰፊ ነገር የያዘ ነው። የተናጋሪውን ሕዝብ ባህል፣ ዕውቀት፣ አስተሳሰብ… ወዘተ ይይዛል ። ከዚህ የተነሳም፣ የአንድን ሕዝብ ቋንቋ ማጥናት ለአጥኚው የሚሰጠው ጠቀሜታ ብዙ ነው። በሀገር ደረጃ ሲሆን ደግሞ በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንጻር የሩሲያና የቻይና መንግሥታት የአማርኛ ቋንቋ በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎቻቸው እንደ አንድ ትምህርት ለመስጠት እየሄዱበት ያለው መንገድ የሚበረታታና የሀገራቱን ሕዝቦች ግንኙነት ማሳደር የሚያስችል መልካም ዕድል ነው። በሀገራቱ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያደረገ ስለመሆኑም ማሳያ ነው ።
ለዚህም ነው በቻይና ቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ ለቻይናውያን ተማሪዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ምረቃ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን፤ የመጻፉ ምረቃ የኢትዮጵያ እና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማደጉን የሚያሳይ እንደሆነ ያመላከቱት ።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከቻይና የምርምር ተቋማት ጋር የዕውቀት ልውውጥ ማድረጋቸው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ መካከል ያለው የአማርኛ ቋንቋ ትብብርም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን የበለጠ ያጠናክረዋል ሲሉም መናገራቸው ።
በርግጥ የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የረጅም ዘመን ታሪክ ያለው፣ በየወቅቱም ከፍ ያለ እመርታ እያሳየ መምጣቱ የሚታወቅ ነው። የቻይና መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በሰው ኃይል፣ በትምህርት መርጃ መሣሪያዎች፣ ቤተ ሙከራ በማደራጀትና ያሉትን በማስፋፋት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በእውቀት እና ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው። ብዛት ላላቸው ኢትዮጵያውያን የትምህርት ዕድል በመስጠትም ተጠቃሽ ነው። ይህ ደግሞ ከቴክኖሎጂና ከእውቀት ሽግግር ባለፈ የባሕል ልውውጥ ከማድረግ አንጻር የማይተካ ሚና እንዳለው ይታመናል ።
የሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያደገ መሄድ፤ የሀገራቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍላጎትን በማሳለጥ ወዳጅነትንም ያጠነክራል። መቀራረብን፣ መተዋወቅንና መፈላለግን ይፈጥራል። ለዚህም ይመስላል ትናንሾቹ የቻይና ሕጻናት አማርኛ ቋንቋን እየለመዱ እንዲመጡ የቻይና መንግሥት መሠረት የሚጥል ተግባር እያከናወነ የሚገኘው ።
ቻይናውያን የአማርኛ ቋንቋን የመልመዳቸው እውነታ እንደሀገር በርካታ ጥቅሞችን ይዞ ይመጣል። ከሁሉም በላይ ቻይናውያን ስለኛ ትናንቶች እና ዛሬዎች የዳበረ እውቀት እንዲኖራቸው ያስችላል። ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር የተሻለ ዕድል ይፈጥራል። ይህ ደግሞ ለጀመርነው ሀገራዊ እድገት ተጨማሪ አቅም መፍጠር የሚያስችል ነው።
በሩሲያ በኩል የሚታየውም ከዚህ የተለየ አይደለም። እንደ ቻይና ሁሉ ሩሲያም በተለያዩ ጊዜያት
ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የኢትዮጵያ ሁነኛ አጋር መሆኗን አሳይታለች፤ እያሳየችም ነው። በተለያዩ ጊዜያት እንደ ሀገር ፈተና ውስጥ በወደቀችበት ሰዓት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን ነበረች። ጉዳያችን ቋንቋ ላይ በመሆኑ ሌላውን በሌላ የአጀንዳ ጽሑፍ ልመለስበት እችላለሁ ።
በቅርቡ በወጣው መረጃ እንደተመላከተው፤ በሞስኮ የሚገኙ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ከመስከረም ጀምሮ አማርኛ ቋንቋ ማስተማር ሊጀምሩ ነው። በርግጥ ቀደም ባለው ጊዜ በሩሲያ በአማርኛ ቋንቋ እስከ ዶክትሬት የደረሰ ትምህርት ይሰጥ እንደነበር የሚታወቅ ነው ።
የእስያ እና አፍሪካ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አሌክሲ ማስሎቭ ከፈረንጆቹ መስከረም 2023 ጀምሮ ቢያንስ አራት የሞስኮ ትምህርት ቤቶች ለሕጻናት የአማርኛ እና የስዋሂሊ ቋንቋ ማስተማር እንደሚጀምሩ ይፋ አድርገዋል። ዮሩባ ቋንቋን የሚያስተምሩበትን ዕድልም እየተመቻቸ መሆኑ ተነግሯል።
ውሳኔው ከሁሉም በላይ አፍሪካ አንድ ትልቅ አህጉር ብቻ ሳትሆን የተለያዩ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ሃይማኖት እና ኅብረ ብሔራዊ ማንነቶች ያሉባት አህጉር መሆኗን ለአዲሱ ትውልድ ለማሳወቅ የሚያስችል ነው።
አዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያ ሆነች በአህጉሪቱ የረጅም ሀገረመንግሥትና የቀደመ ሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን፤ ከምንጩ አንብቦ እንዲያውቅና ቀጣይ የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከቀደሙት ዘመናት በተሻለ መልኩ ስኬታማ እንዲሆን ያስችላል። ሰላም!
ክብረመንግሥት
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015