አዲስ አበባ፡- ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ መግባታቸውን የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰናይት መብሬ ከአምስት ባለሀብቶች ጋር በፓርኩ ገብተው ማልማት የሚያስችል ስምምነት በተደረገበት ወቅት እንደገለጹት፤ በቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው ለማልማት ስምምነት ያደረጉ ባለሀብቶችን ጨምሮ ከ40 ሄክታር በላይ መሬት ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ተላልፏል፡፡
በፓርኩ ውስጥ ገብተው ለማልማት የሚያስችል ፍቃድ ካገኙት ባለሀብቶች መካከል የተወሰኑት የሙከራ ምርት ማምረት ጀምረዋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከባለሀብቶች ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረትም በቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ21 ሄክታር በላይ መሬት ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ላስመዘገቡ አምስት ባለሀብቶች ማስተላለፍ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሁሉም ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ ሲገቡ 10ሺ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ በፓርኩ ፓስታ፣ መካሮኒ፣ የምግብ ዘይት፣ የህጻናት አልሚ ምግቦች፣ የእንስሳት መኖ፣ የወተት ውጤቶችን ማቀነባበርን ጨምሮ 12 ዓይነት ምርቶች የሚመረቱበትና የሚቀነባበሩበት መሆኑን ገልጸዋል፤ እነዚህ ሥራዎች ግብርናን በማዘመንና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማፋጠን በኩል ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱም አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡን ለማተካት በአገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን በማምረት፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር በኩልም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ኢድሪስ በበኩላቸው፤ ክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያለውን ሀብት በአግባቡ ትቅም ላይ ለማዋል የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ገንብቶ አጠናቆ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ በነቀምቴም ተመሣሣይ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ክልሉ ወደ ሥራ ለሚገቡ ባለሀብቶች ብድር በማመቻቸት፣ የሰለጠነ የሰው ሀብትና ጥሬ እቃዎችን እንዲያገኙ ማድረግን ጨምሮ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ራሳቸው ጥሬ እቃዎችን ማምረት ለሚፈልጉ ባለሀብቶችም የኢንቨስትመንት መሬት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን መንግሥት አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን ማሟላትን ጨምሮ 50 መቶ ኢንቨስት ያደረገበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደ ፓርኩ የገቡ ባለሀብቶችም በቶሎ ወደ ምርት ገብተው ለሌሎች ባለሀብቶች አርአያ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ስምምነት የተፈራረሙት ባለሀብቶችም የተረከቡትን ቦታ በአግባቡ በማልማት ወደ ምርት ለመግባትና የሥራ እድል ለመፍጠር ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015