አዲስ አበባ፡– በ130 ሚሊዮን ብር የሚያስገነባው የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ሁለገብ ማዕከል በ2016 ዓ.ም መጀመሪያ ወደ ሥራ እንደሚገባ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በወላይታ ሶዶ ከተማ በ130 ሚሊዮን ብር የሚገነባው የሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ማዕከሉ በመጪው ዓመት መጀመሪያ ወደ ሥራ ሲገባ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ትምህርትና ሥልጠና በማቅረብ በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይልን እጥረት ለመቅረፍ ይረዳል።
ማዕከሉ ሲጠናቀቅ ከሀገር ውስጥ የአማርኛ፣ የኦሮምኛ፣ የትግርኛና የሶማልኛ ከውጭ ደግሞ የቻይንኛ፣ የዓረብኛና የስዋሂሊ ቋንቋዎች ሥልጠና እንደሚሰጥበት አስታውቀዋል።
ባለ አምስት ወለል ማሰልጠኛ ማዕከሉ የወላይታን ባሕላዊ ዕሴት በጠበቀ መልኩ እየተገነባ ይገኛል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ማዕከሉ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል የሚሰጡትን አገልግሎቶች እንዲሰጥ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ 150 መኝታ ክፍሎች፣ መዋኛ ገንዳ፣ የተማሪ መማሪያ ክፍሎች፣ መመገቢያና መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የንግድ ሱቆች፣ ማሳጅና ሳውና ባዝ፣ ክሊኒክ፣ ላውንደሪን ጨምሮ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሮፌሰር ታከለ እንዳስታወቁት፤ የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ዩኒቨርሲቲው ከሥልጠና ባሻገር በሆቴል አገልግሎቶች ገቢ ማግኘት ይችላል።
የማዕከሉ ግንባታ ዓለም አቀፍ የጥራት መመዘኛ መስፈርትን በጠበቀ መልኩ እንዲገነባ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በግንባታ ሂደቱ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከያዛቸው የትኩረት አቅጣጫዎች የቱሪዝምና ቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የማዕከሉ መቋቋም በዘርፉ ከአጭር ጊዜ ሥልጠና እስከ ፒኤች ዲ ደረጃ ሥልጠናዎችን ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው የውስጥ ገቢውን በማሳደግ የራስ ገዝነት አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በወተት ሀብት ልማት፣ በእንስሳት ሕክምና አገልግሎትና የወላይታ ሰንጋ ሥጋን ለውጪ ገበያ በማቅረብ እንዲሁም በአቮካዶና ዓሣ ምርት ገቢ ለማግኘት የሚያስችል ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑን አመላክተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015