በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ሥራቸውን ለማቆም ተገደው ቆይተዋል። ቀሪዎቹም ማምረት ከሚገባቸው ከ50 በመቶ በታች ሲያመርቱ መክረማቸው አይረሳም። ይህም በተለያዩ የዓለም አገራት ከሚከሰቱ ግጭቶች ጋር ተዳምሮ ወደ ውጭ በሚላኩና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጫና በማሳደሩ እንደ ኢትዮጵያን በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጎዳ ታይቷል።
በእነዚህና በሌሎች የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተጎዳውን ኢንዱስትሪ በዘላቂነት ለማቋቋም ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ የሚል ንቅናቄ በአገር አቀፍ ደረጃ ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። እንደ አገር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ አንድ ዓመት ወዲህ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸው የሚታወቅ ሲሆን ሌሎች ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችም ዳግም ወደ ማምረት ተመልሰዋል፡፡
ይህ አገር አቀፍ ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ስራ እየገቡ፤ ባለድርሻ አካላትም ተቀራርበው በመስራት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገብ ችለዋል። በርካታ ክልሎችም በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በተግባር እያመረተች እንደምትገኝ እያስመሰከሩ ይገኛሉ። ለዚህ አንዱ ምሳሌ የኦሮሚያ ክልል ሲሆን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ120 በላይ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ችሏል። ይህም በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በመጨመሩ 41 በመቶ የነበረውን አማካኝ የማምረት አቅም ወደ 51 በመቶ ከፍ አድርጎታል። ለዚህም ክልሉ በንቅናቄው ለኢንዱስትሪዎችና ኢንተርፕራይዞች የተቀናጀ የአቅም ግንባታ፣ የፋይናንስና የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ አድርጎ የማም ረት አቅማቸው እያደገ እንዲሄድ የሰራው ስራ ሳይደ ነቅ አይታለፍም።
በሌሎች ክልሎችም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለይ በጨርቃ ጨርቅ፣ በምግብና ምግብ ነክ፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ምርቶች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። ያም ሆኖ ንቅናቄው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ምርት እንዳያመርቱ ማነቆ የሆኑባቸው ችግሮች ተለይተው መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን መካድ አይቻልም።
‘ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ የአገር ውስጥ ችግሮችና ዓለምአቀፍ ጫናዎችን የሚቋቋም ኢንዱስትሪ እስከመፍጠር የሚዘልቅ ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ በሀገር ውስጥና በውጭ ጫናዎች እየተፈተነ ያለውን ኢንዱስትሪ ለመታደግ ክልሎችና ባለሃብቶች ጉዳዩን የበለጠ አጥብቀው መያዝ ይኖርባቸዋል።
‘ኢትዮጵያ ታምርት’ በተግባር ሲለወጥ በዓለም ላይ በሚያጋጥሙ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችና ማዕቀቦች የሚረበሸውን ኢንዱስትሪ ለመታደግና ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በጥቂት ወራት የተመዘገቡ ዕድገቶች በተግባር አሳይተዋል። ኢትዮጵያ ጠንካራና ተወዳዳሪ አገር ሆና ውጫዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ያላትን አቅም አሟጣ መጠቀምና ማምረት ያለባት ጊዜው አሁን መሆኑን ተገንዝቦ ለዚያም ጠንክሮ መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል።
ራስን መቻል የሉዓላዊነትና የክብር ጉዳይ ነው። በእጃችን ላይ ያለውን ሀብት ተጠቅመን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የምንቀይርበት አንዱ መንገድም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሆኑን ለሰከንድም ቢሆን መዘንጋት የለበትም። ንቅናቄው በ2022 ዓ.ም የበጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለመተግበር ሰፊ ዕድል አለው። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በርካታ ጸጋ እና ሰፊ የሰው ኃይል እንዲሁም የተመቻቸ ፖሊሲ ስላላት ይህንን በተግባር ወደ ሀብት የመቀየር ሥራም አንዱ ገጽታ ነው።
የ’ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአጭር ጊዜ መፍታት ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የሚያጋጥሙ ስጋቶችን ከወዲሁ ለማስቀረት መፍትሄም ነው። የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለድርሻ አካላት፣ መገናኛ ብዙኃንና ሌሎችም ጉዳዩን ትልቅ አገራዊ አጀንዳ አድርገው በመንቀሳቀስ በዘርፉ የተፈጠረውን ትልቅ መነቃቃት ማስቀጠል ይገባቸዋል።
ለዚህም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለመጨመር የኃይል አቅርቦት፣ የመሬት፣ የሥልጠና፣ የብድር አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርቦ በመስራት ‘ኢትዮጵያ ታምርትን’ በውጤት ማጀብ የግድ ይላል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015