የፖለቲካ የአስተሳሰብ ልዩነት ፣ ፉክክርና የሚጋጭ ፍላጎት (Conficting Interest) ባለባቸው አገራት ውስጥ ችግሮች በአንድ ፓርቲ ፣ በአንድ ቡድን ወይንም በጥቂት ሰዎች አይፈቱም። ጥቂቶች በር ዘግተው ቢጨነቁና ቢጠበቡም መፍትሄ ሊሆኑና ሊያመጡም ፈፅሞ አይቻላቸውም፡፡ በመሆኑም ልዩነቶችን ለማጥበብም ሆነ ለማስታረቅ፣ ከተናጥል ይልቅ የጋራ ውይይት፣ ባህልና ልምድ አስፈላጊ ነው።
በተለይ በግሎባላይዜሽን ዘመን ከአግላይ / Exclusive Policy / ይልቅ አሳታፊ /Inclusive policy / የችግር አፈታት መርህ የግድ ይላል፡፡ አንደኛው ሌላውን ከሚያገል ጠባብ አስተሳሰብ ነፃ ወጥቶ ‹‹የጋራ ውሳኔያችን ትክክል ነው ወደ ሚል መርህና አስተሳሰብ መምጣት ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተፈጠሩና ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ ያልተቋጩ ሃሳቦች፣ በይደር የቆዩ አለመግባባቶች እንዲሁም አገር ትቀጥል ዘንድ ቅድሚያ ተነስቷቸው የቆዩ የማያግባቡ አጀንዳዎች የተሸከመች አገር ናት። ውይይት የሞት ያህል የሚከብድበት፣ በአመለካከት የሚለዩ በጠላትነት የሚፈረጁበት አገር ሆናም ዓመታትን አስቆጥራለች። ‹‹እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ›› እኔ የማስበው ሁሌም ትክልል ነው››የሚል የአመለካከትና የባህሪ ችግር ኢትዮጵያን ረጅም ጊዜ ሲያደማት ከርሟል፡፡
‹‹ችግር ካለም እኛው የሥርዓቱ ባለቤቶች እንናገር እንጂ ሌላው ምን ቆርጦትና ምንስ አግብቶት ነው በሥርዓቱ ላይ ትችት የሚሰነዝረው?›› የሚለው ከእኔ እና ከእኛ ውጭ ላሳር አመለካከትና ተግባርም ኢትዮጵያና ህዝቦቿን በሁሉ ረገድ ሊቀይሩ የሚችሉ የተለያዩ ገንቢ አስተያየቶችና መፍትሄዎች ከስመው እንዲቀሩ አድርጓል፡፡
አገሪቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት የአሳታፊነት ባህልና ልምድ የሌለባት መሆኑ ደግሞ ችግሮች በቀላሉ ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙ፣ ውስጥ ውስጡን እንዲብላሉና ከትናንት እስከ ዛሬ እንዲከተላት ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይሁንና ከህልውና ባሻገር ስለ መፅናትና መቀጠል እንዲሁም ስለ ሁለንተናዊ እድገት ሲታሰብ ለእነዚህን ልዩነቶችና አጀንዳዎች መፍትሄ መስጠት የግድ ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ አንድነቷ ተረጋግጦ፣ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የህዝቧን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማርካት የምትችለው በአንድ በኩል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ሲኖራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ምን አይነት ቅርጽ መያዝ አለበት? ምን አይነት የዴሞክራሲ፣ የፖለቲካ፣ የሕግ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋሞች ያስፈልጉናል የሚሉ ትልልቅ አገራዊ ጥያቄዎችን ኢትዮጵያውያን ቁጭ ብለው በመወያየት በጋራ ሲመልሱ ብቻ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡
በተለይ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት የውይይት እሳቤ በኢትዮጵያ ምድር እውን ይሆን ዘንድ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ከተለያዩ አካላት ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ‹‹ይሁን›› የሚል መልስ የሰጠ መንግሥት ግን አልነበረም፡፡ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የብልፅግና ፓርቲ መንግስት በአንጻሩ ይህን ታሪክ ለመለወጥ በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ቁጭ ብሎ ለመምከር በሩን ክፍት አድርጓል። ውይይቱ እውን ይሆን ዘንድ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሟል።
መሰል የውይይት መድረኮች ከመተዋወቃቸው አስቀድሞ በአገራችን ባህል ከቤተሰብ ጀምሮ ጎረቤት ቀበሌ ፣ወረዳ ፣ ዞን ወይም አውራጃ እያለ እስከ ክልል የሚደርሱ ግጭቶቹ ብዙውን ጊዜ የሚፈቱት፤ የሚጋጩት ሰዎች ሁሉ የሚታረቁት ሰላም የሚያወርዱት በሽማግሌዎች፣ በጎሳ መሪዎችና በሃይማኖት አባቶች አነሳሽነት ነው፡፡
የትዳር መሠረቱም ሽማግሌዎች ናቸው። ልጃችሁን ለልጃችን የሚሉበት እና ሦስት ጉልቻ እንዲመሠረት መሠረት የሚሆኑበት ፡፡ ትዳር ሲፈርስም ዕርቅ ተፈጽሞ ሦስት ጉልቻው እንደገና የሚቃናው የሚጸናው በሽማግሌዎች ነው። የጠቀስናቸው ነገሮች ህዝቡ ለታላላቅ ሰዎች፣ ለጎሳ መሪዎች፣ ለሽማግሌዎች እና ለሃይማኖት አባቶች ያለውን ክብር የሚያሳይ ነው፡፡ በአገራችን ሽምግልናን (ማስታረቅን) የሚጠላ የለም፡፡
ማንኛውም ግጭት ዕዳው ለቤተሰብና ለአገር የሚተርፍ ነው፡፡ ግጭትን አቁሞ መነጋገሩና መመካከሩ ሕይወት ከማጥፋት፣ ሰዎችን ከማፈናቀል፣ ሀብት እና ንብረትን ከማውደም ይታደጋል፡፡ የተለያዩ ፖለቲካዊ ዓላማዎችና ሃሳቦች ያሏቸው ፖለቲከኞችና የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖሯቸውን ልዩነቶች በመያዝ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገርና ለመግባባት ምክክር አስፈላጊ ነው፡፡ ተሰባስቦ መወያያትም የሰለጠነ መንገድ ነው፡፡
እንደ ባህላዊው የሽምግልና ሥርዓት በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሚናው ከፍተኛ ነው። ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ የተመሰረተው ለአገር ሰላም በተሰጠው ትኩረት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ሁሉን አካታች ሆኖ ከተመሠረተ ዓመት አልፎታል፡፡
ለሀገር ሰላም እና ለህዝቦች ደህንነት ዋስትና ማግኘት የሚቻለው ውይይትና ምክክር ሲጀመር ብቻ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ምክክሩ ጀምሮ የሁከት እና የጥፋት ሜዳዎችን የሰላምና የልማት ሜዳ ለማድረግ መጣር ይጠበቅበታል። ለዚህ ቅን ተግባር ስኬት መላው ህዝብም ሊተባበር ይገባል፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015