
መንግሥት በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበት ለመቅረፍ እየሠራ ቢሆንም፣ አሁንም የኑሮ ውድነቱ የዜጎች የዕለት ከዕለት ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የግሽበት ምጣኔውም በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ መሆኑን የሚናገሩት የዘርፉ ባለሙያዎች፤ ይህም በተለይ ቋሚ ገቢ ባላቸውና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉ ዜጎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ያነሳሉ። መወሰድ የሚገባቸው የመፍትሔ እርምጃዎች በአፋጣኝ ካልተወሰዱ እንደ አገር አስከፊ ሁኔታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉም ያሳስባሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ክቡር ገና እንደሚሉት፤ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አገራዊ ዋጋ ግሽበቱ ከ33 በመቶ በላይ ነው። ይህም ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ግሽበት ነው። ይህ ማለት የተለያዩ እቃዎችና አገልግሎቶች ዋጋ በዚህ መጠን እየጨመረ ይመጣል ማለት ነው።
ኮቪድ 19 ያስከተለው ተጽዕኖ፣ በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅና በዋናነት ደግሞ በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ጦርነት የዋጋ ግሽበቱን በማባባስ በኩል ጉልህ ሚና መጫወታቸውን የሚጠቅሱት ክቡር ገና፤ የሩስያ- ዩክሬን ጦርነት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በምክንያትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው ይላሉ።
የዋጋ ንረቱ ከመሻሻል ይልቅ አሁንም በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው፤ በዚህም በተለይ ደመወዝተኛ የሆኑና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጎጂ ይሆናሉ ይላሉ።
የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋትና ለመቀነስ ጠንካራ ሥራ እንደሚጠይቅ አመላክተው፤ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ አላስፈላጊ የገንዘብ ሕትመት እንዳይኖር መጠንቀቅ እና አገራዊ ምርትን ማሳደግ ሊወሰዱ ከሚችሉ የመፍትሔ ሀሳቦች መካከል መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ ምርትንና ምርታማነትን ማሳደግና ሌሎችንም አስፈላጊ እርምጃዎች መውሰድ የሚቻለው ግን አገራዊ መረጋጋት ሲሰፍን ነው። በመሆኑም እንደ አገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ በቁርጠኝነት መሥራት ይጠይቃል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ይንገስ ዓለሙ (ዶክተር) በበኩላቸው፤ የዋጋ ግሽበት በውስጣዊና ዓለም አቀፋዊ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል ያነሳሉ።
የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣ የማምረቻ ዋጋና የደመወዝ መጨመር፣ አላስፈላጊ የገንዘብ ሕትመት፣ አላስፈላጊ የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ግሽበቱን በማባባስ በኩል የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ የሚጠቅሱት ዶክተር ይንገስ፤ የገበያ ሰንሰለት መራዘም፣ ኅብረተሰቡ ገንዘብ ላይ እምነት ማጣትና አላስፈላጊ ግብይት መፈጸምና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችም የየድርሻቸውን አስተዋፅዖ ያበረክታሉ ሲሉም ይገልጻሉ።
የሥራ አጥነት መስፋፋት፣ የመንግሥት ገቢና ወጪ አለመመጣጠን፣ የአገሪቱ ምርታማነት መቀነስ፣ አለመረጋጋትና የወንጀልና የሙስና መስፋፋት፣ በምግብ ነክ ሸቀጦች ውስጥ ባዕድ ነገሮችን መቀላቀልና መሰል ችግሮችን እንደሚያስከትል ያመለክታሉ።
የዋጋ ግሽበት በኅብረተሰቡ ሕይወት ላይ በቀጥታ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ መተግበር እንደሚጠይቅ የሚገልጹት ምሑሩ፤ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን ከወቅቱ ጋር በሚጣጣም መልኩ መከለስ፣ ምርትና ምርታማነትን መጨመር ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
በተጨማሪም የሥራ ባሕልን ማሳደግ፣ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች በቀጣይነት ኢኮኖሚው ላይ እሴት የሚጨምሩ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ገቢ ምርት መተካት ላይ ያሉ ሥራዎችን ማጠናከር፣ ሙስናን መከላከልና የገበያ ሰንሰለቱን ማሳጠር ከመፍትሔ ሀሳቦች መካከል መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
ገበያ ላይ ያለው ምርትና ገበያ ላይ ያለው ገንዘብ ካልተመጣጠነ የዋጋ ግሽበቱን ማስተካከል ስለሚያስቸግር ምርትን መጨመር ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ይንገስ፤ ይህ እንዲሳካ ደግሞ ለአምራቾችና ኢንቨስተሮች የሚደረገውን እገዛና ክትትል ማጠናከር ያስፈልጋል። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ የዋጋ ግሽበቶችን ለመቀነስ የተሠሩ ሥራዎችን ከእኛ አገር አንጻር ቀምሮ መተግበር ያስፈልጋል ይላሉ።
እንደ ባለሙያዎቹ ማብራሪያ፤ አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ንረት ከፍተኛ የሚባል ነው። ለዚህ ችግር አስፈላጊ የመፍትሔ እርምጃዎች ተወስደው መስተካከል ካልቻለ ችግሩ ተባብሶ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ በመፍጠር አገሪቱን ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንድትገባ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015