
አዲስ አበባ:- በአመክንዮ፣ በሀሳብ የበላይነት እና በሰላም የሚያምኑ ምሑራንና ፖለቲከኞች ኅብረተሰቡን በተለይ ወጣቱን በማስተማር ሀገራቸውን ከጽንፈኝነት አደጋ ሊጠብቁ እንደሚገባ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ገለጹ፡፡
ዶክተር አረጋዊ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች የጽንፈኞች ሥራ ውጤት ነው፡፡ ጽንፈኞች ለኅብረተሰብ እድገት ደንታ የሌላቸው፤ ለክፉ ነገር የተነሳሱ በመሆናቸው ሰላም ወዳድ ዜጎች ማስተማር አለባቸው።
ጽንፈኛ ኃይሎች ፍላጎታቸው ኢትዮጵያን የጦርነት፣ የግጭት፣ የትርምስ እና የመገዳደል አውድማ ማድረግ ነው። ይህ እንዳይሳካ በሃሳብ ልዕልና እና በውይይት የሚያምኑ ምሑራን የሃሳብ ልዕልና የበላይነት እንዲያገኝና ሕዝቡ ራሱን ከነዚህ ኃይሎች እንዲጠብቅ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማስተማር እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።
ጽንፈኝነት ከአመክንዮ የወጣ አስተሳሰብ በመሆኑ ለእድገት ጸር ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ በአብዛኛው ‹‹የእኔ አመለካከት ብቻ ነው ልክ፣ የሌላው የተሳሳተ በመሆኑ አያስፈልግም መጥፋት አለበት›› የሚል እሳቤ የያዘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በርካታ ሲቪል ማኅበረሰቦች እና ፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ፤ እነዚህ ፓርቲዎች በውይይት መተማመን ባሕል እንዲሆን መሥራት ይኖርባቸዋል። ሚዲያ፣ መንግሥት እና የሃይማኖት ድርጅቶችም ሰዎች በውይይት፣ በጠንካራ የሃሳብ ልዕልና እንዲያምኑ ተከታታይ ውይይቶችን ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸውም መክረዋል።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ የሃሳብ ልውውጥ እንዲኖር በመሥራት ከውይይቱ ጠንካራው ሃሳብ ድጋፍ አግኝቶ ጎልቶ እንዲወጣ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል። ትግበራው የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ድርሻ ሊኖረው ይገባል። የነቃ የኅብረተሰብ ተሳትፎ በማድረግ ይህንን የትግበራው አካል ማድረግ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ የበላይነት የነበረበት ዘመን እንደሚበዛ ያስታወሱት ዶክተር አረጋዊ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው በጦርነት ነው። ለእውቀት፣ ለሃሳብ ልዕልና እና በውይይት ተማምኖ ለመቀጠል እድል ማግኘት አለበት ሲሉም መክረዋል።
በጽንፈኞች በመታፈን ገንቢ ውይይት ማድረግ አልቻለም። ወደኋላ የቀረነው ለዚህ ነው። የነቃው ኅብረተሰብም ይህንን ነገር ለማስተጋባት መነሳት አለበት። ጽንፈኛ አመለካከት ኅብረተሰብን የሚበትን በመሆኑ ይህ አስተሳሰብ ተንሰራፍቶ እስካለ ድረስ አገራዊ አንድነትን ለማስቀጠል እንደሚያዳግትም ገልጸዋል።
ጽንፈኝነት ካለ ትምህርት አይኖርም፣ እውቀት ለመገብየት አይቻልም፣ እድገት አይታሰብም። የአንድ ወገን ሃሳብ ብቻ የበላይነት እንዲያገኝ ያደርጋል። ይህ ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ ጦር ወደመማዘዝ ያስገባል ብለዋል።
ጽንፈኝነት ሁልጊዜ አደጋ ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ ጽንፈኛ አመለካከት ከአመክንዮ የወጣ አስተሳሰብ ነው። በየትኛውም ኅብረተሰብ ላይ ጽንፈኛ አመለካከት ካለ እርስ በእርስ አያስማማም፣ የጋራ አስተሳሰብ አንግቦ ለመሄድም ያስቸግራል ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ጽንፈኞች በየአቅጣጫው ጽንፍ አቋም እየረገጡ ኅብረተሰቡን ያውኩታል፣ ይከፋፍሉታል ለእርስ በእርስ ግጭትም ይዳርጉታል። በዚህ ምክንያትም አንድነትን ለማስጠበቅ ያዳግታል፣ ለኅብረተሰብ እድገትም ጠንቅ ነው። ይህ ሁኔታ በሀገራችን በተግባር እየታየ ያለ ችግር ነው ብለዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015