
አዲስ አበባ፡- የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ ሃገራቸው ከአፍሪካ ሀገራት እና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት እንደገና ለማጠናከር የምትፈልግ መሆኑንና ለዚህም መሳካት ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና እንዳላት አስታወቁ።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ ብራዚል ከአፍሪካ ሀገራት እና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት እንደገና ለማደስ የምታደርገው ጥረት ከሃገራቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና ግቦች አንዱ ነው።
ከአፍሪካ ሃገራት እና ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጋር ጠንካራ የዲፕሎማሲዊ ውይይት ለማድረግና ትብብርን ለማሳደግ ብራዚል ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ብራዚል እና ኢትዮጵያ በብዙ የዓለም ወቅታዊ ፈተናዎች ላይ የጋራ እሴት እና ራዕይ እንደሚጋሩ ያመላከቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ከነዚህም ውስጥ ዘላቂ ልማት አንዱ ነው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ አማራጭ የክፍያ ሥርዓት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አክለዋል ።
“ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ አማራጮችን የማዘጋጀት አስፈላጊነት ላይ ተሟጋች ናቸው። በምዕራብ አሜሪካ ካሉ አገሮች ጋር ያለን የንግድ ልውውጥ እንደ አንድ ተሞክሮ የሚወሰድ ነው።
“በብዙ ወገን መድረክ ላይ ያለው የፖለቲካ ውይይት እና ቅንጅት ሁለቱ ሀገራት እንደ ታዳጊ ሀገራት ያለንን የጋራ ራዕይ እና ዓላማ መሠረት በማድረግ ግንኙነታቸውን የበለጠ ሊያጠናክሩባቸው የሚገቡ ዘርፎች ናቸው” ብለዋል። ማውሮ ቪዬራ።
የቴክኒካዊ ትብብር ሌላው አስፈላጊ የግንኙነት ገጽታ መሆኑን የጠቀሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ፤ “የእኛ የትብብር ማዕቀፍ በክልሉ ውስጥ ውጤታማ ነው። የግብርና እና የምግብ ምርቶች የብራዚል ቴክኒካል ትብብር ሞዴል ለአካባቢው ማኅበረሰቦች ልዩነት ያመጣባቸው ዘርፎች ናቸው።
የኢትዮጵያ እና የቦሌ አየር ማረፊያ በአፍሪካ በዋና ማዕከልነት መጠናከር በቱሪዝም በኩል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ ዕድሎችን እንደሚፈጥር የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ ማዕከሉ ወደ እስያ እና መካከለኛው ምሥራቅ ለሚጓዙ ብራዚላውያን አዋጭ አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል፤ ይህም የቱሪዝም ፍሰትን ለማሻሻል ብዙ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።
“በተራዘመ ዓለም አቀፍ የበረራ ግንኙነት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጥቂት ቀናት ለመቆየት ለሚፈልጉ ብራዚላውያን የቱሪስት ፓኬጆች እንዲሰጡ በቪዛ ማመቻቸት በኩል በጋራ መሥራት አለብን።”
BRICS/ብሪክስ/፤ በዓለም መድረክ ላይ አግባብነት ያለው ተዋናይ ለመሆን የበቃው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ያሉት አምባሳደር ማውሮ፤ ይህ አባላቶቹ ያጋጠሟቸውን ዋና ዋና ተግዳሮቶች እና በአጠቃላይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ የመቻላቸው ውጤት ነው ብለዋል። ደቡብ አፍሪካ በአባልነት መገኘቷ ከአህጉሪቱ ጋር የሚደረገውን ግንኙነት እንደሚያሻሽለውም ተናግረዋል።
ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካም እ.አ.አ በ2024 እና 2025 የቡድን 20 ፕሬዚዳንትነት እንደሚረከቡ ገልፀው ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በመሆን ብሪክስ የጋራ አጀንዳዎችን በማስተዋወቅ ረገድ የበለጠ ሚና እንዲጫወቱ፤ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል መቀራረብ እና ትብብር እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
በአጠቃላይ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ እና ድህነት ቅነሳ እንዲሁም እኩልነትን በማስፈን ሂደት ላይ ፈተናዎችን በጋራ ለመዋጋት እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጉብኝታቸው የመጀመሪያ ቀን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተዋል።
ግርማቸው ጋሻው
አዲስ ዘመን ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም