ከማንም በፊት “ንባስል”ን ካለበት ፈልፍላ በማውጣት፣ ተገቢውን ኪነጥበባዊ ስፍራ በመስጠት ለዓለም አደባባይ ያበቃችው እውቋ ገጣሚት መቅደስ ጀንበሩ ናት። መቅደስ (ግን ምነው ድምፅዋ እንደዚህ ጠፋ??) የመጀመሪያ የሥነግጥም መድበሏን ከግጥሞቿ አንዱና ወካይ በሆነው ርእስ በመሰየም “ንባስል” (1984 ዓ.ም.) ብላው ለአገራችን ሥነግጥም የበኩሏን ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጋለች። ለሥነግጥም አድናቂ-አንባቢያንም በነፍስ ደርሳለች (በወቅቱ)።
“ንባስል” የሥነግጥም መድበል በታተመበት ዘመንም ሆነ ከዛ በኋላ በከፍተኛ ደረጃ ተነባቢ የሆነ፤ በበርካታ ስራዎች አብዝቶ ተጠቃሽ መሆን የቻለ፤ ለበርካታ የሥነጽሑፍ ተመራማሪዎች ከፍተኛ ግብዓት በመሆን እስካሁን ድረስ የዘለቀ … እጅጉን የተዋጣለት የፈጠራ ስራ ነው። (ስለ መድበሉ ከዚህ በላይ መሄድ ስለማንችል አንባቢ ፈልጎ እንዲያነበው እንጠቁማለን።)
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ያዘጋጀው “አማርኛ መዝገበቃላት” (2001 ዓ.ም) “ንባስል” (ንብኣስል)ን በሰዋሰው ክፍሉ “ስም” መሆኑን ከጠቀሰ በኋላ “መጠኑ ከጦስኝ ጋር የሚቀራረብ፣ መልኩ ነጣ ያለና ጥሩ መአዛ ያለው፤ ለቀፎ ማጠኛነት የሚያገለግል የዕፅዋት አይነት።” በማለት ያብራራዋል።
“ንባስል፤ (ንብ፡ አስል) ንጭ ሸቶ የሚመስል ቅጠል። አዲሱን ቀፎ መጀመሪያ ጥድ ሁለተኛ ንባስል ያጥኑታል። የንብ (ማእሰረ እግር) እግረ ማሰሪያ ነው ያላሉ። ዳግመኛም ንብ አስኰብላይ ተብሎ ይተረጐማል።” የሚል ማብራሪያም ከድረ-ገፅ ላይ ማንበብ ይቻሏል። መቅደስ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ይሰፍን ዘንድ ሁሉ ደርዝ ባለው ሁኔታ ሃሳቧን ያሰፈረችበት በ“ንባስል” ብቻም ሳይሆን በ“ሙጋ”ም ትታወቃለችና የሚቀጥለውን
(በበርካቶች የሚጠቀሰውን) ከዚሁ መድበል ጠቅሰንላት ወደ ተነሳንበት “ንባስል ተከላ”ችን እንምጣ።
ያን ጊዜ
እንደ ክፉ ምልኪ … ያስታውቃል ቀኑ
የተራሮችና የኮረብቶች ፍጅት
በእልህ በቁጭት ቃል … ሲበጠስ መረኑ
ከአፋቸው ሲወጣ እንደ’ሚነድ እሳት
ብርሃን አልባ ቀን … ሰማያት ሲጠቁሩ
ወፎቹ ሲሸሹ ነጻነት ፍለጋ
ሲመሽ ያስታውቃል … ያን ጊዜ ጠርጥሩ
ድምጻችሁ ሲታፈን ተስፋችሁ ሲላጋ
ውንጀላ ሲበዛ … መግባባት ሲጠፋ
መተንፈስ እንደ ዕዳ … እጅ ካሳበተ
ህልም ለሽልማት ለሹመት ሲጋፋ
ያ መጨረሻ ነው ምልክት ለእናንተ።
“ንባስል” ማለት ከላይ እንደ ተሰጠው ትርጉም ከሆነ ያለ ምንም ጥርጥር ሁሉም በየ ቀዬው፣ በየደጁ፤ በየ ጓጥ ስልጓጉጡ … ሊተክለው ይገባል ማለት ነው። በየከተሞች (በተለይ አዲስ አበባ) … ንባስልን ሊተክሉ ግድ ይላል ማለት ነው። ንባስልን ግለሰቦች፣ ከተሞች … ብቻ አይደሉም ሊተክሉት የሚገባቸው። ተቋማትም (የሲቪል፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ …) ሊተክሉት፤ ተክለውም አካባቢያቸውን በምርጥ መአዛ ሊያውዱ ይገባል። አካባቢያቸው ላይ ተውሳክ ካለ ከተውሳኩ ይገላገሉ ዘንድ በንባስል ሊያጥኑትና ወደ ነበረ ተፈጥሯዊ ሰላማቸው ሊመለሱ ግድ ይሆናል። ያኔ የንባስል ምንነትና ጥቅሙ ግልፅ ይሆናል ማለት ሲሆን፤ ለተከላውም ርብርቡ ይጧጧፋል።
በተለይ አሁኑ ወቅቱ ለንባስል ተከላ ምቹ ከመሆኑ አኳያ (በወቅትም፣ በፖሊሲም፣ በበጀትና የሰው ሃይልም …) እንደ ሌሎች የዕፅዋት አይነቶች ሁሉ ንባስልም ከላይ በጠቀስናቸውና ባልጠቀስናቸው ስፍራዎች ሁሉ በብዛትና በስፋት ሊተከል ይገባል። ንባስል መትከል አካባቢን ከማስዋብ የዘለለ ፋይዳ እስካለው ድረስ ላለመትከል የሚቀርብ ምንም አይነት ምክንያት ሊኖር ስለማይችል የተከላው ጉዳይ ምንም ሊያከራክር አይገባም ማለት ነው። በተለይ የ“ህዳር ሲታጠን” መስራችና ባለቤት ለሆነች አገር፤ ከ“ህዳር ሲታጠን” በኋላ ያለውን ሥነልቦናዊ፣ መንፈሳዊ፣ ባህላዊ … ወዘተ ፋይዳዎችን በሚገባ ለሚያውቅ ሕዝብ … ንባስል መትከል ብርቅ ሊሆን አይችልምና “ንባስል ይተከል!!!” ስንል ያለ ምክንያት፣ ያለ ምንም ታሪካዊ ዳራ አለመሆኑን ከወዲሁ ልንረዳ የግድ ይሆናል።
ስለ ንባስል አነሳን እንጂ ለነገሩ በአገራችን የእፅዋትን ውለታ ማንም ሊተካው በማይችል መልኩ ፋይዳቸው ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም።
ግዛዋ ካለ ደጅሽ፣
ለምን ሞተብሽ ልጅሽ?
የሚለውን ቃል-ግጥም ላስታወሰ የግዛዋን ሕይወት አድን ተግባር ከመገንዘብም ባለፈ ግዛዋን ጓሮ መትከል ምንኛ ጠቃሚ እንደ ሆነ ሁሉ በውል ይገነዘባልና የዕፅዋት መህበረ-ባህላዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚገመት አይደለም ማለት ሲሆን፤ ንባስልም ከዚሁ አኳያ የሚታይ ይሆናል።
እርግጥ ነው ንባስልን ለየት የሚያደርገው “ማጠንት” መሆኑና የአካባቢን ሰንኮፍ፤ ብልሹ ባህርይን፣ የተጣባን መጥፎ ጋኔል፣ ግደል ግደል የሚልን መጥፎ አባዜ ወይ በመአዛው፤ አልያም በጭሱ (ማጠንቱ) ነቅሎ ከመጣል፣ በሽታን፣ ተውሳክን … ከማስወገድ አኳያ ፋይዳው ከ“ልጅን ማዳን” የዘለለ አገርና ሕዝብን የመታደግ አቅም ስላለው ከግዛዋ ከፍ ያለ፣ በማአዛው አገር ሰፈርን የሚያውድ፤ በጭሱ አካባቢን ሁሉ የሚታደግ መሆኑ ነው። ከዚህ አኳያ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመዝነው ገጣሚት መቅደስ ጀምበሩ የርእስ ምርጫ ከትክክልም በላይ ነውና ስናጨበጭብላት ቆመን ነው – “ንባስል”!!!
የወቅቱ የዓለማችን አጠቃላይ ይዞታ እያንዳንዱን የዓለም አካል “መፍትሄ አምጣ” በማለት የሚያፋጥጥበት ወቅት ነው። ዓለም እንደ ዓለም፣ ሰውም እንደ የሰው ልጅ መቀጠል ያለበት ከሆነ ሁሉም ይህንን የሚያስቀጥል የመፍትሄ ሃሳብ ሊያፈልቅ የግድ ሲሆን ይህ ገጽም እንደ አንድ የመፍትሄ አካል ይወሰድ ዘንድ “ኑ ንባስል እንትከል!!!” በማለት የረር ተራራ ላይ ቆሞ ይጣራል። በተለይ ከአርንጓዴ አብዮትም ሆነ አረንጓዴ ኢኮኖሚ አኳያ ጉዳዩ በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ ሰኔ ግም ሲል የንባስል ተከላው ጉዳይ ይጧጧፍ ዘንድ ወቅቱ ይጋብዛል። ካልሆነ መታጠንና አስቸኳይ ፈውስ ማግኘት የሚገባው ሁሉ ሳያገኝ ሊቀር ይሆናልና ጉዳዩ እዳው ገብስ አይደለም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም