ፌስቡክ እና የዓለም ቅርጽ

የዓለምን ቅርጽ የሚቀይሩ የተለያዩ ክስተቶች ይኖራሉ:: ለምሳሌ፤ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዓለም ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ነው:: የብዙ ነገሮችን ታሪካዊ ዳራ ወይም የተለያዩ የርዕዮተ ዓለም አሰላለፎችን ስታነቡ፤ ሁለተኛው ወይም አንደኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ሆኖ ታገኙታላችሁ:: ‹‹ደግሞ እዚህ ውስጥ ምን አስገባው?›› እስከሚያስብል ድረስ በብዙ ነገሮች ውስጥ ምክንያት ሆኖ እናገኘዋለን::

የቴክኖሎጂ ውጤቶችም እንደዚሁ ናቸው:: በተለይም መገናኛ ብዙኃን የዓለምን መልክ በመቀየር ከፍተኛ ድርሻ አላቸው:: ዓለም መንደር የሆነችው በእነዚህ የቴክኖሎጂ አውታሮች ነው:: እነዚህ የመገናኛ ብዙኃን የቴክኖሎጂ ዓይነቶች ከጋዜጣ ወደ ሬዲዮ፣ ከሬዲዮ ወደ ቴሌቪዥን፣ ከቴሌቪዥን ወደ በይነ መረብ….. እያደጉ ሄደው የበይነ መረቡ ዓለም ዓይነቱንና ቅርጹን እያሳደገ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ መነጋገሪያ የሆኑት የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ደርሷል:: ሰው ሠራሽ አስተውሎት(AI) የሚባለውም የዚሁ ቴክኖሎጂ ውጤት ነው:: ይህ ደግሞ ጭራሽ ይባስ ብሎ ራሱን የሰውን ልጅ የሚተካ ሆኗል:: በዚህ ጉዳይ ላይ ዓለም ወደፊት ምን ዓይነት ዕጣ ፋንታ እንደሚኖራት የዓለም ልሂቃን እየተከራከሩበት ነው::

ነገሩን በኢትዮጵያ ዓውድ እንየውና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የባህል፣ የፖለቲካና የንግድ አብዮት ፈጥረዋል:: ይህ ባህሪ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሁኔታ ነው:: የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲባል ቁጥር አንድ ላይ የሚቀመጠው ፌስቡክ ነው:: በሀገራት ላይ ባላቸው ተፅዕኖ ሲታይም ቁጥር አንድ ላይ የሚቀመጠው ፌስቡክ ነው:: ፌስቡክ በዓለም ላይ የፈጠረውን ተፅዕኖ ጥናቶችን ዋቢ አድርገን እናያለን:: ከዚያ በፊት በኢትዮጵያ ያለውን ድርሻ እና የፈጠረውን አብዮት እንመልከት::

ፌስቡክ ገና ፋሽን በነበረበት ከ2010 ዓ.ም በፊት በነበሩት ዓመታት የጋዜጦችና መጽሔቶች አጀንዳ ሆኖ ነበር:: ጊዜን የሚገድል፣ ሰዎችን የሚያቦዝን፣ ትዳርን የሚያፋታ፣ ባህልን የሚበርዝ…. እየተባለ ይወገዝ ነበር:: በተለይም በኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ ፖለቲካን የሚያቀጣጥል ነው እየተባለ በመንግሥት ይወቀስ ነበር:: የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአንድ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ስለፌስቡክ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ አራጋቢነት ተናግረው፣ ዓለም ቁጥጥር ሊያደርግበት እንደሚገባ አሳስበው ነበር:: በወቅቱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች የወቀሳ ሀሳብ ተሰንዝሮባቸው እንደነበር አስታውሳለሁ:: አቶ ኃይለማርያም የተናገሩት ግን ትክክል ነበር ማለት ነው፤ ከእርሳቸው ንግግር በኋላ የተሠሩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ይህንኑ እውነታ የሚገልጹ ናቸው::

በእነዚያ ዓመታት ፌስቡክ በጊዜ ገዳይነቱ፣ በትዳር አደናቃፊነቱ በመሳሰሉት ወቀሳ ቢሰነዘርበትም ተፅዕኖውን ማስቆም ግን አልተቻለም:: ጭራሽ እየባሰ ሄዶ ዋናዎቹን መገናኛ ብዙኃን (ራሳቸው ጋዜጣና መጽሔቶችን) የሚገዳደር ሆነ:: ይባስ ብሎ እነርሱን ከገበያ አስወጣቸው:: ምንም እንኳን የኅትመት ሚዲያው የራሱ ሀገራዊና ግላዊ (ተቋማዊ) ድክመት የነበረበት ቢሆንም የፌስቡክ ጫናም ቀላል አልሆነም::

ባልና ሚስትን ያፋታል የሚል ወቀሳ ሲወርድበት የነበረ ቢሆንም ብዙ ሰዎችን ደግሞ ባለትዳር አድርጓል:: ይህ እንግዲህ የዘመን ባህሪ ነው:: በድሮው ጊዜ በሎሚ ውርወራ እና በጠቀሳ ይደረግ የነበረው መግባባትና መተዋወቅ አሁን በዲጂታል አማራጭ ሆነ ማለት ነው:: በፌስቡክ ተዋውቀው የተጋቡ ብዙ ታሪኮችን ሰምተናል::

በዚያው ልክ ደግሞ ብዙ ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች እንዲፈጠሩ አድርጓል:: የግለሰቦችን ገመና በማውጣት እስከ ፍርድ ቤት እና ፖሊስ ጣቢያ የደረሱ ወንጀሎች ተፈጽመውበታል:: አማራጩ በፈጠረው ዕድል የውስጥ ሰውነትን ፎቶ በመላላክ በተለይም ሴት ልጆችን ማስፈራሪያ ሆኗል:: በታዋቂ ሰዎች ሳይቀር የከነፈ ፍቅር በገቡበት ወቅት የተነሷቸውን የራቁት ፎቶዎች ልክ ሲጣሉ ‹‹ፎቶውን እንዳላወጣብሽ››› በሚል ማስፈራሪያ ሆኗል:: ይህ ፕላት ፎርሙ የፈጠረው ችግር ብቻ ሳይሆን የሰዎች ደካማ አመለካከት መኖር ነው:: ዲጂታል አማራጩ የውስጥ ገመናን መያዝ የሚያስችል ምሥጢራዊ ኮድ ያለው ነው:: ሆኖም ግን በሰዎች ክፋት እና ደካማነት ማስፈራሪያም አድርገውታል::

በሥራ ዕድል ፈጠራ በኩል ፌስቡክ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል:: ሰዎችን እና ሥራዎችን አገናኝቷል:: ሥራዎቻቸውን በፌስቡክ በማስተዋወቅ ራሳቸውን መሸጥ ችለዋል:: ብዙዎች ያላቸውን የጽሑፍ ችሎታ አስተዋውቀውበት መጽሐፍ ጽፈዋል:: በታዋቂነታቸው ንግድ ጀምረው ተሳክቶላቸዋል:: እነዚህን ዕድሎች የፈጠረው ሰዎችን ከሰዎች የሚያስተሳስር አማራጭ በመሆኑ ነው::

የስዊድኑ ለንድ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የማኅበራዊ ሚዲያ መሣሪያዎች ለፖለቲካ›› በሚል ርዕስ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት (2024) ይፋ ባደረገው ጥናት የማኅበራዊ ገጽ አማራጮችን ንፅፅር ሠርቷል:: ለንፅፅር የተቀመጡት (በቅደም ተከተል)፤ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ትዊተር፣ ዩትዩብ፣ ረዲት፣ ስናፕቻት፣ እና ኋትስ አፕ ናቸው:: ጥናቱ የተሠራው በኃያላኑ ሀገራት ስለሆነ እነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች አይነታቸውና ሥርጭታቸው ከኢትዮጵያ ጋር የተለያየ እንደሚሆን ይጠበቃል:: ለምሳሌ፤ ዩትዩብ ኢትዮጵያ ውስጥ ቴሌቪዥንን ተክቶ የሚሠራ ስለሆነ ምናልባትም ከፌስቡክ ቀጥሎ የፖለቲካ ሚዲያ ሀሳብ ማንሸራሸሪያ ይመስላል::

ጥናቱ የተሠራው ኃያላን እና የሚዲያ ነፃነት ያላቸው ናቸው በሚባሉት እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና ካናዳ ነው:: በእነዚህ ሀገራትም የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች የፖለቲካ ማራገቢያ ሆነዋል ማለት ነው:: ጥናቱ እንደሚለው መረጃው የተሰበሰበው በአውሮፓውያኑ ከ2019 እስከ 2021 ባሉት ሁለት ዓመታት ነው:: የቅርብ ጊዜ መረጃ ነው ማለት ነው::

ጥናቱ እንደሚለው፤ በ50 ሀገራት ላይ በተደረገ ጥናት ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ከፍተኛ የተጠቃሚ ቁጥር ያለው ፌስቡክ ነው:: የፖለቲካ ሀሳቦች ማንሸራሸሪያም ይሄው ፕላትፎርም ነው:: በተለይም ከአውሮፓውያኑ 2012 በኋላ ዓለም አቀፍ ገናና ፕላትፎርም ሆኗል::

የእነዚህ ሀገራት ጥናት ለኢትዮጵያም ተቀራራቢ ይመስላል:: እንደ ኢንስታግራምና ኋትስ አፕ የመሳሰሉት ለዜና ማሰራጫ ሲያገለግሉ አይታይም:: በዚህ ጥናት ውስጥ ያልተካተተው ቴሌግራም በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ሳይኖረው አይቀርም:: ምክንያቱም ዋናዎቹ ሚዲያዎች የቴሌግራም ቻናል አላቸው:: ፌስቡክ ላይ ያለውን የፖለቲካ ንትርክ ማየት የማይፈልጉ ሰዎች መረጃ የሚያገኙት በቴሌግራም ብቻ ስለሆነ ብዙ ተጠቃሚ ይኖረዋል ብሎ መገመት ቀላል ነው::

በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ተጠቃሚ ያለው ፌስቡክ ነው:: ይህ የሆነበት ምክንያት የፕላትፎርሙ ባህሪ ነው:: ረዘም ያሉ ጽሑፎችን ለመጻፍ፣ ጽሑፎችን ለማጋራት፣ ግብረ መልስ ለመመላለስ… የተመቸ ስለሆነ ነው:: ምስል እና ድምፅ ማቀናበር ሳያስፈልግ በቀላሉ በጽሑፍ ብቻ ብዙ ሀሳብ መግለጽ ስለሚቻል ነው:: በቀጣይ ምን ዓይነት አማራጭ እንደሚመጣ ባይታወቅም እስካሁን ባለው በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ስለሆነ ነው:: በሌላ በኩል የኢንተርኔት ዳታ አጠቃቀሙ በቪዲዮ ከሚታዩት የተሻለ ቀለል ስለሚል ነው፤ ይህ ምናልባት በኢትዮጵያ ዓውድ ሊሆን ይችላል::

በአጠቃላይ ፌስቡክ በዓለም ላይ የፖለቲካ፣ የባህል፣ የሥነ ልቦና እና የብዙ ነገሮች አብዮት በመፍጠር ዓለምን የቀረጸ ክስተት ነው:: ይህን ፕላትፎርም የፈጠረው ማርክ ዙከርበርግ የተወለደበትን የግንቦት ወር ምክንያት በማድረግ ፌስቡክ በዓለም እና በኢትዮጵያ ያበረከተውን ድርሻ እናስታውስ ብለን ነው::

በዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You