ግብርና የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕይወት መሰረት ነውና ስለግብርናው ዘርፍ ደግሞ ደጋግሞ ማውራት ተገቢ ነው። በተለይም፣ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛው ዓመታዊ የግብርና ምርት የሚገኝበት፣ የመኸር እርሻ ስራ በሚከናወንበት በአሁኑ ወቅት ስለግብርናው መጠየቅና መከታተል እጅግ አስፈላጊ ነው። የግብርናው ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሰረት ስለሆነ የዚህ ወሳኝ ዘርፍ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል። የእርሻ ስራው፣ የግብዓት አቅርቦቱና ሌሎች ተያያዥ የግብርና ጉዳዮች ዕለታዊ ክትትል ይፈልጋሉ። የጎደለውን መሙላት፤ የተበላሸውን ማስተካከል ያስፈልጋል።
የክረምት ወራት የመኸር እርሻ የሚከናወንባቸው ጊዜያት በመሆናቸው አርሶ አደሩ፣ የልማት ጣቢያ ሰራተኛው እንዲሁም አመራሩ ሁሉ ወደ ማሳ ዘልቆ ደፋ ቀና ሲል መታየቱ የተለመደ ተግባር ነው። አርሶ አደሩ ያርሳል፤ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ሙያዊ/ቴክኒካዊ ድጋፍ ይሰጣሉ፤ አመራሩ ደግሞ ከአርሶ አደሩና ከባለሙያዎች በሚቀርቡ ጥያቄዎች መሰረት የጎደለው እንዲሟላ ትዕዛዝ ይሰጣል፤ ክትትል ያደርጋል። የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ ሀገሪቱ የግብርና አቅሟን ተጠቅማ ከድህነት እንድትላቀቅ ለማድረግ ከሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦች መካከል አንዱ የግብርና ግብዓቶችን አስተማማኝ በሆነ መጠንና ጥራት ማቅረብ ነው። ከእነዚህ የግብርና ግብዓቶች አንዱ የአፈር ማዳበሪያ ነው። የኢትዮጵያ አርሶ አደር ባለፉት ዓመታት የአፈር ማዳበሪያን መጠቀሙ ሀገሪቱ ከእርሻ የምታገኘው ምርት በየዓመቱ እንዲጨምር አስችሏል።
ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ስለአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት የሚሰማው ዜና አምራቹን አርሶ አደርም ሆነ ሸማቹን ከተሜ በየዓመቱ ለጭንቀት የሚዳርግ እየሆነ ነው። የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ለእርሻው ዘርፍ ከባድ ፈተና ሆኗል። እጥረቱ ባለፈው ዓመት እንደነበር ቢታወስም የዘንድሮ ግን ካለፉት ዓመታት ሁሉ የበለጠ ከባድ እንደሆነ ከአርሶ አደሩ ምሬትና ጥያቄ መገንዘብ ይቻላል። አርሶ አደሩ ለእርሻ ስራው የሚያስፈልገውን የአፈር ማዳበሪያ በሚገባ እያገኘ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ እየገለፀ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ በማጣታቸው ምክንያት ያለማዳበሪያ ለመዝራት መገደዳቸውን ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ምርት እንዲቀንስ ማድረጉ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው። ‹‹ጥያቄዬ ሰሚ ቢያገኝ›› በሚል ተስፋም ጅራፋቸውን ይዘው ወደ አደባባይ ወጥተው ጥያቄያቸውን ያቀረቡ አርሶ አደሮችንም ተመልክተናል።
ነገሩን እጅግ አሳዛኝና አስገራሚ የሚያደርገው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያ በነጋዴዎች መጋዘንና በግለሰቦች ቤት ውስጥ ተከማችቶ መገኘቱና እጅግ በተጋነነ ዋጋ ለአርሶ አደሮች ሲቀርብ መታየቱ ነው። ይህ ድርጊት የሚፈፀመው የመንግሥት አመራሮችና ነጋዴዎች በሚፈጥሩት አስነዋሪ የጥቅም ሽርክና ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። አገሪቱን ከላይ እስከታች ድረስ አንቆ የያዛት ሙስና እዚህ ደርሷል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹በሙስና ውስጥ አለመሳተፍ እና ሙስናን መዋጋት ወንጀል ነው›› የተባለ እስኪመስል ድረስ የወንጀሉ ተሳታፊ ለመሆን የሚደረገው እሽቅድድም እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ነው።
በጉቦ፣ በምዝበራ፣ በማጭበርበና በሌሎች የሙስና መልኮች የሚፈፀመው የወንጀል ብዛትና ዓይነት ታይቶም ተቆጥሮም አያልቅም። ይህ አሳፋሪ ተግባር የማዳበሪያ አቅርቦት ድረስ ዘልቆ ገብቶ አርሶ አደሩም ሆነ ከተሜው በረሃብ እንዲያልቅ ምክንያት ሊሆን ነው። በእርግጥ ሙስና በኢትዮጵያ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ መገለጫም እየሆነ ነው። ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› በሚል ብሂል የሚኖር እና ሀቅንና መርህን ተከትሎ ስራን የሚሰራን ሰው ‹‹ሞኝ፣ ጅል›› ብሎ በሚያሸማቅቅ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖር ሙሰኛ ሹመኛና አጭበርባሪ ነጋዴ፤ ማዳበሪያ ከአርሶ አደሩ ነጥቆ በውድ ዋጋ እየሸጠ ሲካፈለው መመልከት ላያስገርም ይችላል። ዝቅጠታችን እዚህ መድረሱ በእጅጉ ያሳፍራል!
በመንግሥት በኩል ለአፈር ማዳበሪያ እጥረት ምክንያት ናቸው የተባሉ ጉዳዮች ሲዘረዘሩ መስማት የተለመደ ነው። አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታትም ሲጠቀሱ የነበሩ ናቸው። ግን ምክንያት መደርደሩ የዘር ወቅቱ ላለፈበት አርሶ አደር ምን ይፈይድለታል? ምንም! ‹‹ከወደብ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች፣ የትራንስፖርት እጥረት፣ ጅቡቲ ደርሷል …›› የሚሉ ምክንያቶች ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ ይሆናሉ? አይሆኑም! ሰላምና ፀጥታን አስፍኖ የማዳበሪያ አቅርቦቱን ፈጣንና አስተማማኝ ማድረግ፣ ነውረኛ በሆኑ ሌባ ሹማምንትና ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ እንዲሁም የማዳበሪያ አቅርቦቱን ሊያሰናክሉ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በማሰብና በቂ ዝግጅት በማድረግ ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው።
በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል። በመንግሥትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ትብብር በተተገበሩት ተከታታይነት ያላቸው የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ያሳደጉና የሕዝቡን፣ በተለይም የአርሶ አደሩን፣ ሕይወት ያሻሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ከግብርና የሚገኘው ምርት በየዓመቱ ጭማሬ አሳይቷል፤ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍልም ከድህነት መላቀቁንና ብዙ ባለሀብት አርሶ አደሮች ማፍራት መቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ካላት አቅም አንፃር ሲመዘኑ ለአገሪቱ የምግብ ዋስትና፣ የስራ እድል ፈጠራና የምጣኔ ሀብት እድገትም ሆነ ለዘርፉ ችግሮች አስተማማኝ መፍትሄ የሰጡ አይደሉም። አሁንም ግብርናው በዘላቂነት ከኋላ ቀር አስተራረስና ከዝናብ ጥገኝነት አልተላቀቀም፤ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ከመጠቀም የራቀ ሆኖ ይታያል። ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች እየኖሩ ነው። በአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥን እስካሁን ድረስ እውን ማድረግ አልተቻለም። የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ በሌሎች የግብርና ግብዓቶች ላይ የሚስተዋለው የአቅርቦት እጥረት እስካሁን በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ወደኋላ እንዳይመልሳቸው ያሰጋል።
የአገሪቱ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች የተሻለ ምርታማና ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የግብርና ግብዓቶች እጥረት ነው። የግብዓቶቹ አቅርቦት መዘግየት እና የዋጋ ውድነት አርሶ አደሩን ከግብዓት በማራቅ ምርቱ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርጉታል። ይህ የአርሶ አደሩ ውድቀት ደግሞ የአገር ውድቀት ይሆናል። በግብርናው ዘርፍ የምትፈፀም አንዲት ቅንጣት ስህተት እጅግ አደገኛ አገራዊ ውድቀትን እንደምትጋብዝ መዘንጋት አይገባም! ስለሆነም የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ለግብርናው ዘርፍ ስኬት አስፈላጊ ለሆኑ ግብዓቶች አቅርቦት ሁሉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። አለበለዚያ ግብዓት ሳያቀርቡ ምርት እንዲያድግና አገር እንድትሻሻል መጠበቅ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ይሆናል።
የዘንድሮው ግብርና ቀደም ባሉት ወራት በተከሰቱት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች (ድርቅና አለመረጋጋት) ምክንያት ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው። በእነዚህ አደጋዎች ምክንያት ባለፈው የምርት ወቅት ምርት የቀነሰባቸውን አካባቢዎች ዘንድሮ የተሻለ ምርታማ በማድረግ ማካካስና ከዘርፉ የሚጠበቀውን አገራዊ የምርት መጠንም ማሳደግ ያስፈልጋል። የግብርናው ዘርፍ ለአፍታም ቢሆን ትኩረት ሊነፈገው አይገባም። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግብርና ዘንግተው መኖር አይችሉም። [ቢያንስ ለዓመታት በምኞት ላይ የኖረው ‹‹ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ›› እውን እስከሚሆን ድረስ ግብርናውን መዘንጋት አንችልም]
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም