በጎልማሳነት የመጀመሪያዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ነው የምትገኘው። ደመ ግቡ ፊቷ ያለፈችበትን አስቸጋሪ ህይወት የሚያሳብቅ ሳይሆን በድሎት የኖረች ያህል ነው የሚያስመስላት። ሶስት ልጆችን ባየችበት ዕድሜዋ ከአረብ አገር የቤት ውስጥ ሥራ ጀምሮ እስከ መንገድ ላይ የጀበና ቡና ጠጡ ሥራ ድረስ የተለያዩ ሥራዎችን ከውናበታለች።
አንዱን ሥራ ስትጀምረው አልሆን ሲላት ሌላውን ስትሞክር እያለች አሁን ላይ በጋርመንት ዘርፉ ሶስት የልብስ መስፊያ ማሽኖችን ይዛ ለማደግ እየጣረች ትገኛለች። የሥራ ጥረቷን የተመለከቱ ጎረቤቶቿ የተትረፈረፈ ሃብት ባይኖራትም ለሌሎችም አርአያ መሆን የምትችል ጠንካራ ሴት መሆኗን ይመሰክራሉ።
የወደፊት ህልሟ ትልቅ ነው፤ በዘመናዊ መልክ ዲዛይን አድርጋ የምትሰፋቸው ልብሶች እስከ ውጭ አገራት ገበያ ድረስ እንዲሄዱ እና በስሟ የጋርመንት ፋብሪካ እንዲኖራት አልማለች። ለዚህ ህልሟ መሳካት እንዲረዳት ደግሞ የእራሷን ሰፊ ሥራ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በአልባሳት ምርት ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሚያመጡላትንም ተባራሪ ሥራ ሳትንቅ እየሰራች ወደገቢ ማስገኛነት እየቀየረችው ይገኛል።
ሙሉ ስሟ ወይዘሮ ዓለም አምታታው ትባላለች ። ትውልድ እና ዕድገቷ አዲስ አበባ መሿለኪያ አካባቢ ነው። በልጅነት ጊዜዋ ገና ሀሁ መቁጠር ከጀመረችበት ወቅት አንስቶ ስታድግ የትራፊክ ፖሊስ የመሆን ፍላጎት እንደነበራት ታስታውሳለች። በአንድ እጁ በሚያሳየው ምልክት በርካታ መኪናዎችን የሚያስተናብረው የትራፊክ ፖሊስነት ሙያ ቀልቧን ቢስበውም ቅሉ ገና ትምህርቷን ሳትጨርስ ነበር ወደ ንግዱ ዓለም የተቀላቀለችው።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ስትሸጋገር በመዲናዋ በሚገኘው ፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤት ነበር የገባችው። በወቅቱ ደግሞ እናቷ በጨርቃ ጨርቅ ንግድ ላይ ይሰሩ ነበርና እርሷንም እንድትገባበት የቤተሰብ ግፊቱ ከፍተኛ ነበር። የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ከቤተሰብ ያገኘችውን አምስት መቶ ብር ይዛ ንግዱን ለመቀላቀል ተነሳች።
የጀመረችውን የዘጠነኛ ክፍል ትምህርት አቋርጣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለች የጨርቃጨርቅ ንግዱን ተቀላቀለች። ንግዱ ደግሞ በድሬዳዋ የሚገኙ በቦንዳ የታሸጉ ያገለገሉ ልብሶችን ገዝቶ አዲስ አበባ ላይ እያመጡ መሸጥ ነበርና ለወጣቷ ዓለም እጅግ ፈታኝ ሆኖባት እንደነበር ታስታውሳለች።
አሁን ወጣቷ ዓለም ቀስ በቀስ ሥራውን እየለመደች መጥታለች። ልብሶቹንም ከድሬዳዋ እያመጣች በልባሽ ጨርቃጨርቅ ንግድ ቦታነቱ በሚታወቀው አዲስ አበባ ኮልፌ 18 የተባለው ስፍራ ላይ በጠዋት መሸጡን ተያያዘችው። የተወሰነ ትርፍም ማግኘት በመጀመሯ ተደስታለች።
እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ለንግድ የሚሆናትን ተጨማሪ አልባሳትን ለማምጣት በባቡር ተሳፍራ ድሬዳዋ ገባች። ያገኘችውንም ሸማምታ በተሳፈረችበት ባቡር ወደትውልድ ከተማዋ ስትመለስ ግን አዋሽ ላይ ያልጠበቀችው ነገር ተከሰተ።በባቡር ይዛቸው ስትጓዝ የነበሩት አልባሳት ቀረጥ ያልተከፈለባቸውና የኮንትሮባንድ አሻራ ያረፈባቸው ነበሩና ከፖሊሶች ጋር ተፋጠጠች።
በወቅቱ ምንም ህጋዊ መከራከሪያ አልነበራትምና በገዛ ገንዘቧ የገዛቻቸውን አልባሳት ለኮንትሮባንድ ተቆጣጣሪዎች አስረክባ ባዶ እጇን ወደአዲስ አበባ ተመለሰች። በወቅቱ የተወረሰባት ደግሞ ሶስት ሺ አምስት መቶ ብር የሚያወጣ ንብረት ነበርና ኪሳራው እጅጉን አበሳጭቷት ነበር።
ከዚህ በኋላ የጨርቃጨርቅ ኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ መሳተፉን አልወደደችውምና በቀጥታ ያመራችው ወደሸቀጣሸቀጥ ንግድ ነበር። አዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ ኮንቴይነር ሱቅ በአራት መቶ ብር ተከራይታ ሸቀጣ ሸቀጦችን መሸጥ ጀመረች።
ለሁለት ዓመታት ቡና፣ ስኳር እና የተለያዩ የምግብ ፍጆታዎችን በአነስተኛ ሱቋ ብታቀርብም ትርፉ ግን ሊያዋጣት አልቻለም። በመሆኑም ለሁለት ዓመታት የሰራችበትን የሱቅ ንግድ ለመተው ወስናለች። እናም በአነስተኛ ዋጋ ማጣሪያ አድርጓ የሱቅ እቃዎቿን ከሸጠች በኋላ ወደ ግሮሰሪ ሥራ ነበር ያመራችው።
ወይዘሮ ዓለም በአዲስ አበባ ቡልጋሪያ ኤምባሲ አካባቢ በወር ስምንት መቶ ብር በተከራየቻት ዛኒጋባ ቤት የተለያዩ መጠጦችን መነገድ ጀምራለች። በተከራየችበት ግሮሰሪ ቤት ደግሞ ሌላ ሴት ምግብ ስትነግድ እርሷ ግን የምትሸጠው አልኮል መጠጦችን ብቻ ቢሆንም ጥሩ ገቢ ታገኝ እንደነበር ታስታውሳለች። ይሁንና ዓለምን ያስቸገራት ነገር የመጠጥ ደንበኞች የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪ ነው።
ሴትነቷን የሚፈልጉ እና የሚያስቸግሯት ወንዶችን ባህሪ ልትቋቋመው አልቻለችም። በጊዜው ደግሞ ትዳር መስርታ ሁለት ልጆችን የምታሳድግበት ወቅት ነበርና የግሮሰሪ ንግዱን መተው እንዳለባት ወስናለች። ገቢው የተስማማትን የግሮሰሪ ንግዱን ለሁለት ዓመታት እንደሰራችበት ‹‹ከእኔ ባህሪ ጋር የሚሄድ አይደለም›› ብላ ንብረቶቿን ሻሸጠች። የተቀሩትንም ቤቷ አስቀመጠቻቸው።
ከግሮሰሪው ንግድ ስትወጣ ግን ህይወቷን ከኢትዮጵያ ውጪ የምትመራበት አዲስ መንገድ ተፈጠረ። የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ የወይዘሮ ዓለም ሴት ጓደኛዋ ወደ አረብ አገር ብትሄድ ሰርታ መለወጥ እንደምትችል እና የተሻለ እንደምትጠቀም ነግራ መንገዱን አሳየቻት። ወይዘሮ ዓለምም የቪዛ ሂደቱን ጨርሳ በኤጀንሲ በኩልም ጉዞ ወደ አረብ አገር አደረገች።
ኑሮ በአረብ አገር እንደጠበቀችው አልሆነላትም። በቤት ሰራተኝነት ከምታገኘው ሁለት ሺ አምስት መቶ ብር የወር ደመወዝ ባለፈ ሥራው እና እንግልቱ አድክሟታል። አንድ ዓመት ከመንፈቅ በቤት ሠራተኝነቱ ተቀጥራ እንደሰራች ግን ለምን ጠፍተሽ ሁለት እና ሶስት ቤቶች በኮንትራት አትሰሪም የሚሉ መካሪዎች አጓጠሟት።
ከተቀጠረችበት ቤት ጠፍታ በህገወጥ መንገድ ሁለት ቤት ተቀጥራ በሰዓት መስራቱን ተያይዛዋለች። ክፍያው እጥፍ ቢሆንላትም በዚያው ልክ የቤት ኪራዩ እና ወጪው ናላዋን ያዞራት ገብቷል። ስድስት ወራትን በህገወጥ መንገድ እንደሰራች ግን የፖሊስ እጅ ላይ ወደቀችና ታስራ ወደ አገሯ ተላከች።
አዲስ አበባ ላይ ድንቡሎ ሳንቲም ሳትይዝ የተላከችው ወይዘሮ ዓለም አሁንም ወደሌላ የአረብ አገር ጉዞ ለማድረግ አቅዳለች። ልጆቿን በጽናት የሚያሳድገው ባለቤቷ የእርሷን መምጣት በደስታ ቢቀበለውም ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ግን ለተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ ኩዌት አመራች። በዚያም ስምንት ዓመታትን ቆይታ በመጨረሻ ከአሰሪዋ ጋር በመጣላቷ ታሰረች። ከአምስት ወራት እስር በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ትመጣለች። በፈተና የተሞላው ህይወቷ ወደ ቤት ሠራተኝነት ቢወስዳትም አሁንም ግን ከቤተሰብ የተማረችውን ንግድ ለመቀጠል ነው ፍላጎቷ።
ከአረብ አገር መልስ ለሦስት ዓመት በቤት እመቤትነተ ከቆየች በኋላ ጅግጅጋ የሚገኙ ዘመዶቿን ልትጠይቅ ጎራ ባለችበት ወቅት አንድ ሥራ ብትሰራ እንደሚያዋጣት ምክር ይለግሷታል። በቤተሰብ ምክርም የጀበና ቡና ጠጡ ሥራ በጅግጅጋ ጀምራ ዳግም ንግዱን ተቀላቀለች። ስድስት ወራትን እንደ ነገደች ግን የቡና ጠጡ ሥራው አላዋጣ ቢላት ጥላው ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች። በአዲስ አበባ ከባለቤቷ እና ልጆቿ አጠገብ ሆና ለመነገድ ወስናለች።
በመሆኑም ቀደሞው ወደምታውቀው የአልባሳት ንግድ ጋር የተጠጋጋ ሙያ ነው ምረጫዋ ያደረገችው። የጋርመንት ዘርፉን በመቀላቀል በእራሷ እጅ ዲዛይን ያደረገቻቸውን አልባሳት በመስፋት ለገበያ ስለ ማቅረቡን አጥንታለች። ለስራዋ የሚሆናትን ስልጠና ከወሰደች በኋላ አነስተኛ የስፌት ማሽን በስድስት ሺ ብር ገዝታ ሥራዋን ‹‹አሀዱ›› ብላ ጀመረች።
በተለምዶ ቡልጋሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የቤተሰቧ ቤት ውስጥ ነው ሥራውን ታከናውን እንደነበር ታስታውሳለች። የደንበኞችን ፍላጎት ያማከሉ አልባሳትን እያዘጋጀች መሸጡ አዋጭ መሆኑን የተረዳችው ወይዘሮ ዓለም አሁን ሙሉ ትኩረቷ ወደ ንግዱ ሆኗል። በጎን ለልብስ ስፌቱ የሚሆናትን ጣቃ ጨርቆች ትገዛና በአማረ ዲዛይን አበጃጅታ ለገበያ ታቀርባለች።
እንዲህ እንዲህ እያለች በአንድ የልብስ ስፌት ማሽን ብቻ መስራቱ ለተሻለ እድገት የማያዋጣ መሆኑን በመረዳቷ አቅሟን ለማጠናከር አስባለች። ቀበሌ በመሄድም ቦታ እንዲሰጣት ስትጠይቅ የሥራ እንቅስቃሴዋን አይተው በአካባቢዋ የሚገኝ የመስሪያ ቦታ ይሰጧታል። መስሪያ ቦታው ከተመቻቸላት ቀጣዩ ተግባር የመሳሪያ አቅሟን ማጠናከር መሆኑን ተረድታለችና ወደ አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ነበር ያመራችው።
ከአዲስ ካፒታል ያገኘቻቸውን ሁለት ዘመናዊ የስፌት ማሽኖች በ25ሺ ብር በመያዝ ሥራዋን አንድ እርምጃ አሸጋገረችው።አሁን በሦስት የስፌት ማሽኖች የተለያዩ ካናቴራ፣ ሙሉ ልብስ እና በዲዛይን የተዋቡ የተለያዩ አልባሳትን እያመረተች ወደ ገበያ ታቀርባለች።
ለወይዘሮ ዓለም ትልቁ ፈተና ግን ቋሚ የገበያ አማራጭ አለመገኘቱ ነው። አንዳንድ ቀን እስከ አራት ሺ ብር የሚሸጡ አልባሳትን ገበያ ብታገኝም አንዳንድ ጊዜያት ደግሞ በወርም ቢሆን አምስት ሺ ብር ድረስ የማትሰራበት ጊዜ ሊኖር እንደሚችል ትናገራለች። በመሆኑም ቋሚ የገበያ ትስስር ቢፈጠርላት የተሻለ መንቀሳቀስ እንደምትች ነው የምታስረዳው።
‹‹ትልቅ አምራች የምባል አይደለሁም የምትለው›› ወይዘሮ ዓለም ‹‹ከዚያ ሁሉ የህይወት ፈተና በኋላ ግን የእራሴ ምርት እና ንግድ ስላለኝ ደስተኛ ሆኜ እየሰራሁ ገንዘብም እያገኘሁ ነው›› ትላለች። በአሁኑ ወቅት ያላት አጠቃላይ ሃብት 55 ሺ ብር እንደሚገመት እና በቀጣይ የአልባሳት ምርት እና ንግዱን አስፋፍታ እስከውጭ አገራት የመሸጥ እቅድ እንዳላት ነው የምትናገረው።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የጋርመንት ፋብሪካዎች መነሻቸው ከአነስተኛ ደረጃ መሆኑን የምትናገረው ወይዘሮ ዓለም የእርሷም ሥራ ነገ ከነገ ወዲያ እንደሚያድግ ተስፋ አድርጋለች። ለዚህ ደግሞ በቻለችው አቅም ሁሉ አልባሳትን አምርታ እየሸጠች በጎንም በቁጠባው በርትታ የተሻለ መሳሪያዎችን ለማስገባት እየጣረች ትገኛለች። ማንም ሰው መክሊቱን አግኝቶ በጥንካሬ ከሰራ እንዲሁም ሥራን ሳይንቅ መንቀሳቀስ ከቻለ ያለመበት የመድረስ ዕድሉ ሰፊ ነው የሚለው ደግሞ ምክሯ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በጌትነት ተስፋማርያም