ስለወጋየሁ ንጋቱ ለማውራት ምክንያቶች ብዙ ናቸው:: በነገራችን ላይ በወጋየሁ ስም የተሰየመ የቴሌቭዥን ፕሮግራምም አለ፤ ፕሮግራሙ የኪነ ጥበብ ፕሮግራም ነው:: እውቁን የትያትር ሰው ወጋየሁ ንጋቱ የፍቅር እስከ መቃብር ብቻ ሳይሆን የጥበብ ነፍስ አባት ማለትም ይቻላል::
ወጋየሁን ለማስታወስ ምክንያት ባያስፈልግም ነገ የተወለደበት ቀን መሆኑን ምክንያት አድርገን ግን ዘርዘር ባለ ሁኔታ እናስታውሰዋለን:: ወዲህ ደግሞ ፍቅር እስከ መቃብር በቴሌቭዥን ድራማ እየመጣ ስለሆነ የወጋየሁ ነገር አብሮ መነሳቱ አይቀሬ ነው::
ትያትርን ከእርሱ፤ እርሱንም ከትያትር ነጥለው ለማየት የሚቸገሩ ብዙዎች ናቸው:: ሲሻው የሃይማኖት አባት፣ ሲሻው ወታደር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አርበኛ፣ ምሁር፣ እብድ፣ ጠንቋይ … ሆኖ መልከ ብዙ ገፀ ባሕርያትን ተላብሶ አስደናቂ የትወና ብቃቱን አሳይቷል:: በአስደናቂ የትወና ብቃት 94 ትያትሮችን ሰርቷል:: ብዙዎችም የትያትር ወዳጅ የሆኑት በእርሱ ምክንያት ነው:: ስለምትሃታዊ የትወና ብቃቱ ሰምተውና ወደ ትያትር አዳራሾች መጥተው የትያትር ደንበኛ ሆነው ቀርተዋል::
ተወዳጁንና ዝነኛውን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ረጅም ልብ ወለድ የተረከበት ድምፁ አሁንም ድረስ በብዙዎች እዝነ ህሊና ውስጥ ይመላለሳል:: ‹‹ሐዲስ ጽፈውበት እርሱ ነፍስ ዘራበት›› ተብሎ ተመስክሮለታል:: ‹‹ … ‹ፍቅር እስከ መቃብር› … ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ … ተራኪ ወጋየሁ ንጋቱ …›› የሚለው ድምጽ በብዙዎች ውስጥ አለ::
ወጋየሁ የተወለደው ከ79 ዓመታት በፊት ግንቦት 28 ቀን 1936 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው በእንጦጦ የስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አጠናቋል:: በትምህርት ቤት ቆይታውም በበርካታ ድራማዎችንና በሌሎች የኪነ ጥበብ ስራዎች ላይ ተሳትፎ አድርጓል፤ በስራዎቹም በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ዘንድም ተወዳጅ ነበር::
ወጋየሁ ለትወና የነበረው ፍቅር ጎልቶ መውጣት የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚማርበት ወቅት ነበር:: በዚያን ጊዜ ወጋየሁ ‹‹ተራ ወሬ ነው›› ብሎ ለጓደኞቹ የሚነግራቸው ነገር እነርሱን በጣም ያስቃቸው ነበር። ወጋየሁ በዚህ ተበረታታና ቀልዶቹን እያሳመረ የእነአለቃ ገብረሀናን ቀልድ ሲያቀርብ ይበልጥ ተደናቂ ለመሆን ቻለ። ፊልም በጣም ይወድ ስለነበር በተለይ ሁልጊዜ ቅዳሜ ከፊልም ቤት አይቀርም ነበር። ያያቸውን ፊልሞች አንድም ሳያስቀር ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ ሲያቀርብ የተመለከቱት ሁሉ የተዋጣለት ተዋናይ መሆን እንደሚችል ይናገሩ ነበር። ተማሪ ሳለ ያያቸው የነበሩ ፊልሞች ለትወና መነሻ እንደሆኑትም ይነገራል::
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከሆነ በኋላ በወቅቱ ‹‹ኪነ ጥበብ ወትያትር›› ይባል ወደነበረው የአሁኑ የዩኒቨርሲቲው ‹‹የባህል ማዕከል›› ገብቶ ተሰጥኦውን በወጉ መፈተሽ ጀመረ:: አንጋፋው የትያትር ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ባዘጋጁት ‹‹ሮሚዮና ዡሊዬት›› ትያትር ላይ የሮሚዮን ገፀ ባህርይ ተላብሶ ተወነ:: የትወና ብቃቱ ከሕዝቡ ያስገኘለት ምላሽ ወጋየሁ ቀሪ ዘመኑን በትያትር ባሕር ውስጥ እንዲዋኝ አደረገው:: ወጋየሁ በዩኒቨርሲቲው ስለትወና፣ ዝግጅትና ጽሕፈተ ተውኔት ተምሯል::
ከመድረክ በተጨማሪ በቴሌቪዥን እየቀረበ አጫጭር ድምፅ አልባ የእንቅስቃሴ ተውኔቶችን ማቅረብ ጀመረ:: ይህም ከሕዝብ ጋር በስፋት እንዲተዋወቅ አስቻለው:: ከቴሌቪዥን ትርኢቶቹ ጎን ለጎን ‹‹የድል አጥቢያ አርበኛ››፣ ‹‹ደመ መራራ››፣ ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››፣ ‹‹የወሬ ፈላስፋ›› የተሰኙና ሌሎች ተውኔቶችን በመጫወት ገፀ ብዙ ተዋናይነቱን አስመሰከረ:: ‹‹ጠልፎ በኪሴ››፣ ‹‹የከርሞ ሰው››፣ ‹‹መድሃኒት ቀምሰዋል››፣ ‹‹ዳንዴው ጨቡዴ››፣ ‹‹የዋርካው ሥር ምኞት›› እና ‹‹ላቀችና ድስቷ›› በተባሉ የትርጉምና ወጥ ተውኔቶች ላይ አብይ ሚናዎችን ይዞ በመጫወቱም ተደናቂ ሆነ::
ከዚያም በ1959 ዓ.ም ወደ ቡዳፔስት፣ ሀንጋሪ ተልኮ የሥነ ተውኔት ሙያን ለሁለት ዓመታት አጥንቶ ተመለሰ:: ከሀንጋሪ እንደተመለሰም በሬዲዮና በቴሌቪዥን አጫጭር ተውኔቶችን ማቅረብ ቀጠለ:: በተለይም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካች እንግዳ የሆኑ ‹‹አስማተኛው››፣ ‹‹ቁንጫ››፣ ‹‹ባሉን››፣ ‹‹ቀለም ቀቢው››፣ ‹‹የተዘጋ በር›› እና ሌሎች ተውኔቶችን እያቀረበ ተደናቂነትን አተረፈ።
ወጋየሁ በአስደናቂ ብቃቱ ታግዞ ትወናውን እየከወነ ሳለ የ1966 ዓ.ም ሕዝባዊ አብዮት ተከሰተ:: አብዮቱን ተከትለው የታዩት ‹‹እናት ዓለም ጠኑ››፣ ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹ዋናው ተቆጣጣሪ››፣ ‹‹አፅም በየገፁ›› እና ሌሎች ተውኔቶች የወጋየሁን ልዩ ተሰጥኦ ለማሳየት መልካም አጋጣሚን ፈጠሩ:: ወጋየሁ በተውኔቶቹ ውስጥ የተላበሳቸውን ገፀ ባሕርያትን ከተመልካች አዕምሮ እንዳይፋቁ አድርጎ ተጫውቷል:: በተለይ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ›› እና ‹‹ሀሁ በስድስት ወር›› በወቅቱ ብዙ ሕዝብ የተመለከታቸው ትያትሮች ለመሆን በቅተዋል::
ወደ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ከተዛወረ በኋላም የትያትር ክፍሉ ኃላፊ፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይና እንዲሁም በሙያው ለመስራት የሚፈልጉ ወጣቶችን በማስተማር ሁለገብ አገልግሎት ሰጥቷል:: በኢትዮጵያ ሬዲዮ ደግሞ በመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢነትና በዜና አንባቢነት ሰርቷል::
ብሔራዊ ትያትር ከገባ በኋላም ‹‹የበጋ ሌሊት ራዕይ››፣ ‹‹ትግላችን››፣ ‹‹ደመ መራራ››፣ ‹‹ደማችን››፣ ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹ሞረሽ››፣ ‹‹አፅም በየገፁ››፣ ‹‹ፀረ ኰሎኒያሊስት››፣ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ››፣ ‹‹የአዛውንቶች ክበብ››፣ ‹‹ዋናው ተቆጣጣሪ››፣ ‹‹ፍርዱን ለእናንተ››፣ ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››፣ ‹‹ክራር ሲከር››፣ ‹‹ሀምሌት››፣ ‹‹ሊየር ነጋሲ››፣ ‹‹የድል አጥቢያ አርበኛ››፣ ‹‹ዘርዓይ ደረስ››፣ ‹‹ገሞራው››፣ ‹‹አሉላ አባነጋ›› እና ‹‹እናት ነሽ›› በተሰኙ ስራዎች ላይ አብይ ሚናዎች እየወከለ ተጫውቷል::
አንጋፋው ከያኒ ወጋየሁ ንጋቱ በሕይወት ዘመኑ በመድረክ 30፣ በቴሌቪዥን 18፣ በሬዲዮ 46 በአጠቃላይ 94 ትያትሮችን በገፀ ብዙና በአስደናቂ ብቃት ተጫውቷል።
ወጋየሁ ለኢትዮጵያ ትያትር ትልቅ ባለውለታ ነው:: ተመልካችን መፍጠር የቻለ ባለሙያ ነው:: ብዙ ሰዎች በወጋየሁ አስደናቂ የትወና ብቃት ምክንያት የወጋየሁም የትያትርም አድናቂ ሆነው ቀርተዋል::
በ2010 ዓ.ም ያረፈው አንጋፋውና ተወዳጁ ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ‹‹ … ወደ ሙያው ከሳቡኝ ሰዎች መካከል አንዱ ወጋየሁ ነው:: የወጋየሁን ስራዎች በምከታተልበት ጊዜ ስሜቴ የበለጠ ወደሙያው እየተሳበ መጣ:: የወጋየሁ ትወና ከሌሎቹ የተለየ ነበር:: እንቅስቃሴው፣ አነጋገሩ፣ የሰውነቱ ሁኔታም የተመቸና ልዩ ነበር … ›› በማለት ወጋየሁ አርዓያው ስለመሆኑ ተናግሮ ነበር::
ወጋየሁ የላቀ ተዋናይ ስለመሆኑ ብዙ ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል:: ከወጋየሁ ጋር ለ18 ዓመታት አብሮ የሰራው አርቲስት ተክሌ ደስታ በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ ምልልስ ‹‹ … ወጋየሁ ራሱ ጥበብ ነው:: ጥበብን ይጠበባል:: ሰውነቱም ጥበብ ነው:: በመድረክ ሕይወቱ ይዞን ይመጥቅ ነበር:: ደራሲውና አዘጋጁ ያላዩትን ነገር የማየት ብቃት አለው …›› ብሏል::
ወጋየሁ የሰራቸው የመድረክ ትያትሮች በቴሌቪዥን የመቀረፅ እድል ስለነበራቸው እርሱ መድረክ ላይ ሲተውን የመመልከት እድል ያላገኙ ሰዎችም ስራዎቹን በቴሌቪዥን ተመልክተው ስለትወና ብቃቱ መስክረዋል፤ የትያትር አፍቃሪም ሆነዋል::
ወጋየሁ የግሉ ተሰጥኦ የሆነውን ዕውቀቱን ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ ነበር። በ1967፣ በ1969 እና በ1970 ዓ.ም ብሔራዊ ትያትር በሰጠው የተዋንያን ሥልጠና አስተማሪ በመሆን የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከተማሪዎቹ መካከል ሲራክ ታደሰ፣ ዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ ተክሌ ደስታ፣ ዓለምፀሐይ በቀለ፣ ዓይናለም ተስፋዬ፣ ኃይሉ ብሩ ሌሎች ባለሙያዎች ይጠቀሳሉ።
ወጋየሁ ስለትወና አጀማመሩና ስለሙያው ሲናገር …
‹‹… የስቴጅ ዓይኔን የከፈተው ተስፋዬ ገሠሠ ነበር። የድራማ መምህሬ፤ የተውኔት አባቴ እርሱ ነው … ተዋናይ ለመሆን ሌትም ቀንም ማለም ያስፈልጋል። ሕልሙም የሕዝቡን ስሜት ለመያዝና ለማርካት ትያትር አይቶ ለመውጣት እንዲችል ማድረግ ነው። ሕዝብ ተውኔቱን መጫወት አለመቻሉ ብቻ ጥሩ ተዋናይ ሲያገኝ ማድነቅ፤ ሳያገኝ ሲቀር ደግሞ ማንቋሸሽ አይችልም ማለት አይደለም። ስለዚህ ራስን ረስቶ ገፀ ባሕሪውን ፍጹም ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል። ሠዓሊና ደራሲ በብዕራቸውና በብሩሻቸው የሚያዩትን ለመግለጽ የሚጥሩ ከሆነ ተዋናይ ደግሞ በራሱ፣ በአካሉ፣ በስሜቱ፣ በመንፈሱ መስሎ መገኘት ይኖርበታል። ግልጽ ባይሆንም እንኳን ከደራሲው ስሜት ውስጥ ፈልቅቆ ለማምጣት መቻል አለበት…›› ብሎ ነበር::
ወጋየሁ ከተውኔት አዘጋጅነቱና ተዋናይነቱ በተጨማሪ በመጻሕፍት ትረካዎቹም ይታወቃል:: በተለይ ደግሞ የክብር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ የፃፉትን ተወዳጁንና ዝነኛውን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ረጅም ልብ ወለድን የተረከበት መንገድ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅና የሚታወስ ነው:: ለዚህም ደራሲው የክብር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁም ‹‹ፍቅር እስከመቃብርን እኔ ጻፍኩት፤ ወጋየሁ ነፍስ ዘራበት፤ እኔ ከፃፍኩት ይልቅ አንተ በሕዝቡ አዕምሮ የሳልከው ይበልጣል›› በማለት ለወጋየሁ የትረካ ብቃት ምስክርነታቸውንና ምስጋናቸውን ሰጥተዋል::
ከ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› በተጨማሪ የብርሃኑ ዘሪሁን ሶስት መጻሕፍት (‹‹ማዕበል የአብዮት ዋዜማ››፣ ‹‹ማዕበል የአብዮት መባቻ›› እና ‹‹ማዕበል የአብዮት ማግስት››) እንዲሁም የገበየሁ አየለ ‹‹ጣምራ ጦር›› ከተደራሲያን አዕምሮ የማይጠፉ ናቸው::
ደራሲ ተሾመ ብርሃኑ ከማል ‹‹ወጋየሁ ንጋቱ የትያትር ፈርጥ›› በሚለው ጽሑፋቸው፤ ‹‹ … አባትና እናቱን ያጣው ገና በልጅነቱ ነው፤ ወንድምና እህት የለውም። ሆኖም፣ በትወና ጥበቡ የብዙ ኢትዮጵያውያን ወንድምና ልጅ ነበር። ችሎታው የሚፈቅድለትን ያህል የብዙዎቻችንን ሕመም ሲታመም፣ ቁስላችንን ሲቆስል፣ ችግራችንን ሲቸገር የነበረ የመድረክ ፈርጥ ነው፤ ነበር ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ።
ወጋየሁ ንጋቱ፣ ባለትልቅ ተሰጥኦ መሆኑን ለማስረዳት ብዙ መተንተን አያስፈልግም። ሆኖም በረዥም ጊዜ የትምህርት ቤት ክትትል ሊገኝ የማይችል የትያትር ጥበብ በአጭር ጊዜ የተገለጠለትና ለብዙ ሰዎች የተሰወረውን የዕውቀት ብርሃን የጨበጠ ነበረ። ይህንንም በመድረክና በሬዲዮ ከተጫወታቸው ድራማዎች መዝኖ መረዳት ይቻላል። ይህ ወጋየሁ የሚለካበት ሚዛን ግን በተጫወታቸው ትያትሮች ሁሉ ሕይወታችንን ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ መስተዋትም ጭምር ነው።
እርግጥ ነው፣ ስለወጋየሁ ስናነሳ ብዙ ትዝ የሚሉን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። በነጋሽ ገብረማርያም ‹‹የድል አጥቢያ አርበኛ›› እና ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› ፤ በመንግስቱ ለማ ‹‹ፀረ ኮሎኒያሊስት››፣ በፀጋዬ ገብረ መድህን ‹‹እናት ዓለም ጠኑ›› እና ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››፣ በመላኩ አሻግሬ ‹‹አንድ ጡት››፣ በማሞ ውድነህ ‹‹አሉላ አባነጋ››፣ በተስፋዬ ገሠሠ ‹‹ፍርዱ ለእናንተ›› ወ.ዘ.ተ. ትያትሮች ውስጥ መልኩን እየለዋወጠ በተጫወታቸው ገፀ ባሕሪያት መታወሱ አንደኛው ነው።
ዳሩ የወጋየሁ መልክ ምን ይመስል ነበር? ብዙዎቻችን አብዛኛውን ጊዜ ያየነው በመድረክ ላይ እንዳልሆነ ብናውቅም ባስታወስነው ብቻ ሳይሆን ባየነውና ባስተዋልነው ቁጥር ከእርሱነቱ ይልቅ በገፀባሕሪያቱ በዓይነ ሕሊናችን ይታየናል…
በመሠረቱ ወጋየሁ በገጸባሕሪይ መረጣ እምብዛም የሚጨነቅ አልነበረም። አልታዬወርቅ ዘለቀ ባዘጋጀቸው የሕፃናት ቴያትር (‹‹ዲምቱ በከተማ››) አንዳንድ ተዋንያን የልጆችን ነገር በመናቃቸው ችግር እንደገጠማት ገልጻ በጣም የታወቀው ወጋየሁ ንጋቱ ግን ከትልልቆች ይልቅ የትንንሾቹ እንደሚከብድ፣ እርሱም በዚህ ተውኔት ለመካፈል ዝግጁ መሆኑን እንደገለጸላት በኢትዮጵያን ሔራልድ የባህል መድረክ ተናግራለች።
‹በጣም የሚገርመኝ ከመድረክ ውጭ ሳየው ጭብጥ ይልብኛል። አንዳንድ ጊዜም ኩፍ ያለች ዶሮ መስሎ የሚታየኝ ጊዜ አለ። በዚያው በመድረክ ግን ሲያስፈልገው ስፖርተኛ፣ ሲያስፈልገው ተወዛዋዥ፣ ሲያስፈልገው እንደ መኳንንት ተንጐማላይ ወይም እንደኔቢጤ መሆን ነው› ሲል የሰማሁት አንድ ታዳሚ የተናገረው ምንጊዜም ትዝ ይለኛል …
የዚያ ትልቅ ሰው ባለቤት የሆነችው ወይዘሮ አምሳለ ገነት ይመር እንደነገረችኝ ከሆነ ‹‹የልጆቹን ነገር አደራ›› በማለት ነበር ይህችን ዓለም በሞት የተሰናበተው። ወደር የሌለው ችሎታውን ለሕዝብ ሲያቀርብ በነበረበት ጊዜ የልጆቹን ጉዳይ በሁለተኛ ደረጃ ይዞ ነበር …››
ስሜነህ ጌታነህ ደግሞ ‹‹ስለወጋየሁ ይህን ብታነቡ›› በሚል አጭር ጽሑፉ ስለወጋየሁ አስቂኝ አስገራሚ ነገሮች ጠቃቅሷል:: ከነዚህም መካከል አንዱ ስለ‹‹አረንጓዴዋ የወጋየሁ አጀንዳ›› የጻፈው ነው::
‹‹ … ብዙ ጊዜ የሰዎች የግል ዳያሪ ውስጥ እውነት ይኖራል የሚል እምነት አለኝ። እውነት ስል ያ ሰው ስለምን እንደሚያስብ፣ ምን ሲያደርግ እንደዋለ … ከእውነተኛ ስሜቱ በመነጨ መልኩ ከግል ማስታወሻው ማየት ብሎም ማወቅ ይቻላል። የወጋየሁ የልደት ቀን ግንቦት 28 መሆኑን ከዚህ የግል ዲያሪው ነው ለማየት የቻልኩት … ይህ አጀንዳ በመጨረሻው ገጽ ላይ የታዋቂ ሰዎች ስልክ ቁጥርን ይዟል። በዚያን ጊዜ የወጋየሁ ቅርብ የነበሩ ሰዎች የቤት ስልክ ቁጥራቸው አጀንዳው ላይ ሊሰፍር ችሏል።
የተወሰኑትን ልጥቀሳቸው። ፍቅርተ ደሳለኝ፣ ወይዘሮ ጠለላ ከበደ፣ አቶ መንግስቱ ለማ፣ አቶ ተስፋዬ ገሰሰ፣ ጓድ ገዳሙ አብርሃ፣ ወይዘሮ ትሩፋት ገብረየስ፣ ጓድ ካሳ ገብሬ (ሚኒስትር ናቸው)፣ ወይዘሮ አስናቀች ወርቁ፣ የእነዚህን ሰዎች ስልክ ነበር ወጋየሁ በአጀንዳው ላይ ያሰፈረው።
በዚህ አጀንዳ ላይ ወጋየሁ በአብዛኛው ‹በዚህ ቀን ይህን ቴአትር እናሳያለን፤ በዚያ ቀን እዚህ ቦታ ቴአትር ለማሳየት እንሄዳለን …› እያለ የወር እና የሳምንት እቅዱን አጀንዳው ላይ ያሰፍር ነበር። ይህ አጀንዳ ለእኔ ታሪካዊ ነው። ለምን ቢባል ብዙ ጊዜ የታዋቂ ሰዎች የግል አጀንዳ በቀላሉ ስለማይገኝ ነው …››
ስለግለሰባዊ ባህሪውና ስለፊልም ወዳጅነቱ ደግሞ ‹‹ … አቶ ዘመዴ ንጋቱ የወጋየሁ ታላቅ ወንድም ናቸው። እርሳቸው የወጋየሁን ታዛዥነት ያደንቃሉ። ያኔ በልጅነት ወጋየሁ መረበሽ የሚባል ነገር እንደማያውቅ ወንድሙ ይናገራሉ:: ወጋየሁ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንጦጦ ሚሲዮን ሲማር ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጨርሷል … የወጋየሁ የትወና ፍቅር መውጣት የጀመረው ከሀይስኩል በኋላ ነበር። ኮሚኩ ወጣት ፊልም አብዝቶ ይወዳል። ሮጦ ወደ ፊልም ቤት ይገባል። በተለይ ቅዳሜ ሲመጣ ምንም ቢሆን ከፊልም ቤት አይቀርም። ያያትን ፊልም አንድም ሳያስቀር ገልብጦ ለተማሪዎች ያቀርባል …›› በማለት ጽፏል::
ስመጥሩና ገፀ ብዙው የተውኔት ፈርጥ ወጋየሁ ንጋቱ ባጋጠመው ሕመም ምክንያት ለስምንት ወራት ያህል የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ከቆየ በኋላ ኅዳር 6 ቀን 1982 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ:: ስርዓተ ቀብሩም በእንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2015