በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት ከሰጠቻቸው ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሽ ነው:: ይህን ተከትሎም ቱሪስቶችን በመሳብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ::
ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በውስጥ ገጥሟት በነበረው አለመረጋጋትና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተካሄደው ጦርነት እንዲሁም የዓለም ስጋት ሆኖ ከፍተኛ ቀውስ ባስከተለው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ሳቢያ የቱሪዝም ኢንደስትሪዋ ክፉኛ ተጎድቶ እንደነበር ይታወቃል:: በተለይም የፀጥታ ሥጋት በነበረባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ዘርፉ ተዳክሞ ቆይቷል::
በአንጻሩ ደግሞ ከጸጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ ብዙም ችግር ውስጥ ባልነበረባቸው አካባቢዎች ደግሞ የተሻለ የተባለ እንቅስቃሴ የታየበት ሁኔታም እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ:: ለዚህም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይጠቀሳል::
በክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ መስህብ መዳረሻዎችን በማልማት ለቱሪስቱ ምቹ የማድረግ እንቅስቃሴ ተከናውኗል:: በዚህም የክልሉ ሕዝብ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የተከናወኑ ተግባራት ስለመኖራቸውና በሥራ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሄዱበት መንገድ ምን እንደሚመስል በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪስት መስህብ ጥናት ልማትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው በቀለ ጋር ቆይታ አድርገናል::
የክልሉ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻ ሀብቶች
አቶ እንዳሻው እንዳስረዱት፤ በክልሉ የቱሪስት መዳረሻዎች በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ተለይተዋል:: አንዱ የተፈጥሮ መስህብ ሲሆን፣ ይህም ብሔራዊ ፓርኮችን ያካትታል:: በክልሉ ማሊ፣ ማጎ፣ ጊቤ ሸለቆ፣ ነጭ ሳርና ኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች ይገኛሉ:: በክልሉ የሚገኙትን ነጭ ሳርና ኦሞ ብሄራዊ ፓርኮችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ባለሥልጣን ነው:: አርባ ምንጭ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የአዞ እርባታ የሚከናወንበት ሥፍራም ሌላው የክልሉ የቱሪስት መስህብ ነው::
አርባ ምንጭ ዙሪያ የሚገኙት የጫሞና አባያ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች፣ በአነስተኛ ፏፏቴዎች ደግሞ እንደ አጆራ መንትያ ፏፏቴዎች፣ በልዩ ሁኔታ የሚጠቀሰው አመበሪቾ ኢኮ ቱሪዝም የመሳሰሉት በተፈጥሮ መስህብ ውስጥ የሚገኙ የክልሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው::
በሁለተኛ ደረጃ ክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ብሎ የለያቸው ደግሞ በአልባሳት፣በምግብ፣ በጭፈራና በተለያዩ መገለጫዎች የሚጠቀሱ የባህል እሴቶች ናቸው::ክልሉ በሰፊ ቱባ የባህል እሴቶቹም ይታወቃል:: ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ተነጥለው ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ቢሆኑም በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች አካባቢውን በቱሪዝም መስህብነት ተጠቃሽ እንዲሆን አደርገውታል:: በክልሉ ከ40 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ይገኙበታል:: እነዚህ ሁሉ የተለያዩ ያልተበረዘ ቱባ የባህል እሴት መገለጫዎች አሏቸው::
በተለያየ ጊዜ በሚዘጋጁ ባህላዊ ክዋኔዎች ወቅት እነዚህ እሴቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኝት የሚካሄድባቸው እየሆኑ መጥተዋል:: በዚህም የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን ችለዋል::
የባህል እሴቶችን ለቱሪስቱ መስህብ ምቹ እንዲሆን የሚደረገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየታየበት መጥቷል:: የውጭውንም ሆነ የሀገር ውስጥ ጎብኚውን ቀልብ ከሚይዙት ባህላዊ እሴቶች፣ በባህላዊ ጭፈራው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው የኢቫንጋዲ ጨዋታ ይጠቀሳል::
ሌላው ከዘመን መለወጫ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ክብረበዓል የሚደምቀው የወላይታ ብሔረሰብ ጊፋታ፣ የጋሞ ዮዮ መስቀላ፣ የሀዲያ፣ የከንባታ በሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች የሚከበሩ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓላት እንደ ሀገርም ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ በዓል ተደርገው የተወሰዱ ናቸው::
ከታሪክ አንጻርም የማይናቅ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉት ክልል ነው:: ከእምነት ጋር በተያያዘም የሶስት ሺ ዘመን ታሪክ ያላቸው በርካታ የቱሪስት መስህቦች በክልሉ የሚገኙ ሲሆን፣ በጉራጌ፣ በወላይታና በሌሎችም መንፈሳዊ የቱሪስት መዳረሻዎች ይገኛሉ::
በክልሉ የተለያዩ ዞኖች የሚገኙት ትክል ድንጋዮች የክልሉ መገለጫዎች ናቸው::በዚህ ረገድም ትክል ድንጋዮችና የተለያየ መካነ ቅርጽ የሚገኙበት ጌዲዮ ዞን ይጠቀሳል:: በአካባቢው በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ ባህልና ትምህርት ድርጅት(ዩኔስኮ)ሊመዘገቡ የሚችሉ ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ:: ታሪካዊ ቅርስ ተብሎ የሚጠቀሰው የጥያ ትክል ድንጋይን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል:: በታችኛው አዋሽ ሸለቆና ኦሞ ሸለቆም በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ:: አቶ እንዳሻው የጠቀሱልን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ከብዙ በጥቂቱ ናቸው::
ጎብኚዎችን ለመሳብ የተደረጉ ጥረቶች
አቶ እንዳሻው እንደገለጹት፤ መስህቦች፣ ተደራሽነትና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ዋና የቱሪዝም ዘርፉ ምሰሶ ናቸው:: መዳረሻዎችን በማልማትና ምቹ በማድረግ ለጎብኚው ተደራሽ ማድረግ ካልተቻለ ከቱሪዝም ኢንደስትሪው ውጤት መጠበቅ አይቻልም:: ከተደራሽነት አንጻር መንገድ፣ መብራት፣ ስልክ፣ ትራንስፖርት እንዲሁም የመኝታና የመዝናኛ አገልግሎቶች ወሳኝ ናቸው:: በዚህ ረገድ ሥራዎች ቢሰሩም አጥጋቢ ናቸው ለማለት አያስደፍርም::
ቢሮው ከክልሉ በሚመደብለት በጀት የሆቴልና የመዝናኛ አገልግሎት በሌለባቸው የቱሪስት መዳረሻዎች ማረፊያዎች (ገስት ሀውስ) በመገንባት፣ በየመዋቅሩ ያሉ የመንግሥት አስተዳደሮችም ለቱሪስት ፍሰቱ የየድርሻቸውን እንዲወጡ በማሳተፍ የተቀናጀ ሥራ ተሰርቷል:: ከማልማቱ ጎን ለጎንም ቱሪስቱን ለመሳብ የሚያስችሉ የማስተዋወቅ ሥራዎች እንዲሰሩ በማድረግ ልማትና ግብይቱ የተጠናከረ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል::
ሀብቱን ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተደራሽነት ባላቸው የመገናኛ ዘዴዎችና ማህበራዊ ድረ ገጾች በመጠቀም ተደራሽ ለመሆን በማስተዋወቁ ሥራ ላይ ቢሮው ተንቀሳቅሷል:: በዚህ የማስተዋወቅ ሥራ ቱሪስቱ ካለበት ስፍራ ከመነሳቱ በፊት ዝግጅት አድርጎ ወደ መዳረሻው ለመሄድ እንዲወስን የሚረዳው አጠቃላይ መረጃዎች በእጅ ተንቀሳቃሽ ስልኩ የሚያገኝበትን ዘዴ በመጠቀም የመስህብ ሥራ ተሰርቷል:: ቢሮው እንዲህ ያሉ የቴክኖሎጂ ዘዴዎችን (ሶፍትዌር) አበልጽጎ ለመተግበር ከዩኒቨርሲቲና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ጋር በጋራ ሰርቷል::
የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ እንዲህ ያሉ ተግባራት ቢከናወኑም ሥራዎቹ ሙሉ እንዳልሆኑ የሚገልጹት አቶ እንዳሻው ከልማት አንጻር መሠረተ ልማት ማሟላት ላይ ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ነው ያመለከቱት::
በተከናወኑት ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች
ከውጤት አንጻርም በዘርፉ የሚከናወኑት የተለያዩ ተግባራት የመጨረሻ ግባቸው የቱሪስት ፍሰቱን በማሳደግ ከዘርፉ ገቢ በማግኘት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ማድረግ መሆኑን የጠቀሱት አቶ እንዳሻው፣ ከዚህ አንጻር በተለይም ባለፉት ሶስት አመታት በኢትዮጵያ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ የዘርፉን እንቅስቃሴ እንደጎዳው ነው የሚናገሩት::
በዓለም አቀፍ ደረጃና በኢትዮጵያም በ2012 የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ በእጅጉ ነው ተጽእኖውን ያሳረፈው:: የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በባህሪው በመሰባሰብ ላይ ያተኮረ ነው:: ወረርሽኑ ደግሞ ይህንን የሚከለክል በመሆኑ ቱሪስቱን የሚያበረታታ አልነበረም:: ኮቪድ ጫናውን በማሳደሩ በወቅቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እንቅስቃሴው ተገትቷል::
በወቅቱ በድህረ ኮቪድ የተጎዳው ዘርፍ እንዲያገግም እንደ ሀገርም እንደ ክልልም መነቃቂያ (ሪከቨሪ) ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ እንዳሻው፤ስትራቴጂውን ለመተግበር ወደ ሥራ በተገባበት ወቅት ደግሞ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከፈተው ጦርነት ሌላ ችግር ሆኖ የዘርፉን እንቅስቃሴ እንደገታው ገልጸዋል::
ምንም እንኳን ጦርነቱ በሰሜኑ ኢትዮጵያ የተካሄደ ቢሆንም በተዘዋዋሪ ከጦርነት ከቀጠናው ውጭ ባሉ አካባቢዎችም ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን አቶ እንዳሻው ጠቅሰዋል::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሌላው ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተግዳሮት የነበረው የመዋቅር ወይንም ከክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ነው:: አርባ ምንጭ፣ ኮንሶን ይዞ በሚዘልቀውና ካልቸራል ሩት ተብሎ በተለየው አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ከተለያየ የዓለም ሀገራት ወደ ስፍራው ይሄዱ የነበሩ ቱሪስቶችን በማስቀረቱ በወቅቱ የሚጠበቀውን ያህል የቱሪስት ፍሰት እንዳይኖር አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል::
አቶ እንዳሻው በተያዘው 2015 በጀት አመት ዘጠኝ ወራት ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊየን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እንዲሁም 7ሺ850 የውጭ ቱሪስቶችን ክልሉን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል:: ከዚህም 205ሚሊየን ብር ገቢ ለመስብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል:: በአጠቃላይ ገቢው ለመግቢያ ከተቆረጠ ደረሰኝ፣ ከፊልም ቀረጻ፣ በህጋዊ መንገድ ከሚታደኑ የዱር እንስሳትና ከሌሎችም በቀጥታ በደረሰኝ የተሰበሰበ የውስጥ ገቢ የተካተተበት መሆኑን ያብራራሉ::
ከቅድመ እቅድ ጋር በማነጻጸርም አቶ እንዳሻው የተገኘውን ገቢና የቱሪስት ፍሰት ሲያብራሩ እንደገለጹት፤ ቢሮው የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለመሳብ በእቅድ የያዘው አራት ነጥብ አንድ ሚሊየን ሲሆን፣ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ለመሳብ የታቀደው ደግሞ 16 ሚሊየን ነበር:: በገቢ ደረጃ ደግሞ ከጎብኚዎች ለማግኘት የታቀደው ወደ 260 ሚሊየን ብር ሲሆን፣ በደረሰኝ ደግሞ ሶስት ነጥብ ሰባት አምስት ሚሊየን ብር ነው::
ለእቅድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን እንደ ሀገር ካጋጠመው ችግር ውጭ የቱሪስት ሩት ወይንም መዳረሻ በሚባሉት የደቡቡ አካባቢዎች በተለይም ኮንሶ፣ ደራሼ በተወሰነ ደረጃ ጂንካ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ተግዳሮት መሆናቸውን ጠቁመዋል::
ከኮቪዱና አለመረጋጋቶች ወደ ሰላም ከተመለሱ ወዲህ ያለው እንቅስቃሴ
የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በተለያየ ተግዳሮቶች ውስጥ ቢያልፍም፣ ችግሩን ተቋቁሞ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እንደ ሀገር በተደረገው ጥረት ውስጥ ክልሉም ስለነበረው ድርሻና ያለውን ተስፋም በተመለከተ አቶ እንዳሻው ሲያብራሩ፤ ሰላምና መረጋጋቱ ትልቅ ተስፋ ማሳደሩን ጠቅሰዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪው ላይ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ለማድረግ በክልሉ የአስር አመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል:: ፍኖተ ካርታው በክልሉ ያሉ የቱሪዝም መስህቦችንና መዳረሻዎችን በአግባቡ የለየ፣ መዳረሻዎች የተሟላ መሠረተ ልማት እንዲኖራቸውና ተያያዥ ጉዳዮችን በጋራ ለመሥራት የባለድርሻ አካላትን የነቃ ተሳትፎንም ያመላከተ ፍኖተ ካርታ ሲሆን፣ እመርታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎም የሚጠበቅ ነው::
ዘርፉ ከአካባቢው ባለፈ የሌሎችንም ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከፌዴራል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በግልና በጋራ እቅድ በመንደፍ የተለያዩ ተግባራትን የመፈጸም ተሞክሮ መኖሩንም አቶ እንዳሻው ጠቅሰዋል:: ይህም በዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ትልቅ ድርሻ እንዳለውና በዚህም ላይ በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራ ገልጸዋል::
በተለየ ሁኔታ ተከናውነው ለአብነት የሚጠቀሱ
ቢሮው ካከናወናቸው ከፍተኛ እሴት የተጨመረባቸው ብሎ ከሚጠቅሳቸው፤ከምባታ ዞን ላይ የሚገኘው ሀመበሪቾ ኢኮ ቱሪዝም ተብሎ የሚጠራው አካባቢን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል:: የተለያየ የእጽዋት ሽፋን ያለው፣ በውስጡም መጠነኛ የዱር እንስሳት በሚገኝበት በዚህ በተፈጥሮ በተዋበ አካባቢ ላይ የተፈጥሮ ገጽታውን በጠበቀ መልኩ የማልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል:: በዚህ ተራራ ላይ 77 ደረጃዎች ተገንበተውለትና የተለያዩ ማስዋቢያዎችም ተካትተውበት ውበቱን ከፍ በማድረግ ውብ መስህብ ያለው ማድረግ መቻሉንና በአርአያነት የሚጠቀስ አካባቢ ማድረግ እንደተቻለ አቶ እንዳሻው ገልጸዋል::
የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ከማበረታታት አንጻር ምንም እንኳን ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችና ከውጭም የሚመጡ ቱሪስቶችም ወሳኝ ቢሆኑም በተለያየ ምክንያት ከውጭ የሚመጡ ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚደረገው ጥረት ሚዛን የደፋ ተደርጎ ይወሰዳል:: አሁን ላይ ኢትዮጵያን እንደገጠማት የውስጥ አለመረጋጋትና በዓለም አቀፍ ተጽእኖም እንደ ኮቪድ ያለው ወረርሽኝና ሌሎችም ችግሮች ሲያጋጥሙ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ::
ከዚህ አንጻር ክልሉ ያከናወነውንም አቶ እንዳሻው ሲገልጹ፤ ቱሪስት ሲባል በተለምዶ በብዙዎች አእምሮ የሚመጣው የውጭ ሀገር ጎብኚ መሆኑን ጠቅሰው፣ይህ አይነት ተለምዶ ግን አይደገፍም ይላሉ:: የሀገር ውስጥ ጎብኚ ከውጭ ከሚመጣው ባልተናነሰ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል:: ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ ኢንዱስትሪውን መታደግ የሚቻለው በሀገር ውስጥ ጎብኚ መሆኑንም ገልጸው፣ ይህ ሲሆን ኢንዱስትሪው ችግሮችን የመቋቋም አቅም ያገኛል ብለዋል::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የሀገር ውስጥ ጎብኚ ቀጥታ የቱሪስት መዳረሻዎችን ባይጎበኝም ህክምና ፍለጋ፣ ቤተሰብ ለመጠየቅ፣ አመታዊ መንፈሳዊና ባህላዊ ክብረ በዓላትን ለመካፈል፣ ለስብሰባዎችና ስልጠናዎች በአጠቃላይ ለተለያየ ጉዳይ በሚያደርገው መዘዋወር ወጪ ስለሚያወጣ ገቢ ይገኛል:: በኮቪድ ምክንያት የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እንቅስቃሴ ሲቀንስ የሀገር ውስጥ ጎብኚው ግን አልተቋረጠም:: ቢሮውም ቀውሶች በተፈጠሩበት ወቅት ቀደም ሲል ከነበረው ትኩረት በተለየ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲበረታቱ ጥረት አድርጓል:: በዚህ በኩል ሲቪል ተቋማትንና ትምህርት ቤቶችን በመድረስ አካባቢያቸውን እንዲጎበኙ በማድረግ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ይጠቀሳል::
የማህበረሰብ ተጠቃሚነት
መዳረሻዎችን በማልማትና ቱሪስት በመሳብ ከሚገኘው ገቢ የአካባቢው ነዋሪ ተጠቃሚ ሲሆን መዳረሻዎችና የቱሪስቱም ደህንነት እንደሚጠበቅ በዘርፉ ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ በማድረግ ረገድም ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ደረጃ እያከናወነ ስላለው ተግባር አቶ እንዳሻው ሲገልጹም፤ ፓርኮችን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙት መዳረሻዎች ማህበረሰቡ ጠብቆ ያቆያቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ቢሮው በተጨማሪ በመዳረሻ ቦታዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል::
ከፓርኮች፣ ደረሰኝ ተቆርጦላቸው ከሚገኝ የቱሪዝም ገቢ በመቶኛ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንደሆነ ተናግረዋል:: ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ይሆናል ሲባል ማህበረሰቡ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ለአብነትም ምንጭ በማጎልበት፣ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ወይንም የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በማሟላትና ሌሎችም ማህበረሰቡ እንዲሟሉለት ለከተማ አስተዳደሮች የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ የማሟላት ተግባሮች መሆናቸውንም አብራርተዋል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም
Hello there! Do you know if they make any plugins to assist with SEO?
I’m trying to get my site to rank for some targeted keywords but I’m not seeing very good gains.
If you know of any please share. Kudos! I saw similar text here:
Eco wool