የየትኛውም ሃይማኖት አስተምሮ በአንድም ይሁን በሌላ ፍቅርና ሰላምን መሰረት ያደረገ፤ ሰውም ለእነዚህ ሃይማኖታዊ እና ሰብአዊ እሴቶች የተገዛ ነው። የየሃይማኖቶቹ አስተምህሮትም ስክነትን ፣ መደማመጥን ፣ መቻቻልን እና ሆደ ሰፊነት በመስበክ የማህበረሰብን አብሮነት የማጽናት መንፈሳዊ አቅምን የሚያጎለብት ነው።
ከራስ ወዳድነት የጠራ ፤ ወንድማማችነት እና ቤተሰብነትን በመፍጠር ሰላምና ፍቅር የሰፈነበት ማኅበረሰብ መገንባት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ የየትኛውም ማኅበረሰብ ዛሬን ጨምሮ የነገ ብሩህ እጣ ፈንታ መሰረት ሰላምና ፍቅር እንደሆነም የሚያስተምር ነው።
ይህንንም የሚጨበጥ እውነት ለማድረግ ከሁሉም በላይ ለመንፈሳዊ እሴቶች ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ፤ አጠቃላይ በሆነው የማኅበረሰብ ግንባታ ውስጥ ትልቁን ስፍራ የሚይዝ ፤ የየትኛውም ማህበረሰብ የሰብአዊ እሴቶች ምንጭ ነው።
እኛ ኢትዮጵውያንም በተለያዩ ወቅቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ እውቅና ያላቸውን ሃይማኖቶች በመቀበል በሃይማኖታዊ እሴቶች የበለጸገ ማኅበረሰብ በመገንባት የረጀም ታሪክ ባለቤቶች ነን። ይህም የታሪካችን አንዱ አካል እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያትታሉ።
የቀደሙት አባቶቻችን እነዚህን ሃይማኖታዊ እሴቶች በመጠቀም ፤ ሀገርን እንደሀገር በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም፤ ትውልዶችንም ከፍ ባሉ መንፈሳዊ እሴቶች ለመገንባት በስፋት ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም የተገኙ ስኬቶች የዛሬይቱን ኢትዮጵያ መፍጠር አስችሏል።
የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት፤ የሃይማኖት ብዝሃነት የሚስተናገድባት ፤ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ምሳሌ የምትጠቀስ ሀገር አስረክበውናል። በብዙ መቻቻል፣ እና ልበ ሰፊነት ላይ የተመሰረተ ወንድማማችነትን ፈጥረው በተጨባጭ አሳይተውናል።
ልዩነቶች የችግር ምንጭ ከመሆን ይልቅ ፤ ሀገራዊ ውበት የሚሆኑበትን የአስተሳሰብ መሰረት በመጣል፤ ልዩነቶች በርግጥም ሃገራዊ ውበቶች መሆናቸውን በተግባር ማሳየት ችለዋል። ይህም በትውልድ ቅብብሎሽ ረጅም ዘመናትን ተሻግሮ አሁን ላይ ደርሷል። ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ምስረታም ዋነኛ አቅም በመሆን አገልግለዋል።
ሃገሪቱ እንደ ሃገር በየዘመኑ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ከፍ ባለ ጽናት ተሻግራ አሁን ላይ እንድትገኝ እነዚህ ሃይማኖታዊ እሴቶች የነበራቸው አስተዋጽኦ ከግምት የላቀ ነው። ዛሬ ላይም እያጋጠሟት ያሉ ተግዳሮቶችን ለመሻገር ዋነኛ አቅሞች እንደሚሆኑም ይታመናል።
አሁን ላይ እንደሀገር እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎቻችን ተሻግረን ተስፋ ያደረግናቸውን ብሩህ ነገዎች የራሳችን ለማድረግ እነዚህ ከሰብአዊነት የሚመነጩ መንፈሳዊ እሴቶቻችንን ከጣልንበት ማንሳት ይጠበቅብናል።
ለዚህ ደግሞ ፖለቲካችንም ሆነ የትኛውም ማኅበራዊ መስተጋብራችን ሰላምን፣ ፍቅርን እና ወንድማማችነትን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡ ማህበራዊ ስክነትን፣ መደማመጥን ፣ መቻቻልን እና ሆደ ሰፊነትን አብልጠን መለማመድና የማንነት ግንባታችን ትልቁ መሰረት አድርገን ልንወስደው ይገባል።
ይህንን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት፤ ከሁሉም በላይ የሃይማኖት አባቶች ኃላፊነት ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል። ትውልዱን ከመንፈሳዊ አስተምህሮ በሚመነጩ የሞራል እሴቶች በመገንባት ስለራሱ ፣ ስለወንድሞቹ ፣ ከዚያም አልፎ ስለሃገሩ ቀና አሳቢ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ይሄ ትውልድን ከፍ ባሉ የሞራል እሴቶች የመገንባት ኃላፊነት ፤ እንደ ሃገር ዛሬ ላይ እየተፈታተኑን ያሉና ዘመን እየተሻገሩ ብዙ ዋጋ እያስከፈሉን ችግሮቻችንን ለዘለቄታው በመፍታት፤ ነገ ላይ እንድትሆን የምንመኛትን የበለጸገች ኢትዮጵያ በጠንካራ መሰረት ላይ ለማዋቀር የሚያስችለን ትልቁ አቅማችን ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም