ለመኪና ቅርብ ሆና ነው ያደገችው:: ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሳለች የተለያዩ የመኪና አካላትን በመጠሪያ ስማቸው ለይታ አውቃለች:: የመኪና አካላትን አንድ በአንድ ለይታ እንድታውቅ እድሉን የፈጠረላት ከወላጅ አባቷ ሕልፈት በኋላ መኪኖችን በማስተዳደር ከላይ ታች ሲሉ ከነበሩት ወላጅ እናቷ ስር ስር ማለቷ እንደሆነ ታምናለች::
የከባድ መኪና ሾፌር እንዲሁም የመኪኖች ባለቤት የነበሩት ወላጅ አባቷ፣ በመኪና አደጋ ሲለዩ እሷን ጨምሮ ሦስት ልጆችን ማሳደግ እንዲሁም መኪኖችን የማስተዳደር ድርብ ኃላፊነት ከወላጅ እናቷ ጫንቃ ላይ ወደቀ:: ወላጅ እናቷም እጅ አልሰጡም፤ በሴትነት አቅማቸው ወጥተው ወርደው መኪኖቹን በማሠማራት ልጆቻቸውን አሳድገዋል::
የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው የዛሬ የስኬት እንግዳችን የኢክራም አውቶሞቲቭ መሥራችና ባለቤት ወይዘሮ ኢክራም ኢድሪስ ወላጅ እናቷ ከመኪኖች ጋር የነበራቸውን ቁርኝት በቅርብ ርቀት እየተከታተለች ስለማደጓ ስትናገር፤ ‹‹ሴትነት ሳይበግራት ከመኪኖች ጋር እዚህም እዚያም ብላ፤ ሲበላሹ አሠርታ፤ የመኪና ዕቃ ገዝታ፤ ጭነት አፈላልጋ አስጭና፤ ስምሪት ሰጥታ ሂሳብ ለመሰብሰብና ለመክፈል ጭምር ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ተመላልሳለች::
ከልጅነት እስከ ዕውቀት ስለመኪና እየሰማችና የመኪና አካላትን እየተመለከተች ያደገችው ወይዘሮ ኢክራም፣ የመኪና አካልን ዘመናዊ በሆነ መንገድ የመጠገንና የማስዋብ ሥራን ከተቀላቀለች ከአምስት ዓመት በላይ አስቆጥራለች:: ከመኪና ጋር የነበራት ቅርበት ወደ ሥራው እንድትገባ በር ከፍቶላታል:: ስለመኪኖች አካል ከምታውቀው ዕውቀት በተጨማሪ አጋጣሚዎች ሁሉ ወደ መኪኖች ዓለም ይመሯት እንደነበርም ትናገራለች::
ደሴ ተወልዳ ያደገችው ወይዘሮ ኢክራም፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ደሴ ጦሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረች ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ ደሴ ካቶሊክ ትምህርት ቤትና ሻሸመኔ ኩየራ አድቬንቲስት አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲሁም 12ኛ ክፍልን ደሴ ወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት ተምራለች:: ከደሴ ወደ ሻሸመኔ ኩየራ አዳሪ ትምህርት ቤት የሄደችበትን አጋጣሚ ስታስታውስ፤ ወላጅ እናቷ እሷን ጨምሮ ሦስት ሴት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከመኪና ጋር የነበራቸው ሩጫ ፋታ ነስቷቸው እንደነበረ ትገልጻለች::
‹‹ሴት ልጆች እንደመሆናችን ክፉ ነገር እንዳይገጥመን ከነበራት ስጋት እና ከመሳሳቷ የተነሳ ልጆቼ ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ይቀመጡ በሚል ኩየራ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገባችን›› የምትለው ወይዘሮ ኢክራም፤ ወላጅ እናቷ ሦስቱንም ሴት ልጆቻቸውን አዳሪ ትምህርት ቤት አስገብተው እሳቸው በነፃነት መኪኖቻቸውን ማስተዳደር እንደቻሉ ነው የምትናገረው:: ‹‹የእናቴ ጥንካሬ ጉልበትና ብርታት ዕምቅ አቅምና ትልቅ ስንቅ ሆኖኛል›› በማለትም ወላጅ እናቷ ብርቱ፣ ጠንካራና እጅ የማይሰጡ ትጉህ እናት መሆናቸውን ትናገራለች::
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ የኮሌጅ ትምህርቷን አቡዳቢ የመማር ዕድል የገጠማት ወይዘሮ ኢክራም፤ ትምህርቷን ሳታጠናቅቅ ወደ አውሮፓ ተጉዛለች:: በአውሮፓ ቆይታዋም በወጣትነት ዕድሜዋ የውጭውን ዓለም ሁኔታ ከማጣጣም ባለፈ የሕይወትን ውጣ ውረድ መረዳት ችላለች:: ከጥቂት ቆይታ በኋላም ወደ ትውልድ አገሯ ኢትዮጵያ በመምጣት ትዳር መሥርታ ልጆች ወልዳ በማሳደግ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዳለች::
ባለቤቷ የመኪና መለዋወጫ መሸጫ ነበረው:: ይህ ሁኔታም ከመኪና አካል ጋር ያላትን ቁርኝት ይበልጥ አጠናከረው:: ይህ ግጥምጥሞሽ ዘመናዊ የመኪና ጥገና አገልግሎት መስጫ ድርጅት /ጋራዥ/ ለማቋቋም ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረላት::
በመኪና መለዋወጫ መሸጫ ውስጥ የሚገኙ የመኪና አካላትን እንዲሁም የሞተር ዕቃዎችንም ጠንቅቃ የምታውቀው ወይዘሮ ኢክራም፤ ዕቃውን አስመጥቶ መሸጥ አዋጭ ቢሆንም እርካታ ግን አላገኘችበትም:: እናም ሥራውን እንዴት ማዘመንና ማሻገር እንዳለባት ማሰብ ውስጥ ገባች፤ በዚህ መካከልም ከአንድ የውጭ ድርጅት ጋር የመተዋወቅ ዕድል ገጠማት:: በድርጅቱ አማካኝነት የመኪና አካል እንዴት ይሠራል፤ በምን አይነት መንገድ መሠራት አለበት፤ የሚለውን ለማወቅና ለመረዳት ከፊንላንድ ኩባንያ ጋር በመነጋገር ሥልጠና ወሰደች::
ከፊንላንድ ኩባንያ የመኪና አካል ሥራና ማስዋብ የሚለውን ሥልጠና በልዩ ሁኔታ ያገኘችው ወይዘሮ ኢክራም፤ ያላትን ዕውቀትና ልምድ ከሥልጠናው ጋር በማዋሓድ በአዲስና ባልተለመደ ሁኔታ የመኪና አካል መጠገንና ማስዋብ ሥራን ተቀላቅላለች:: በተለይ የመኪና ማስዋብ በኢትዮጵያ ያልተለመደና አዲስ እንደሆነ የጠቀሰችው ወይዘሮ ኢክራም፤ ይህን ለየት ያለና አዲስ ነገር ወደ ገበያው ይዛ እንደመጣች ታስረዳለች:: ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም ድረስ የመኪና አካል የሚሠራው ብዙም ዘመናዊ ባልሆነ መንገድ ነው:: እኔ ወደ ገበያው የገባሁት የመኪና አካል የሚሠራበትን ዘመናዊ የሆኑ ቴክኖሎጂ ጭምር በመያዝ ነው›› ትላለች::
የመኪና ጥገና ሥራውንም ባልተለመደና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ውበት ጨምራ እንደምትሠራ የምትናገረው ኢክራም፤ መነሻዋ የውጭው ዓለም ተሞክሮ እንደሆነ ትናገራለች:: በውጭው ዓለም የመኪና አካል ሥራ እንደ ሰው ልጅ ሁሉ እጅግ ጥንቃቄ የሚደረግለት እንደሆነ በማመላከትም፤ መኪኖቹን ዘመናዊ በሆነ መንገድ የማስዋብ ሥራና የጥገና አገልግሎት እየሰጠች መሆኗን የምትገልጸው::
ወይዘሮ ኢክራም፤ የአውቶሞቲቭ ባለሙያ እንደመሆኗ በድርጅቱ ውስጥ አሠሪ ብቻ ሳትሆን ሠራተኛም ነች:: ከመኪኖች ስር ደፋ ቀና በማለት የጎበጡ መኪኖችን ታቀናለች፤ የደበዘዙትን ታፈካለች፤ የነጡ የገረጡትን የተለያዩ ምርቶችን በመጠቀም አሽታና አለስልሳ ወዛቸውን ትመልሳለች፤ ታስውባለች፤ ታስጊጣለች:: መኪና ማስዋብ፣ ማሳመርና ማስጌጥ ማለት ሜክአፕ መጠቀም እንደማለት መሆኑን በማስረዳትም ሴቶች ለፊታቸው እንክብካቤ እንደሚያደርጉት ሁሉ መኪኖችም ከመጎዳታቸው አስቀድሞ ጥንቃቄ ይደረግላቸዋል ትላለች::
ለዚህም ጉዳት ከደረሰባቸው መኪኖች በተጨማሪ አዳዲስ መኪኖች ጭምር ወደ ድርጅቱ እንደሚመጡም ነው የገለጸችው:: አገልግሎቱን ፈልገው ወደ ድርጅቱ የሚመጡት መኪኖች በአብዛኛው እጅግ ዘመናዊ የሆኑ መኪኖች እንደሆኑም ትናገራለች:: መኪኖቹ ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸውና ሃብት የፈሰሰባቸው በመሆናቸው ጥንቃቄ ያሻቸዋልም ትላለች::
ከልጅነቷ አንስቶ በቤት ውስጥ የመኪኖችን አካል አብጠርጥራ የማወቅ ዕድል የገጠማት ወይዘሮ ኢክራም፤ የመኪኖቹ አካላት ሲጎዱ መጠገን ከመጎዳታቸው አስቀድሞ ደግሞ ውበታቸው እንዳይረግፍ የመጠበቅና የመንከባከቡን ሥራ ከውስጥ በመነጨ ፍላጎት ወዳውና አምናበት እንደምትሠራው ነው ያጫወተችን::
ሥራውን ለሕዝብ ለማስተዋወቅና ለማስተማርም ጊዜ አልፈጀባትም:: መኪኖች ጉዳት ሲደርስባቸው ከጉዳታቸው እንዴት ማገገም እንደሚችሉ በመገናኛ ብዙኃን ታስተምራለች:: በሚዲያ ወጥቶ ማስተማር ድንገት የመጣላት ሃሳብ መሆኑን ጠቅሳለች:: በዚህም በርካታ ደንበኞች ማፍራት እንደቻለችና እነዚህ ደንበኞቿ እንደሚያበረታቷትም ነው ያጫወተችን::
ይዛ የመጣችውን አዲስ ነገር ለማስተዋወቅ፣ ለማስተማርና ቴክኖሎጂውንና አገልግሎቱን ለመሸጥ በተለያዩ ጋራዦች ተዘዋውራለች፤ ይህም አድካሚ እንደነበር ታስታውሳለች:: ከአዲስ አበባ ውጭም በክልል ከተሞች ሳይቀር ተዘዋውራ መኪኖች ሲጎዱ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም እንዲያሠሩ ቴክኖሎጂዎቹን እያሳየች አስተምራለች:: እንዲህ እየተዘዋወሩ ማስተዋወቁና ማስተማሩን አቁማ ዛሬ በአርትስ ቴሌቪዥን ባላት የአንድ ሰዓት ፕሮግራም እያስተማረች ብዙዎች ዘንድ መድረስ ችላለች::
‹‹ሴት ሆኖ መኪና መጠገን ወይም የጋራዥ ሥራ መሥራት የተለመደ ባይሆንም ወደ ገበያው ለመግባት ብዙ አልተቸገርኩም፤ ተቀባይነትም አግኝቻለሁ›› ስትል ወይዘሮ ኢክራም ትገልጻለች፤ የሥራ ቦታዋ በተለምዶ እንደሚታወቀው ጋራዥ አይነት እንዳልሆነም ጠቅሳ፣ ደህንነቱና ንጽሕናው የተጠበቀ ለሥራ ምቹ መሆኑንም ነው ያመለከተችው::
ሴቶችም ደስተኛ ሆነው በዘርፉ መሳተፍ እንደሚችሉ ገልጻ፣ ብዙ ጊዜ በሴቶች የማይደፈረው የጋራዥ ሥራ አሁን ላይ በዓይነቱ ለየት ባለና ዘመናዊ በሆነ መንገድ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በማሽን መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁማለች:: በአሁኑ ወቅትም በርካታ ሴቶች ወደ ዘርፉ እየገቡ ስለመሆናቸው ኢክራም አውቶሞቲቭ ውስጥ የሚሠሩ ሴት የአውቶሞቲቭ ባለሙያዎች ተጠቃሾች ናቸው:: በሌሎች ጋራዦች ውስጥም ሴቶች ማየት እየተለመደ መምጣቱን ወይዘሮ ኢክራም አስታውቃለች::
ዘመናዊ በሆነ መንገድ መኪኖችን መጠገንና ማስዋብ ሲባል፤ በተለምዶ በአብዛኛው በሰው ኃይል የሚካሄደውን የጋራዥ ሥራ አብዛኛው ሥራ የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ በማሸን መሥራት እንደሆነ ያስረዳችው ወይዘሮ ኢክራም፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገሪቱ እየገቡ ያሉት አዳዲስና ዘመናዊ መኪኖች ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት እንደሚፈልጉ ትናገራለች::
‹‹መኪኖቹ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የሚገቡ እንደመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል:: የሚጠገኑበት ቦታም ንጹሕ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ መሆን አለበት::›› ስትል ገልጻ፣ ኢክራም አውቶሞቲቭ ደግሞ ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁማለች:: ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን አገልግሎት ይዛ በመምጣት ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሳ፣ በርካታ ደንበኞች ማፍራት እንደቻለችም ተናግራለች::
የመኪና አካል የሚሠራበት ቦታም ደህንነቱና ንጽሕናው የተጠበቀ ምቹ መሆን እንዳለበት የምትናገረው ኢክራም፤ ይህ ሁኔታ በአውቶሞቲቭና በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ የተመረቁ ሴት ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ እንደገቡ ዕድል ይፈጥራል ነው የምትለው:: እርግጥ ነው ሴት ልጅ ለማንኛውም ሥራ ታማኝና ትጉህ ብትሆንም፣ በመኪና አካል ጥገና ሥራ ብዙም ስትሳተፍ አይስተዋልም:: ምቹ ሁኔታው ካለ ግን ከመሥራት የሚያግዳት ምንም ነገር የለም›› ትላለች::
በአሁኑ ወቅትም በርካታ ሴት የአውቶሞቲቭ ባለሙያዎች በኢክራም አውቶሞቲቨ ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን፤ ሠራተኞቹ መኪኖችን በማስዋብ ቀዳሚዎች ናቸው:: መኪኖች በጸሐይና በሳሙና እንዳይጎዱ መከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይደረጋል፤ ጉዳት የደረሰባቸውም ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂና አገልግሎት ተገቢው ጥገና ይደረግላቸዋል::
አሁን ላይ መኪኖች የሆነ ችግር ከደረሰባቸው ወደ ኢክራም አውቶሞቲቭ እንደሚላኩ ጠቅሳ፣ ከሌሎች ትልልቅ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት በመፈራረም እንደምትሠራም ነው ወይዘሮ ኢክራም የገለጸችው:: ለአብነትም ከሞኤንኮ ጋር እንደምትሠራ ገልጻለች::
ኢክራም አውቶሞቲቭ በዲግሪ ደረጃ የተማሩ ባለሙያዎችን ሲቀጥር ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ ሥልጠና ሰጥቶ ነው ወደ ሥራ የሚያስገባው የምትለው ኢክራም፤ በአሁኑ ወቅት 30 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጻለች:: ከሠራተኞቹ አብዛኞቹ ሴቶች ስለመሆናቸውም ትናገራለች:: በቀጣይም ሴት የአውቶሞቲቭ ባለሙያዎችን ወደ ዘርፉ ለማምጣት ሰፊ ሥራ የመሥራት ዕቅድ እንዳላት ጠቁማለች::
ወይዘሮ ኢክራም እንዳለችው፤ በቀጣይ የሥልጠና ማዕከል መክፈትና መኪና እንዴት መዋብ እንዳለበት በማስተማር በየአካባቢው የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻልበትን መንገድ እያመቻቸች ትገኛለች:: በተለይም ቦታ ያላቸው እናቶችን በማሰልጠን በቤታቸው ሆነው የሚሠሩበትን ዕድል ለመፍጠር እየሠራች ነው::
ከልጅነት ጀምሮ የመኪኖችን አካል የምታውቀው ወይዘሮ ኢክራም፤ ቤተሰቦቿ ለሥራ ትልቅ ትኩረት የሚሰጡ እንደሆነ ስትናገር አያቷ ደጋግመው የሚሉትን አባባል በመጥቀስ ነው:: ‹‹የጥዋት መኝታ የድህነት ቦታ፤ የማታ ማምሸት ማገዶ መፍጀት›› ይሉ እንደነበር አስታውሳ፣ ‹‹ይህን እየሰማሁ በማደጌ ብርቱና ጠንካራ መሆን ችያለሁ›› ትላለች::
ደፋ ቀና እያለች ከመኪና ጋር የምትታገለው ኢክራም፤ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም አስተዋፅዖ አላት:: በተለይም በሙያዋ ለአገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አላቸው ብላ ለምታስባቸው ሰዎች የነጻ አገልግሎት ትሰጣለች:: ታዋቂና አንቂ የሆኑ ሰዎች የኃይማኖት አባቶችን መኪኖችም በነፃ ትጠግናለች፤ ታስውባለች:: በተጨማሪም ለመንግሥታዊ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ትናገራለች:: ዘርፉን ለማስፋት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሥልጠና በመስጠት የሥራ ዕድል መፍጠርና ዘርፉን በርካታ ባለሙያዎች እንዲሳተፉበት የማድረግ ዕቅድ አላትም::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2015