የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ከሳሽ ሆኖ ከደብረ አማን ተክለኃይማኖት ቤተክርስቲያን ጋር ፊት ለፊት ተፋጠዋል:: አንዱ ከሳሽ ሌላው ተከሳሽ ሆነው ቀርበዋል:: ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ፍትህ እንዲሰጣቸው ሁለቱም በየፊናቸው ጠበቃ አቁመዋል::
ኅዳር 17 ቀን 2006 ዓ.ም ደግሞ፤ የመዝገብ ቁጥር 88959 የመጨረሻ እልባት ይሰጠው ዘንድ ግድ ሆኖ ችሎት ተጨናንቋል:: ጉዳዩ ዘለግ ያሉ ዓመታትን የወሰደ ሲሆን፤ አያሌ ባለድርሻ አካላትም ጣልቃ የመግባት ሙከራዎችን አድርገዋል:: ሂደቱ ግን የዋዛ አልነበረም::
በእርግጥ በሁለቱም ወገን በዚህ ደረጃ ለሽኩቻ ያበቃቸው ጉዳዩ ቀላል አለመሆኑን ያሳያል:: በተለይም ደግሞ የከተማ ቦታ እንደዚህ በከፍተኛ ደረጃ ዋጋው በየቀኑ እየጨመረ ባለበት ወቅት ለዓመታት በአግባቡ ሳይለማ ለፓርኪንግ አገልግሎት ብቻ የዋለው ቦታ፤ ለዚያውም ዘመናዊ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ያለመሆኑ ምናልባትም ቦታው ባለቤት አልባ ሳይመስለው አልቀረም::
ወረዳው ይህን ቦታ ማስተዳደር ያለብኝ እኔ ነኝ ብሎ የክስ መዝገብ ለመክፈት የተገደደው ከዚህ መነሻ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም:: ቤተክርስቲያኒቱም ብትሆን በዚህ ቦታ ላይ የዋዛ አልሆነችም:: ታዲያ ‹‹ሀ›› ብሎ መዝገብ ተከፍቶ የተጀመረው ክርክር ሰበር ለመድረስ ተገዷል::
በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ከሥር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ አንደኛው ወገን አልዋጥ ሲል ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምርቷል:: በከፍተኛው ፍርድ ቤትም መግባባት በመጥፋቱ ነገሩ እየጦፈ ሰበር ችሎት ደርሷል:: በሁለቱም ወገን ግን በማሸነፍ ወኔ ጠበቆችን አቁመው፤ አንቀጽ እና ምዕራፍ እያጠቀሱ ወንጀልን ከፍታብሔር እየቀላቀሉ መከራከራቸውን ቀጠሉበት:: ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኝ እየተመከለተ ፋይሎችንም በየውሉ ለማስቀመጥ ተገደደ:: ጉዳዩ ቀላል የሚመስል ግን ውጥረት የነገሰበት ነበር::
አመልካች የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 190802 ጥቅምት 5 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደግሞ በመዝገብ ቁጥር 128307 ጥር 14 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለባቸው በመሆናቸው፤ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ለሰበር አቤቱታ አቀረበ:: በዋናነት ጉዳዩ የሁከት ይወገድልኝ ክስን የሚመለከት ነው:: በስር ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል::
በዚህ መዝገብ ተጠሪ የሆነችው ቤተክርስቲያን በካርታ ቁጥር 11/35/77/00 በሚታወቀው ይዞታ ኃይማኖታዊ አገልግሎት ለሕዝብ የምሰጥበት ህጋዊ ይዞታዬ ነው ስትል፤ ከሳሽ ኃይማኖታዊ በዓላት የማከብርበት ምዕመናኑ መኪና የሚያቆሙበት፤ በከፍተኛ ወጪ ያፀዳሁትና ከቀበሌ አስተዳደር በብሔራዊ ደህንነትና ከፖሊስ ጋር በመተባበር የፓርኪንግ አገልግሎት ሥር በሆኑ ወጣቶች የምሰጥበት 124 ዓመታት የያዝኩት ቦታ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጠቴን እንዳቆም ተከሳሽ ታኅሳስ 16 ቀን 2004 ዓ.ም በፅሑፍ ትዕዛዝ በመስጠት ሁከት የፈጠርብኝ በመሆኑ፤ ሁከቱ እንዲወገድ ውሳኔ ይሰጥልኝ የሚል ይዘት ያለው ክስ አቅርባለች::
ይሁንና ግን ቤተክርስቲያን የሁከት ክስ ያቀረበችበት ቦታን በተመለከተ፤ ወረዳው ከከሳሽ ህጋዊ ይዞታ እና አጥር ውጭ የሚገኝ ክፍት ቦታ ነው ሲል ተከራከረ:: በተጨማሪም ቦታው በካርታው ውስጥ የተጠቃለለ አይደለም:: በቦታው ላይ ቀደም ሲል የኢትፍሩት ኮንቴነርና ተንቀሳቃሽ ሽንት ቤት ተቀምጦበት ነበር የሚለውንም አከለበት:: በመሆኑም የመንግስት ቦታ የማስተዳደር ስልጣን በህግ የተሰጠኝ በመሆኑ ከህብረተሰቡ በቀረበልኝ አቤቱታ መሰረት ወረዳው የፓርኪንግ አገልግሎት እንዳይሰጥ መከልከሉ የሁከት ተግባር አይደለም፤ ይልቁንም ህግና ደንብን በአግባብ ማስከበር ነው ሲል ይከራከራል::
ታዲያ ጉዳዩ በሥር ፍርድ ቤት በሚገባ መታየት ስለነበረበት፤ የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በአግባቡ ሰማ:: ከሰማም በኋላ ቦታው ከአጥር ውጭ የሚገኝ ቢሆንም ቤተክርስቲያን በእጇ አድርጋ ይዛ ስትገብርበት የኖረችው ይዞታዋ ነው:: በመሆኑም በዚህን ቦታ ወረዳው ቤተክርስቲያን የፓርኪንግ አገልግሎት እንዳትሰጥ የፃፈው ማስጠንቀቂያ የሁከት ተግባር ነው:: በመሆኑም የፓርኪንግ አገልግሎት እንዳይሰጥ የሰጠው ትዕዛዝና ክልከላ ተወግዷል:: በመሆኑም ከሳሽ ይዞታ ላይ የፈጠረው ሁከት ይወገድ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል:: በዚህ ቅር የተሰኘው ወረዳው ይግባኝ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቀረበ::
ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የአመልካችን ይግባኝ በፍታብሔር ሥነ ስርዓት ቁጥር 337 መሠረት ሰርዘው:: ወረዳው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን ሳይስማማበት ቀረ:: ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ጉዳዩን መመልከት ጀመረ:: አቤቱታውም ቦታው የተጠሪ ይዞታ አይደለም፤ በቦታው የነበረው የኢትፍሩት ኮንቴነርና ጊዜያዊ ሽንት ቤት የተነሳው በአስተዳደሩ ፈቃድ ነው:: አመልካች ተጠሪ ቦታውን የፓርኪንግ አገልግሎት እንዳይሰጥበት የፃፈው ደብዳቤ የሁከት ተግባር አይደለም:: ስለዚህ ወረዳው የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ በአግባቡ ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመለከተ::
ቤተክርስቲያን በበኩሏ፤ መሬቱ ለረዥም ዓመታት በእጃችን አድርገን ስንጠቀምበት የነበረ ህጋዊ ይዞታችን ነው:: ስለዚህ በይዞታችን ላይ የተለያዩ ሃይማኖታዊ በዓላት እንድናከብር ለምዕመናን የፓርኪንግ አገልግሎት እንዳንሰጥ የወሰነው ውሳኔ የሁከት ተግባር በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጠች:: ወረዳው በበኩሉ፤ በመልስ መልሱ ውሳኔው ደንብ ቁጥር 14/1996 ድንጋጌዎችን ያገናዘበ አይደለም በማለት ተከራከረ::
የምርመራ ውጤት
ታዲያ ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን፤ እናም በቤተክርስቲያኗ በአጥር ከታጠረውና በካርታ ቁጥር 01-11.35/77/00 ከሚታወቀው ቦታ ፊት ለፊት የሚገኘው ቦታ ላይ የምትሰጠውን የፓርኪንግ አገልግሎት ቤተክርስቲያን እንድታቆም ወረዳው የፃፈው ደብዳቤ የሁከት ተግባር ነው በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ የህግ መሰረት ያለው ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጥልቅ ምርመራ ተደረገበት::
ጉዳዩ ሲመረመር፤ ‹‹ተጠሪ የሁከት ይወገድልኝ ክስ ያቀረበችበት ቦታ ከቤተክርስቲያኑ አጥር ክልል ውጭ የሚገኝና የቤተክርስቲያኗን ህጋዊ ይዞታ በሚያረጋግጠው የካርታ ቁጥር 11-35/77/00 የማይጠቃለል ነው:: ነገር ግን አከራካሪው ቦታ በቤተክርስቲያኗ ፊት ለፊት የሚገኝ ተጠሪ ከመቶ ዓመታት በላይ ኃይማኖታዊ በዓላትን ለማክበር ምእመናን ፀሎት ለማድረግና መኪኖቻቸውን ለማቆም ሲጠቀሙበት የኖሩ መሆኑን ተጠሪ ከስር ፍርድ ቤትና ለዚህ ሰበር ችሎት ባቀረበችው ክርክር በግልፅ አስፍራለች::
ከዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ የከተማ ቦታ የማስተዳደርና የትኛው ቦታ ለምን አይነት አገልግሎት መዋል እንዳለበት የመወሰን ስልጣን ያለው የከተማው አስተዳደር ነው ወይስ የቦታው ተጠቃሚና ባለይዞታ ነን የሚለው ግለሰብ ድርጅት ወይስ ኃይማኖታዊ ተቋም? የሚለው ጥያቄ ነው›› ሲል ይደመድማል::
በተጨማሪ ሰበር እንዲህ ሲል ያትታል:: በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ የሚገኘውን መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ማስተዳደር ሥልጣን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሆነ በአዋጁ ቁጥር 361/1995 አንቀፅ 11 በግልፅ ተደንግጓል:: ከዚህ አንፃር ሲታይ ከወረዳው ክልል ሥር ያለውን ከተማ መሬት ማስተዳደር የትኛው ቦታ ለፓርኪንግ አገልግሎት የሚውል ስለመሆኑ የትኛው ለፓርኪንግ አገልግሎት እንደሚሆን የከተማዋን መሪ ፕላን የማህበረሰብ ደህንነትና የፀጥታና ሌሎች ቦታዎችን በማገናዘብ የመወሰን ሥልጣን ያለው አመልካች ስለመሆኑ የአዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀፅ 11 ንዑስ አንቀፅ 2(ለ) እና አንቀፅ 38 ድንጋጌዎች ይዘት በማየት ለመረዳት ይቻላል::
በመሆኑም ወረዳው ከላይ በተገለፀው ህግ ድንጋጌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የወረዳ አስተዳደር ስልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን የወጣውን አዋጅ መነሻ በማድረግ ቤተክርስቲያን ከይዞታዋ ፊት ለፊት ባለው ቦታ ላይ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጠቷ ለሕዝብ ደህንነትና ፀጥታ አስጊ በመሆኑ አገልግሎቱን እንድታቆም የፃፈው ደብዳቤ አመልካች በህግ የተጣለበትን ኃላፊነትን እየተወጣ መሆኑን የሚያሳይ እንጂ የሁከት ተግባር አይደለም::
በመሆኑም ወረዳው፤ ቤተክርስቲያኒቷ በአጥር ከታጠረውና ከህጋዊ ይዞታዋ ፊት ለፊት ባለው ቦታ ላይ የምትሰጠውን የመኪና ፓርኪንግ አገልግሎት እንድታቋርጥ በቁጥር ል/ክ/ከ/ወ/አስ/624/2004 ታኅሳስ 12 ቀን 2004 ዓ.ም የፃፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የሁከት ተግባር ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ የአዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀፅ 11 ንዑስ አንቀፅ 2(ሰ) አንቀፅ 33 እና የፍታብሔር ህግ ቁጥር 1149 ንዑስ አንቀፅ 3 ድንጋጌዎችን ያላገናዘበና መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል ሲል የደመደመው::
ውሳኔ
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ ተሻረ፡፡ ወረዳው ለቤተክርስቲያኒቱ የፃፈው ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የሁከት ተግባር አይደለም በሚልም ተወሰነ፡፡ አመልካች በወረዳው ክልል ውስጥ ያለውን መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ማስተዳደርና የከተማውን ፕላን መሰረት በማድረግ የትኛው ቦታ ለምን ዓይነት አገልግሎት መዋል እንዳለበት የመወሰን ስልጣን አለው ሲል በአዋጅ ቁጥር 36/1995 እንደተሻሻለ ደብዳቤ መፃፉ ሁከት አይደለም በሚል የመጨረሻውን ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2015