ምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ እና ነገ›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የዲስኩር፣ የወግ፣ የግጥም እና የሙዚቃ መርሃ ግብር ላይ ከቀረቡ የአዕምሮ ምግብ ንግግሮች የመጋቢ ሐዲስ እሸቱን፣ የዲያቆን ዳንኤል ክብረትና የአርቲስት ሰርጸ ፍሬስብሃትን አስነብበናችኋል። በዚያ መድረክ ላይ ከተደረጉ ንግግሮች የመጨረሻ እናድርገውና ለዛሬው የዑስታዝ አቡበከር አህመድን ንግግር እናስነብባችሁ።
ስለአገራዊ ስሜት አገራዊ አንድነት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያለው ማህበረሰብ ላይ ሆኖ ማውራት ከባድ ነው። ኢትዮጵያዊነትን ከሚነገረው በላይ የሚኖር ስለሆነ ይህንን ለመሆን እያሰብን ያለን ሰዎች ውስጥ ቆመን እኛ ተናጋሪ እናንተ አድማጭ ስትሆኑ ቃሉ ይከብዳል። ግን እንድናገር ስለተፈቀደ። ኢትዮጵያ ዛሬና ነገ በሚል በተሰጠው ርዕስ ትንሽ ነገር ልበል።
ትልቁ መሰረታችን ዛሬ ነው፤ የትናንትና ያለፈው ማንነታችን ትውስታን እንዲሁም ደግሞ የነገን ራእያችንን የምንገነባበት ዛሬ ነው። ዛሬ ላይ መቆም የግድ ይላል። ዛሬን በትክክል ማየት ይሻል፣ ዛሬን ማስተካከል ስንችል ዛሬን መለወጥ ስንችል ባስተሳሰባችን በምንኖረው ማንነታችን በእውነታዊ ገፅታችን ዛሬን በትክክል ስንኖረው ነገን የተሻለ ማድረግ እንችላለን፤ የትላንት የተበላሹ የጠፉ እኛን የጎዱ ማንነቶች እንዳናስታውሳቸውና በእነሱ እንዳንቆጭ እንሆናለን።
ያን ግን ዛሬ ላይ በትክክል መቆም ስንችልና ዛሬን ማስተካከል ስንችል ነው። ለዚህ ነው ዛሬ በሁሉም መልኩ ሰዎች ትናንት ባለፈ ጉዳይ ራሳችንን እያሳመምን ባልመጣ ነገር ውስጣችንን በጥፋት እየቆዘምን ዛሬን እያሳለፍነው ከሆነ አይደለም ሀገርን፣ አይደለም ማህበረሰብን፣ አይደለም ትውልድን፣ አይደለም የምንሻውን ሰላምና ምቾትን እኛነታችንን ሳናይ ያልፍብናል።
ሰዎች ማለት የቀናቶች ስብስብ ነው፤ የዛሬዋ ቀን ስታልፍ ከኛነታችን አካል የሆነ ነገር እያለፈ ነው፤ የማይመለስ መቼም የማናገኘው ዛሬ ማለት ነው። አገራችን ባለችበት የለውጥ ሂደት ውስጥ ተስፋ ሰጪ ብዙ ነገሮችን አይተናል፤ በዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ አደጋና ውስጣችን ላይ ፍርሀት የሚጭሩ ነገሮችን እያስተዋልን እንገኛለን።
ይህን አደጋ የምንቀንሰው ተስፋውን የምናሳድገውና የተሻለ ደረጃ የምናደርሰው እኛው ነን። እኛ በእኛነት ስሜት የጋራ ሆነን መስራት ስንችል። ከእኔነት ስሜት ወጥተን አንዱ አንዱን ከመግፋት ከማግለል ግለሰብን ማህበረሰብን ሰብስበን በሆነ ሀሳብ ለመግፋት ሳይሆን በሁሉ ማንነታችን አንዱ አንዱን ለመቀበል ሲዘጋጅ ነው።
ኢትዮጵያ ዛሬ ባለችበት ተጨባጭ ትናንት ያለፉትን ጥቁር ነገሮች መልካሙን ረስተን እያሰብን ዛሬ ላይ የትናንቱን ትውስታ አምጥተን መሬት ላይ ወርደን ሂሳብ ለማወራረጃ ካደረግነው ኢትዮጵያን እንኳን ማዳን አገዳደሏ ምናልባት እኛ ካሰብነው በፈጠነ መልኩ የሚፈፀምበት ሂደት ሩቅ አይደለም።
ሰው አካባቢ መንደር ቀበሌ ሳይሆን ሀገር እንደ ሀገር ሲፈርስ ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ በጎረቤቶቻችን ብዙ አይተናል። ይሄን ለመጠበቅ ዛሬን በትክክል መጠቀም ይሻል ዛሬ ላይ የአንዱ ውድቀት የሌላው እድገት ተደርጎ የሚታሰብ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው። ሌላው ሲወድቅ የምንደሰትበት የኛ እድገት የነገ ውድቀታችንን ማሳያ ካልሆነ ሌላውን ጥለን ስንሄድ እኛ በትክክል እኛነታችንን ሳናውቅ እየኖረን እንደሆነ እናያለን።
ለዚህ ነው በትክክል ዛሬን መገንዘብ ዛሬን ማየት ለዛሬ መስራት የሚያስፈልገው። ዛሬ ላይ ቆም ብለን ሁላችንም መነጋገር ይሻል፣ መመካከር መተሳሰብ አንዱ የአንዱን ሀሳብ ማክበርና በልዩነታችን ተከባብረን ለመኖር ሁላችንም መዘጋጀት አለብን። ያን ስሜት ይዘን መጓዝ ስንችል ብቻ ነው ዛሬ የምንደሰትበት ትናንት የሰራነው መልካም ነገር ለዛሬ ስላዋለን ነው።
ፖለቲከኞች ምን የሚል አባባል አላቸው ‹‹ታሪክ ማለት የትናንት ፖለቲካ ነው››፤ ይላሉ ‹‹ዛሬ ደግሞ የነገ ታሪክ ነው›› ይላሉ። የፖለቲካው ስሪት ሰዎች የሚቃኙበት ማህበረሰብ እድገቱ ውድቀቱ የሚለካበት በተለያየ አይነት መልክ መልካም ሰርተው የሚያልፉ መልካም የሚሰሩበት ከዛ ባለፈ መልኩ ደግሞ ጥፋትን ለማህበረሰብ የሚያስተላልፉበት ተጨባጭ ታሪክ ሆኖ እናየዋለን የዚህ የፖለቲካው ውጤት።
ዜጎች በእኩል ማንነታቸው ዛሬ ላይ ስንመለከት እዚች ሀገር ላይ ምን አልባት ጥሩ የሚባል ህገ መንግስት ወረቀት ላይ አለ። ያ ወረቀት ላይ የሰፈረው ህገ መንግስት ዜጎችን በእኩልነት ወይንም ባሳታፊነት ጥሩ መደላድል ላይ በማድረግ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲሰማቸው።
እዚች ኢትዮጵያ ላይ ዛሬ የተፈጠረው የለውጥ አየር ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ተብሎ ከሚታሰበው ኢትዮጵያውያኖች ኢትዮጵያ እየኖሩ አሜሪካም ይኖሩ ነበር። ዛሬ ግን ኢትዮጵያውያኖች ውጪ ያሉት እንኳን ኢትዮጵያውያን ሆነው ኢትዮጵያ ገብተዋል ይሄን የኢትዮጵያዊነት ስሜት መፍጠሩ የለውጡ አየር ማሳያ ነው።
ትናንት አቅም ያላቸው ብዙ መናገርና መስራት የሚችሉ ለሀገር ለውጥ ትልቅ ራእይ ያላቸው ሰዎች ከሀገር ተገፍተው ኢትዮጵያን የናፈቁ ሸሽተው ዛሬ እነዛን ሰዎች ኢትዮጵያ መሬት ላይ ወርደው ስለዚች ሀገር እንዲያስቡ እድሉ ተሰጥቷል።
ይሄ እድል ለኛ ተስፋ ሰጥቷል። ይሄ ተስፋ ደግሞ የበለጠ ሆኖ ለኛም ለልጆቻችንም ለትውልዱም መልካም ነገር አፍርቶ ውጤት እንዲመጣ ከፈለግን ዛሬን መጠበቅ ግድ ነው። ዛሬም በመካከላችን ያሉትን ክፍተቶች እየሞላን እያስተካከልን እየተከባበርን ስንሄድ ውጤቱን የምናመጣው እኛው ነን።
ሌላው ያመጣውን ውጤት እየጠበቅን ወይንም ሌላው ውጤት ይዞ እንዲመጣ እየጠበቅን እኛ ቁጭ ካልን ለውጡ እኛ ጋ ለመድረሱ ዋስትና የለንም። ምክንያቱም እሱ ሩቅ ነው። ለመድረስ ብዙ እንቅፋቶች ስለሚያጋጥሙት ይሄን የማስተካከል ኃላፊነት የሁላችንም ነው። ሁላችንም ከእኔነት ስሜት ወጥተን በእኛነት ስሜት ውስጥ ስንኖር ነው።
እዚች ሀገር ላይ ስንኖር በብዙ ማንነታችን ኢትዮጵያን እናስባታለን። በእምነታችን በብሄራችን ብዙ ነገሮቻችንን ከኛ ጋር ናቸው። ነገር ግን እኛነታችንን የሚሰበስብ ኢትዮጵያዊ ማንነት አለን። ያ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን እኛን እንዲያስተባብረን ምክንያት መሆን ካልቻለ ግን መጣያ ምክንያቶቻችን በጣም ብዙ ነው የሚሆኑት። የሚያሰባስበንን ነገር ባሳነስነው ቁጥር የሚያጣላንን ነገር እያበዛን ነው የምንሄደው።
በትንንሽ ጉዳዮች እየተቆጣን መስከን ሲገባን ስሜታዊ እየሆንን ሀገር ያለችበት የለውጥ እርከን ምእራፍ አለ። ሁሉም ሀገሮች እንደ ሀገር ሲለወጡ ሲገነቡ የሚያርፉበት እርከን አለ። እዛ እርከን ውስጥ እኛም ገብተናል ይሄን እርከን ግን ከመነጋገር መወጋገዝን አንድ ከመሆን መገፋፋትን።
ከመሰባበሰብ ማግለልን ከመደማመጥ አንዱ አንዱን ማነወርን መርህ አድርገን ከያዝን ይህን እርከን መሻገር ሳንችል ሀገር እንድትፈርስ ምክንያት እንሆናለን። ያ እንዳይመጣ ግን ዛሬ በእኛ እጅ ላይ አለ። ነገ መልካም ነገር ይዞ እንዲመጣ የተሻለ ነገር እንድናይ ዛሬ ደስተኞች የምንሆነው ትናንት የሰራነው ስራ ውጤት ማሳያ ሆኖ ነው። ዛሬ ላይ እየተከፋን የምንገኘው ትናንት የተሰራው መጥፎ ተግባር ውጤት ዛሬ ላይ ስለደረሰ ነው።
የዛሬው መጥፎ ነገ እንዳይቀጥል ማድረግ የምንችለው እኛ ስናቆመው ነው። የዛሬው ደስታ የተሻለ እንዲሆን የምናደርገው ነገን አስበን መሥራት ስንችል ብቻ ነው። ለዚያ ደግሞ ከእኛ የሚፈለግ ነገር አለ። ተጎድተናል፣ ከፍቶናል፣ ተቸግረናል፣ ተገፍተናል፤ አንደኛችን መተው ሳንችል ከሌላው የሚመጣው መልካም ነገር እንዲመጣ መጠበቅ ከባድ ነው። እንደ ወገን የምንሰማቸው ነገሮች ራሳችንን እንድንጠላ ውስጣችንን እንድናጣ የሚያደርጉ ነገሮች እንዳሉ ይሰማናል። ይሄ ድርጊት እስከመቼ ድረስ ነው እንድንቀጥል የምንፈቅድለት? ሰዎች በስሜት እየተነዱ፣ የግል ስሜታቸውን እያራመዱ፣ ከመሰማማት መጠፋፋትን እየመረጡ ነው።
ኢትዮጵያ ትናንት ያለፈችበትን ማንነት ማስቀጠል አያቅታትም። እየተዋጋን፣ እየተዳማን፣ እየተገዳደልን ትናንት በነበረችበት ማንነት መቀጠል ትችላለች። ዛሬ የመጣውን ለውጥና የተሻለ አድርጎ መቀጠሉ ነው ከባድ የሚሆነው። መሥራት ባንችል እንኳን እጃችንን መሰብሰብ። መልካም መሆን ባንችል እንኳን ለክፋት ዕድል አለመስጠት። ሁላችንም አንድ ቦታ መጠቆም ሳይሆን ‹‹እኛስ የት ጋ ነን›› ብሎ መጠየቅ።
የአስተሳሰብ ለውጥ በዕውቀት ብቻ አይደለም፤ ከዕውቀት አልፎ ወደ ተግባር ሲለወጥ ነው። ያ መሆን ካልቻለ ሁሉ ነገር ይጠፋል። ከምናስበው ውጭ ይሆናል ማለት ነው።
የሰለጠነ ማህበረሰብ ከሌለ የሰለጠነ ፖለቲካ አይመጣም። አዋቂዎች የሚሉት አባባል አለ፤ ‹‹ከሰልን ለማጥፋት የፈለገውን ያህል ሳሙና ብንጠቀም ጥቁረቱን አናስለቅቀውም›› ይላሉ። ይሄ የሳሙናው ችግር ሳይሆን የከሰሉ ባህሪ ነው። እኛ ለመለወጥ ካልተዘጋጀን የፈለገውን ያህል መሪ ቢቀያየር ለውጥ አይመጣም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011